Administrator

Administrator

በ2015 የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ቅድመ ማጣርያ ደደቢትና ቅዱስ ጊዮርጊስ   ዛሬ እና ነገ በባህርዳር ስታድዬም የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከሜዳ ውጭ ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች ወደ 1ኛ  ዙር ማጣርያ ለመግባት  እድል አላቸው፡፡ 50 ሺህ ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው የባህርዳር ስታድዬም   ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያስተናግድ ከአፍሪካ እግር ኳስ  ኮንፌዴሬሽን እውቅና አግኝቷል፡፡ስታዲየሙ  የእግር ኳስ  ሜዳን ጨምሮ ሌሎች ሁለገብ ሩጫ፣ውርወራን፣ዝላይን ያካተተ የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲኖረው ተደርጎ ተሰርቷል፡፡ 21 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ግዙፍ ስታዲየም በ2ኛ የግንባታ ምእራፉ 27ሄክታር ቦታ ላይ የሚያርፍ ግዙፍ የስፖርት መንደር  ይሰራለታል፡፡ አጠቃላይ ወጪው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ከቅደመ ማጣርያ አንስቶ በ1ኛ እና በሁለተኛ ዙር ማጣርያዎች ውጤታማ በመሆን ወደ የምድብ ማጣርያዎች ለመግባት ከባድ ፈተና ገጥሟቸው ቆይቷል፡፡በተለይ በቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን ማለፍ ከቻሉ በኋላ ወደ አንደኛ ዙር የማጣርያ ውድድር ሲሸጋገሩ ከሰሜን  እና ምዕራብ አፍሪካ ክለቦች በጥሎማለፍ ለደርሶ መልስ ጨዋታዎች እየተደለደሉ በዚህ ምእራፍ የሚገጥማቸውን ፉክክር ማለፍ ይከብዳቸዋል፡፡ ደደቢት በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ሲሳተፍ ዘንድሮ አራተኛው ነው፡፡
በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ብቸኛውን ተሳትፎ በ2014 እኤአ ላይ እንዲሁም ለሁለት ጊዜያት ደግሞ በ2011 እና በ2013 እኤአ ላይ በኮንፌደሬሽን ካፕ በመሳተፍ ውጤቱ በ1ኛው ዙር ማጣርያ ላይ በመሰናበት ተወስኖ ቆይቷል፡፡ አንጋፋው የኢትዮጵያ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ከ20 በላይ የውድድር ዘመናትን ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በአዲስ መዋቅር መካሄድ ጀምሮ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዘንድሮ ሲሳተፍ 10ኛው ተሳትፎ ይሆናል፡፡ ባለፉት 9 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ለ3 የውድድር ዘመናት ተሳትፎው በቅድመመማጣርያ ላይ ሲወሰን በ6 የውድድር ዘመናት እስከ 1ኛ ዙር ማጣርያ ብቻ ተጉዟል፡፡
በ8ኛው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ደደቢት ከሜዳው ውጭ የሲሸልሱን ኮት ዲ ኦርን በስታደ ደ አሚቴ 3ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ነበር፡፡ ዛሬ በባህርዳር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ  በማንኛውም ውጤት አቻ መለያየት እና ማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፈዋል፡፡ ደደቢት በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የሚመራ ሲሆን የሲሸልሱን ክለብ ኮትዲኦር ባሻነፈበት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ዳዊት ፍቃዱ ከመረብ ሲያሳርፍ ናይጄሪያዊው 3ተኛውንና የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል፡፡  ዛሬ ደደቢት የሲሸልሱን ኮት ዲኦር ጥሎ ካለፈ ከቡርኪናፋሶው አርሲ ሮቦ ወይም ከናይጄርያው ዋሪ ዎልቭስ አሸናፊ ጋር በ1ኛ ዙር ማጣርያ የሚገናኝ ይሆናል፡፡በሁለቱ ክለቦች የቅድመ ማጣርያ  ጨዋታ የናይጄርያው ክለብ በሜዳው 1ለ0 እንዳሸነፈ ታውቋል፡፡
በ19ኛው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ በኤምሲ ኤል ኡልማ የተሸነፈው 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ነበር፡፡ ነገ በባህርዳር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2 ንፁህ ጎሎች ካሸነፈ ወደ ቀጣዩ የአንደኛ ዙር ማጣርያ ያልፋል፡፡ በአንደኛ ዙር ማጣርያ ከጋናው አሻንቲ ኮቶኮ ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም ታውቋል፡፡ የጋናው ክለብ በቅድመማጣርያው ከኢስት ላንድስ ጋር ተደልድሎ የነበረ ቢሆንም የሴራልዮኑ ክለብ ከውድድሩ በመውጣቱ በፎርፌ ሊያልፍ ችሏል፡፡
የፖርኩፒን ጦረኞች ተብሎ የሚጠራው የጋናው ክልብ አሻንቲ ኮቶኮ፤ ከተመሰረተ ከ82 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ አሻንቲ ኮቶኮ በጋና ፕሪሚዬር ሊግ ለ24 ጊዜያ ሻምፒዮን በመሆን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ ሲሆን ከአፍሪካ የኛው ክፍለዘመን ምርጥ ክለቦች አንዱ ሆኖ የተመዘገበ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ለሁለት ጊዚያት አሸናፊ በመሆን በውድድሩ  የከፍተኛ ውጤት ታሪክ በ7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት  በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል፡፡ ሻምፒዮናውን በብቃት ለማካሄድ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታድዬም በ5 ሚሊዮን ብር  ወጭ ሙሉ እድሳት ተደርጎለታል፡፡ እድሳቱ የስታዲየሙ አጥር፣ የመጸዳጃ ቤቶች ማስፋፋት፣ የመብራት፣ የተመልካቾች መቀመጫዎች፣ የትንሿን ስታዲየም የአስፓልት ንጣፍ፣ የፖውዛ መብራቶች ያካተተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናውን በማስተናገድ ወደፊት ትልልቅ ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍላጎቷን ታነቃቃለች፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ እና 12 ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማንቀሳቀስ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ስታድዬም ሙሉ እድሳትና ለውድድሩ አጠቃላይ መስተንግዶ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ  ለበጀት እንደተመደበም ታውቋል፡፡
በሻምፒዮናው ላይ ለመሳተፍ  33 የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን አባል አገራት ማረጋገጫ ልከዋል፤ 618 የአፍሪካ ወጣት አትሌቶች በሜዳ እና በትራክ ላይ በሚካሄዱ 40 የስፖርት ውድድሮች ይሳተፋሉ፡፡ በመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ውድድሮች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በተለይ የኢትዮጵያ እና የኬንያ በፍፁም የበላይነት ፉክክር እንደሚገቡ  ሲጠበቅ፤ የምእራብ አፍሪካ አገራት አትሌቶች በአጭር ርቀት ውድድሮች እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ በሜዳ ላይ ስፖርቶች ብልጫ እንደሚኖራቸው በመገለፅ ላይ ነው፡፡ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ኢትዮጵያ 100፣ ናይጀሪያ 97 ፣ ሴራሊዮን 37፣ ሞሮኮ 35፣ ሱዳን 33፣ዚምባቡዌ 31፣ ካሜሮን 28፣ ቱኒዚያ 26፣ ቡርኪናፋሶ 23፣ ኮንጎ ብራዛቢል 19፣ ኡጋንዳ 19፣ ሴኔጋል 16፣ዛምቢያ 14፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ 13፣ ሩዋንዳ 7 ፣ ሲሼልስ 17፣አንጎላ 14  ፣ሶማሊያ 13፣ ኬንያ 12፣ ማሊ 11፣ ማዳጋስካር 8፣ አልጀሪያ 8፣ናምቢያ 8 ፣  ጋቦን 6 ግብፅ 6፣  ሌሴቶ 5፣፣ኮትዲቯር 5፣  ኬቬርዴ አይስላንድ 3፣ ፣ ስዋዚላንድ 3 እና  ጊኒ ቢሳው 1፣  ስፖርተኞችን አስመዝግበዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሞሪሽዬስ፤ ባምቦስ በተባለች ከተማዋ ባስተናገደችው 11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ29 አገራት የተውጣጡ 223 አትሌቶች በ40 የስፖርት ውድድሮች ተሳትፈው ነበር፡፡  15 አገራትአንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያ በማግኘት የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተው 119  ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡ ናይጄርያ በ19 ሜዳልያዎች (9 የወርቅ፤ 7 የብርና 3 የነሐስ) አንደኛ ደረጃ ነበራት፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ24 ሜዳልያዎች  (7 የወርቅ፤ 9 የብርና 8 የነሐስ) ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ 41 አትሌቶችን አሳትፋ የነበረችው ኢትዮጵያ በ22 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፤ 7 የብርና 8 የነሐስ) ሶስተኛ ደረጃ አግኝታ ነበር፡፡ ግብፅ በ11 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ፤ 4 የብርና 2 የነሐስ)፤ ኬንያ በ17 ሜዳልያዎች፤(4 የወርቅ፤ 9 የብርና 4 የነሐስ) እንዲሁም ኡጋንዳ በ4 ሜዳልያዎች (2 የወርቅ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ) እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በ11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 7 የወርቅ ሜዳልያዎች 6 ስድስቱን ያስመዘገቡት ሴቶች ሲሆን በወንዶች የተገኘው 1 የወርቅ ሜዳልያ ብቻ ነበር፡፡ እነሱም በ800 ሜትር ወንዶች በረከት ካህሳይ አዳነ፤ በ800 ሜትር ሴቶች አለም ገብረእግዚአብሄር፤ በ1500 ሜትር ሴቶች ዳዊት ስዩም፤ በ3000 ሜትር ሴቶች ሃፍታምነሽ ተስፋዬ ሃይሉ፤ በ5000 ሜትር ሴቶች ሩቲ አጋ ሶራ፤ በ3ሺሜትር መሰናክል ወየንሸት አንሳ ወልደፃዲቅ እንዲሁም በ5000ሜትር የርምጃ ውድድር አስካለ ቲካሳ በንቲ ናቸው፡፡

ከ19 ወራት በኋላ በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ  በሚደረገው 31ኛው ኦሎምፒያድ  ኢትዮጵያ በብስክሌት 2  ኦሎምፒያን ፍቅረኛሞችን ታሳትፋለች፡፡ ከ1940ዎቹ መጨረሻ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት አምስት ኦሎምፒኮችን የተሳተፈች ሲሆን ሁለቱ ኦሎምፒያኖች ፅጋቡ ግርማይ እና ሃድነት አስመላሽ ለኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት ስድስተኛው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ማሳካት ችለዋል፡፡ ሁለቱ ኦሎምፒያኖች በኦሊምፒክ ለመካፈል የሚያበቃቸውን ሚኒማ ያስመዘገቡት  ከ2 ሳምንት በፊት ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ በነበረው የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና ላይ ነው፡፡ በኦሊምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን ለመወከል የበቁት ሁለቱ የብስክሌት ኦሎምፒያኖች ፅጋቡ ገብረማርያምና ሐድነት አስመላሽ በትዳር ለመጣመር ከጫፍ የደረሱ ፍቅረኛሞች መሆናቸው ስኬታቸውን አስደናቂ አድርጎታል፡፡
ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ የሆነው ፅጋቡ ግርማይ፣ በስፖርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፉክክር ደረጃ ያሳደገ እና የቀየረ የመጀመሪያው ብስክሌተኛ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ የጎዳና ላይ የብስክሌት ሻምፒዮና ላይ በመጀመርያው  በግሉ የወርቅ ሜዳልያ በመጎናፀፍ በአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ አስመዘገበ፡፡ ከዚህ ስኬቱ በኋላ ደግሞ በ48 ኪሎ ሜትር የነጠላ ውድድር  ርቀቱን 1 ሰዓት 03 ደቂቃ 05 ሰከንድ በማጠናቀቅ አምስተኛ ደረጃ ቢያገኝም ለኦሊምፒክ የሚያበቃውን ሚኒማ አሳክቷል፡፡  ስለሆነም ኢትዮጵያ በወንድ ብስክሌተኛ በኦሎምፒክ መድረክ ለመሳተፍ ስትበቃ ከ44 ዓመታት  በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የ23 ዓመቱ ፅጋቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የብስክሌት ሻምፒዮና ለሁለት ጊዜያት አሸንፏል፡፡ ፅጋቡ የፕሮፌሽናልነት ዕድል አግኝቶ የመጀመርያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ክለብ ለመቀላቀል  ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመሄዱ በፊት የትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ ተወዳዳሪ ነበር፡፡በፕሮፌሽናል ብስክሌተኛነት  ከ2012 እኤአ ጀምሮ ለሶስት ዓመታት በደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ኩቤካ ስር ሲወዳደር ቆይቶ ላምፕሬ ሜሪዳ ለተባለ ክለብ ኮንትራት የፈረመው ከሁለት ወራት በፊት ነበር፡፡ አሁን አባል በሆነበት የጣሊያኑ የብስክሌት ክለብ ሳምፕሪ ሜሪዳ ፅጋቡ በዓመት እስከ 40,000 ዩሮ ክፍያ የሚፈፀምለት ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ ሆኗል፡፡ ከዓመት በፊት በቱር ዴ ታይዋን የጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድር በማሸነፍ በዓለም አቀፍ ውድድር በኢትዮጵያ ብስክሌተኛ ለመጀመርያ ጊዜ የተመዘገበ ውጤት ሲያገኝ፤ በታላቁ የዓለማችን የብስክሌት ውድድር «ቱር ዴ ፍራንስ» ላይ በመሳተፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ለመሆን ችሏል፡፡
በሴቶች ምድብም ደግሞ ሃድነት አስመላሽ የኦሎምፒክ ሚኒማ ያመጣችው 3ኛ ደረጃ ባገኘችበት የጎዳና ላይ የብስክሌት ሽቅድምድም ሲሆን ውጤቱ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሴት ብስክሌተኛ እንድትሳተፍ አድርጓል፡፡ ሃድነት  ተወልዳ ያደገችው በአክሱም ከተማ ሲሆን  የብስክሌት ስፖርትን ከጀመረች 10 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ለሜታ አቦ ቢራ ክለብ ስትወዳደር ቆይታ ከዚያም ትራንስ ኢትዮጵያን ተቀላቅላለች፡፡ሐድነት አስመላሽ በስፖርት ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች፡፡ በብስክሌት ስፖርት የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ሴቶች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማድረግ የጀመሩት ባለፈው ዓመት ሲሆን በአገር ውስጥ በሚካሄዱ ውድድሮች ለተከታታይ ስምንት ዓመት የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበረችው ሃድነት አስመላሽ የኦሎምፒክ ተሳትፎን በማግኘቷ ከፍተኛ መነቃቃት ትፈጥራለች፡፡
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያ በፈርቀዳጅነት ከተሳተፈችባቸው  ውድድሮች አንዱ የብስክሌት ስፖርት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከ60 ዓመታት በላይ እድሜ ላስቆጠረው የብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ የሚወክሏትን ሁለት ኦሎምፒያኖች ማግኘቷ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

እስላማዊ መንግስትን የማስፋፋት አላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው አይሲስ በቅርቡ በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች በሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ውስጥ ጭምብል አጥልቆ አሰቃቂ ግድያዎችን ሲፈጽም የሚታየውና ጂሃዲ ጆን በሚል ሃሰተኛ መጠሪያ የሚታወቀው ግለሰብ ትክክለኛ ማንነት መታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ግለሰቡ፣ ሞሃመድ ኢምዋዚ እንደሚባልና በትውልድ ኩዌታዊ፣ በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊ እንደሆነ ተረጋግጧል ያለው ዘገባው፣ ቀደም ሲል በእንግሊዝ የደህንነት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡
 ግለሰቡ ባለፈው ነሐሴ ወር  በተለቀቀው የአይሲስ ቪዲዮ፣ አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ጄምስ ፎሌን አንገት  ሲቀላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደታየ ያስታወሰው ዘገባው፣ በማስከተልም አሜሪካውያንና እንግሊዛውያንን በጭካኔ ሲገድል መታየቱን አስታውቋል፡፡ በዚህ ወር መጀመሪያ በተለቀቀውና ጃፓናዊው ጋዜጠኛ ኬንጂ ጎቶ ሲገደል በሚያሳየው የአይሲስ ቪዲዮ ውስጥም፣ ይሄው ግለሰብ ግድያውን ሲፈጽም እንደታየ ዘገባው አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ የግድያ ተግባሩን ሲፈጽም ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሶ፣ ፊቱን በጭንብል ጋርዶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ አንገት ከመቅላቱ በፊትም በእንግሊዛውያን የአነጋገር ቅላጼ ምዕራባውያን መንግስታትን ያወግዝ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በአይሲስ ቁጥጥር ስር ቆይተው በቅርቡ የተለቀቁ የአይን እማኞች፣ ግለሰቡ በሶሪያ ከሚንቀሳቀሱ የቡድኑ እንግሊዛውያን ጂሃዲስት መሪዎች አንዱ እንደሆነ መመስከራቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡እስላማዊ መንግስትን የማስፋፋት አላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው አይሲስ በቅርቡ በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች በሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ውስጥ ጭምብል አጥልቆ አሰቃቂ ግድያዎችን ሲፈጽም የሚታየውና ጂሃዲ ጆን በሚል ሃሰተኛ መጠሪያ የሚታወቀው ግለሰብ ትክክለኛ ማንነት መታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ግለሰቡ፣ ሞሃመድ ኢምዋዚ እንደሚባልና በትውልድ ኩዌታዊ፣ በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊ እንደሆነ ተረጋግጧል ያለው ዘገባው፣ ቀደም ሲል በእንግሊዝ የደህንነት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡
 ግለሰቡ ባለፈው ነሐሴ ወር  በተለቀቀው የአይሲስ ቪዲዮ፣ አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ጄምስ ፎሌን አንገት  ሲቀላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደታየ ያስታወሰው ዘገባው፣ በማስከተልም አሜሪካውያንና እንግሊዛውያንን በጭካኔ ሲገድል መታየቱን አስታውቋል፡፡ በዚህ ወር መጀመሪያ በተለቀቀውና ጃፓናዊው ጋዜጠኛ ኬንጂ ጎቶ ሲገደል በሚያሳየው የአይሲስ ቪዲዮ ውስጥም፣ ይሄው ግለሰብ ግድያውን ሲፈጽም እንደታየ ዘገባው አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ የግድያ ተግባሩን ሲፈጽም ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሶ፣ ፊቱን በጭንብል ጋርዶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ አንገት ከመቅላቱ በፊትም በእንግሊዛውያን የአነጋገር ቅላጼ ምዕራባውያን መንግስታትን ያወግዝ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በአይሲስ ቁጥጥር ስር ቆይተው በቅርቡ የተለቀቁ የአይን እማኞች፣ ግለሰቡ በሶሪያ ከሚንቀሳቀሱ የቡድኑ እንግሊዛውያን ጂሃዲስት መሪዎች አንዱ እንደሆነ መመስከራቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡

- አልቃይዳ በዋይት ሃውስ ላይ ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ ነበረው


ኦሳማ ቢላደን በህይወት በነበሩበት ጊዜ በምዕራባውያን  አገራት የሽብር ጥቃቶችን ለመሰንዘር በተያዙ ዕቅዶች ዙሪያ ከአልቃይዳ መሪዎች ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች መገኘታቸውን  ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
ከአልቃይዳ ጋር በመተባበር በእንግሊዝ የሽብር ጥቃቶችን ለመሰንዘር አሲሯል በሚል ክስ የተመሰረተበትን አቢድ ናስር የተባለ ፓኪስታናዊ ተማሪ ጉዳይ በመመርመር ላይ የሚገኘው የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ባለፈው ረቡዕ በዋለው ችሎት፣ ቢላደን ከቡድኑ መሪዎች ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በማስረጃነት ቀርበዋል፡፡ ደብዳቤዎቹ ቢላደን በሩስያ፣ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በሌሎች የምእራቡ አለም አገራት ላይ የሽብር ጥቃቶችን ለመሰንዘር ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ያጋለጡ ሲሆን በአቦታባድ ተደብቀውበት በነበረው ግቢ ውስጥ በአሜሪካ ወታደሮች እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከሚኖሩ የቡድኑ የጥቃት መሪዎች ጋር የሽብር ሴራ መልዕክቶችን ይለዋወጡ እንደነበር ያረጋገጡ ናቸው ተብሏል፡፡ አልቃይዳ በዋይት ሃውስ ላይ የሽብር ጥቃት የመሰንዘር ትልቅ እቅድ እንደነበረው የሚገልጽ ደብዳቤ ከመገኘቱ በተጨማሪ፣ ቢላደን አዳዲስ የጥቃት መፈጸሚያ መንገዶችን መቀየስ እንደሚገባ ከጥቃት መሪዎቹ  ጋር ያደረጉትን ውይይት የሚጠቁሙ  ደብዳቤዎችም ተገኝተዋል፡፡

የ5ጂ ፍጥነት ከ4ጂ በ65ሺህ እጥፍ ይበልጣል
 - 100 ፊልሞችን በሶስት ሰከንድ ማውረድ ያስችላል

   የሱሬ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በታሪክ እጅግ ፈጣኑ የተባለለትን የ5G (የአምስተኛው ትውልድ) የኢንተርኔት መረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በጥቅም ላይ ከሚውሉት የመረጃ ልውውጦች ፍጥነት በብዙ ሺህዎች እጥፍ የላቀ ነው የተባለለት የ5ጂ ፈጠራ፣ በሰከንድ አንድ ቴራ ባይት መጠን ያለው መረጃ የማስተላለፍ አቅም ያለው ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የ5ጂ ፈጠራ ማዕከል ሃላፊ፤ አዲሱ ቴክኖሎጂ ከሶስት አመታት በኋላ በይፋ ተጠናቅቆ ለህዝብ እይታ እንደሚበቃ የተናገሩ ሲሆን ምርምሩን የሚመራው ኦፍኮም የተባለ ኩባንያም፤ ፈጠራው እስከ 2020 ድረስ በእንግሊዝ ተጠቃሚዎች እጅ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁሟል፡፡
የቴክኖሎጂው ፍጥነት እጅግ የላቀ እንደሆነ የጠቆመው ቢቢሲ፤ የአንድ ሙሉ ፊልም መቶ እጥፍ ያህል መረጃ ያለውን ፋይል በሶስት ሰከንድ ብቻ ማውረድ (ዳውንሎድ ማድረግ) እንደሚያስችል  አስረድቷል፡፡ የ5ጂ ፍጥነት፣ በአሁኑ ሰአት ጥቅም ላይ እየዋለ ከሚገኘው 4ጂ አንጻር ሲወዳደር ከ65 ሺህ እጥፍ በላይ እንደሚበልጥም አመልክቷል፡፡

ስልጣን ከያዝን ቦኮ ሃራም በናይጀሪያ አይኖርም ብለዋል

በመጪው ወር በሚካሄደው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኦል ፕሮግሬሲቭስ ኮንግረስ የተባለውን  የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ በመወከል የሚወዳደሩት የፓርቲው መሪ ሙሃሙዱ ቡሃሪ፣ ፓርቲያቸው ስልጣን ቢይዝ ቦኮ ሃራም ከተባለው አሸባሪ ቡድን ጋር ሰላማዊ ድርድር እንደማያደርግ አስታወቁ፡፡ ጽንፈኛውን ቡድን ለማጥፋት ብቸኛው አማራጭ የሃይል ጥቃት መሰንዘር ነው ያሉት ቡሃሪ፤ በስልጣን ላይ ያለው የአገሪቱ መንግስት በቡድኑ ላይ የሚያሳየውን መለሳለስ ክፉኛ ነቅፈውታል፡፡
“ቦኮ ሃራም የሰላም ፍላጎት የሌለው የጥፋት ቡድን ነው፤የሰላም ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ 13 ሺ ናይጀሪያውያንን አይገድልም ነበር” ያሉት የቀድሞው የአገሪቱ የጦር አዛዥ ሙሃሙዱ ቡሃሪ፣ ፓርቲያቸው በምርጫው አሸንፎ ስልጣን ከያዘ፣ ቦኮ ሃራም በናይጀሪያ ግዛት ውስጥ ስንዝር መሬት እንደማይኖረው አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን መንግስት፣ ሰሞኑን በአሸባሪ  ቡድኑ ላይ የተጠናከረ ዘመቻ ማወጁን ያስታወቀ  ሲሆን የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ግን  “ፍሬ ቢስ” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

የሰዓሊ ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲ ማን) ከ30 በላይ የካርቱን ስዕሎች የቀረቡበት “ስዕላዊ ምፀት እና ስዕላዊ ስላቅ” የተሰኘ የስዕል ትርዒት ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም በጋለሪያ ቶሞካ መከፈቱ የሚታወስ ሲሆን በነገው ዕለት ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በሥራዎቹ ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡
የጋለሪው አርት ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ሰዓሊያን፣ የስዕል አፍቃሪያን፣ ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በውይይቱ ላይ እንደሚሳተፉ የጋለሪው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ ተናግሯል፡፡ ውይይቱ በሰዓሊው ስራዎች፣ በአሳሳል ፍልስፍናው፣ ስዕሎቹ ለአገራችን ስነ-ጥበብ ባላቸው ፋይዳና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል ተብሏል፡፡ ጋለሪያ ቶሞካ 14ኛውን የስዕል ትርዒት ከአንድ ወር በኋላ ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሆነም ታውቋል፡፡

Monday, 02 March 2015 10:26

የፍቅር ጥግ

(ዝነኛ ሴቶች ስለወንዶች)
ራስህን በሌላ ሰው መነፅር እየተመለከትክ ህይወትህን መምራት አትችልም፡፡
ፔኔሎፕ ክሩዝ (ተዋናይ)
ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው የተለወጠው አሁን ራሱን የሚያውቅ ወንድ መፈለጌ ነው፡፡ ራሱን የሚገነዘብ፣ ከራሱ ጋር የታረቀና “ቀደም ሲል የቱ ጋ እንደተሞኘው አውቃለሁ፤ ዳግም ግን አልሞኝም” ማለት የሚችል ወንድ ነው የምፈልገው፡፡
ካሜሮን ዲያዝ (ተዋናይ)
አንድ ወንድ ስከታተል እንደነበረ አልክድም፡፡ ጥሩ ጓደኛሞች ነበርን፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ተለያየን፡፡ አንድ ቀን የሚሰራበት ምግብ ቤት ሄድኩና እዚያ መስራቱን እንደማላውቅ አስመስዬ አንተ፤ እዚህ ነው እንዴ የምትሰራው? እኔ እኮ አላውቅም ነበር” አልኩት፡፡ ይሄ በመላ ህይወቴ ከፈፀምኩት ሁሉ የላቀ ሴራ ነው፡፡ ነገር ግን ሰርቶልኛል፤ ስለዚህም አልፀፀትም፡፡
ራሄል ማክአዳምስ (ተዋናይ)
በአሁኑ ሰዓት ከወንዶች ጋር መቅበጥ ያስደስተኛል፡፡ ሴተ-ላጤ ስለሆንኩ ነፃነነቴን እያጣጣምኩ ነው፡፡ ሆኖም ስልክ ቁጥሬን አዘውትሬ አልሰጥም፡፡ የፍቅር ግንኙነት ከጀመርኩ ግን ቀልድ አላውቅም፤ ወንዱን ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ነው የምመረምረው፡፡
ሪሃና (ዘፋኝና ተዋናይ)
ወንዶችን በተመለከተ ማር አይጥምሽ ነኝ፡፡ ከልቤ የተማረኩለት ወንድ የሚያጋጥመኝ በየአምስት ዓመቱ አንዴ ነው፡፡
ኢቫንጄሊን ሊሊ
ፍቅረኛ መፈለጉን ትቼዋለሁ፡፡ የሚስማማኝ ወንድ ባገኝ ግን አልፈልግም ማለት  አይደለም፡፡ ሆኖም አልቸኩልም፡፡ ከጓደኞቼና ከጥሩ ፊልም ጋር ቤት ውስጥ ብቀመጥ እመርጣለሁ፡፡
ኢሚሊ ቫንካምፕ

Monday, 02 March 2015 10:20

የግጥም ጥግ

በሁለት ድንጋይ
ልሰህ እንዳትጨርሰኝ -
እጅግ አልጣፈጥኩም
አንቅረህ እንዳትተፋኝ -
እሬት ብቻ አልሆንኩም
ሁሌም እባብ ሆኜ -
በልቤ አልተሳብኩም
እንደእርግብ ታምኜም -
ከታዛ አልበረርኩም
በሁለት ድንጋዮች -
አንዲት ወፍ ልመታ
አነጣጥሬያለሁ -
እየኝ በለዘብታ፡፡

ንገረኝ ሳኩራ
እንደ አገሬ አደይ ቀለመ ደማቁ
እንደ መስኩ ንጣፍ ህብረ ፍልቅልቁ
ደመናው ማለፉን ጉሙ መገፈፉን
የጨቀየው ቀዬ በብራ መግፈፉን
ትተህ ክፉ ክፉን
አውጋኝ ደግ ደጉን፡፡
ይቺ ምስኪን ነፍሴ የምስራች ናፍቃ
በ-ብ ---ዙ ተጨንቃ
ትለምንሃለች ልቧ እየደወለ
ርዳ ተርበድብዳ ሰው እንደገደለ፡፡
ጣቷ ተቆላልፎ
ሆዷ ተንሰፍስፎ
አይኗም የብሶቱን የጨው ውሃ አርግፎ
ት-ማ-ጠ-ን-ሐ-ለ-ች
እያሽቆጠቆጣት የጃፓን ክረምቱ
አል-ገፋ ብሏት ጠንቶባት በብርቱ፡፡
የአገራችን አደይ ክረምትና በጋ
እርቃለችና አትሔድም ፍለጋ
ምላሽ አትንፈጋት እባክህ ሳኩራ
እንደ ቅርንጫፍህ እሷም ተንጨባራ
ክርችው! እንዳትለው በቁሟ በድና
መቼ ነው ንገራት ጥጡስ የሚያባራው የጃፓን ክረምቱ
እንኳንስ ለመጤው ለራሱም አልሳሳ አልተፈታ ፊቱ፡፡
ወይም አስተምራት እንዳንተ ጽናቱን
አረንጓዴ ቅጠል፤ ቅርንጫፍ አርግፎ፤ ሞቶ መነሳቱን፡፡
በራሔል አሸናፊ
“እንካችሁ አደራ” ከተሰኘው የግጥም መድበሏ - የካቲት 2007 ዓ.ም)