Administrator

Administrator

አሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን ገደለ
የሟች ቤተሰቦች ሐዘን ተቀምጠዋል - በኢንተርኔት ፎቶና ቪዲዮ አይተው


በሊቢያ የአሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ታጣቂዎች፣ ’30 ኢትዮጵያዊያን ክርስትያኖችን ገድለናል’ ብለው በቪዲዮ የተቀረፀ አሰቃቂ የጭካኔ ግድያ ያሰራጩት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነው። በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በደረሰው ዘረኛ ጥቃት ማግስት፣ በሊቢያ ሲቪል ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የተፈፀመው የአሸባሪ ቡድን ዘግናኝ ግድያ፤ የኢትዮጵያውያን ሐዘንና ቁጭት አክብዶታል።
በኢንተርኔት የተሰራጨው ቪዲዮና ፎቶ፣ የሟቾቹን ማንነት ወዲያውኑ ለማወቅና ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ለብዙዎች አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ለቤተሰቦች ግን አጠራጣሪ አልነበረም። ወላጆችና ቤተሰብ፣ ወንድምና እህት፣ ጎረቤትና ወዳጆች ሁሉ ውስጥን በሚያደማ ቅፅበታዊ ሐዘን ነው የተመቱት።  
በአዲስ አበባ የኢያሱ ይኩኖአምላክ እና የባልቻ በለጠ ቤተሰቦች ድንገተኛ መርዶ የደረሳቸው እሁድ እለት ነው። በሰላሳዎቹ ዕድሜ ላይ የነበሩት ኢያሱና ባልቻ በአንድ ሰፈር ውስጥ ያደጉ ጎረቤታሞች ናቸው - በቀድሞው ወረዳ 21 ቀበሌ 25፤ በአሁኑ ወረዳ 10። የሟቾቹ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት አጠገብ ለአጠገብ ስለሆነ ለቅሶውም አንድ ላይ ነው፡፡
ኢያሱና ባልቻ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ወደ ሊቢያ የሄዱት አንድ ላይ እንደሆነ የገለፀልን የኢያሱ ወንድም፤ የሊቢያውን የግድያ ወሬ የሰማው እሁድ ዕለት ነው - ስልክ ተደውሎ። የደወለለት ሰው፣ “የናንተ ሰፈር ልጆች ሊታረዱ ሲሉ የሚያሳይ ፎቶ በፌስቡክ ተለጥፏል” ብሎ ሲነግረው፤ በደንጋጤ “እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀ። “የወንድሜን ስም ጨምሮ ነገረኝ፤ የወንድሜን ስም አያውቅም ነበር” ይላል የኢያሱ ወንድም።
“የኔ ፌስቡክ ስለማይሰራ ጓደኛዬ ጋር ሄጄ አየሁ። በደንብ ስላልታየኝ እንደገና ከምሽቱ አራት ሰአት ስንከፍት ወንድሜን ተንበርክኮ አየሁት። ባልቻን ደግሞ ቀይ ቱታ ካደረጉት መሀል ለየሁት፡፡ ለእናቴ ከመንገሬ በፊት ለሩቅ ዘመዶች ለመናገር እያሰብኩ እያለ እነሱ ቀድመው ሰምተው ለቅሶ ላይ አገኘኋቸው” ብሏል የኢያሱ ወንድም።
ኢያሱ ኳታር ሰርቶ የተወሰነ ገንዘብ ይዞ ስለመጣ የባልቻንም ወጪ ሸፍኖለት ነው አብረው የሄዱት። ከኢትዮጵያ ወጥተው በሱዳን ጉዞ የጀመሩት ከሁለት ወር በፊት ነው። “ሱዳን እያሉ በስልክ እንገናኝ ነበር። ገንዘብ ሲያስፈልጋቸው እልክላቸው ነበር” የሚለው የኢያሱ ወንድም፤ “ወደ ሊቢያ ከተሻገሩ በኋላ ግን ስልክ ቁጥር እሰጥሃለሁ ቢለኝም አንገናኝም ነበር” ብሏል።  
 

 ሶስት ኢትዮጵያውያን በጥቃቱ ህይወታቸው አልፏል
- ብዙዎች ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ በእሳት ተለብልበዋል
“ስደተኞችን በጉያችን ይዘን የምናባብልበት ጊዜ ማብቃት አለበት!” - የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ልጅ
“ስደተኞች ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደመጡበት መመለስ አለባቸው!” - የዙሉ ንጉስ ዝዌሊቲኒ  
    ከሶስት ሳምንታት በፊት...
እትብታችን በተቀበረባት አፈር ላይ የሌሎች አገራት ዜጎች ተደላድለው ተቀመጡ፣ የዕለት እንጀራችንን ነጠቁ፣ ሃብት አፈሩ በሚል ሰበብ የተበሳጩ ደቡብ አፍሪካውያን ጎበዛዝት፣ በቁጣ ነድደው ወደ አደባባይ ወጡ። ቆንጨራቸውን ይዘው፣ ከላይ እስከ ታች ታጥቀው፣ ደም ሊያፈስሱ ተንደረደሩ፡፡
ለአመታት ጊዜ እየጠበቀ ሲፈነዳ የቆየውና ከወራት በፊት በሶዌቶ ዳግም የተቀሰቀሰው የጥላቻ መንፈስ ያደረባቸው እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያን፣ በኢስፒንጎና ቻትስዎርዝ ከተሞች የሚገኙ የውጭ ዜጎችን ሱቆችና ግሮሰሪዎች በእሳት አነደዱ፡፡ ከእሳት የተረፉትም ዘረፉ፡፡
ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፤ ጥፋቱን ለማስቆም የፓርላማ አባላትንና ሚኒስትሮችን የያዘ ግብረ ሃይል አቋቁመው እየሰሩ እንደሚገኙ ቢያስታውቁም፤ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልታየም፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ይህንን የጥፋት እሳት ለመግታት ደፋ ቀና ሲል ቢሰነብትም አልተሳካለትም፡፡ ቁጣና ጥፋቱ በያቅጣጫው መሰራጨቱን ቀጠለ፡፡ ወደ ክዋማኩታ... ወደ ኡምላዚ... ወደ ሌሎች የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ተዛመተ፡፡ አገሬው ስደተኛውን እያሳደደ ማጥቃቱን ገፋበት፡፡ ሰርቼ ሰው እሆናለሁ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሌሎች አፍሪካ አገራት ስደተኞች፣ ከጥፋቱ ለማምለጥ በየአቅጣጫው ተበተኑ፡፡ ላባቸውን አፍሰው ያፈሩትን ሃብትና ንብረት ታግለው ለማዳን የደፈሩ ጥቂቶችም፣ ከሞት ጋር ተፋጠጡ፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ግን፣ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በቡድን የተንቀሳቀሱትን እነዚሁ ስደተኞች ሊያግዛቸው አልፈለገም፡፡ ይልቁንም ባለፈው ረቡዕ በአስለቃሽ ጭስ በተናቸው፡፡
ባለፈው ሳምንት አርብ፣ ምሽት ላይ...
የውጭ አገራት ስደተኞችን ለማጥቃት የወጡት ደቡብ አፍሪካውያን፣ ፊታቸውን ከደርባን በስተ ደቡብ ወደምትገኘው ኡማልዚ ከተማ አዞሩ፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የስደተኞች ሱቆችን በእሳት አቀጣጠሉ፡፡ በሱቆቻቸው ውስጥ እያሉ በድንገተኛው የእሳት ወላፈን ከተለበለቡት የውጭ አገራት ስደተኞች መካከል፣ ሁለቱ ወንድማማች ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ አንደኛው በደረሰበት ቃጠሎ ለሞት ተዳርጓል፡፡
የያዝነው ሳምንትም በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ስደተኞች የመከራ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ምሽት...
ይባስ ብሎም የአገሪቱ መሪ ጃኮብ ዙማ ወንድ ልጅ፣ የውጭ አገራት ዜጎችን በጉያችን ይዘን የምናባብልበት ጊዜ ማብቃት አለበት ሲል አፍ አውጥቶ በመናገር ጥፋቱን የባሰ የሚያቀጣጥል ድርጊት ፈጸመ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ይሄን ባለባት ምሽት፣ አገሬው ለባሰ ጥፋት ታጥቆ ተነሳ፡፡ የደቡብ አፍሪካዋ የወደብ ከተማ ደርባን ጎዳናዎች፣ ስደተኞችን ለማጥፋት ቆርጠው በተነሱ፣ እሳትና ስለት በታጠቁ ዜጎች ተጥለቀለቁ፡፡ በከተማዋ ጥፋት ሆነ፡፡
በርካቶች ራሳቸውን ከሞት ለማዳን ድቅድቁን ጨለማ እየሰነጠቁ፣ እግራቸው የመራቸውን አቅጣጫ ተከትለው ሮጡ፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፤ ከሁለት ሺህ በላይ ስደተኞች በፖሊስ ጊዚያዊ መጠለያ ካምፖች፣ በስታዲየሞችና በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተጠለሉ፡፡
በዚህ የጥፋት ዘመቻ፣ ሰሞኑን ብቻ የ14 አመት ዕድሜ ያለውን ብላቴና ጨምሮ ሁለት የውጭ አገራት ዜጎችና 3 ደቡብ አፍሪካውያን ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ ፖሊስም በዚህ የጥፋት ዘመቻ ተካፍለዋል ያላቸውን 74 ያህል ሰዎች በቁጥጥር ውስጥ ማዋሉን አስታውቋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵውያን ኮሚኒቲ መሪ ኤፍሬም መስቀሌን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ባለፈው ማክሰኞ እንደዘገበው፣ ባለፈው አርብ ሱቁ በእሳት የጋየበትን ግለሰብ ጨምሮ 3 ኢትዮጵያውያን በጥቃቱ ህይወታቸው አልፏል፡፡
ይህንን የዘረኝነትና የጥፋት ዘመቻ ለመቃወም ያለመና 10 ሺህ ያህል ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ በደርባን ከተማ ተካሂዷል። ማላዊ ባለፈው ረቡዕ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎቿን ለማውጣት መዘጋጀቷን ስትገልጽ፣ ሞዛምቢክም በበኩሏ፤ ከደቡብ አፍሪካ በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ የስደተኞች መሸጋገሪያ ካምፕ ማዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 ሶዌቶ ውስጥ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ጥቃት፣ ከ62 በላይ የሌሎች አገራት ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከሰሞኑ የተከሰተውን ጥፋት ያቀጣጠለው ዝዌሊቲኒ የተባሉ የዙሉ ንጉስ የተናገሩት ንግግር ነው እንደተባለ ጠቁሟል፡፡
እኒሁ ተሰሚነት ያላቸው ንጉስ ባለፈው ወር ስደተኞች ወደየአገራቸው መመለስ አለባቸው ብለው ተናግረዋል በሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው እንደሆነ ዘገባው ገልጾ፣ ይሄም ሆኖ ንጉሱ ግን እንዲህ ብለው አለመናገራቸውን በመግለጽ፣ ወቀሳውን ማጣጣላቸውን አክሎ አስታውቋል።
በተለይም ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያንን ታላሚ አድርጎ የተጀመረው የዘረኝነት ጥቃት፣ አሁን ወደ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ስደተኞች መስፋፋቱን የዘገበው ቪኦኤ፤ አገሬው የስደተኞቹን ንብረት በመዝረፍና በእሳት በማጋየት እንዲሁም በጭካኔ በመደብደብ ተግባሩ እንደገፋበት አመልክቷል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግስት ጥቃቱን ያወገዘ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ የተለያዩ ሚኒስትሮች ንግግር አድርገዋል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ሚኒስትር ናቲ ንህሌኮ፣ጥቃቱ አፍሪካውያን የራስ ላይ ጥላቻቸውን ያንጸባረቁበት መንገድ ነው ማለታቸውን News24.ዘግቧል፡፡
“አንዳንዶቻችን የውጭ ዜጎች ጥላቻ ነው ብለን ለማሰብ ተቸግረናል፡፡ የተወሰነ የፖለቲካ ችግርን የሚወክልም ይመስለኛል፡፡ የአውስትራሊያ ዜጎች በመንገድ ላይ ሲሳደዱ አታዬም፤ እንግሊዞች መንገድ ላይ ሲሳደዱ አታዩም፡፡” ብለዋል የፖሊስ ሃላፊው፡፡
እሳቸው እንዲህ ይበሉ እንጂ ፓኪስታኖችና ባንግላዲሾች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የሚያመለክቱ ዘገባዎች አሉ፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ ኖሲቪዌ ማፒሳ-ንኳኩላ በበኩላቸው፤ “የውጭ ዜጎች በመሆናቸው ብቻ ንጹሃን ላይ ጥቃት ከሚፈጽሙ ወገኖች ጋር ደቡብ አፍሪካውያን መተባበር የለባቸውም” ብለዋል፡፡

ኤምባሲው በጥቃቱ ማዘኑን ገልጿል
“ኢትዮጵያውያን ለደቡብ አፍሪካ ህዝብ ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አሁን መጠቀሚያ ሊያደርጉት አይገባም”  -  (የፕሬዚዳንቱ ልጅ)
“ከደቡብ አፍሪካ አመራሮች ጋር እየተገናኘን ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው”  - (ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር)

ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተወሰደ ያለው የጥቃት እርምጃ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውን ስደተኞች የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ መምጣታቸውን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ድርጊቱን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ሲሆን ጥቃቱ አሁንም እልባት አለማግኘቱንና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ስደተኞች በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሆኑ እነዚሁ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
እስከአሁን የሶስት ኢትዮጵያውያንን ህይወት የቀጠፈውና የብዙዎችን ሰርቶ የመኖር ተስፋ ያጨለመው የሰሞኑ የደቡብ አፍሪካ ጥቃት፣ አድማሱን እያሰፋና እየተባባሰ ሄዷል የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ፤ ጥቃቱ እንዳይፈፀም የሚያደርግና ስጋታችንን የሚቀንስ ምንም አይነት እርምጃ በአገሪቱ መንግሥትም እየተወሰደ አይደለም ብለዋል፡፡ የአገራችን መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ልጅ ኤድዋርድ ዙማ፤ ጥቃቱን አስመልክቶ በሰጠው ቃለ ምልልስ፤ እርምጃው አግባብ መሆኑን ጠቁሞ ጥቃቱ መወሰድ ያለበት በአፍሪካውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ያለምንም ህጋዊ ሰነድ በደቡብ አፍሪካ እየኖሩ ባሉ የውጪ ዜጎች ላይ ጭምር ነው። እነሱን በማባበል ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፡፡ ቀደም ሲል ስለአደረጉልን ድጋፍ እናመሰግናለን፡፡ ያንን ድጋፋቸውን ግን ለአሁን መጠቀሚያ ማድረግ አይችሉም” ብሏል፡፡
“በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጪ አገር ዜጎች በሙሉ ወደሚመለከተው የመንግስት አካል ሄደው መመዝገብ አለባቸው፤ ምን እናውቃለን… ISISን ወይም አልሻባብን እየረዱ ሊሆኑ ይችላሉ” ሲልም የፕሬዚዳንቱ ልጅ ተናግሯል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በበኩላቸው፤ በስደተኞቹ ላይ የተፈፀመውን ጥቃቅ አውግዘው “በችግራችን ወቅት ነፃነታችንን እንድናገኝ የእርዳታ እጃቸውን ዘረጉልን እንጂ አላሳደዱንም፤ ይህንንም ማስታወስ ይገባናል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የደቡብ አፍሪካውን ጥቃት አስመልክተው ሲናገሩ፤ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሙሉ ጊዜውን ለጉዳዩ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ከአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርና ከሌሎች የደቡብ አፍሪካ አመራሮች ጋር ተገናኝተው ችግሩን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ “ሚኒስትሯ በሁኔታው በጣም እንዳዘኑና እንዳፈሩበት ነግረውናል” ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካውያን ቤታቸው ነች፤ በነፃነት ትግላችን ወቅት ያደረጋችሁልንን ድጋፍ አንረሳውም፤ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን” ብለውናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያውያኑ ሁሉ ዜጎቻቸው የሰሞኑ ጥቃት ኢላማ የሆኑባቸው የዚምባቢዌና ማላዊ መንግስታት፣ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ጥቃት በማውገዝ ድርጊቱ እንዲቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአገሪቱ ኤምባሲ አስገብተዋል፡፡ በማላዊም በዚህ ጉዳይ የተሰባሰበ ቡድን የማላዊ ዜጎች የደቡብ አፍሪካ ምርቶችን ከመግዛት እንዲቆጠቡና በደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ እንዳይጠቀሙ ጠይቋል፡፡  
በሌላ በኩለ፤በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ ኢምባሲ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፣ የአገሪቱ ፖሊስ ዜጎቹንና የውጭ አገራት ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና ጥቃትና ዝርፊያ የሚፈጽሙ ህገወጦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የአገሪቱ መንግስት በውጭ አገራት ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለማስቆምና ጸጥታን ለማስፈን የተቀናጀ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡ ይህም ሆኖ ከችግሩ ስፋት አንጻር የበለጠ የተቀናጀና ዘላቂነት ያለው ስራ መስራት የሚገባ መሆኑ ስለታመነበት አዲስ አቅጣጫ እየተቀየሰ መሆኑንም ገልጧል፡፡
ደቡብ አፍሪካውያን በታሪክ አጋጣሚ ከአገራቸው ወጥተው በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ይኖሩ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለደቡብ አፍሪካ የነጻነትና የአመራር ንቅናቄዎች ያደረገውን ድጋፍ ዛሬም በክብር እናስታውሰዋለን ብሏል፡፡
የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ትስስር ለወደፊትም ይቀጥላል፤ ለአፍሪካ ልማት እውን መሆን የጀመርነው የጋራ ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያለው ኢምባሲው፣ በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች የተሰማውን ሃዘን ገልጾ፣ የቆሰሉትም በቶሎ እንዲያገግሙ ያለውን መልካም ምኞት ገልጧል፡፡

የአለም ባንክ ቡድን አባል የሆነው ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ተቀማጭነቱ በኢትዮጵያ ለሆነው አፍሪፍሎራ ግሩፕ የተባለ የአበባ አምራች ኩባንያ ማስፋፊያ የሚውል የ90 ሚሊዮን ፓውንድ (2ቢ.880ሚ. ብር ገደማ) የገንዘብ ብድር ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ከ9ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት አፍሪፍሎራ ከአለም ባንክ በሚያገኘው የገንዘብ ብድር የአበባ ምርቱን 60 በመቶ ለማሳደግ፣ ውሃን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመገንባት፣ የፈጠረውን የስራ ዕድል ከ50 በመቶ በላይ ለማሳደግና ሌሎች የማስፋፊያ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያውለው ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አፍሪፍሎራ በአበባ ምርት ዘርፍ የስራ ዕድል በመፍጠር በኢትዮጵያ ቀዳሚው እንደሆነ የጠቆመው የኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን መግለጫ፣ በቀጣይም አለማቀፍ የአካባቢና የማህበራዊ ዘላቂነት መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ ምርቱን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
በዝዋይ አካባቢ በሚገኘው የኩባንያው ዋና እርሻ እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን በቀጥታ፣ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እያደረገ  ሲሆን ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታልና ስቴዲየም በመገንባት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ባለፈው የፈረንጆች የበጀት አመት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ለሚከናወኑ የግብርና ቢዝነስ ፕሮጀክቶች 686 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም መግለጫው አክሎ አስታውቋል፡፡

ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል
ዕጣ የደረሰው በዱባይ የንግድ ትርኢት ይሳተፋል

ታላቱ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ (ኮካኮላ) ጋር በመተባበር ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ የነበረውን የኮካኮላ የጎዳና ላይ ውድድር በ “ዳሳኒ የጎዳና ሩጫ” መተካቱን አስታወቀ፡፡ በቅርቡ በሚካሄድ የጐዳና ሩጫ ላይ ላሸነፉ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡
የሩጫው አዘጋጆች ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ ዳሳኒ ውሃ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያለው የኮካኮላ ምርት መሆኑን ጠቅሰው፣ ውድድሩ ከስም ለውጥ በስተቀር አራት ዓመት ሲካሄድ ከቆየው ውድድር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 15ሺህ ተሳታፊዎች የተሳተፉበት ትልቅ የጐዳና ላይ ውድድር ማካሄዱን ጠቅሰው ዘንድሮ በሁለቱም ፆታ በሚካሄደው ውድድር 18ሺ ያህል ራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በመጪው ሰኔ 7 በዳያስፖራ አደባባይ ለሚካሄደው ውድድር ሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን ምዝገባ እንደሚጀመር ጠቅሰው ሩጫውም 7.5 ኪ.ሜ ለጤና ሯጮች፣ 15 ኪ.ሜ ደግሞ ለአትሌቶች እንደሚሸፍን የተገለፀ ሲሆን አሸናፊዎች እስካሁን በኢትዮጵያ ታሪክ ለሯጮች ተሰጥቶ የማያውቅ የገንዘብና የቁሳቁስ ሽልማት እንደሚሸለሙ አስታውቀዋል፡፡
በወንድና በሴት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው ውድድር፤ ከ1ኛ እስከ 10ኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች 285 ሺህ ብር የተዘጋጀ ሲሆን በሁለቱም ፆታ 1ኛ የሚወጣ 60ሺ ብር፣ 2ኛ 30 ሺህ ብር፣ 3ኛ 20,500 ብር እንደሚሸለም ታውቋል፡፡ በውድድሩ ለሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች በ2008 በዱባይ በሚካሄደው የንግድ ትርዒት ለመሳተፍ የሚያስችል የዕጣ ዕድሎች የተዘጋጁ ሲሆን ዕጣው የደረሰው ተወዳዳሪ የደርሶ መልስ ቲኬትና የሁለት ቀን ወጪ እንደሚሸፈንለት ተጠቁሟል፡፡ የላፕቶፕና የሞባይል ቀፎ ዕጣ ዕድሎችም እንደተዘጋጁ ታውቋል፡፡

ሲኒማ ቤቱ ህገወጥ የንግድ አሰራርን ይከተላል ተብሏል

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አቃቤ ህግ፤ በሴባስቶፖል ኢንተርቴይንመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ክስ መሰረተ። ክሱ የተመሰረተውና የታየው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ረፋድ ላይ በባለስልጣኑ አስተዳደር ችሎት ሲሆን የባለስልጣኑ አቃቤ ህግ ሴባስቶፖል በፈጸመው ፀረ ውድድር  የንግድ አሰራር ምክንያት ክሱ እንደተመሰረተበት በክስ ቻርጁ አመልክቷል፡፡
ሴባስቶፖል ክስ የተመሰረተበት ኤግዚቢሽን ማዕከል በሚገኘው ሲኒማ ቤቱ አዳዲስ ፊልሞችን ለማሳየት የሚመጡ ፕሮዲዩሰሮችን ፊልሞቻቸው የሚታዩት ኢዮሃ ሲኒማ ላለማሳየት የሚስማሙ ከሆነ ብቻ እንደሆነ በመግለፅና በፊልም ፕሮዲዩሰሮች ላይ ጫና በማሳደር ተገቢ ያልሆነ የንግድ አሰራር እያካሄደ በመሆኑ ነው ይላል የክስ ቻርጁ፡፡
የሴባስቶፖል ኢንተርቴይንመንት ድርጊት በአቅራቢያው የሚገኘው ኢዮሃ ሲኒማ በገበያው የፊልም አቅርቦት እንዳያገኝና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዳይቀጥል ብሎም ከገበያ እንዲወጣ የሚያደርግ ፀረ-ውድድር የንግድ አሰራር እንደሆነ በክስ ቻርጁ ያተተው የባለስልጣኑ አቃቤ ህግ፤ ድርጊቱም የፌደራል የንግድ ውድድርና የሸማቾችን አሰራር መብት አዋጅን የሚቃረን በመሆኑ ይህን የሚያደርግበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተከሳሹ ድርጅት መልስ ይዞ ለሚያዚያ 8 እንዲቀርብ ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም በዕለቱ የሴባስቶፖል ሲኒማ ባለቤት አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ “ጊዜው አጥሮኛል” በሚል ምክንያት መልሱን ይዞ አልቀረበም፡፡ በእለቱ ተሰይሞ የነበረው የባለስልጣኑ አስተዳደር ችሎት፤ ተከሳሹ ድርጅት መልሱን ይዞ እንዲቀርብ ለሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የኢዮሃ ሲኒማ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዩ ዓለሙ፤ ሴባስቶፖል ባደረሰባቸው ጫና ላለፉት ሁለት ዓመታት በፊልም እጥረት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። “እስከዛሬም ሲኒማ ቤቱን ያልዘጋነው በአንዳንድ ደፋርና የመጣው ይምጣ ብለው ፊልማቸውን ኢዮሃ በሚያስገቡ ፕሮዲዩሰሮች ብርታት ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጇ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቢታገሱም እንዳልተሳካ ገልፀዋል፡፡
የሴባስቶፖል ሲኒማ ባለቤት አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልኩ ባለመነሳቱ ሃሳባቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡

በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በየሳምንቱ ቅዳሜ ለንባብ የምትበቃው “ፍቱን” መጽሄት ከህትመት ታገደች፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የግልም ሆነ የመንግስት ማተሚያ ቤቶች መፅሔቷን እንዳያትሙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ባስተላለፈው መልዕክት የመፅሄቷን አሳታሚ አቶ ፍቃዱ በርታን ለጥያቄ ቢፈልጓቸውም ሊያገኟቸው አለመቻላቸውን ጠቁሟል፡፡ አሳታሚዎቹ፤ ከመንግስት ደረሰኞች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ደረሰኞችን በማሳተም ህገወጥ ስራ ሲሰሩ ተደርሶባቸዋል ያለው የባለስልጣኑ መግለጫ፤ በዚህ ምክንያትም መፅሄቷ ከህትመት ውጪ እንድትሆን ለማድረግ የሚያስችል የፍርድ ቤት ማገጃ ማውጣታቸውንና የትኛውም ማተሚያ ቤት መፅሄቷን ከማተም እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡
“ፍቱን” መፅሄት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አተኩራ በየሳምንቱ ቅዳሜ ለንባብ የምትበቃ መፅሔት ነበረች፡፡

ተመላሽ ኢትዮጵውያኑ በማቆያ ውስጥ ተቀምጠው ክትትል እየተደረገባቸው ነው
የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ወደ አገር ውስጥ አይገቡም ተብሏል፡፡
በሽታው ወደ አገር ውስጥ ቢገባ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

በምዕራብ አፍሪካ አገራት በድንገት ተከስቶ ለሺዎች ሞት ምክንያት የሆነውና ዓለምን ስጋት ላይ የጣለው የኢቦላ በሽታ አሁንም ሥጋት መሆኑ አላበቃም። በበሽታው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት በሽታው ወደተከሰተባቸው አገራት ሄደው ለወራት የቆዩት ኢትዮጵያውያን ኮንትራታቸው በመጠናቀቁ ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ተመላሽ ኢትዮጵያውያኑ ለኢቦላ ክትትልና ቁጥጥር በተዘጋጁት የማቆያ ማዕከላት ውስጥ ሆነው ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኢቦላን አስመልክቶ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ዳዲ ጂማ እንደተናገሩት፤ ኢቦላ የዓለም ስጋትነቱ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቁመው የስጋቱ መጠን ቀደም ብሎ ከነበረው የተለየ አለመሆኑንና ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ ከበሽታው ነፃ መሆኗ መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡ በሽታው በአገሪቱ ቢከሰት እንኳን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በሽታውን በቀላሉና በፍጥነት ለመለየት የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ግዥ መፈፀሙንም ገልፀዋል፡፡
በኢቦላ ወደተጠቁ አገራት በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት አማካኝነት ለስራ የሄዱ ኢትዮጵያውያን የሥራ ኮንትራታቸውን አጠናቀው ወደአገራቸው እየተመለሱ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳዲ፤ እነዚህ ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ለሥራ በቆዩባቸው ጊዜያት ለበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ተመላሾቹ በኢቦላ ክትትል ማዕከል ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ክተትልና ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በመግታት እዚያው ባሉበት ቦታ ላይ ክትትልና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ጠቁመው በዚህም በሽታው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በበሽታው ወደተጠቁ አገራት በመንግስት የተላኩ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችም በቅርቡ የቆይታ ጊዜያቸውን አጠናቀው እንደሚመለሱና በእነሱም ላይ ተመሳሳይ ክትትል እንደሚደረግ ዶ/ር ዳዲ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  

“የኛ” የሬዲዮ ፕሮግራም አምስተኛ ሲዝን ጀምሯል

ታዋቂ ድምጻውያን ለመሆን በሚጥሩ አምስት ወጣት ሴቶች የህይወት ውጣውረድ ዙሪያ የሚያጠነጥነው “የኛ” ፊልም ከዛሬ ጀምሮ በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች ለእይታ እንደሚበቃ ፕሮዲውሰሮቹ አስታወቁ፡፡
ፊልሙ በክልሉ በሚገኙ 26 ከተሞች በትምህርት ቤቶችና የማህበረሰብ አዳራሾች ውስጥ በነጻ እንደሚታይና 40ሺህ ያህል ተመልካቾች ያዩታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡
የኛ በተባለው የሬዲዮ ድራማ ላይ የሚታወቁት ሚሚ፣ ሜላት፣ እሙየ፣ ሳራ እና ለምለም የተባሉት ገጸባህሪያት የሚሳተፉበት ይህ ፊልም፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በኢቢኤስ እና በአማራ ክልል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ልዩ ፕሮግራሞች ለእይታ እንደሚበቃም ተገልጧል፡፡
የናይኪ ፋውንዴሽንና የእንግሊዝ መንግስት አለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዲፊድ) ጥምረት በሆነው ገርል ሃብ ኢትዮጵያ የሚከናወነው የኛ ፕሮጀክት በሸገር ኤፍ ኤም እና በአማራ ክልል ሬዲዮ ጣቢያዎች፤ ሲያስተላልፈው የቆየውን የኛ የሬዲዮ ፕሮግራም አምስተኛ ሲዝን መጀመሩንም የኛ ቤት የተባለው የ3 ተቋማት ጥምረት አስታውቋል፡፡
የኛ የሬዲዮ ድራማ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችና እና በአዲስ አበባ ከ1 ሚሊዮን በላይ አድማጮች እየተከታተሉት እንደሚገኙና፣ ድራማውን ከሚከታተሉት ልጃገረዶች 84 በመቶው በህይወታቸው ስኬታማ ለመሆን የራስ መተማመናቸው እንዳደገና፣ 76 በመቶ የሚሆኑትም ድራማው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲቀጥሉ እንዳነሳሳቸው በጥናት መረጋገጡም ተገልጧል፡፡
የኛዎች በለቀቋቸው ነጠላ ዜማዎችና የቪዲዮ ክሊፖች እንዲሁም በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በሚያቀርቧቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች ተወዳጅነትን ማትረፍ መቻላቸው ይታወቃል፡፡

     የአገራችንን የኢኮኖሚ እድገት የሚያበስሩ ዜናዎችን በየግዜው በሚዲያ እንሰማለን፡፡ ሆስፒታሎች፤ ፋብሪካዎች፤ ት/ቤቶች፤ ድልድዮች ወዘተ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች መንግስት መስራቱን በሰማሁ ቁጥር የላቀ ደስታ ይሰማኛል፤ እሰየው! ብራቮ ኢትዮጵያ እላለሁ፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ሰፋ ባለ እቅድ፤ ብዙ ልፋትና የህዝብ ገንዘብ ፈሶባቸው ለህዝብ አገልግሎት በሚበቁበት ግዜ ይሄንን ትልቅ ስኬት ማክበር አግባብ ነው፡፡ ደስም ይላል፤ የሁላችንም ድል ስለሆነ፡፡
እድለኛ ሆኜ አንዳንድ ምርቃቶች ላይ ብገኝም አብዛኞቹን ያየሁት ግን በቴሌቪዥን ነው፡፡ እነዚህን በዐሎች ስመለከት ግን ሁልግዜ የሚከነክነኝ አንድ ነገር አለ፡፡ አስተውላችሁ እንደሆነ ባለስልጣኖችም ሆነ ተጋባዥ እንግዶች ለምርቃቱ የተዘጋጁ ልዩ ካናቴራዎችና ኮፍያዎች ለብሰው እናያለን፡፡ እነዚህን ካናቴራዎችና ኮፍያዎች በብዛት ለማዘጋጀት ብዙ ብር ያስፈልጋል፡፡ ፅሁፍ ያላቸው ኮፍያና ካናቴራዎች  እያንዳንዳቸው በአማካይ 100 ብር ድረስ ያወጣሉ፡፡ ለአንድ ምርቃት በግምት ከ500 እስከ 1000 ሊዘጋጅ ይችል ይሆናል፤ እንግዲህ ሂሳቡን እናንተ አስሉት፡፡
ጥቅምና ፋይዳ ቢኖረው ግድ ባልሰጠኝ ነበር፤ ግን እነዚህ ካናቴራዎችና ኮፍያዎች አገልግሎታቸው ለዚያች ቀን ብቻ ነው፤ በእለቱ የተገኙት ሰዎች ሌላ ቀን ደግመው የሚለብሱትም አይመስለኝም፡፡ ጥቂቶቹ ቢጠቀሙባቸውም እንኳን ለካናቴራውና ለኮፍያዎቹ ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነፃፀር ከጥቅሙ ጉዳቱ  ያይላል፡፡ በየአመቱ፤ በየክልሉ ስንት የምርቃት በዐል እንደሚደረግ እንግዲህ አስቡት፡፡ አንድ ብዙ የምርቃት በዐል የተካፈለ ጓደኛዬ ሴት ልጅ፤ ‹ቤት ያሉትን ኮፍያዎችና ካናቴራዎች ሰብስቤ ቡቲክ ልከፈትበት--› እያለች በአባትዋ ስትቀልድ ሰምቼአለሁ፡፡ የበዐሉ ዋናውና መሰረታዊ አላማው የመሰረተ ልማቱን ስኬት ማክበር እንጂ ተሳታፊዎቹን በኮፍያና ካናቴራ ማንበሽበሽ አይደለም፤ መንግስትም ይሄን ማድረግ አይጠበቅበትም፡፡  
ለበዐሉ ማስታወሻነትም ከተፈለገ፤ ስለስራው የሚገልፁ ብሮሽሮች፤ መፅሄቶች--- ማዘጋጀት የተሻለና ዘላቂ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ሠው ቤቱም ሆነ ቢሮው ስለሚያስቀምጠው በበዐሉ ላይ ላልተገኙ ወይም በሚዲያ ላልተከታተሉ ሰዎች በማስታወሻነትም በመረጃነትም ለረጅም ግዜ ሊያገለግል ይችላል፡፡
በአገራችን እንጭጭ ኢኮኖሚ ከድህነት ጫና ለመውጣት ገና ዳዴ በምንልበት ወቅት፤ ለምርቃት በሚል ኮፍያና ካናቴራ ማሰራት አላስፈላጊ ወጪ ይመስለኛል፡፡ ይሄንና ሌሎች አላስፈላጊ ወጪዎችን ከዚህም ከዚያም መቀናነስና መቆጠብ ከቻልን ትልቅ የገንዘብ ሀይል ይሆኑናል፤ አንዳንድ አንገብጋቢ የልማት ቀዳዳዎችንም ሊደፍኑልን ይችላሉ፡፡ ግብር ከፋይ ነኝና ጉዳዩ ያገባኛል ብዬ ነው ሃሳቤን የሰነዘርኩት፡፡  በእርግጥ ነገሩ የግል ድርጅቶችን ወይም ግለሰቦችን አይመለከትም።
ኃይለማርያም ገ/ሕይወት- ከቀጨኔ