Administrator

Administrator

 • ለአንድ አመት የታሰሩት እንዲፈቱ ጠይቀዋል  
 •    የሼኩ ግድያ ድራማ ነው ብለዋል

በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ “የታሰሩ ይፈቱ” የሚል ተቃውሞ ባለፈው ሳምንት አርብ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በትናንትናው እለት በበኒ መስጊድ ብዙ ህዝብ በተገኘበት ሰፊ ተቃውሞ ታይቷል፡፡ ተቃውሞው፤ ታሳሪዎች አንድ አመት እንደሞላቸው ምክንያት በማድረግ የተካሄደ ነው ተብሏል፡፡ መፍትሔ አፈላላጊ በሚል ስያሜ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኮሚቴ አባላት፤ በሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸው ከታሰሩ አንድ አመት የሞላቸው ሐምሌ 14 እንደሆነ የገለፁት ተቃዋሚዎቹ፤ “በአንድነታችን እንቀጥላለን” ከሚል መልዕክት ጋር በኢንተርኔት የተቃውሞ ጥሪ አስተላልፈው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ትናንት ቀትር ላይ ወደ ተክለሃይማኖትና ወደ ኩርቱ ህንፃ አቅጣጫ እንዲሁም ባንኮ ዲሮማ ድረስ ባሉት መንገዶች በርካታ ህዝብ በመስጊዱ ዙሪያ ተሰብስቦ ተቃውሞ ተስተጋብቷል፡፡ የታሳሪዎችን ፎቶ ያነገቡ ተቃዋሚዎች “ድምፃችን ይሰማ”፣ “የታሰሩት ይፈቱ”፣ “የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል”፣ “የሼሁ ግድያ ድራማ ነው” ብለዋል፡፡ ትላንት በተካሄደው ተቃውሞ በርካታ አድማ በታኝ ፖሊሶች በአንዋር እና በበኒ መስጊድ የነበሩ ሲሆን የሃይማኖት ስርዓቱ ያለ እንከን እንደተካሄደና ተቃውሞውም በሰላም እንደተጠናቀቀ ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ አሰፋ አቢዩ፤ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው እንደተሾሙና ሰሞኑን ከሠራተኞች ጋር ተዋውቀው ስራ እንደጀመሩ ተገለፀ፡፡የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙትን የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየሁን በመተካት ነው አቶ አሰፋ ሃላፊነቱ የተሰጣቸው፡፡ በክልልና በፌደራል መንግስት በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃዎች ሲሰሩ የቆዩት አቶ አሰፋ አቢዩ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሁለት የመጀመሪያ ድግሪና የማስተርስ ድግሪ እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት የህብረት ሥራ ማህበራት፤ የቀድሞዎችም ሆነ አዲሶቹ ማህበራት በአዲሱ መመሪያ እንዲደራጁ ይገደዳሉ ተባለ፡፡ መስተዳድሩ ትላንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የማህበራቱ የአደረጃጀትና የምዝገባ መስፈርት ከ20/80 መስፈርት ጋር ሙሉ ለሙሉ እንደሚመሳሰልም ተናግረዋል፡፡ በመስተዳድሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሺሰማ ገ/ስላሴ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የማህበራቱ አደረጃጀትና ምዝገባ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ የሚለየው ማህበራቱ በራሳቸው ገንዘብ መገንባት መቻላቸውና ለተነሺዎች የካሳ ክፍያ ራሳቸው መክፈላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞዎቹ ማህበራት የተረጋገጡ ጉድለቶች እንደነበሯቸው የጠቆሙት ሃላፊው፤ ከነዚህም ውስጥ በህይወት የሌሉ ሰዎችን በአባልነት መመዝገብ፣ ህገወጥ መሬት እንዲገዙ ማድረግ፣ በተጓደሉ አባላት ምትክ ለሚገቡ አባላት አላስፈላጊ ገንዘብ መቀበል፣ ከግንባታ ፈቃድ ውጭ መገንባትና መሬትን ያለ አግባብ መውረር ይገኙበታል ብለዋል፡፡ ሃላፊው አክለውም፤ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ እንዳማራጭ የቀረበው የማህበራት የቤት ግንባታ መመሪያው ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ በአዲሱ መመሪያ መሠረት መስፈርቱን የሚቀርቡ ማህበራት መመዝገብ እንደሚችሉም ተብራርቷል፡፡ የመደራጃ ቦታዎችን በተመለከተ በመኖሪያ አካባቢ፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በንግድ ቦታዎች አካባቢ መደራጀት የሚቻል ሲሆን ለቀድሞ ማህበራት 16 አባላት፣ ለአዲሶቹ ደግሞ 24 አባላት እንዲያደራጁ መመሪያው ያዝዛል፡፡ ሠራተኛዬ ከደሞዙ ቀስ ብሎ ይከፍላል የሚሉ መስሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን በማህበራት አደራጅተው መገንባት ይችላሉም ተብሏል፡፡

ማህበራት የመነሻ ዲዛይን ከመንግስት የሚቀርብላቸው ሲሆን የከተማዋን ማስተርፕላን በጠበቀ መልኩ የዲዛይን ለውጥ ማድረግ ከፈለጉ የገንዘቡም መጠን እንደሚቀየር የተናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም ናቸው፡፡ አቶ ጌታቸው አክለውም፤ የቤቶቹ የግንባታ ዋጋ ግምትን በሚመለከት የቤቱ ግንባታ ፎቅ ሆኖ ባለ አንድ መኝታ 210ሺ፣ ባለ ሁለት መኝታ 280ሺ እና ባለ ሶስት መኝታ ክፍል 385ሺ ብር ሲሆን የዲዛይን ለውጥ ሲኖር ዋጋው እንደሚያቀያይርና የማጠናቀቂያ (Finishing) ስራን እንደማያካትትም ገልፀዋል፡፡ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በየኤምባሲው ምዝገባ የሚካሄድ ሲሆን በውጭ የሚኖሩና በአገር ቤት ያሉ አባላት ተቀላቅለው መደራጀት እንደማይችሉም ተነግሯል፡፡ መመሪያው ከሀምሌ 15 ጀምሮ ምዝገባ ይካሄዳል ተብሎ እስከዛሬ የቆየው ጠቃሚ ሀሳቦችን እንዲያካትትና መጠነኛ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ የተናገሩት ሀላፊዎቹ፤ ለባከኑት ቀናት ተመጣጣኝ ቀናትን እንጨምራለን፣ ቀኑን ዝግ አላደረግንምም ብለዋል፡፡

ክፍያውን ሙሉ ለሙሉ መፈፀም የሚችሉና በ40/60 ተመዝግበው ወረፋ የሚጠብቁም ወደ ማህበራቱ በመምጣት በ40/60 ላይ ያለውን ወረፋ ቀለል ማድረግ ይችላሉም ተብሏል፡፡ ማህበራቱ የመጀመሪያ ስራቸው ማደራጀትና መመዝገብ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ መስፈርቱን አሟልተው ለመጡ ምዝገባው ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ የማህበራት ማጭበርበሮች እንዳይካሄዱ የአሻራ ምርመራም እንደሚካተት ተገልጿል፡፡ ማህበራት አባሎቻቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሆናቸውን፣ የትም ቦታ ቤት የሌላቸው መሆኑን፣ እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ መሆኑንና 50 በመቶ ቅድሚያ መክፈል የሚችሉ መሆኑን በአፅንኦት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የካሳ ተመንን በተመለከተ በግለሰቦች ሳይሆን በካቢኔ የሚወሠን ስለሆነ ለሙስናም ሆነ ለአድልኦ የተጋለጠ እንደማይሆን ሃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

በዚህ ሳምንት ምን ተቀዳጀ፡- “የዩቲውብ ንጉስ” የሚል ማዕረጉን ሳያስነጥቅ ቀጥሏል እሱ ማነው፡- የኮሪያ ፖፕ ስልትን ለአለም ስተዋዋቀው፤ ፒ ኤስአይ ታዋቂ ያደረገው ነጠላ ዜማ ፡- ጋንግናም ስታይል ጋንግም ስታይል ምን አተረፈለት፡- 10 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ በጋንግናም እስታይል ብቻ፡፡ *በጋንግናም ስታይል የዜማና የዳንስ ስልት በመላው አለም ከ33ሺ በላይ የሙዚቃ ቪዲዮዎች ተሰርተዋል፡፡ *የተባበሩት መንግሥታት ሊቀመንበር ባንኪ ሙን፣ “ሙዚቃ የአለም ሰላም ሃይል መሆኑን ያስመሰከረ አርቲስት” ብለውታል፡፡ በጋንግናም ስታይል ነጠላ ዜማው ደንሰዋል፡፡ አለም አቀፍ ተቋሙ አብሮት ሊሰራ እንደሚፈልግ ገልፀዋል፡፡

የአለም አቀፍ ተወዳጅነቱ ማሳያዎች ፡- በጋነግነም ስታይል አደናነስ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ እና የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ተማርከውበታል፡፡ ዳንሱ በፓሪስ፣ በሮም እና በሚላን ከተሞች ተከታዮች ከአብዮት ባልተናነሰ መልክ ተዛምቷል፡፡ * በደቡብ ኮርያ እና ኢንዶኔዥያ እስከ 15ሺ ህዝብ በአንድ ላይ ተሰብስቦ ጋንግናም ስታይልን በአደባባይ ጨፍረዋል፡፡ 1.74 ቢሊዮን ተመልካች በዩቲውብ ድረ ገፅ ጋንግናም ስታይልን ተመልክቷል፡፡ ሌሎች ሥራዎችስ ? ከጋንግናም ስታይል በፊት አምስት አልበሞች ያሳተመ ቢሆንም ከሀገሩ ኮርያ የዘለለ ታዋቂነት አላተረፈለትም ነበር፡፡ ታዋቂዎቹ ነጠላ ዜማዎቹ፡- “ጋንግናም ስታይል” እና “ጀንትልመን

*“የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጉዞ” መፅሐፍ ለገበያ በቃ “ጳጉሜ፣ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠርያ የማን ነው?” የሚል መፅሐፍ ዛሬ ገርጂ በሚገኘው የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ እንደሚመረቅ አዘጋጁ አስታወቁ፡፡ የመፅሐፉ አዘጋጅ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ፋሲል ጣሰው፤ የቀን አቆጣጠሩ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም የሚል መሟገቻ በመፅሐፋቸው ያቀረቡ ሲሆን ወርሃ ጳጉሜ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት አለባት በማለትም፣ ሠራተኞች ተጨማሪ ደመወዝ፣ የቤት አከራዮች የኪራይ ገንዘብ ጳጉሜን ታሳቢ በማድረግ ማግኘት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ዶ/ር አረጋ ይርዳውን ጨምሮ ሌሎች የሚድሮክ የሥራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መፅሐፉ ለሀገር ውስጥ በ100 ብር፣ ለውጭ ሀገራት በ35 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡በሌላም በኩል “ነገር በምሳሌ” ቁጥር 1 መፅሐፍ በመጪው ሐሙስ በ10፡30 በብሉ በርድ ሆቴል ይመረቃል፡፡ አቶ አብርሃም ሐዲሽ ያዘጋጁት ባለ 103 ገፅ መፅሐፍ፤ የሥራ ባህል እንዳይዳብር መሰናክል ሆነው የቆዩ ልማዶችን ለመዋጋት የመፍትሄ ሀሳቦችን ያቀርባል፡፡

መፅሐፉ በ30 ብር እየተሸጠ ነው፡፡በፈለቀ ደምሴ (ኤርምያስ) የተዘጋጀው “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ” መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በበርካታ መረጃዎች እና ፎቶግራፎች የተደገፈው ባለ 179 ገፅ መፅሐፍ፤ በፋርኢስት ትሬዲንግ የታተመ ሲሆን ዋጋው 47 ብር ነው፡፡ በመፅሐፉ የኋላ ሽፋን ላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቡና ክለብ ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬ፣ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እና የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አልፊያ ጃርሶ አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡

ላለፉት 15 አመታት በፊልም ሙያ ላይ የተሰማራው ቴዎድሮስ ተሾመ፤ በፊልም ፅሁፍ ደራሲነት፣ በተዋናይነት፣ በዳሬክተርነትና በፕሮዲዩሰርነትም ሰርቷል፡፡ በሙያ ዘመኑ አምስት ፊልሞችን ሰርቶ ለእይታ ያበቃው አርቲስቱ፤ ስድስተኛውን ፊልሙን “ሦስት ማዕዘን” በሚል ርዕስ የሰራ ሲሆን የነገ ሳምንት ሐምሌ 21 ያስመርቃል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ በአዲሱ ፊልሙ ላይ በማተኮር ከአርቲስት ቴዎድሮስ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ እነሆ፡፡


“ቀይ ስህተት” የተሰኘው ፊልምህ ሲወጣ የቀይ ሽብር ሰማእታት ታሰቡ፡፡ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ሲታይ አባይን መገደብ ተጀመረ፡፡ አሁን ደግሞ የስደተኞች ጉዳይ ትኩረት ሲይዝ በስደት ዙርያ የሚያጠነጥነው “ሦስት ማእዘን” የተሰኘ ፊልምህ ሊወጣ ነው፡፡ ፊልሞችህ ወቅት ተኮር ሆኑሳ?
የ“ሦስት ማእዘን” ቀረፃ ያለቀው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ የተፃፈው ከሦስት ዓመት በፊት ነው፡፡ በተለይ በሙያው ውስጥ ያሉ እንደዚህ ሊያስወሩ ይችላሉ፡፡ በትግል የማትጥለውን ሰው ለመጣል እንዲህ አይነት ስትራተጂ ትቀይሳለህ፡፡ የዚህን ፊልም ማስታወቂያ ከጀመርን አስራ አንድ ወር ሆኖናል፡፡ የሕገወጥ ስደት ወሬ ሰፊ ሽፋን ማግኘት የጀመረው ከስድስት ወር ወዲህ ነው፡፡ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ፕሮጀክት ሁለት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ይኼ ፊልም መታየት ከጀመረ በኋላ ነው የግድቡ አዋጅ የታወጀው፡፡ “አበድኩልሽ” ከሚል የገበያ ሥራ ስታልፍ ችግሮች ቀድመው ሊታዩህ ይችላሉ፡፡
“ሦስት ማእዘን”ን በልደትህ ቀን ለገና ለማስመረቅ አስበህ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ለምን እስካሁን ዘገየህ?
ፊልሙ አልደረሰልኝም፡፡ ፊልሙን በልደቴ ቀን ለማስመረቅ አስቤ ነበር፡፡ ይኼ መረጃ እንዴት እንደደረሰህ አላውቅም፡፡
ማትያስ ሹበርት የፊልሙ የፎቶግራፊ ዳይሬክተር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን ባለሙያው ሙሉ ቀረፃውን እንዳልሰራ ይናገራሉ፡፡
ዘጠና ዘጠኝ በመቶውን ቀረፃ የሰራው እሱ ነው፡፡ እዚህ የቆየው ለስልሳ ቀናት ነው፡፡ ቀረፃው በሰባ አምስት ቀናት ተጠናቀቀ፡፡ እሱ ከሄደ በኋላ አስራአምስት ቀን ሙሉ ተቀረፀ ማለት አይደለም፡፡ ከሱ መሄድ በኋላ የሦስት ቀን ቀረፃ ብቻ ነው የነበረው፡፡
ፊልሙን በውጭ ሀገር ፊልም ዘርፍ ለኦስካር ሽልማት እንዲታጭ ለማድረግ አስባችኋል፡፡ ከምን ተነስታችሁ ነው?
ሥራችን ለኦስካር ይመጥናል ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ካሁን በፊት የሰራኋቸው ፊልሞች እዚህ ውድድር ውስጥ አልገቡም፡፡ የኦስካር ፈተና ከባድ ነው፡፡ ውጤቱን አብረን እናያለን፡፡ የእኛ መዝገበ ቃላት ሁልጊዜ “አይቻልም” የሚል ነው፡፡ አይቻልም ስለሆነ ሁሌም አንችልም፡፡ “ሦስት ማእዘን” ግን ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ የሚከፈለውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡ ኦስካር መግባታችን ግን ከማትያስ ሹበርት ጋር አይገናኝም፡፡
ሀገር ውስጥ ፍጆታ በተሰራ ፊልም ለዓለም አቀፍ ሽልማት መታጨት ይቻላል?
የሚያጨው ሌላ አካል ነው፡፡ እኛ እንደማንኛውም ተወዳዳሪ እንወዳደራለን፡፡ ስራችንን ለውድድር አቅርበን ዘመቻ እናደርጋለን፡፡ ይህ ራሳችንንና ፊልሙን ለማሳደግ ያለን ፍላጐት አካል ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ሙከራ እናደርጋለን፡፡
በፊልሙ ውስጥ ለተሳተፈ ለእያንዳንዱ የውጪ አገር ዜጋ ተዋናይ 40ሺ ዶላር ከፍለሃል ተብሏል…
ውሸት ነው፡፡ በነፃም አልሠሩም፣ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብም አልተከፈላቸውም፡፡
“ሦስት ማእዘን” ከሌሎቹ ፊልሞችህ በተለየ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መቀረፁን ፊልሙን ለጋዜጠኞች ባሳየህ ወቅት ተናግረሃል፡፡ እስቲ ስለእሱ አብራራልኝ…
በ49 ሴ.ግሬድ ሙቀት በበረሀ መቀረፁ ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ፊልም የራሱ ተግዳሮት አለው፡፡ የባለሙያ፣ የበጀት…ችግር አለ፡፡ ይኼን የተለየ የሚያደርገው በረሃው ነው፡፡ ከቤት ውጭ ነው የተቀረፀው፡፡ የውሃ ጥሙ ስቃይ ነው፡፡ ቀዝቃዛ ውሃ አፍ ከመድረሱ በፊት ይሞቃል፡፡ በእርግጥ ሁላችንም ተሰዳጅ ሆነንበታል፡፡ ሌላው ደግሞ ውጭ ሀገር ሲቀረጽ የገጠመን የውጭ ምንዛሬ ችግር እና የቋንቋ መሠናክል ነው፡፡
ወደ ፊልም ሙያ በገባህበት የጀማሪነት ጊዜህ ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ሚሼል ፓፓታኪስ ያመቻቹልህን የውጭ ሀገር የትምህርት እድል ሳትጠቀምበት እንደቀረህ ሰምቻለሁ፡፡ ለምን ይሆን?
ከጀመርን የባህል ተቋም ጋር በመሆን ጋና እንድሄድ ነበር የታሰበው፡፡ አጋጣሚው ጥሩ ነበር፡፡ ግን በዚያ ሰዓት ለአራት ዓመት እዚያ ሄጄ ቢሆን ኖሮ አሁን ላለሁበት ደረጃ አልደርስም ነበር፡፡ የራሴ ራእይ ነበረኝ፡፡ የአሁኑን ጊዜ ያለመ፡፡ የባህል ተቋም ኃላፊዋን ለአራት ዓመት ከምትልኪኝ የሦስት ወር ካለ ላኪኝ ብያት ነበር፡፡ እናቴ በህይወት ስላልነበረችና የቤተሰብ ሃላፊነት እኔ ላይ በመውደቁ፣ ለረዥም ጊዜ ውጭ ሀገር መቆየቱን እምቢ አልኩ፡፡ ወንድሞቼንና እህቶቼን ሜዳ ላይ በትኜ መሄድ አልችልም ነበር፡፡
ከዚያ በኋላስ የፊልም ትምህርት የመማር እድል ገጠመህ ወይስ በልምድ ብቻ ቀጠልክ?
ሎስ አንጀለስ የፊልም ትምህርት ቤት ተምሬአለሁ፡፡ ዲግሪዬን በሚቀጥለው ወር እወስዳለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ውጭ የነበርኩት ለዚህ ነው፡፡
በልጆችህ ላይ ወዳንተ ሙያ የመግባት አዝማሚያ አይተህባቸዋል?
ሦስተኛ ሴቷ ልጄ በተለይ ሙዚቃ ላይ ክንፍ ትላለች፡፡ ያልተለመደ ነገር አላት፤ አካሄዷን እናያለን፡፡ ልጆቼ ምርጫቸውን የሚወስኑት በራሳቸው ጊዜ እንጂ በእኔ ምርጫ አይደለም፡፡ ድራማ እና ፊልም ያያሉ፡፡
“ሦስት ማእዘን” ሲመረቅ መግቢያው 300 ብር መሆኑ “ራስን ማዋደድ ነው” ብለው የሚተቹ ወገኖች አሉ…
ይሄ በዛብን የሚሉ በሌላ የምርቃት ቦታ በመቶ ብር መግባት ይችላሉ፡፡ ከበዛ በሚቀጥለው ቀን በመደበኛ ዋጋ ይታያል፡፡ አምስት መቶ ብር እና አንድ ሺህ ብር ለማድረግም አስበን ይበዛል ብለን ነው የተውነው፡፡ የምርቃት ፕሮግራሙ ልዩ ሥነ ሥርአት ስላለው እኮ ነው፡፡
ለ15 ዓመታት በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ እንደቆየ ባለሙያ የአገራችንን የፊልም እድገዘ እንዴት ትገመግመዋለህ?
የሁሉም ሀገር የፊልም ኢንዱስትሪ የራሱ ዝግመተ ለውጥ አለው፡፡ ይወለዳል፡፡ ይድሃል፡፡ ያድጋል፤ ትልቅ ኢንዱስትሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለፍን ነው ያለነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የሁሉም ኢንዱስትሪ ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ከሁለት አቅጣጫ እየተጐተተ ነው፡፡ የሚለፋ ሰዎች አሉ፡፡ ወደ ፊት ያራምዱታል፡፡ ወደ ፊት ሄደ ብለህ ስታስብ ደግሞ አሸር ባሸር የሚሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ ወደ ኋላ ይጐትቱታል፡፡ ስለዚህ መሀል ላይ ተወጥሮ ነው ያለው - ወደ ፊትም ወደ ኋላም እየተጐተተ፡፡
የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ የግሎባላይዜሽን ተፅእኖ ያሰጋዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
ኢንዱስትሪውን ኢንዱስትሪ ለማድረግ ሦስት ግብአቶች ያስፈልጋሉ፡- ተመልካች፤ ፕሮዲዩሰር እና አከፋፋይ፡፡ አከፋፋይ ሲኖር የጥራት ደረጃ ይመጣል፡፡ ይኼንን ደረጃ ለማምጣት ፕሮዲዩሰርም ተጠንቅቆ ይሰራል፡፡ ተመልካችም ጥራት ምን እንደሆነ ስለሚገባው ያንን መጠየቅ ይጀምራል፡፡ እኛው እንሰራለን፣ እኛው እናስተዋውቃለን፣ እኛው እናከፋፍላለን፡፡ “ሦስት ማእዘን” የራሱ ዓለም አቀፍ አከፋፋይ አለው፡፡
አሁን ሰዎች በፊልም ገቢ ብቻ መተዳደር ጀምረዋል፡፡ ስለዚህ ፊልም እንደ ኢንዱስትሪ ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለመንግስት ቀረጥ እየተከፈለበት ነው፡፡ የፊልሞች በዓለምአቀፍ የባህልና ቋንቋ ተጽእኖ ሥር መውደቅ እንደፊልም ሰሪዎቹ የአእምሮ ዝግጅት የሚወሰን ነው፡፡ ሁሉም ፊልም ግሎባላይዝድ ሆኗል ማለት ይከብዳል፡፡
ዘንድሮ ከወጡ የአማርኛ ፊልሞች መካከል የወደድከው አለ?
“የመጨረሻዋ ቀሚስ” ጥሩ ነው፡፡ “ኒሻን” የተለፋበት ቆንጆ ፊልም ነው፡፡ ኮሜዲ የሆነው “ኢምራን” ጥሩ ነው፡፡ “ሰምና ወርቅ” በጣም ቆንጆ ነው፡፡ ሁሉንም ፊልም አያለሁ፡፡ ግዴታም አለብኝ፤ በሲኒማ ቤቴ ምክንያት፡፡ ዘንድሮ የወጡትን ፊልሞች ሁሉ ለመዘርዘር ጊዜም የለንም፡፡ ልቤ ውስጥ የቀሩትን ፊልሞች ከሞላ ጐደል ጠቅሼልሃለሁ፡፡
ድርጅትህም ስምህም ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ስለ ሴባስቶፖል መድፍ ፊልም ለመስራት አስበህ ታውቃለህ?
ሴባስስቶፖል ለኔ የመጀመርያው የቴክኖሎጂ ሙከራ ነው፡፡ መድፍ ነው፡፡ እኔ የምመራው የፊልም ድርጅት የእኔ መድፍ ነው፡፡ እስካሁን ስድስት ተኩሼበታለሁ፡፡ ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝ አስር እያልኩ እተኩሳለሁ፡፡ ታሪክን አጣቅሼ የራሴን አርማ ለማውጣት ከሴባስቶፖል የበለጠ የለም፡፡ አፄ ቴዎድሮስና ገብርዬ ያሉዋቸውን ታሪኮች ፊልም የማድረግ ህልም አለኝ፡፡ አንድ ቀን ይሰራል፤ ግን ጥናት ይፈልጋል፡፡
ከ”ሦስት ማእዘን” ቀጥሎ ምን እንጠብቅ?
“ሦስት ማእዘን” ቁጥር ሁለት ይከተላል፡፡ ቀረፃው ተጠናቋል፡፡ “ሦስት ማእዘን” ቁጥር ሦስትም አለ፡፡ ምንአልባት ይኸው ፊልም እስከ አስር ሊቀጥል ይችላል፡፡ መፅሔት ተፈራ የምትባል ልጅ ያመጣችው “ሀገር” የሚል የፊልም ፅሁፍም አለ፡፡ የሷን ቆንጆ ድርሰት እንደገና እያዋቀርኩት ነው፡፡ እሱን የመስራት እቅድ አለኝ፡፡ ዳግማዊ ፈይሳ የፃፈው “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ” የሚል ፅሁፍም በፕሮጀክት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከዚያ “ግድብ” የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለውን ግን እወስናለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ምን አደረግህላት፣ ኢትዮጵያስ ምን አደረገችልህ?
ኢትዮጵያ ወለደችኝ፤ አሳደገችኝ፡፡ እኔ ምን እንዳደረኩላት አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የማደርገው ነገር በሙሉ ለመኖር፣ ለራሴ ደስታ ለማግኘት፣ ህይወት ጣፋጭ እንድትሆንና ልጆቼን ለማሳደግ በማደርገው ሩጫ ውስጥ የሚካተት ስለሆነ፣ ለኢትዮጵያ ይህን አደረግሁላት ልል አልችልም፡፡

 

 • ሮበርት ዳውኒንግ ጁኒየር፤ 75 
 • ሚሊዮን ዶላር
 • ቻኒንግ ታተም፤ 60 ሚሊዮን ዶላር
 • ሂውጅ ጃክማን፤ 55 ሚሊዮን ዶላር
 • ማርክ ዎልበርግ፤ 52 ሚሊዮን ዶላር
 • ዘ ሮክ ወይም ድዋይን ጆንሰን፤ 46 
 • ሚሊዮን ዶላር
 • ሊያናርዶ ዲካርፒዮ፤ 39 ሚሊዮን ዶላር
 • አዳም ሳንድለር፤ 37 ሚሊዮን ዶላር
 • ቶም ክሩዝ ፤ 35 ሚሊዮን ዶላር
 • ዴንዘል ዋሽንግተን፤ 33 
 • ሚሊዮን ዶላር
 • ሊያም ኔሰን፤ 32 ሚሊዮን ዶላር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትርን ላለፉት ሁለት አመታት በተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ በቆዩት አቶ ደስታ ካሳ ምትክ አርቲስት ተስፋዬ ሽመልስ የትያትር ቤቱ አዲስ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ተሾመ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተፈረመ የሹመት ደብዳቤ የደረሰው አርቲስት ተስፋዬ፤ ከሐምሌ 4 ጀምሮ ትያትር ቤቱን እንዲመራ በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡ መደበኛ ሥራውን ከመጀመሩ በፊትም ዘንድሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በተሾሙት አቶ ሙልጌታ ሰኢድ አማካኝነት ከትያትር ቤቱ ሠራተኞች ጋር ተዋውቋል፡፡ በትያትር ፀሃፊነቱ የሚታወቀው አርቲስት ተስፋዬ፤ “ስንብት” እና “ሰማያዊ አይን” የተሰኙ ትያትሮችን ለመድረክ ማብቃቱ ይታወቃል፡፡
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጋዜጠኛነት የሰራው አርቲስቱ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ የአየር ሰአት ገዝቶ የራሱን ፕሮግራም ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

የ“አለ ኪነጥበባት” ትምህርት ቤት ሰዓሊዎች ከ“ነፃ አርት ቪሌጅ” ጋር በመተባበር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ስለ ሥዕል እና ቅርፃ ቅርፅ ያላቸው ግንዛቤ እንዲዳብር “ሰምና ወርቅ” የተሰኘ የጐዳና ላይ ትርዒት በማዘጋጀት የመነጋገርያ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ባለፈው ረቡዕ የቀረበው ዝግጅት በ”አለ ኪነጥበባት” ትምህርት ቤት ተጀምሮ ከአራት ሰአታት የከተማዋ ጉብኝት በኋላ የተጠናቀቀ ሲሆን አራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ተክለሃይማኖት፣ ሜክሲኮ፣ ራስ መኮንን ድልድይ፣ መርካቶና ጃንሜዳን ያካተተ ነው፡፡ በጐዳና ትእይንቱ ሰዓሊ ታምራት ገዛኸኝ፣ ተስፋሁን ክብሩ፣ ዳንኤል አለማየሁ፣ ሙልጌታ ካሳ እና ለይኩን ናሁሰናይ እና ሌሎች ተሳትፈዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን፣ ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ እና የውጭ አገር ኮሙኒቲ አባላት በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡

 

“የሰው ነገር” የተሰኘ አዲስ የሬዲዮ መዝናኛ ፕሮግራም ነገ በሸገር ኤፍኤም 102.1 እንደሚጀመር ማርቭል ፕሮሞሽን እና ኮሙኒኬሽን አስታወቀ፡፡ በየሳምንቱ እሁድ በ8 ሰዓት የሚቀርበውን ዝግጅት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኞች የነበሩት ሲሳይ ጫንያለው፣ ዘላለም ሙላቱ፣ ብስራት ከፈለኝና ስዩም ፍቃዱ እንደሚያቀርቡት ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ “የሰው ነገር” በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በስዕል እና ሌሎች የጥበብ ዘርፎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን ፕሮግራሙ መዝናኛና ቁምነገርን በሚዛናዊነት እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡