Administrator

Administrator

Saturday, 31 May 2014 14:42

6ቱ ላጤዎች

የኔ አይን እዚች ላይ
የዚች አይን እሱ ላይ፤
የሱ አይን እዛች ላይ
የዛች አይን እኔ ላይ፤
አቤት ክፉ እጣ
የሃብታም ቤት ጠኔ፡፡
ሶስቱ ኮረዳዎች
ሶስቱ ኮበሌዎች
ይኸው ስንት ዘመን መለያ ስማችን “ስድስቱ ላጤዎች”
(አንድነት ግርማ)


=========

እኔና እሱ
የኔ አበቃቀል፤
በጌሾና ብቅል፡፡
በጥንስስ መጥቼ፤
እሱኑ ጠጥቼ፤
አለሁት በዋዛ፤
እንዲሁ ስንዛዛ፡፡
ያ…ግን ጐረቤቴ፤
ያለው ፊት ለፊቴ፤
ጥንስሱ በወተት፤
ዕድገቱ በእሸት፡፡
እሱ ማር ወተቱን፤
ብርቱካን ካሮቱን፤
ክትፎና ዱለቱን፡፡
አኗኗሩን አውቆ፤
አካሉን ጠብቆ፤
አምሮበታል ፋፍቶ፤
ቦርጩ ከፊት ገፍቶ፡፡
እኔ ግን መጥጬ፤
ቡቅርን ለጥጬ፤
ጨጓራዬን ልጬ፤
በጌሾ ለፍልፌ፤
በሱ ተለክፌ፤
በጥንስስ መንምኜ፤
እንዲሁ ባክኜ፤
ይኸውና አለሁት፤
እሱን እያየሁት፡፡
በመጨረሻ ግን ጥሎ አይጥለኝ ጌታ፤
ድንገት አሳስቦኝ እንዲያ ወደ ማታ፤
አስታወሰኝና ሰጠኝ መፅናናቱን፤
እኔም እሱም ሞተን ከሳጥን መግባቱን፡፡
(ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ)

         በደቡብ ክልል በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን፣ በኮንሶ ወረዳ በካራት ከተማ የተዘጋጀው የባህል ፌስቲቫል ዛሬ ይከፈታል፡፡ የኮንሶ ወረዳ አስተዳደር ባለፈው አመት ተመሳሳይ የባህል ፌስቲቫል ያዘጋጀ ሲሆን የፌስቲቫሉ አላማ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደረጋትን በዓለም ቅርስ መዝገብ የተመዘገበውን የኮንሶ ባህላዊ መልክአ ምድር ጨምሮ በወረዳው ያለውን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር እንዲሁም የአለም አቀፍ ጐብኚዎችን ትኩረት ለመሳብ እንደሆነ የኮንሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በላቸው ተናግረዋል፡፡
ዛሬ በሚከፈተው በዚህ የባህል ፌስቲቫል ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን የኮንሶ ዲስትሪክት ሆስፒታል ምረቃ፣ በተለያዩ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም፣ የመሰረተ ልማት ጉብኝት፣ የጐዳና ላይ የባህል ትዕይንትና ኮንሶን ለአለም የሚያስተዋውቁ ሌሎች ትርኢቶች ይገኙበታል ተብሏል፡፡ ፌስቲቫሉ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፊታችን ሰኞ የሚካሄድ ሲሆን በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ላለፉት 40 ዓመታት በማህበረሰብ እድገትና በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጐ እየሰራ ሲሰራ የቆየው “ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች ኢትዮጵያ”፤ ለአርቲስቶችና ጋዜጠኞች የጉብኝት ፕሮግራሞችን ያዘጋጀ ሲሆን ጉብኝቱ የድርጅቱን 40ኛ ዓመት በዓል በማስመልከት የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ድርጅቱ የሚከተለው የህፃናት አስተዳደግ ፍልስፍና፤ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞችና ታዋቂ ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ የበለጠ እንዲሰሩ የሚያነሳሳቸው እንደሚሆን ኤስ ኦ ኤስ የላከው መግለጫ ይጠቁማል፡፡ ግንቦት 29 ከጠዋቱ 2፡30 በዋናው የድርጅቱ ቢሮ በጋዜጣዊ መግለጫ የሚጀመረው ፕሮግራሙ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ተቋማቱን በማስጐብኘት እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስነ - ጥበባት ኮሌጅ የማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎች ከህንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር፣ በአገራችን የመጀመሪያ የተባለውን የአጫጭር ፊልሞች ፌስቲቫል ያካሂዳሉ፡፡ ፌስቲቫሉ ዛሬና ነገ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሚገኘው የባህል ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን አላማውም የአጫጭር ፊልሞችን ጥበብ ለአገራችን ተመልካቾች ለማስተዋወቅና በአገራችን ለሚገኙ የአጫጭር ፊልም ፀሐፊዎች፣ አዘጋጆች፣ ፕሮዱዩሰሮችና ተዋንያን እውቅናና ክብር ለመስጠት እንዲሁም ሙያቸውን ለማበረታታት እንደሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በላከው መግለጫ አስታውቋል፡ 

የኒታ የቀለም ማዕከል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ በሆኑት በኬሚካል መሐንዲስ ጌታሁን ሔራሞ ባለፉት አስር ዓመታት ከወጣት ሠዓሊያን የተሰበሰቡ 80 የሥዕል ስራዎች የተካተቱበት ዐውደ ርዕይ የፊታችን ሐሙስ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተመርቆ ይከፈታል፡፡ “የማይሸጡ ሥዕሎች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው አውደርዕይ ላይ የሚቀርቡት የሥዕል ሥራዎች፤ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በተመረቱ የዘይትና አክሪሊክ የሥዕል ቀለሞች የተሰሩ መሆናቸው አውደርዕዩን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል አዘጋጁ፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ለተመልካቾች ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡ 

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር የተዘጋጀው “ቅጥልጥል ኮከቦች” የተሰኘ ቴአትር የፊታችን ሰኞ ይመረቃል፡፡ ቴአትሩ የሙሉ ሰዓት ሲሆን ሰኞ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ለጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች በቴአትር ቤቱ አዳራሽ እንደሚቀርብ ታውቋል፡

በካህሳይ አብርሃ በተፃፈው “የአሲንባ ፍቅር” መፅሃፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት እንደሚደረግ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ አስታወቀ፡፡
ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡ ሲሆን ተጨማሪ የውይይት ሀሳቦች በፕ/ር ገብሩ ታረቀ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

ርዕስ - ውለታ ለነብስ (የግጥም መድበል)
ደራሲ - እዩኤል ደርብ
የመፅሃፉ መጠን - በ89 ገፆች 88 ግጥሞች
ዋጋ - 46 ብር
*          *           *
ርዕስ - የነጎድጓድ ልጆች (ልብወለድ)
ደራሲ - ቃልኪዳን ኃይሉ
የመፅሃፉ መጠን -208 ገፆች
ዋጋ - 46ብር

Saturday, 31 May 2014 14:32

የጸሐፍት ጥግ

የአንዱ ደራሲና የሌላው ደራሲ ቃል አንድ አይደለም፡፡ አንዱ ሃሞቱን ቀዶ ሲያወጣ፣ ሌላው ከካፖርቱ ኪስ መዥርጦ ያወጣል፡፡
ቻርልስ ፔጉይ
በጣም ልታነበው የምትፈልገው መፅሃፍ ካለና ገና ያልተፃፈ ከሆነ፣ ራስህ ልትፅፈው ይገባል፡፡
ቶኒ ሞሪሰን
ከጥሩ ፀሐፊ የምወድለት የሚለውን ሳይሆን የሚያንሾካሹከውን ነው፡፡
ሎጋን ፒርሳል
ወረቀትህን በልብህ እስትንፋሶች ሙላው፡፡
ዊሊያም ዎርድስ ዎርዝ
የጨረቃዋን መፍካት አትንገረኝ፤ የብርሃኑን ፍንጣቂ በተሰበረ መስተዋት ላይ አሳየኝ፡፡
አንቶን ቼኾቭ
አንዳንዴ ቀለምና ወረቀት እፍ ፍያሉ ፍቅረኛሞች ይሆናሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ወንድምና እህት ናቸው። አልፎ አልፎ ደግሞ የለየላቸው ጠበኞች፡፡
ቴሪ ጉሌሜትስ
ተለዋጭ ዘይቤዎች (Metaphors) ግዙፉን እውነት በትንሽዬ ቦታ የመያዝ ብልሃት አላቸው።
ኦርሶን ስኮት ካርድ
የምፅፈው ታሪክ አዲስ አይደለም፤ ያለነው፤ በወጉ ተፅፎ የተቀመጠ፤ የሆነ ቦታ፤ አየሩ ላይ። ከእኔ የሚጠበቀው ፈልጐ መገልበጥ ብቻ ነው።
ጁሌስ ሬናርድ  

Saturday, 31 May 2014 14:31

የፍቅር ጥግ

ለእኔ ፍቅር ማለት አንድ ሰው “ቀሪውን ህይወቴን ካንቺ ጋር ለማሳለፍ እሻለሁ፤ከፈለግሽ ላንቺ ስል ከአውሮፕላን ላይ እዘልልሻለሁ” ሲለኝ ነው፡፡
ጄኒፈር ሎፔዝ
ጀግንነት ማለት ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ማፍቀር ነው፡፡ በምላሹ ምንም ሳይጠብቁ ማፍቀር፡፡ በቃ ፍቅር መስጠት፡፡ ይሄ ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ራሳችንን ለጉዳት አጋልጠን መስጠት አንፈልግማ፡፡
ማዶና  
ፍቅር ሲይዝህ እንቅልፍ አይወስድህም፡፡ ምክንያቱም ተጨባጩ እውነታ ከህልምህ የተሻለ ነውና፡፡
ዶ/ር ሴዩስ
ከፍቅር የሚገኘው ደስታ ጊዜያዊ  ሲሆን  የፍቅር ስቃይ ግን  ለእድሜ ልክ ይዘልቃል፡፡
ቤቲ ዴቪስ
ልብ የሚፈልገውን ያውቃል፡፡ ለዚህ ምንም አመክኖ የለውም፡፡ አንድ ሰው ታገኛለህ፤ከዚያም ታፈቅራለህ፡፡ በቃ ይኼው ነው፡፡
ዉዲ አለን
ፍቅር ሲይዝህ ሁሉ ነገር እንደ ብርሃን ግልጥልጥ ይልልሃል፡፡
ጆን ሌኖን
በፍቅር ውስጥ ስትሆኚ  አደገኛ ስሜት መፈጠሩ አይቀርም---- የገዛ ልብሽን አሳልፈሽ ለሌላ ሰው እኮ ነው የምትሰጭው፡፡ ያውም በስሜትሽ ላይ የማዘዝ ስልጣን እንዳለው እያወቅሽ። ሁልጊዜም አይበገሬ ለመሆን ለምጥረው ለእኔ፣ ይሄ አደገኛ ነገር እንደሆነ አውቃለሁ፡፡  
ቢዮንሴ ኖውሌስ