Administrator

Administrator

ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለጉዳቱ መባባስ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያን ተጠያቂ አድርገዋል
“ቃጠሎው ከጃዝ አምባ አልተነሳም” የጃዝ አምባ ዋና ሥራ አስኪያጅ
እሣቱ ከጣይቱ ኪችን አለመነሳቱን አረጋግጣለሁ - አቶ አያሌው ታደሰ የጣይቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ
አጋጣሚው ምትክ የማላገኝላቸውን ነገሮች ያጣሁበት ክፉ አጋጣሚ ነው - የፊልም ፕሮዳክሽን ባለቤት

ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ታሪካዊው የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል እሣት መነሻ እያወዛገበ ነው፡፡ ፖሊስ እሳቱ የተነሳው በጃዝ አምባ አዳራሽ ውስጥ በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች መጠላለፍ ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ቢገለፅም እሳቱ ከጃዝ አምባ አለመነሳቱን የጃዝ አምባ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርምያስ ፋንቱ ገልፀዋል፡፡የጃዝ አምባ የኤሌክትሪክ ሲስተም አዲስና ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ለእንዲህ አይነት አደጋ የሚጋለጥበት ምንም ምክንያት እንደሌለና ላለፉት አራት ዓመታት ምንም ዓይነት ችግር አጋጥሞ እንደማያውቅ የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፤ ፖሊስ እሳቱ የተነሳው ከጃዝ አምባ ነው ማለቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ “ከሙዚቃ መሳሪያ ጋር በተገናኘ እሳቱ ተነስቷል እንዳይባል እንኳን እሁድ ጠዋት የጃዝ አምባ ሰራተኛ የሆነው ልጅ ገብቶ መድረኩን ለቴአትር ዝግጁ ለማድረግ ሁሉንም የሙዚቃ መሳሪያ አነሳስቶ ነበር” ብለዋል፡፡ ሌላው እሳቱ ከጃዝ አምባ እንዳልተነሳ እርግጠኛ የሆኑበትን ምክንያት አቶ ኤርሚያስ ሲናገሩ፤ የህብረት ባንክና የጃዝ አምባ ሲስተም አንድ መሆኑን ጠቁመው፣ እሳቱ ተነስቶ ከጀርባ በኩል ጭስ ሲታይ ሰዎች ከኤቲኤም ማሽን ብር እያወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ እሳቱ ከጃዝ አምባ ቢነሳ ኖሮ ኤቲኤም ማሽኑ አይሰራም ነበር  ሲሉ እሳቱ ከጃዝ አምባ ተነሳ መባሉን እንደማይቀበሉት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም በታዋቂዎቹ ሙዚቀኞች አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ሄኖክ ተመስገን፣ ግሩም መዝሙር፣ ዮናስ ጎርፌና ሳሙኤል ገዛኸኝ የተቋቋመው ጃዝ አምባ፤ በቃጠሎው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት ደርሶብኛል ብሏል፡፡ የጃዝ አምባው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ፋንቱ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በአደጋው የተለያዩ እጅግ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልፀው እሳቱ ገና በጀመረባቸው ደቂቃዎች ጉዳዩን ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ብናሳውቅም አፋጣኝ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም ብለዋል፡፡ “እሳት አደጋዎች ዘግይተው መድረሳቸው ሳያንስ ከስፍራው ከደረሱም በኋላም አደጋውን ለመከላከል ያሳዩት ቸልተኝነት ጉዳቱ እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል፡፡
እነመርሃዊ ስጦታ፣ ጋሽ ባህታ፣ ግርማ ነጋሽና መሰል አንጋፋ የሙዚቃ ሰዎች ወደ ሙዚቃ እንዲመለሱና ሞራላቸው እንዲጠገን በማድረጉ በኩል ጃዝ አምባ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፤ ቃጠሎው በእነዚህ ሰዎችም ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጃዝ አምባውን ወደ ቀድሞው ሥራው ለመመለስ በኮንሰርትም ሆነ በሌላ መንገድ ገቢ ለማሰባሰብ ቃል መገባቱንና ብዙ ተዘግቶ ይቆያል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡ የአዲስ ተስፋ ኮሙኒኬሽንና ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ ተስፋ በበኩላቸው፤ በቃጠሎው ምትክ የሚያገኙላቸውን ውድ ነገሮች ማጣታቸውን ጠቁመው፣ “ይህ በህይወቴ ብዙ ነገሬን ያጣሁበት ክፉ አጋጣሚ ነው” ብለዋል፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት ጊዜ አርቲስቶች የሰሩትን ስራ በኃላፊነት ተረክበው ሲሰሩ እንደነበር የተናገሩት አቶ አዲስ፤ ሥራው ያለ ቀሪ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልፀዋል፡፡ በቀርቡ ሠርተው ያጠናቀቁት “በቅኝትሽ” የተሰኘ አዲስ ፊልምን ጨምሮ የሠርግ ስነስርዓታቸውን ሲፈፅሙ የተቀረፁ የቪዲዮና የፎቶግራፍ ቅጂም ያለምንም ምትክ ወድሞብኛል ብለዋል፡፡ በገንዘብ ልተካቸው የማልችላቸው በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችና ምትክ የማላገኝላቸው ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወድመውብኛል ሲሉም ሁኔታውን በሃዘን ገልፀዋል፡የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ፤ በቃጠሎው ወቅት በፍጥነት ከቦታው አለመድረሳቸውንና ከደረሱም በኋላ እሣቱን ለማጥፋት ቸልተኝነት ማሣየታቸውን አስመልክቶ የቀረበባቸውን ቅሬታ፤ የሥራውን ባህርይ ካላማወቅና ከግንዛቤ ማነስ የተሰጠ አስተያየት ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
የእሣት አደጋው ጥሪ በተደረገልን በሁለት ደቂቃ ውስጥ ከሥፍራው ደርሰናል ያሉት ኦፊሰሩ፤ የሆቴሉ እድሜ፣ ርዝማኔና የተሠራበት ቁሳቁስ በፍጥነት ተቀጣጣይ መሆን አደጋውን አባብሶታል ብለዋል፡፡
ሠራተኞቹ ከሥፍራው እንደደረሱ ምንም አይነት ቸልተኝነት አላሣዩም ያሉት አቶ ንጋቱ፤ እሣት እንደ ሻማ እፍ ተብሎ የማይጠፋ በመሆኑና ህዝብ የማይረዳቸው ብዙ ቴክኒካል ነገሮች በመኖራቸው እነሱ እስከሚስተካከሉ ድረስ ደቂቃዎች ማለፋቸው አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡  

ያጨሰ 1 ሺህ ብር፣ ያስጨሰ 3 ሺህ ብር ይቀጣል

የመቐለ ከተማ አስተዳደር በመዝናኛ ስፍራዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በመሳሰሉት ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክል ህግ ተግባራዊ ማድረጉ ተገለፀ፡፡በመዝናኛ ስፍራዎች ሲጋራ ሲያጨሱ የተገኙ ግለሰቦች ከ1 ሺህ ብር በላይ፣ ሲጋራ እንዲጨስ የፈቀዱ የመዝናኛ ስፍራዎች ባለቤቶች ደግሞ ከ3ሺህ ብር በላይ ቅጣት እንደሚጣልባቸው የጠቆመው የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደውን ይህን ህግ በስራ ላይ በማዋል መቐለ የመጀመሪያዋ ከተማ መሆኗንም አስታውቋል፡፡ህጉ ከዚህ በተጨማሪም በስታዲየሞችና ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች በሚከናወኑባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ እንደሚከለክል ታውቋል፡፡በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አንድ አስረኛ ያህሉ የሲጋራ ሱስ ተጠቂ እንደሆኑ የአለም የጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል፡፡የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክልና በሲጋራ ሽያጭ ላይ ገደብ የሚጥል  አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

በሲሚንቶ ገበያ የታየው ለውጥ በቢራ እየተደገመ ነው

   ከነባር የሲማንቶ አምራቾች ላይ ግዙፉ የደርባ ሚድሮክ ፋብሪካ ከዚያም የድሬዳዋው ናሽናል ሲሚንቶ ሲታከልበት እንደታየው በቢራ አምራቾች የተጧጧፈ ውድድርም በአጭር ጊዜ አስደናቂ የዋጋና የአቅርቦት ልዩነት እየታየ ነው፡፡ የዋጋ ንረት በተለመደበት አገር ደንበኞችን የመማረክ ብርቱ ፉክክርና ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ከመታየቱም በተጨማሪ፤ ዘንድሮ ውድድሩን የሚያጠናክሩ አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎች ስራ የሚጀምሩበት ዓመት ሆኗል፡፡
ሰሞኑን ሄኒከን ካስመረቀው ፋብሪካ ብዙም ሳይቆይ፣ በጥቂት ሳምንታትና ወራት ሃበሻ ቢራና  ሌላ ግዙፍ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡
በቢዝነስ ውስጥ የመንግስት ድርሻና ጣልቃ ገብነት በቀነሰ ቁጥር፣ የምርቶች ዋጋና የአገልግሎት ጥራት እንደሚሻሻል እንደ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን የመሳሰሉ ምሁራን በበርካታ አመታት ጥናትና ምርምር ያረጋገጡ ቢሆንም የነፃ ገበያ ውድድር ትሩፋት ያለጥናትና ምርምር በገሃድ ከታየባቸው መስኮች አንዱ የሲሚንቶ ገበያ ነው፡፡ አነስተኛ የግንባታ ስራ የጀመሩ ዜጐች በሲሚንቶ የዋጋ ውድነት፣ ትልልቅ ፕሮጀክት የጀመሩ ኢንቨስተሮች ደግሞ ለባለ አስር ፎቅ ህንፃ የሚበቃ ሲሚንቶ ሲጠይቁ የአንድ ፎቅ ብቻ እየተፈቀላቸው፣ ለዚያውም ተራ እስኪደርሳቸው ግማሽ አመት እየዘገየ፣ የዋጋው ውድነት ታክሎበት ለዓመታት ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ አነስተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንቶችና የነባሮቹ የማስፋፊያ ውጥኖች ላይ ግዙፉ የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ማምረት ሲጀምር ግን የቀድሞው የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ተረት ሆነ፡፡ የሲሚንቶ ዋጋ በግማሽ ቀነሰ፡፡ የድሬዳዋው ናሽናል ሲሚንቶ መጠናቀቁና ወደፊትም የናይጄሪያው ናሽናል ሲሚንቶ መጠናቀቁና ወደፊትም የናይጄሪያው ባለሃብት ፕሮጀክት እየተስፋፋ መሆኑ ደግሞ፤ የሲሚንቶ ችግር በነፃ የገበያ ውድድር ለዘለቄታው እንደሚቀየር ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መንግስት ከቢራ ቢዝነስ እየወጣ በመጣ ቁጥር፣ የምርትና የአገልግሎት ማሻሻያዎች  እየታዩ መምጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን የነፃ ገበያ ፉክክሩና ትሩፋቶቹ ጐልተው የታዩት ከአዲስ አመት መግቢያ ጀምሮ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሄኒከን፤ ዋልያ ቢራ ምርቱን በ10 ብር ሲያቀርብ ነው፤ አይቀሬው የነፃ ገበያ ትሩፋት በራሱ ጊዜ መዛመት የቀጠለው፡፡ ሌሎቹም ግንባታው እያጠናቀቁ ነው - ለዚያውም በየፊናቸው ሪኮርድ የሚሰብሩ ግዙፍ ፋብሪካዎችን፡፡ እዚህም ጋ ኒያላ፣ ዘመን የመሳሰሉ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ጋር፣ ደንበኞችን ለመማረክ የዋጋ፣ የአገልግሎት ፉክክር አጧጥፈዋል፡፡ ቢጂአይ  በ11 ብር የሚሸጠውን አንድ ጃንቦ ብርጭቆ ድራፍት “ሃፒ ሃወር” በማለት ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ በ8 ብር መሸጥ ጀመረ፡፡ ዲያጆ በፊናው፤ በዘጠኝ ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ጃንቦ ሜታ ድራፍት በ8 ብር እንደሚሸጥ ካስታወቀ በኋላ፤ በቅርቡ “ዘመን” በማለት የሰየመውን የቢራ ምርት በ10 ብር መሸጥ ጀምሯል፡፡ ቢጂአይ በበኩሉ፤ ከሰሞኑ  ሁለት ጠርሙስ ጊዮርጊስ ቢራ ለሚጠጣ ደንበኛ አንድ ጠርሙስ መመረቅ ጀምሯል፡ ደንበኞችን ለመማረክ የሚደረገው የዋና የአገልግሎት ፉክክር በዚህ አይቆምም፡፡ በቅርቡ ወደ ገበያ ለመግባት የተቃረቡ አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ከደጃችን እየደረሱ ነው፡፡ ሃበሻ ቢራ በቅርብ ሳምንታት ወደ ገበያ እንደሚገባ የገለፀ ሲሆን፣ ዳሽን ቢራ በደብረ ብርሃን የማስፋፊያ ግንባታውን አጠናቆ በመጋቢት ወር በቀን 3 ሚሊዮን ጠርሙስ ቢራ የሚያመርት ግዙፍ ፋብሪካ ያስመርቃል፡፡ ራያ ቢራም ግንባታውን ጨርሶ ወደ ገበያ ለመግባት እየተንደረደረ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ሲያስገቡ ፉክክሩ ይበልጥ እንደሚጦፍ መገመት ይቻላል፡፡ የሄኒከን እና የዳሽን ቢራን ዘገባ በገጽ 11 መልከቱ፡፡

በመቶ ከሚቆጠሩ አገራት ከአስር ሺ በላይ ተሳታፊዎችን በማስተናገድ በአዲስ አበባ ከተካሄዱ አለማቀፍ ጉባኤዎች መካከል አንዱ ይሆናል የተባለው 3ኛው “ፋይናንስ ለልማት” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በሰኔ ወር ለማካሄድ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዋና አማካሪዎች እየተዘጋጁ ነው፡፡
የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ሚኒስትሮች፤ እንዲሁም የቢዝነስ ሰዎችን ጨምሮ 10 ሺ ተሳታፊዎች በኮንፈረንሱ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ኮንፍረንሱ የእዳ ቅነሳና ስረዛ ላይ የሚያተኩር ይሆናል ብለዋል፡፡ ከፍተኛ እዳ የተከማቸባቸው የአፍሪካና የሌሎች ድሃ አገሮች መንግስታት ባለፉት አስር አመታት የእዳ ስረዛ እንደተረገላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ እንደገና እዳ ውስጥ እየገቡ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ በእዳ ብዛት ሌሎች የአፍሪካ መንግስታት በርካታ ቢሆኑም፤ በኢትዮጵያ መንግስት ስር የሚገኙ ድርጅቶች በብድር የተከማቸባቸው እዳ በጥቂት አመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡
ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ (ወደ 300 ቢሊዮን ብር ገደማ) የውጭ እዳ፣ እንዲሁም የዚያን ያህል 300 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ የባንክ እዳ እንዳለባቸው ከመንግስት ተቋማት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሰኔ ወር የሚካሄደው አለማቀፍ ጉባኤ ለድሃ አገራት የእዳ ቅነሳና ስረዛ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ የሚወያይ ቢሆን፤ ከዚሁ ጐን ለጐን የድሃ አገር መንግስታት ራሳቸውን የሚችሉበት ጉዳይም ይነሳል ተብሏል፡፡ ጉባኤው የአገር ውስጥና ፋይናንስ መፍጠሪያ ዘዴዎችን በማስፋፋት ላይ ትኩረትን ያደርጋል ብለዋል፡፡ የሀገር ውስጥ አለማቀፍ ፋይናንስን እንዴት ማንቀሳቀስ ይቻላል በሚለው ጥያቄ ላይም  ይመከራል ተብሏል፡፡  
ሚኒስትሩ ሐሙስ ጥር 7 ቀን ከአሜሪካ ከመጡ የፕሬዚዳንት ኦባማ ከፍተኛ አማካሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ የሰኔው ጉባኤ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፋቸውን ለመስጠት መምጣታቸውን ከኦባማ ዋና አማካሪዎች መካከል ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ጆን ፓዴስታ ተናግረዋል፡፡
 ዶ/ር ቴዎድሮስ አዳኖም በበኩላቸው፤ የኦባማ ዋና አማካሪዎች እዚህ መምጣታቸው ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ በገንዘብ ሚኒስትሩ ሶፍያ አህመድ የሚመራ የበላይ ኮሚቴ የጉባኤውን ዝግጅት እያከናወነ ሲሆን፤ የመጀመሪያው አለማቀፍ የፋይናንስ ለልማት በ2002 ዓ.ም በሞንትሪያል ሁለተኛው አለማቀፍ “ፋይናንስ ለልማት” ደግሞ በ2008 ዓ.ም በዶሀ መካሄዱን ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከ15 ዓመታት በላይ በምሽት ክበቦች ሰርቷል፡፡ “ስያሜ አጣሁላት” በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ ከህዝብ ጋር የተዋወቀው ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ ሦስተኛ አልበሙን (ስወድላት) ሰሞኑን ለቋል፡፡ በአዲሱ ስራውም ስለ ሃገር፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ታማኝነት፣ ስለ ጎንደር፣ ስለ ወሎና ምንጃር ብዙ አቀንቅኗል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከድምፃዊ ማዲንጐ ጋር በአዲሱ አልበሙና በሙያው ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡
የመጀመሪያ ስራህ “ስያሜ አጣሁላት” የሚል ነበር፡፡ በሁለተኛው “አይደረግም” ብለህ መጣህ፡፡ አሁን ደግሞ “ስወድላት” እያልክ ነው…
የመጀመሪያው አልበሜ የልጅነት ስራዬ ነው፡፡ ያኔ ጠቆር ያልኩ ነበርኩኝ፤ እንዳሁኑ አልገፈፍኩም ነበር፡፡ አሁን እንደ እባብ ቆዳ ቀይሬያለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ “ስያሜ አጣሁላት” በልጅነት እድሜ ከህዝብ ያገናኘኝ ስራ ነው፡፡ ወቅቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ ታዲያ “ስያሜ  አጣሁላት” እና “አማን ነው ወይ ጎራው” የተሰኙት ሁለት ዘፈኖች በተለየ መልኩ ተወደውልኝ ነበር፡፡ ሁለተኛው ስራዬ የትዝታ ዘፈን ያለበት “አይደረግም” በሚል ስያሜ የወጣው ነው፡፡ አሁን “ስወድላት”ን ይዤ ወደ አድማጭ ቀርቤያለሁ፡፡
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት “ስያሜ አጣሁላት” እና “አማን ነው ወይ ጎራው” የተወደዱበት ምክንያት ምንድን ነው? ከጦርነቱ ጋር የተገናኘ ሃሳብ ይዘዋል እንዴ?
በተለይ “ስያሜ አጣሁላት” ከኤርትራ ጠብ አጫሪነት ጋር ሳይያያዝ አይቀርም፡፡ እኔ በወቅቱ እንደነገርኩሽ ልጅ ስለነበርኩ ጉዳዩ አይገባኝም ነበር፡፡ ግጥሙን የፃፈው አንጋፋው የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ይልማ ገ/አብ ነበር፡፡ ይልምሽ ደግሞ ወቅታዊ ፈጠራዎችን በመስራት አይታማም፡፡ አሁን ነው የሚገባኝ፡፡ እኔ ከሴት ልጅ ፍቅር ጋር ብቻ ነበር አገናኝቼ የዘፈንኩት፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን ግጥሙ ከወቅቱ ጦርነት ጋር እንዲሄድ ሆን ተብሎ ይሰራ አይሰራ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግምቴን ነው የነገርኩሽ፡፡
ሁለተኛው አልበምህ “አይደረግም” የሶስት አራት ድምፃዊያንን ትዝታ አፈራርቀህ የሰራህበት ሲሆን የትዝታው ዘፈን ድምፅህ የተፈተነበትና ወደ አድማጭ በደንብ የቀረብክበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
በጣም ትክክል ነው፡፡ እኔም ባለውለታዬ የምለው ዘፈን ትዝታው ነው፡፡ የእኔ የመዝፈን ብቃት ምን ያህል እንደሆነ ለህዝብ ግልፅ ያደረገ ስራ በመሆኑ በሚባለው ነገር መቶ በመቶ እስማማለሁ፡፡
“አይደረግም” ከወጣ ረዘም ያለ ዓመት ሆኖታል… ባልሳሳት ሰባት ዓመት አካባቢ… ለምን እንደዚህ ቆየህ?
ተቃርበሻል! ስምንት ዓመት አልፏል አልበም ሳልሰራ፡፡ በመሃል ግን የተሳኩና የተወደዱ ነጠላ ዜማዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ለምሳሌ “የበላይ ዘለቀ”፣ “አንበሳው አገሳ”፣ ለ“አባይ ወይስ ቬጋስ” ፊልም የሰራሁት ማጀቢያ ሙዚቃ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ህዝቡ ስምንት ዓመት አልበም አለመስራቴን እንዳያስታውስ አድርገውታል፡፡ ከህዝብ ጆሮ አልጠፋሁም ነበር ማለት ነው፡፡ በዚያ ላይ ኮንሰርቶች እሰራለሁ፤ የሰርግ ስራዎችንም እንደዚሁ፡፡ ይህን ስታይው ስምንት ዓመት ሙሉ የጠፋሁ አይመስልም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን እንደዚህ አልጠፋም፤ በየሁለት አመቱ አልበም ይኖረኛል፡፡
አዲሱ አልበምህ በግጥማና ዜማ የነማን አስተዋፅኦ አለበት? ምን ያህል ጊዜስ ወሰደ?
በመጀመሪያ ደረጃ የአልበሙን ስራ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የወሰድኩት እኔ ነኝ፡፡
ምን ማለት ነው?   
ይሄ ማለት ግጥምና ዜማ የመምረጡን ስራ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የተወጣሁት እኔው ነኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ሙዚቃ ውስጥ እንደመሆኔ፣ ግጥምና ዜማን በማስተዋል በኩል ጥሩ ተሰጥኦ አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ የአልበሙን ግጥምና ዜማ የመረጥኩት ራሴ ነኝ፡፡ ነገር ግን ግጥምና ዜማ እንዲሰሩ ትልልቅ የሚባሉና የካበተ ልምድ ያላቸውን ሰዎች አሳትፌአለሁ፡፡ ይልማ ገ/አብ፣ ጸጋዬ ደቦጭ፣ አበበ ብርሃኔ፣ አማኑኤል ይልማ፣ ታመነ መኮንን፣ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ)፣ መኮንን ለማ (ዶክተሬ) እና መሰል ታዋቂዎች ተሳትፈዋል፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት የተለያዩ ግጥምና ዜማዎችን ስሰበስብና ስመርጥ ነው የቆየሁት፡፡ 30 ዘፈኖች መረጥኩና ስቱዲዮ ተቀረፅኩ፤ ከ30ው ግን 14ቱን ነው የመረጥኩት፡፡ 14ቱም ዘፈኖች አንዱ ከአንዱ እንዳይበልጥና በጥሩ ሁኔታ እንዲደመጥ ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ እነዚህ ዘፈኖች የቀደመውን (የወርቃማውን ዘመን) የሙዚቃ ደረጃ እንዲይዙ ነው የፈለግሁት፡፡
የወርቃማው ዘመን ድምፃዊያን የሚባሉት እነማን ናቸው? የአሁኑ አልበህም ያስቀመጥከውን ደረጃ አሳክቷል ብለህ ታስባለህ?
ኤፍሬም ታምሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ ያሉበት ዘመን  ለእኔ ወርቃማውና የምወደው ዘመን ነው፡፡ እኔም ያን ዘመን ሊያስታውሱ የሚችሉ በሳል ዘፈኖችን ከአሁኑ ትውልድም እንዳይርቁ አድርጌ ሰርቻለሁ፡፡ አልበሙ ሰሞኑን ነው የወጣው፤ በእነዚህ ጥቂት ቀናት ውስጥ የደረሰኝ የአድማጮች አስተያየትና ምላሽ ያለምኩትን ግብ እንደመታሁ አመላካች ነው ብዬ አምኜያለሁ፡፡
በአንድ ወቅት አልበም ማሳተም ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ አሁን አሁን ዘፋኞች ደፈር እያላችሁ የመጣችሁ ትመስላላችሁ?
ልክ ነው፤ የአልበም ስራ የተኛበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሄ የቅጂ መብት ጉዳይ ዘፋኙንም አሳታሚውንም ተስፋ አስቆርጦት ነበር፡፡ አሁን እነ ሸዋንዳኝ፣ እነ ሚካኤል በላይነህ፣ እነ ታምራት ደስታ፣ እነ አብነትና ሌሎችም ደፍረው አልበም በማውጣታቸው ሌሎቻችንን አበረታተውናል፡፡ አሁን ሰውም ኦሪጂናል አልበም የመግዛት ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱን ያወቅሁት፣ የእኔ አልበም በወጣ በሶስተኛው ቀን እንኳን በጥሩ ሁኔታ በመሸጥ ላይ መሆኑን ስመለከት ነው፡፡
አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በትክክል ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?
ግጥምና ዜማ መምረጥ የጀመርኩት ከስምንት ዓመት በፊት ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ስቱዲዮ መግባትና ስራውን በደንብ መስራት የጀመርኩት ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡ ያልገባሁበት ያልወጣሁበት ስቱዲዮ የለም፡፡
ለምንድነው በየስቱዲዮው እየገባህ የወጣኸው?
ያሉትን ግጥምና ዜማዎች ይዤ ስራውን እጀምራለሁ፤ ነገር ግን መርካት አልቻልኩም፡፡ አንድ ስራ ይዤ እገባና አያስደስተኝም ትቼ እወጣለሁ፡፡ ይህን ሳደርግ በራሴ የገንዘብ ኪሳራ ነው፤ ዛሬ አንድ ዘፈን ለመስራት ከ20 ሺህ ብር በላይ ይጠይቃል፡፡ ቅንብር 10 ሺህ ብር፣ ግጥምና ዜማ በቀላሉ 10 ሺህ ብር ወጪ ይጠይቃሉ፡፡ ሌሎች ጥቃቅን ወጪዎችን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር የዛሬ ስድስት ዓመት ነው የተፈራረምኩት፡፡ ስንፈራረም ግን በራሴ ስራውን አጠናቅቄ ማስተሩን ላስረክበው ተስማምተን ነው፡፡ ይሄ ማለት ዜማ፣ ግጥም ቅንብር… እያንዳንዱ ወጪና ልፋት በእኔ ላይ ነበር፡፡ ታዲያ ከስድስት አመት በፊት የነበረው ዋጋና የአሁኑ ልዩነቱ ሰማይና ምድር ነው፡፡ በዚያ ላይ ስቱዲዮ ገብቼ ጀምሬ የተውኳቸው አሉ፡፡ ያ ኪሳራ በራሴ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ 30 ዘፈን ሰርቼ፣ 14ቱን ብቻ ነው የመረጥኩት፡፡ 16ቱ ቀሩ ማለት ነው፡፡
ታዲያ ምን ያህል ወጪ ወጣበት አዲሱ አልበምህ?
ያለማጋነን ከ500 ሺህ ብር በላይ አውጥቻለሁ፤ ሆኖም ለህዝብ ጆሮ የሚመጥን ስራ እንደሰራሁ ይሰማኛል፡፡ ራሴን በጣም አስደስቶኛልና፡፡
ከአንተና ከእህትህ ትዕግስት አፈወርቅ ሌላም ታናናሽ ድምፃዊ እህትና ወንድሞች አሉህ ይባላል፡፡ እንደነ አምስቱ እርጎዬዎችና እንደነ ጃክሰን ፋሚሊ “የአፈወርቅ ቤተሰቦች” ለመባል እየተቃረባችሁ ነው ወይስ?
እኛ እንኳን የአፈወርቅ ቤተሰቦች ለመባል አልበቃንም፤ ምክንያቱም በሙዚቃው ነጥረን የወጣነው እኔና ትዕግስት ብቻ ነን፡፡ አንድ ወንድሜ ፍላጎት ስላለው በመሞከር ሂደት ላይ ነው፡፡ ካናዳ ነው የሚኖረው፡፡ ጂጂ የምትባለው የታናሼ ታናሽ በጣም የሚገርምና የሚመስጥ ድምፅ አላት፤ ነገር ግን ዘማሪ መሆን ነው የምትፈልገው፡፡ አሁን እንግሊዝ ነው የምትኖረው፤ ስለዚህ የአፈወርቅ ቤተሰቦች ለመባል አልደረሰንም፡፡ እኔና  ትዕግስት ግን ወደፊት አስተዳደጋችንን፣ ባህላችንን የሚያሳይ አንድ ዘፈን የመስራት ሃሳብ አለን፡፡
ብዙ አድናቂዎች እንዳሉህ ይታወቃል፡፡ አንተስ የማን አድናቂ ነህ?
ኢትዮጵያ የቅዱስ ያሬድ አገር ናት፡፡ በቤተክርስቲያን ስትቀርቢ ዜማ ማህሌትና የመሳሰሉት ያስደምሙኛል፡፡ ወደ ዘፈኑ ስትመጪ አገራችን ብዙ አንጋፋና ተሰጥኦ ያላቸው ድምፃዊያንን አፍርታለች፤ ከእነ ጥላሁን ገሰሰ ጀምሮ፡፡ እኔ ሞዴል ብዬ የያዝኩትና ወደ ሙዚቃው እንድገባ የተሳብኩት በኤፍሬም ታምሩ ነው፤ በጣም ነው የምወደው፡፡ ሙሉቀን መለሰን፣ ቴዎድሮስ ታደሰን፣ እነ ጸጋዬ፣ አረጋኸኝ… እንዲሁም ቀደም ሲል ወርቃማው ዘመን ላይ የነበሩ ብዬ የገለፅኩልሽን በሙሉ አደንቃለሁ፡፡ ቀደም ካሉት ፍሬው ኃይሉ የቤተ-ክህነት አይነት ድምፅ ስላለው እወደዋለሁ፡፡ ከወጣቶች ጎሳዬ፣ ብዙአየሁ፣ አብነት፣ ቴዲ አፍሮን አደንቃለሁ፡፡
ግጥምና ዜማ ድርሰት ላይ እንዴት ነህ?
ባለፈው አልበም ላይ “አፋር” የተሰኘውን ዜማ ሰርቻለሁ፡፡ “ማን እንደኔ ንገሪኛ”፣ “አባይ ወይስ ቬጋስ” እና “አንበሳው አገሳ” የኔ ዜማዎች ናቸው፤ ዜማ ላይ ምንም አልልም፡፡ ግጥም ግን ሰርቼ አላውቅም፡፡ በአሁኑ አልበሜ ላይ በዜማም አልተሳተፍኩም፤ ሁሉንም በሌሎች ባለሙያዎች ነው ያሰራሁት፡፡
በአዲሱ አልበምህ እስካሁን ከመጡት አስተያየቶች በጣም ያስደመመህ አለ?
ያው ብዙ አስተያየቶች ይመጣሉ፡፡ በአብዛኛው አድናቆትና ማበረታታት ናቸው፡፡ አንድ ሰው ግን ደውሎ “ለገና ለበግ መግዣ ያስቀመጥኩትን ብር የአንተን ሲዲ እየገዛሁ ለወዳጅ ዘመድ አድዬበታለሁ፤ በጉን አንተ ግዛልኝ” ብሎኛል፡፡ በጣም ገርሞኛል፡፡ አንዳንዴ ሰው ሲወድሽ እንዲህ ሁሉ ያደርጋል፡፡ ሌላው ችሎታህን በአሁኑ አልበም ላይ በአግባቡ ተጠቅመሃል የሚል አበረታች አስተያየት ነው፡፡
ታዲያ ምን አሰብክ… በጉን ትገዛለታለህ?
 እገዛለታለሁ፡፡ ይሄ ሰው እኮ ሲዲውን ሲገዛ ገንዘቤ በተዘዋዋሪ እኔው ኪስ ገብቷል፡፡ ስለዚህ ደስ እያለኝ እገዛለታለሁ፡፡
በመጨረሻስ….
በመጨረሻ እንግዲህ ይሄ አልበም እንዲህ አምሮ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት የግጥምና ዜማ ደራሲዎች አመሰግናለሁ፡፡ የተለያዩ ጉዳዮችን በማስጨረስ ድካሜን ሲያቀልልኝ የነበረው የአቻሬ ጫማ ባለቤት (አቻሬ) ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡ አቀናባሪ ሙሉጌታ አባተና ኤልያስ መልካ፣ እህቴ ትዕግስት አፈወርቅን፣ ማርታ ዘለቀን፣ አህመድ ተሾመንና ሌሎችም በመዘንጋት ስማቸውን ያላነሳሁትን ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ በደከመበት በአሁኑ ወቅት ከጎኔ ሆኖ የክብር ስፖንሰር የሆነኝን ዳሽን ቢራንና የኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤትን አቶ ተሾመ ፀጋዬን እንዲሁም በአስተያየት እየኮተኮተ ያሳደገኝን የኢትዮጵያን ህዝብ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉም ብድሩን ይክፈልልኝ እላለሁ፡፡ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን የገናን በዓል በሰላም አሳለፋችሁ፤ መጪው የጥምቀት በዓል የምትደሰቱበት ይሁን እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

(በእውቀቱ ስዩም)

በሰላላው መንገድ
የትየለሌ እግር፣ እንደ ሊጥ ባቦካው
ጸአዳ ጣትሽን ፣ጉድፍ እንዳይነካው
ማጡን እየዘለልሽ
ዳጥ ዳጡን እያለፍሽ
ጤዛ የወረረው ዛፍ እየተደገፍሽ
ትንሽ ስትመጭ
ብዙ ስታዘግሚ
ሁለቴ ተራምደሽ፣ አስሬ ስትቆሚ...
ለተደናገረው ፣መንገድ ስትጠቁሚ
የተላከ ሕጻን ፣አስቁመሽ ስትስሚ…

እኔ ስናፍቅሽ
እኔ ስጠብቅሽ
እንደ ጉድ ተውቤ
ላማልልሽ ጥሬ
በጆንትራ ዘይቤ
ጠጉሬን አበጥሬ
ጅማት እያጠበቅሁ፣ጅማት እያላላሁ
የገዛ ከንፈሬን ፣ቀርጥፌ እየበላሁ፡፡
ስጠብቅሽ በጣም
ምስልሽ ነው እንጂ አካልሽ አልመጣም፡፡

ባይኖቼ ስፈልግ
መስኮት እከፍትና
ሌላ ነው የሚያልፈው ፣በሰፊው ጎዳና
ያው ገጣባ አህያ፣ያቻት ድኩም በቅሎ
በግ እየጎተተ፣አለፈ ቆለኛ
ቅርጫት ያጎበጣት ፣ሚስቱን አስከትሎ
ያውና ድሀ አደግ ፣መንገድ ዳር የተኛ
የተጎነጎነ፣የሣር አምባር መስሎ፡፡
ባይኖቼ ሳማትር ፣መስኮት እከፍትና
ሌላ ነው የሚያልፈው፣ በሰፊው ጎዳና፡፡

ሁሉም ተለውጦ
ያ ገጣባ አህያ፣ ጸጉር አቆጥቁጦ
ያች ድኩም በቅሎ ፣ሰጋር ፈረስ ቀድማ
ቆለኛው ሰውየ፣ ሙክት በጉን ሽጦ
ለሚስቱ ነጭ ሻሽ ፣ለሱ ሸራ ጫማ
በትርፉ ሸምቶ
ሁሉም ከሄደበት ፣ቀንቶት ተመልሶ
ሁሉም ከድቀቱ፣ በወግ ተፈውሶ
እኔ ብቻ ቀረሁ፡፡
መንገድሽ ረዝሞ፣ ባሳብ እያሳጠርሁ፡፡
አንቺን እየናፈቅሁ
አንቺን እየጠበቅሁ
ጅማት እያላላሁ፣ ጅማት እያጠበቅሁ፡፡

በደራሲ ቤል ፍቃዱ ተፅፎ የተዘጋጀውና ፕሮዱዩስ የተደረገው “የማይደገም ስጦታ” የተሰኘ ፊልም ባለፈው ሃሙስ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተመረቀ፡፡ በያኔት ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው ፊልሙ፤ ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ድራማ ዘውግ ያለው ሲሆን አንድ ሰው ለፍቅር የሚከፍለውን መስዋእትነት እንደሚያሳይ ደራሲውና አዘጋጁ ቤል ፍቃዱ ተናግሯል፡፡ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ተኩል እንደፈጀ የተነገረለት ፊልሙ፤ ከ350 ሺህ ብር በላይ እንደወጣበትና የ90 ደቂቃ ርዝማኔ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ መስፍን አስፋው፣ በለጠ አንፃኪያ፣ ብሩክታዊት ፋንታሁን፣ ማርታ አሸናፊ፣ አለማየሁ በዛብህና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡

በአዲስ ዓመት ዋዜማ “አስታራቂ” በሚል ርዕስ አልበም አውጥቶ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ድምፃዊ አብነት አጐናፍር “አስታራቂ” የተሰኘ ኮንሰርት ዛሬ በጊዮን ሆቴል ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ያቀርባል፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ኮንሰርት ላይ ሚካኤል በላይነህ ከዘመን ባንድ ጋር የቀድሞ ስራዎቹን ካቀረበ በኋላ ዋናው የኮንሰርቱ አቅራቢ አብነት አጐናፍር በ “ኬር” ባንድ በመታጀብ ተወዳጅ ስራዎቹን እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጊዮን ሆቴል ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በሩ የሚከፈት ሲሆን ከ10-12 ሰዓት በዲጄ ሙዚቃ እና በወጣት ድምፃዊያን፣ እንዲሁም በሚካኤል በላይነህ ስራዎች ታዳሚዎች እየተዝናኑ ቆይተው ወደ አብነት ስራዎች ይሸጋገራሉ ተብሏል፡፡ የኮንሰርቱ መግቢያ ለቪአይፒ 650 ብር ሲሆን ሌላው በ400 ብር እንደሚታደም ታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና ወጣቱ ድምፃዊ አቤል መሉጌታ ዛሬ ምሽት በኤግዚቢሽን ማዕከል “ልብ በ40 ዓመት” የተሰኘ ኮንሰርቱን ያቀርባል፡፡
በሀለ ኮሙኒኬሽን ኤንድ ኤቨንትስ ባዘጋጀው በዚህ ኮንሰርት ላይ ድምፃዊ አቤልን “ጊዜ ባንድ” ያጅበዋል የተባለ ሲሆን፤ በዲጄ ኪንግሰትን (ወዝወዝ) ፋታ እየወሰደ ስራዎቹን እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ለታዳሚው እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኤግዚቢሽን ማዕከል በር ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ክፍት የሚሆን ሲሆን መግቢያው አንድ መቶ ብር እንደሆነም ታውቋል፡፡

የወጪ ንግዱ ባለፉት አምስት ወራት መሻሻል እንዳሳየ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በአገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት በህዳር ወር ከነበረበት 5.9 በመቶ ጭማሪ በማሳየት፣ በታህሳስ ወር ወደ 7.1 በመቶ ማደጉን ትናንት አስታወቀ፡፡ የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ባለፉት አምስት ወራት በ10.7 በመቶ እድገት ማሳየቱን ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
ሮይተርስ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የዋጋ ንረቱ ጭማሪ ሊያሳይ የቻለው በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ ከፍ ያለ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ ሲሆን ስኳር፣ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ በህዳር ወር ከነበረበት 4.8 በመቶ፣ በታህሳስ ወር ወደ 6.5 በመቶ ከፍ እንዳለ አስታውቋል፡፡
ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ላይም በተመሳሳይ ወቅት ከ7.1 ወደ 7.8 በመቶ ጭማሪ መታየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአመቱ የአገሪቱ የዋጋ ንረት 9.1 ደርሶ እንደነበር አስታውሶ፣ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲቀንስ እንደቆየ ገልጿል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አማከለ ይማም በበኩላቸው፤ አገሪቱ ባለፉት አምስት ወራት ለወጪ ንግድ ካቀረበቻቸው የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የማዕድን ምርቶች 1.16 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ለአናዶሉ ኤጀንሲ ገልጸዋል፡፡
ለወጪ ንግዱ ገቢ መሻሻል አስተዋጽዖ ካበረከቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል የቡና ምርት በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ የገለጸው ዘገባው፣ አገሪቱ በተጠቀሰው ጊዜ 62 ሺህ 560 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዳ፣ ከእቅዱ በላይ 64 ሺህ 228 ሺህ ቶን ቡና ለገበያ ማቅረቧን ጠቁሟል፡፡

ፍርዱ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደረግ ተጠይቋል
በሳዑዲ አረቢያ ከሁለት አመታት በፊት አሰሪዋን በመጥረቢያ ደብድባ ገድላለች በሚል ክስ የተመሰረተባት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ፤ በጣይፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ እንደተፈረደባት አረብ ኒውስ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
በደቡባዊ ጣይፍ ግዛት በምትገኘው ሙሳይላት የተባለች መንደር በቤት ሰራተኛነት ስታገለግል የነበረችውና ስሟ ያልተገለጸው ኢትዮጵያዊቷ፣ ፍርዱን በመቃወም ይግባኝ መጠየቋን የጠቆመው ዘገባው፣ የመካ ፖሊስ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ግለሰቧ ዝርፊያ ለመፈጸም በማሰብ ወንጀሉን እንደፈጸመች ተናግረዋል፡፡
በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደምትገኝ የተነገረላት ኢትዮጵያዊቷ፤ በስግደት ላይ በነበረችዋ አሰሪዋ ላይ ወንጀሉን ከፈጸመች በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏንና በወቅቱም በእጇ ላይ 7 ሺህ የሳዑዲ ሪያል (ገንዘብ) መገኘቱን ዘገባው ያስረዳል፡፡
የሟቿ ባለቤት በበኩሉ፤ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደተደሰተ ገልጾ፣ የሞት ፍርዱ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደረግ መጠየቁምን አረብ ኒውስ አክሎ ገልጿል፡