Administrator

Administrator

የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለባቸውን አለመግባባት ለመፍታትና ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል እንዲረጋገጥ ለማድረግ ባለፈው ሰኞ የፈረሙትን የትብብር ስምምነት እንደሚያደንቅ ማስታወቁን ኢጂብት ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጄን ፓስኪ ባለፈው ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ ሶስቱ አገራት በአባይ ወንዝ የውሃ ድርሻ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስችላል የተባለውን ስምምነት፣ አገራቱ በጉዳዩ ዙሪያ አንድ እርምጃ መራመዳቸውን የሚያሳይ ጠቃሚ ሁነት በመሆኑ ታደንቀዋለች ብለዋል፡፡
መንግስታቸው በአገራቱ መካከል የትብብር መንፈስ እንዲፈጠር ለማድረግና የሁሉንም አገራት ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ አባይን በዘላቂነት ለማልማት ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽና ከሱዳን ጋር በትብብር እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
ሶስቱ አገራት የአባይን ውሃ በፍትሃዊነት መጠቀም የመቻላቸው ጉዳይ፣ በአገራቱ መካከል ዋነኛ የውጥረት መንስኤ ሆኖ መቆየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የተፈረመው ስምምነት በሁሉም አገራት የውሃ ደህንነት ላይ ጉዳት እንዳይከሰት የሚያደርግ መሆኑንና ግብጽና ሱዳን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይፋዊ እውቅና መስጠታቸው የታየበት ነው መባሉን አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ዳር እስከዳር ታዬም፤ የግብጹ ፕሬዚዳንት ወደ ድርድር መምጣታቸውና የግድቡን መገንባት አለመቃወማቸው ከዚህ በፊት አገራቸው ስታራምደው ከነበረው አቋም የተለየና አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደ ነው ብለዋል፡፡ የትብብር መንፈሱ ጠቃሚነት እንዳለው የጠቆሙት ምሁሩ፣ የትብብሩ መንፈስ እውነት መሆንና አለመሆን ግን በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ የሚታይ ይሆናል ብለዋል፡፡
የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤የግብጹ ፕሬዚዳንት የአባይን ውሃ ከፈጣሪ እንደተበረከተ የግል ስጦታ ከማየት አስተሳሰብ ተላቀው፣ ውሃው የሌሎች አገራትም ሃብት እንደሆነ እውቅና መስጠታቸውን አድንቀው፣ስምምነቱን መፈረማቸው ብስለታቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡ “ትብብሩ የሁለቱንም አገራት ህዝቦች በሚጠቅም መልኩ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል፤ የአልሲሲ ጅምር መልካም ቢሆንም ውጤቱ በሂደት የሚታይ ይሆናል” ሲሉ አቶ ልደቱ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያግዙ የጅምናዚየም መሳሪያዎችን እያመረተ በአለማቀፍ ደረጃ በማቅረብ የሚታወቀው ላይፍ ፊትነስ ኩባንያ፣ “ላይፍ ፊትነስ ሮው ጂ ኤክስ” የተባለ ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ አዲስ የአካላዊ እንቅስቃሴ መሳሪያ ለገበያ ማቅረቡን በተለይ ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
ኩባንያው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳለው፣ ዘመኑ በደረሰበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሳሪያዎች ቴክኖሎጂና የጥራት ደረጃ የተመረተው ላይፍ ፊትነስ ሮው ጂ ኤክስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ ተጠቃሚዎች ምቹና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት መሳሪያ ነው፡፡
በተለያዩ የአካል ብቃት ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ተጠቃሚዎች ከአቅማቸው ጋር በሚመጣጠን መልኩ ተስማሚ አድርገው እንዲገለገሉበት በሚያስችል ሁኔታ እንደተሰራና የተጠቃሚዎችን ሁሉንም የሰውነት ክፍሎች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲዳብሩ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
መሳሪያው በግልና በቡድን ለሚደረጉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አገልግሎት መስጠት በሚችልበትና ቦታ በማይፈጅ መልኩ ዲዛይን እንደተደረገም የጂምናዚየም መሳሪያዎችን በአለም ዙሪያ ለሚገኙ ከ120 በላይ አገራት በማቅረብ የሚታወቀው ኩባንያው በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

  • ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያርኩን ምደባዎች በደብዳቤ ተቃውመዋል
  •   ቋሚ ሲኖዶሱ፤ጠቅ/ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡትን አቤቱታ መመልከት ጀምሯል

    ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ ስኪያጅ መሾማቸውን ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተገለጸ፡፡ኹለቱ ሥራ አስኪያጆች ለሀገረ ስብከቱ መመደባቸው የተገለጸው፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በደብዳቤ በተሰጠ መመሪያ ነው፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ የሚመደቡ ሓላፊዎችን የመምረጥና የመመደብ ጉዳይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ መያያዙን፣ በዚኽም መሠረት ሲሠራ እንደቆየ በመመሪያው የተጠቀሰ ሲኾን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኹለቱ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆች ምደባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲያደርሷቸውና ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይደረግ ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በአድራሻ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ተገልጧል፡፡ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የሥራ አስኪያጆቹ ሹመት ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቃለ ዐዋዲው እና ከሀገሪቱ የሕግ አሠራር ውጭ መኾኑን በመግለጽ ምደባውን በትላንትናው ዕለት ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ የተቃወሙ ሲኾን፣ ፓትርያርኩ ከሕግ አግባብ ውጭ የሰጡትን መመሪያ እንደገና እንዲያጤኑት መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነታቸው ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ እንጂ ለፓትርያርኩ ኾኖ እንደማያውቅና ሊኾንም እንደማይችል የገለጹት አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የፓትርያርኩ አካሔድና የሥራ አስኪያጆች ምርጫ ‹‹የሕግ ድጋፍ የሌለው፣ ያልተለመደና የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ አሠራር በእጅጉ የሚፃረር ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቡነ ማትያስ የሰጡት መመሪያ ተቀባይነት የሚኖረውም ተሿሚዎቹ በሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመርጠው ከቀረቡ በኋላ ምርጫቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር የጋራ ስምምነት ተደርሶበት በፓትርያርኩ ሲሾሙ እንደኾነ በተቃውሟቸው አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በሰጡት መመሪያና በሥራ አስኪያጆች ምርጫዎቻቸው እንደማይስማሙና ምደባውንም ለማስተናገድ እንደሚቸገሩ ያስታወቁት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ ‹‹ይህ አሠራር ከትዝብት ላይ የሚጥል መኾኑን ተረድተውልን ለቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ አሠራርና ለኹላችንም ሰላም ሲባል ውሳኔዎን እንደገና እንዲያጤኑ በታላቅ አክብሮት አሳስባለኹ›› ብለዋል - በተቃውሞ ደብዳቤአቸው፡፡
የፓትርያርኩን መመሪያ እንዲያስፈጽሙ በአቡነ ማትያስ መመሪያ የተሰጣቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ትላንት ከቀትር በፊት በተደረገው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ ስብሰባ መመሪያውን በመቃወም አስተያየታቸውን በቃል ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩም አጀንዳው ውሳኔአቸውን የሰጡበት በመኾኑ መታየት የለበትም በሚል ቢቃወሙም ቋሚ ሲኖዶሱ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተቃውሟቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ማዘዙ ተገልጧል፡፡ ከትላንት በስቲያ በድንገት ይፋ የኾነው የሀገረ ስብከቱ ተተኪ ሥራ አስኪያጆች ምደባ፥ ‹‹የመልካም አስተዳደር ሒደቱን ማቀላጠፍ›› በሚል ከኹሉ አቀፍ የትምህርት ዝግጅት፣ ከሥነ ምግባርና ከብሔር ተዋፅኦ መስፈርቶች አንጻር ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሳቸውን ላለፉት ሦስት ወራት ሲያወዛግብ መክረሙን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡




   ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) በ100 ቢሊዮን ብር ወጪ በአስር አመት ጊዜ ውስጥ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ የነዳጅ ማጣሪያ የመገንባት ዕቅድ እንዳለው ማስታወቁን ሮይተርስ ከኬፕ ታውን ዘገበ፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን በመገንዘብ በቀን ከ200 ሺህ እስከ 300 ሺህ በርሜል ነዳጅ የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን የነዳጅ ማጣሪያ የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡
በአገሪቱ ያለው የነዳጅ ፍላጎት በየአመቱ በአስር በመቶ እያደገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ የነዳጅ ፍላጎት በመጪዎቹ አስር አመታት በእጥፍ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅና፣ ኩባንያው የነዳጅ ማጣሪያውን በአስር አመት ውስጥ ገንብቶ እንደሚያጠናቅቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ለአምስት ቀናት በተካሄደውና ትናንት በተጠናቀቀው የአፍሪካ የነዳጅ አጣሪ ኩባንያዎች ማህበር ስብሰባ ላይ የተገኙት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታውን የፋይናንስ ምንጭ በተመለከተ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ሌሎች ኢንቨስተሮች የፕሮጀክቱ አካል የሚሆኑበት ዕድል እንዳለ ከዚህ ቀደም መናገራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ግጥሚያው የምር አይደለም ተብሏል
  የቀድሞው የማሳቹሴትስ ገዢና የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ሚት ሩምኒ  ከቀድሞው የከባድ ሚዛን ቦክስ የአራት ጊዜ የአለም ሻምፒዮን ኢቫንደር ሆሊፊልድ ጋር ቦክስ ሊጋጠሙ ነው ሲል ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
በመጪው ግንቦት 15 ሶልት ሌክ ሲቲ በተባለችው የአሜሪካ ከተማ የሚከፈት አንድ ኤግዚቢሽን አካል እንደሚሆን የተነገረለት ይህ የምር ያልሆነ የቦክስ ግጥሚያ፣ አላማው ለድሃ አገራት ዜጎች የአይን ቀዶ ህክምና አገልግሎት ለሚሰጠው ቻሪቲ ቪዥን የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ገቢ ማሰባሰብ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ የዓለም ሻምፒዮኑን ቡጢኛ ለመግጠም ቆርጠው እንደተነሱ የገለጹት የ68 አመቱ ፖለቲከኛ ሚት ሩምኒ፣ ፍልሚያው በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ አለበት፣ ያለዚያ አፈር ድሜ መግባቴ አይቀሬ ነው ሲሉ ስጋታቸውን አበክረው ገልጸዋል፡፡
ከ18 አመታት በፊት ከታዋቂው ቦክሰኛ ማይክ ታይሰን ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ ጆሮውን በከፊል ያጣው የ52 አመቱ ኢቫንደር ሆሊፊልድ፣ ከ3 አመታት በፊት ከባራክ ኦባማ ጋር የፖለቲካ ፍልሚያ አካሂደው ከተረቱት ሚት ሩምኒ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ከወዲሁ በጉጉት እየተጠበቀ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ለ20 አመታት ያገለገለው ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር በፕሮጀክት ስፓርታን ይተካል
ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ እጅግ የተራቀቀ የተባለለትን አዲሱ ዊንዶውስ 10 ኦፐሬቲንግ ሲስተም በመጪዎቹ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ በይፋ በማስተዋወቅ በስራ ላይ እንደሚያውል ገለጸ፡፡
በአለም ዙሪያ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚነገርለትንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ  አዳዲስ አሰራሮችን በመላበስ በመቅረብ ላይ የሚገኘውን ዊንዶውስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም የሚያመርተው ማይክሮሶፍት ምክትል ፕሬዚዳንት ቴሪ ሜርሰንን ጠቅሶ ቴሌግራፍ እንደዘገበው፣ ኩባንያው አዲሱን ኦፐሬቲንግ ሲስተም እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ በስራ ላይ ለማዋል አቅዷል፡፡
አዲሱ ኦፐሬቲንግ ሲስተም በ111 የተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚዘጋጅና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ 190 አገራት የኩባንያው ደንበኞች እንደሚዳረስ የጠቆመው ዘገባው፣ ኦፐሬቲንግ ሲስተሙ ነባሮቹን ዊንዶውስ 7፣ 8.1 እና ዊንዶውስ ፎን 8.1 ለሚጠቀሙ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞች ለአንድ አመት ያህል በነጻ እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡
ዊንዶውስ 10 በዴስክቶፕ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ላይ እንዲሁም የማይክሮሶፍት ኩባንያ ምርቶች በሆኑ ታብሌቶችና የሞባይል ስልኮች ላይ እንደሚሰራ ያስታወቀው ኩባንያው፣ ለ20 አመታት ያህል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ነባሩን ሰርች ኢንጂን ኢንተርኔት ኤክስፕሎረርን፣ ፕሮጀክት ስፓርታን በተሰኘ አዲስ ፈጠራው መተካቱንም ጠቁሟል፡፡
ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር ምንም እንኳን በመላው አለም የሚገኙ ከ1 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ታዋቂ ሰርች ኢንጂን ቢሆንም፣ ተሻሽለው ከተሰሩትና ከፈጣኖቹ ፋየርፎክስ እና ጎግል ክሮም ጋር መወዳደር ባለመቻሉ፣ ኩባንያው ፕሮጀክት ስፓርታን የተሰኘውን አዲሱን ሰርች ኢንጂን ለመስራት መወሰኑንም ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል፡፡

Saturday, 21 March 2015 10:43

የየአገሩ አባባል

የተከፈተ አፍ ፆሙን አያድርም፡፡
ረዥሙም ዛፍ እንኳን እግሩ ስር የሚጠብቀው መጥረቢያ አለ፡፡
ሁሉም ድመት በጨለማ ጥቁር ነው፡፡
ሞኝ ሃብትን ሲያልም፤ ብልህ ደስታን ያልማል፡፡
የምግብ ፍላጎቱ የተከፈተለት ሰው፣ ማባያ አይፈልግም፡፡
ጥሩ ባልንጀራ ረዥሙን መንገድ ያሳጥራል፡፡
ልማድ ከብረት የተሰራ ሸሚዝ ነው፡፡
ባዶ ሆድ ጆሮ የለውም፡፡
ንዴት መጥፎ አማካሪ ነው፡፡
በአንዴ ሁለት አጋዘኖችን የሚያሳድድ ጅብ ፆሙን ያድራል፡፡
በእጅህ ዱላ ይዘህ ውሻን አትጥራ፡፡
የመፍትሄው አካል ካልሆንክ የችግሩ አካል ነህ፡፡
ሞኝ ሲረገም የተመረቀ ይመስለዋል፡፡
ከሰፈሩ ወጥቶ የማያውቅ ፣ እናቱ የባለሙያ ቁንጮ ትመስለዋለች፡፡
ታላላቆችን የሚያከብር ለራሱ ታላቅነት መንገዱን ይጠርጋል፡፡
ዓለም ለማንም ተስፋ (ቃል) አትሰጥም፡፡
ሌሊቱ ምን ቢረዝም መንጋቱ አይቀርም፡፡
ሳይወለድ ትችትን የሚፈራ ህፃን ጨርሶ አይወለድም፡፡
ከሴት ጋር ማውራት የማይወድ፣ ወንደላጤ ሆኖ ይቀራል፡፡
አባወራው መሬት ላይ የተቀመጠበት ቤት ውስጥ ወንበር እንዲሰጥህ አትጠብቅ፡፡
ወፍ በመመላለስ ብዛት ጎጆዋን ትሰራለች፡፡
የውሃውን ጥልቀት በሁለት እግሮቹ የሚለካ ሞኝ ብቻ ነው፡፡
የጅብ ዣንጥላ ይዞ የተመለሰ አዳኝን ስለአደኑ አትጠይቀው፡፡

Saturday, 21 March 2015 10:33

የሲኒማ ጥግ

ፊልሙ ከመሰራቱ በፊት የገበያ ኃይሎች የተወሰኑ ህጎች ይጭኑበታል፡፡
አላን ሪክማን
ተዋናይ አብዛኛውን የመጀመሪያ የሙያ ዘመኑን የሚያሳልፈው ያገኘውን እየሰራ ነው፡፡
ጃክ ኒኮልሰን
እንደምተውናቸው ገፀባህሪያት ነው ብላችሁ ለአፍታም እንኳን እንዳታስቡ። አይደለሁም፡፡ ለዚያም ነው “ትወና” የተባለው፡፡
ሊኦናርዶ ዲካፕሪዮ
እያንዳንዱ የፊልም ተማሪ፤ ት/ቤት የሚገባው የራሱን ፊልም ለመፃፍና ዳይሬክት ለማድረግ በማሰብ ይመስለኛል። ያንን ለማድረግ ምን እንደሚያስፈልግ አይገነዘቡም፡፡ ሂደቱ እንዴት ያለ እንደሆነ አያውቁትም፡፡
አሌክሲስ ብሌደል
አብዛኞቹ እኔ የሰራኋቸው ፊልሞች የተበላሹት በሚሰሩ ወቅት ሳይሆን ከተሰሩ በኋላ ነው፡፡
ቼቪ ቼስ
ጥሩ ተዋናይ ከራሱ በስተቀር ማንንም መውደድ የለበትም፡፡
ዣን አኖሊህ
ራሴን እንደልብወለድ ገፀባህርይ መፍጠር እፈልግ ነበር፡፡ እናም አደረግሁት፡፡ ከዚያማ ብዙ ግራ መጋባት ፈጥሮ ነበር፡፡
ዣኔት ዊንተርሰን
ሆሊውድ ብዙ ተዋናዮችን ሳይሆን ብዙ ምስሎችን የሚቀርፁበት ስፍራ ነው፡፡
ዋልተር ዊንሼል
ማንም ሰው መሰረታውያኑን ካወቀ፣ ፊልም ዳይሬክት ማድረግ ይችላል፡፡ ፊልም ማዘጋጀት (መስራት) ተዓምር አይደለም፤ ጥበብም አይደለም፡፡ የዳይሬክቲንግ ዋናው ነገር የሰዎችን ዓይን በካሜራ ማስቀረት ነው።
ጆን ፎርድ
ጡረታ የወጣ ተዋናይን ሚና በመጫወት እስካሁን ስኬታማ የሆንኩ አይመስለኝም፡፡ እናም እዚያ ላይ መስራት እፈልጋለሁ፡፡
ሰን ፔን

Saturday, 21 March 2015 10:29

ከበደች ተክለአብ አርአያ

ሰዓሊ፣ ቀራጺ፣ ገጣሚ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር
  የስነጥበብ ትምህርት መማር የጀመርኩት በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በ17 ዓመቴ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ በስነጥበብ ሙያ እተዳደራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ስነጥበብን የመስራት ፍላጎት ብቻ ነው የነበረኝ፡፡ ህይወት ግን መንገዴን ወደ ስነጥበብ አቅጣጫ መራችው፡፡ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በተካሄደው የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳትፎ በማድረጌ መታደን ስጀምር፣ በጅቡቲ በኩል ለማምለጥ ሞከርኩ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በወቅቱ ሶማሊያና ኢትዮጵያ በድንበር ግጭት ውስጥ ስለነበሩ፣ ድንበር ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች በቁጥጥር ውስጥ አዋሉኝ፡፡ ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍኩት በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነበር፡፡ ህይወት ግን ለሁሉም ነገር ምክንያት ነበራት፡፡ “በገሃዱ አለም የምናስተናግዳቸው ሽንፈቶቻችን፣ በስነጥበቡ አለም ድሎቻችን ይሆናሉ፡፡ በስነ ውበት አይን ሲታይ፤ ችግሮቻችንን፣ ስቃዮቻችንንና ሽንፈቶቻችንን በመውደድና በእነሱ ከመማረር ይልቅ ወደ ስነጥበብ ስራነት በመቀየር፤ የኋላ ኋላ በቁጥጥራችን ውስጥ እናደርጋቸዋለን” በማለት ጽፋለች ሜልቪን ራደር። በእስር ቤት ያሳለፍኳቸው አመታት፣ ከተቀረው አለም የሰው ልጅ ጋር ትስስር ለመፍጠሬ ሰበብ ሆነውኛል፡፡ ለስነጥበብ ስራዎቼ የመነቃቃት ምንጭ የሆኑኝም እነዚያ የግዞት አመታት ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ መርካቶ የሚባለው ሰፈር ውስጥ በ1950 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ መጠነኛ ገቢ ያላቸው ወላጆቼ ካፈሯቸው አራት ልጆች፣ እኔ የመጨረሻዋ ነኝ፡፡ ዛሬም ድረስ የሚከተለኝን ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረችብኝ አሁን በህይወት የሌለችው እናቴ ናት፡፡ እናቴ መንፈሳዊውን አለም ከምድራዊው አለም ጋር በሚገርም ሁኔታ አጣጥማ ህይወቷን ስትመራ የኖረች፣ ፍጹም ሃይማኖተኛ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበረች፡፡ መደበኛ ትምህርት ባትከታተልም እጅግ ብሩህ አእምሮ ያላትና ለስነጽሁፍ ፍቅር የነበራት ሴት ነበረች። የማክሲም ጎርኪን መጽሃፍት አነብላት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከጎርኪ ስራዎች፣ ‘እናት’ ለሚለው ረጅም ልቦለድ የተለየ አድናቆት ነበራት፡፡ አማርኛ ማንበብና መጻፍ የቻለችው በራሷ ጥረት ነው፡፡ ለስነግጥም፣ በተለይ ደግሞ ለቅኔ እንዲሁም ለቲያትር የተለየ ፍቅር ነበራት፡፡ የስነጥበብ ስሜትም ነበራት። የራሷን የጥልፍ ዲዛይኖች ትሰራ ነበር፡፡ ለፍትህ መከበር ጠንካራ አመለካከት ያላት እናቴ፣ ከቁሳዊ ስኬቶች ይልቅ ለእሴቶች ራሳቸውን ከሚያስገዙ ጥቂት ሰዎች አንዷ ነበረች፡፡ በትምህርት አጥብቃ ታምናለች፡፡ አባቴ ወደ መቀሌ ከተማ ሄዶ መድሃኒት ቤት ሲከፍትና ፊቱን ወደ ንግድ ሲያዞር፣ እሷ ግን እኛን ልጆቿን ለማስተማር አዲስ አበባ መቅረትን ነው የመረጠችው፡፡ ከትምህርት ቤት ስንመለስ  ውሏችንንና የተማርነውን  ትጠይቀናለች፡፡ የቤት ስራችንን በአግባቡ እንድንሰራም ታበረታታናለች፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህራን  መጽሃፍትን ሲያነቡልን በጽሞና አዳምጣቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይሄን የማደርገው ወደ ቤቴ ስመለስ ታሪኩን በአግባቡ ለእናቴ ለመተረክ ስል ነበር፡፡ እናቴ ሁሌም ከጎኔ ነበረች፡፡ በተደጋጋሚ ባጋጠሙኝ ፈታኝ የመከራ ጊዜያት ሁሉ በጽናት እንድቆም ትደግፈኝ ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ስነጽሁፍ የመማር ሃሳብ  ነበረኝ፡፡ ንባብ ስወድ ለጉድ ነው፡፡ ግጥም ነፍሴ ነው፡፡ ቅኔ የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እየሄድኩ ግዕዝ መማር የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ በየጉራንጉሩ ግጥሞችን እየጻፉ መበተን ትልቅ የትግል ስልት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ግጥሞችን መጻፍ የጀመርኩት፡፡ እርግጥ የስዕል ስሜትም ነበረኝ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሆኜ፣ የሳይንስ ትምህርት ስዕሎችን መሳል እወድ ነበር፡፡ በስተመጨረሻም ስዕልና ቀለም ቅብ ይወዱ የነበሩት ወንድሜና አንድ ጓደኛዬ  ባሳደሩብኝ ተጽዕኖ፣ አስራ አንደኛ ክፍልን ተምሬ እንደጨረስኩ ስነጥበብ ለማጥናት ወስኜ፣ በ1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅም ትምህርቴን ተከታተልኩ፡፡
በቀበሌና በወጣት ሊግ አማካይነት በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጠልኩበት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ወታደራዊው መንግስት፤ የቀይ ሽብር ዘመቻን አውጆ ተማሪዎችን ከያሉበት እያደነ ማሰርና በጅምላ መጨፍጨፍ ሲጀምር፣ እኔም ለዚህ ክፉ ዕጣ ከታጩት ታዳኝ ተማሪዎች አንዷ መሆኔን አወቅሁት፡፡ ከተጋረጠብኝ አደጋ ማምለጥ ነበረብኝ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ከሌሎች አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀን ቆየን፡፡ በስተመጨረሻም ድንበር አቋርጠን ጅቡቲ ለመግባትና ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ፣ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወጣን፡፡ በድብቅ ድንበሩን ሊያሻግሩን ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎች ብናገኝም፣ ሙከራችን ግን እጅግ አደገኛ ነበር፡፡ አቋርጠነው ልናልፍ ባሰብነው ድንበር ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ ይህ መሆኑን ሳናውቅ ነው፣ በእግራችን ጉዞ የጀመርነውና የሶማሌ መደበኛ ጦርና  የሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች ሰፍረውበት ወደነበረው የጦር ካምፕ ሰተት ብለን የገባነው። በቁጥጥር ስር ውለን ወደ ሶማሊያ ተወስደን ታሰርን። በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ እኛ ግን ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍናቸው በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነው፡፡ በስተመጨረሻም በኢጋድ ስብሰባ ላይ በተደረገ ስምምነትና በአለማቀፉ የቀይመስቀል ድርጅት አግባቢነት ይመስለኛል፣ ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኞች ሆኑ፡፡ እኛም በ1981 ዓ.ም ከእስር ተፈታን፡፡
እነዚያ በእስር ያሳለፍናቸው አመታት እጅግ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ከእስር ቤቱ ቅጽር ውጪ ካለው አለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረንም። ከጉሮሮ የማይወርድ ምግብ እየበላን፣ ንጽህና በጎደለው ማጎሪያ ውስጥ አስከፊ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ውለን ማደር ነበረብን፡፡ ወባና በደም ኢንፌክሽን የሚፈጠረው ቺስቶሶሚያሲስ የተባለ በሽታ፣ ዘወትር ከእስር ቤቱ የማይጠፉ የተለመዱ የእስረኞች የስቃይ ምንጮች ነበሩ፡፡ ልንፈታ አንድ አመት ገደማ ሲቀረን፣ የኮሌራ ወረርሽኝ ሳይቀር ተከስቶ ነበር፡፡ እስር ቤት ውስጥ፣ ፍጹም ስለ ራሳቸው ግድ የሌላቸው አልያም ፍጹም አደገኛና ራስ ወዳድ ሰዎችን ልታገኚ ትችያለሽ፡፡ እኛ ጋ ሁለቱም አይነት ሰዎች ነበሩ፡፡ ፈጣሪ ከዚያ መከራ ያተረፈኝ ለእናቴ ብሎ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እሷ ለኔ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ ትልቅ ስጦታ ነበረች፡፡
 እንደ እስረኛ እርስ በርስ እንረዳዳ ነበር - በቁሳቁስ ሳይሆን መከራን አብሮ በመጋፈጥ። የጽሁፍ መሳሪያዎችን  ባገኘሁበት አጋጣሚ ሁሉ፣ በርካታ ግጥሞችን ጽፌያለሁ፡፡ የመድሃኒት ፓኮዎችንና የዱቄት ወተት ክርታሶችን እንደ ወረቀት እየተጠቀምን ነበር የምንጽፈው፡፡ እርግጥ በአማርኛ መጻፍ ክልክል ስለነበር፣ የጻፍኳቸውን ግጥሞች በየስርቻው እደብቅ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ግጥሞቼ በአይጥና በድመት ተበልተዋል፣ በርካቶችም ጠፍተዋል፡፡ መጻፌ ከአእምሮ መቃወስ አድኖኛል። ቀስ በቀስ ትምህርት ቤት አቋቁመን ለእስረኞች ፊደላትን ማስቆጠርና ሌሎች ትምህርቶችን ማስተማር ጀመርን፡፡ ሳይንስ እና እንግሊዝኛን የመሳሰሉ ትምህርቶችን አስተምር ነበር፡፡ ትልቁ አስተዋጽኦዬ አማርኛ ማስተማር ሲሆን የተለያዩ ታሪኮችና ግጥሞችን እየጻፍኩ ለማስተማሪያነት እጠቀምባቸው ነበር፡፡ እኛ ከእስር ስንፈታ ማንበብና መጻፍ የማይችል እስረኛ አልነበረም። ትምህርቱም እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል አድጎ ነበር፡፡ መጽሃፍትን የምናገኘው አልፎ አልፎ ነው። በተለየ ሁኔታ የማስታውሳቸው፣ የፕሪሞ ሌቪን መጽሃፍትና የአሌክስ ሄሊን ‘ሩትስ’ የተሰኘ መጽሃፍ ነው፡፡ በሄሊ መጽሃፍ ውስጥ የተሳሉት የመስክ ሰራተኞች ህይወት፣ ከእኛ ህይወት ጋር በሚገርም ሁኔታ መመሳሰሉ ቀልቤን ማርኮት ነበር፡፡ ራሳችንን ዋጋ እንዳለው ሰብአዊ ፍጡር እንድናስብ ያገዙን  እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡
እንደተፈታሁ ወዲህ ወዲያ ሳልል በቀጥታ የመጣሁት ወደ አዲስ አበባ ነበር፡፡ ምክንያቱም ወንድሜ እኔን ፍለጋ አዲስ አበባ መምጣቱን ሰምቻለሁ፡፡ ወንድሜ ያንን ማድረጉ ለእኔም ሆነ ለእሱ አደገኛ ነበር፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቄ፣ መላው ቤተሰቦቼ ወደሚኖሩባት አሜሪካ አቀናሁ፡፡ ከረዥም ጊዜያት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከእናቴ፣ ከወንድሜ፣ ከእህቴና ከቀሩት ቤተሰቦቼ ጋር ለመቀላቀል ቻልኩ። ለዓመታት ያቋረጥኩትን የስነጥበብ ትምህርት በመቀጠልም፣ በዋሽንግተን ዲሲው  ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በስነጥበብ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ፡፡ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ስከታተል ግሩም  መምህራን  ገጥመውኛል፡፡ ሁለት ድንቅ መካሪ ዘካሪም  አግኝቻለሁ፡፡ የስነጥበብ መምህሬ እስክንድር ቦጎሲያንና የፊልም መምህሬ አብይ ፎርድን፡፡ ከእስክንድር ጋር በመሆን ‘ኔክሰስ’ የተሰኘ የሥነጥበብ ስራ ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመስራት እድል አግኝቻለሁ፡፡
በስዕሎቼ ስሜቶቼን፣ ትዝታዎቼን እንዲሁም ጊዜና ቦታ ከሚገድባቸው ግላዊ ገጠመኞቼ፣ ዘመን እስከማይሽራቸው አለማቀፍ ጉዳዮች የተዘረጋውን ምናቤን መግለጽ ጀመርኩ፡፡ ራሴን በግላዊ ገጠመኞቼና ልምዶቼ ላይ ብቻ አልገደብኩም። ምናቤን ሰፋ በማድረግ ጦርነት፣ ስቃይና በስተመጨረሻም ፈውስን ወደመሳሰሉ አለማቀፍ ጉዳዮች ገባሁ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ፣ በቀላሉ የሚለዩ የእይታ ተረኮችን በመጠቀም የግል ልምዶቼን በአለም ዙሪያ ከሚታዩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር እያስተሳሰርኩ፣ ኤክስፕሬሽኒስት በተባለው የአሳሳል ዘዬ ነበር ስዕሎቼን የምሰራው። በመቀጠልም ከዚህ ቀደም እንደማደርገው ሁሉ ትኩረቴን በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ከቀድሞዎቹ በበለጠ ምስል አልባ የሆኑ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ከዚያም ቴክስቸር፣ ቀለምና ቅርጽን በመሳሰሉ የእይታ  መሰረታዊ ነገሮች በመጠቀም፣ ስሜትን የሚያጭሩ ሙሉ ለሙሉ ምስል አልባ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መሳል ቀጠልኩ፡፡ አሁን ብርን የመሳሰሉ ባህላዊ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በመገጣጠም እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ብር በውስጡ ብርሃን ስለሚያሳልፍ እወደዋለሁ፡፡ ከሌሎች ቁሳቁሶች ጋር በመሸመን የተለያዩ ተደራራቢ ትርጉም ያላቸው መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ ስዕሎችንና ቅርጻቅርጾችን ከስነግጥም፣ ሙዚቃና ስነጽሁፍ ጋር እያዋሃድኩ የራሴን ህብር እፈጥራለሁ፡፡ አንደኛው ጥበብ በሌላኛው እንዲሁም በእኔ ላይ መነሳሳትና ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡
ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ በስቱዲዮ ስራዬን እየሰራሁ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስነጥበብ ትምህርት አስተምር ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጆርጂያ በሚገኘው ሳቫና የስነጥበብና የዲዛይን ኮሌጅ እያስተማርኩ እገኛለሁ፡፡ መምህር መሆኔን እወደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ራሴን ሙያው በየጊዜው ከሚደርስበት  ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለማድረስ ስል፣ በስፋት እንዳነብና ጥናት እንዳደርግ ያስገድደኛል፡፡ ሌላው ሙያውን እንድወደው የሚያደርገኝ ነገር ደግሞ፣ ከዚህ በፊት ልምዱ ባልነበረኝ የስነጥበብ ጉዞዎች ላይ በተደጋጋሚ እንድሳተፍ ዕድል የፈጠረልኝ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ባስተምር ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም በሙያዬ  የማበረክተው አስተዋጽኦ በእነዚህ አገራት የተሻለ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ቀን የሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሰዓሊ የምሆንበትና በጽሁፍ ስራ ላይ ብዙ ጊዜዬን ማሳለፍ የምችልበት ዕድል ይፈጠርልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስነጥበብ ለኔ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ነው። ስነጥበብን የምኖርለት ሙያዬ ለማድረግ ችያለሁ ብዬ የማስበው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንድም ስለ ቁሳዊ ስኬት ተጨንቄ አላውቅም፡፡ ሁለትም ሙያው የሚጠይቀውን ዲስፕሊን አክብሬና ሙሉ ትኩረቴን በእሱ ላይ አድርጌ ነው የኖርኩት፡፡
የዛሬ ዘመን ወጣት ሴቶች ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባሉ የምላቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ነገር አደጋዎችን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ፈቃደኛ ካልሆኑ ምንም ነገር ሊያሳኩ አይችሉም። አደጋን መጋፈጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰርጸው የኖሩና ቅቡል የሆኑ አመለካከቶችን መገዳደር ሊሆን ይችላል፡፡
ሴቶች ይህን ማድረጋቸው ህልማቸውን እውን ለማድረግ ያግዛቸዋል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ አደጋን መጋፈጥንና ከባህል  ልንማራቸው የምንችላቸውን ነገሮች ማክበራችንን በተመጣጠነ ሁኔታ ማስኬድ ይኖርብናል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ወጣት ሴቶች እውቀትን መሻት ብቻ ሳይሆን እውቀትን ፍለጋ ከተጉ፣ ግሩም የሚባሉ ነገሮችን ለማሳካት እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡
(ሰዓሊና ገጣሚ ከበደች ተክለአብ የዛሬ 15 ዓመት አዲስ አድማስ መታተም ስትጀምር  የጋዜጣው እንግዶች ሆነው ከቀረቡት የጥበብ ባለሙያዎች መካከል ቀዳሚዋ ነበረች፡፡ ከላይ የቀረበውን ግለ ታሪክ የወሰድነው ባለፈው ጥቅምት ወር ለንባብ ከበቃውና የስኬታማ ኢትዮጵያውያንን ሴቶች ታሪኮች ከሚያስነብበው ተምሳሌት የተሰኘ መጽሐፍ ነው፡፡)

Saturday, 21 March 2015 10:31

የፍቅር ጥግ

ፍቅርንና ጉንፋንን መደበቅ አይቻልም፡፡
ጆርጅ ኸርበርት
የብቸኝነት እስረኛ ሆኖ የሚያውቅ ሰው፣ የፍቅር እስረኛ ሆንኩ ብሎ አያማርርም፡፡
ሮበርት ብራውልት
ፍቅር፤ ማብሪያ ማጥፊያውን ሌላ ሰው የሚቆጣጠረው የኤሌክትሪክ ብርድልብስ ነው፡፡
ካቲ ካርሊሌ
ህይወት የሚጀምረው ፍቅር ሲመጣ ነው፡፡
“Bill of Divorcement” ከ
ሚለው ፊልም”
ትክክለኛውን ፍቅር ከመፍጠር ይልቅ ትክክለኛውን አፍቃሪ በመፈለግ ጊዜ እናጠፋለን፡፡
ቶም ሮቢንስ
ፍቅር የህይወት ህግ ነው፡፡
ሞሃንዳስ ካራምቻንድ ጋንዲ
ፍቅርን በልብ ቅርፅ የምንስለው የነፍስን ቅርፅ ስለማናውቀው ነው፡፡
ሮበርት ብራውልት
ላንቺ ያለኝን ፍቅር ሁሉ ለመሸከም 100 ልቦች በቂ አይደሉም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
ፍቅር ሰዎችን ይፈውሳል - ሰጪዎቹንም ተቀባዮቹንም፡፡
ካርል ሜኒንገር
ፍቅር እንደ ድንጋይ ባለበት ዝም ብሎ አይቀመጥም፤ እንደ ዳቦ መጋገር አለበት፤ ሁልጊዜ እንደገና መሰራት፣ እንደ አዲስ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
ኡርሱላ ኬ.ሊ.ጉይን
መሸ ተብሎ የፍቅር ጨዋታ አይቀርም፡፡
ቶም ማሶን
ፍቅር የያዘው አዛውንት፣ እንደ ክረምት አበባ ነው፡፡
የፖርቹጋሎች ምሳሌያዊ አባባል
ፍቅር የስሜቶች ቅኔ ነው፡፡
ኦኖር ዲ ባልዛክ
ፍቅር ሁለቱም ተጫውተው ሁለቱም የሚያሸንፉበት ጨዋታ ነው፡፡
ኢቫ ጋቦር