Administrator

Administrator

በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮ ፓረንትስ ት/ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ታዳጊ፤ የት/ቤቱን ዩኒት ሊደር አቶ ወንደሰን ተሾመን ሦስት ቦታ በጩቤ በመውጋት ተጠርጥራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስትውል፣ ተጐጂው በኮርያ ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ለት/ቤቱ አዲስ ነች የተባለችው ተማሪ ትናንት ከጠዋቱ 5፡30 ላይ ወደ ዩኒት ሊደሩ ቢሮ ለቤተሰብ ስልክ ደውልልኝ በማለት ከገባች በኋላ አደጋውን እንዳደረሰች ታውቋል፡፡ ተማሪዋ አስተማሪውን ለምን በጩቤ እንደወጋች እስካሁን አልታወቀም።
አደጋው የደረሰባቸው የት/ቤቱ ዩኒት ሊደር አቶ ወንድወሰን ተሾመ፤ ከመምህርነታቸው በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እንደሆኑ ታውቋል።

የተከሳሾች መቃወሚያ ውድቅ ሆኗል

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወ/ችሎት የሙስና ክስ የቀረበባቸውን የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታንና በሶስት መዝገቦች የተከሰሱ ሌሎች ተከሳሾችን የክስ መቃወሚያና የአቃቤ ህግን ምላሽ መርምሮ በትናንትናው እለት ብይን ሰጠ፡፡ ፍ/ቤቱ አብዛኛውን የተከሳሾችን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል፡፡
ፍ/ቤቱ ብይኑን ከመስጠቱ በፊት ተከሳሾቹ ያመለከቱትን የክስ መቃወሚያና የአቃቤ ህግን ምላሽ አስታውሷል፡፡
በመዝገቡ 1ኛ ተጠሪ የሆኑት አቶ መላኩ በዚህ መዝገብ በቀረቡባቸው ክሶች፤ የቀረቡብኝ ክሶች በስነ ስርአት ህጉ አንቀፆች መሰረት የተሟሉ አይደሉም፣ ከባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ክስ አንስተሃል ለተባልኩት ኃላፊነት የለብኝም” የሚሉና ሌሎች መቃወሚያዎችን ያስታወሰው ችሎቱ፤ አቶ ገ/ዋህድ በበኩላቸው፤ “በተነሱና በተቋረጡ ክሶች ልጠየቅ አይገባም፤ ክሶችን እንዳነሣ አዋጁም ይፈቅድልኛል፤ ከተፈቀደልኝ ወሰን በላይ ህግ አልጣስኩም” ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡
ሌሎች በመዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች “የቀረበው ክስና ማስረጃ ግልፅ አይደለም፣ በተሻረ የህግ አንቀፅ ተከሰናል፣ ኮሚሽኑ በማይመለከተው ስልጣንና በሌለው ውክልና ነው የከሰሰን፣ ክሱ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ነው” የሚሉና ሌሎች በርካታ መቃወሚያዎች እንዳቀረቡም ችሎቱ አስታውሷል፡፡
ለተከሳሾቹ መቃወሚያ ከአቃቤ ህግ ከተሰጡ ምላሾች መካከልም፤ ከማስረጃና ከክስ ጭብጥ ጋር ተያይዞ የቀረቡት መቃወሚያዎች በብይን ሳይሆን በክርክር ሂደት ነው መታየት ያለባቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡
እነ አቶ መላኩ በእርግጥም ክስ የማንሳት ስልጣን በአዋጅ እንደተሰጣቸው የጠቀሰው አቃቤ ህግ፤ ነገር ግን ተከሳሾቹ ከተፈቀደላቸው የህግ ወሰን በላይ የተሰጣቸውን መብት ተጠቅመዋል ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያም ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲደረግለት አቃቤ ህግ የጠየቁ ሲሆን፡፡
የግራ ቀኙን መከራከሪያ ሲመረምር መቆየቱን ያስታወሰው ፍ/ቤቱም፤ በዚህ መዝገብ ላይ ክሱ መስፈርቱን አሟልቶ መቅረቡን እንዲሁም ገቢዎችና ጉምሩክ ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን ውክልና መስጠት እንደሚችል በመግለፅ በመዝገቡ ከተጠቀሱት 93 ክሶች 90ዎቹ ባሉበት እንዲቀጥሉ ሶስቱ ተሻሽለው እንዲቀርቡ በይኗል፡፡
ፍ/ቤቱ ቀጣይ ሂደቱን ለማየት ሁሉንም መዝገቦች ለሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

ህብረት ባንክ ለሚያስገነባው ባለ 32 ፎቅ ህንፃ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ ፊት ለፊት በሚገኝ ቦታ ላይ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ፡፡
የባንኩን ዘመናዊ ህንፃ ዲዛይን ለማድረግ ከ40 በላይ የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎች የተወዳደሩ ሲሆን ህንፃው ባለ 4 ደርዝ የምድር ውስጥ የመኪና ማቆሚያ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ከትናንት በስቲያ የመሰረት ድንጋይ የመጣል ስነ-ስርአት ላይ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ፤ ባንኩ ከእለት ወደ እለት በሁሉም ረገድ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ የራሱን ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ማስገንባቱ በህብረተሰቡ ዘንድ የገነባውን መልካም ስምና ዝና ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግር ያግዘዋል ብለዋል፡፡
በስነ-ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኘው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በበኩሉ፤ ባንኩ በግሉ ሴክተር የተሰማሩ ባለሀብቶችን በመደገፍ ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ጎን ለጎን አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ መሆኑን ጠቁሞ፣ ህንፃው መገንባቱ የሚጠበቅና አስፈላጊም ጭምር ነው ብሏል፡፡  

ከኦስትሪያ የሚመጡት አሰልጣኝ በቀን 28 ሺ ብር ይከፈላቸዋል

ለዳቦና ኬክ ምርቶች ጥሬ እቃዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ዴልታ የማምረቻና የንግድ ኩባንያ፤ የኢትዮጵያ የዳቦና የኬክ ሼፎችን በውጭ ባለሙያ ሊያሰለጥን እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ከኦስትሪያ ቪየና የሚመጡት የዳቦና የኬክ ሥራ አሰልጣኝ ሚስተር ገንተር ኮክሲደር፤ በቀን 28 ሺህ ብር እንደሚከፈላቸው ታውቋል፡፡
ስልጠናው የሚሰጠው በክልልና በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች ለሚልኳቸው የዳቦና የኬክ ሼፎች ሲሆን በሀርመኒ ሆቴል በሚሰጠው ስልጠና ላይ በቀን 30 ሼፎችን በነፃ ለማሰልጠን መዘጋጀታቸውን የዴልታ ኩባንያ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አደም ሙዲ ገልፀዋል፡፡ ከ10 አይነት በላይ በሆኑ የኬኮችና የዳቦ አይነቶች አሰራር ላይ የሚሰጠው ስልጠና፤ በአገራችን የሚመረተውን የኬክና የዳቦ የጥራት ደረጃ በማሳደግ፣ ከየትኛውም አለም ለሚመጡ ሰዎች የሚመጥን እንዲሆን ያስችላል ተብሏል፡፡
ዴልታ ኩባንያ፤ የኬክና የዳቦ ምርቶችን ጥራት ባለው ደረጃ ለማምረት የሚስችል ፋብሪካ እየገነባ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አደም፤ ፋብሪካው የስልጠና ማዕከል እንደሚያካትትም ገልፀዋል፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ሥልጠና ለመስጠት ምን እንዳሳሰባቸው የተጠየቁት የዴልታ ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪጅ አቶ አደም ሲመልሱ፤ “ከውጭ የምናስገባቸው ለኬክና ለዳቦ ምርት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ጥሩ ሙያተኞች ጋ ካልደረሱ እኛ ዋጋ እናጣለን፤ ለዚህ ነው ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የወሰንነው” ብለዋል፡፡ ስልጠናው የተዘጋጀው ጥሬ እቃ ከውጭ ከሚልኩላቸው ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ለበርካታ አመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰፋፊ የምግባረ ሰናይ ስራዎችን በመስራት የሚታወቀው ‘ሰዎች ለሰዎች’ (Menschen für Menschen) የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራች ኦስትሪያዊው በጎ አድራጊና ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ካርልሀይንስ በም፣ ከትናንት በስቲያ በ86 አመታቸው አረፉ።
ባለፈው አመት የአልዛይመር በሽታ ተጠቂ መሆናቸው በይፋ የተነገረ ሲሆን ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው፣ ከትናንት በስቲያ ምሽት በኦስትሪያ ከሳልዝቡር አቅራቢያ በምትገኘው ግሮዲግ ከተማ፣ በመኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው ማለፉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1928 ጀርመን ዳርምስታድ ውስጥ የተወለዱት ካርልሀይንስ በም፣ በስነጥበብ ታሪክና በትወና ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ለረጅም አመታት በፊልም ትወና ሙያ ተሰማርተው በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1981 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ‘ሰዎች ለሰዎች’ (Menschen für Menschen) የተባለውን የበጎ አድራጎት ድርጅት በመመስረትና በመምራት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ከትምህርት፣ ከጤናና ከሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ስራዎችን በማከናወን ይታወቃሉ፡፡
‘ሰዎች ለሰዎች’ን ለረጅም ጊዜያት ሲመሩ የቆዩት ባለቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ፣ ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ ድርጅቱን የማስተዳደሩን ሃላፊነት ለሌሎች አስረክበው ወደ ኦስትሪያ በመሄድ ባለቤታቸውን ሲያስታምሙ እንደነበር  እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  
በበጎ አድራጎት ስራቸው ላከናወኑት የላቀ አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ መንግስት በ1995 ዓ.ም የክብር ዜግነት የሰጣቸውና ሳር ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በስማቸው አደባባይ  ተሰይሞ ሃውልት የቆመላቸው ካርልሀይንስ፣ ታዋቂዎቹን የ‘ባላንዛ የሰብዓዊነት፣ የሰላምና የወንድማማችነት ሽልማት’ እና ‘ኢሴል የማህበራዊ አስተዋጽኦ ሽልማት’ ጨምሮ፤ ከተለያዩ አገራት በርካታ የስኬትና የአገልግሎት ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡
ካርልሀይንስ ‘ሲሲ’፣ ‘ፎክስ ኤንድ ሂዝ ፍሬንድስ’፣ ‘ላ ፓሎማ’፣ ‘ዘ ስቶው አዌይ’ እና ‘ካም ፍላይ ዊዝ ሚ’ን ጨምሮ፤ በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በኦስትሪያና በሌሎች አገሮች በተሰሩ 45 ያህል ፊልሞች ላይ በመተወን ችሎታቸውን ያስመሰከሩ ተዋናይ መሆናቸውን ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
በ1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያዊቷ ባለቤታቸው አልማዝ ተሾመ ጋር በመሰረቱት ትዳር ሁለት ልጆችን ያፈሩት ካርልሀይንስ በም፤ ከቀድሞ ትዳሮቻቸው ያፈሯቸው አምስት ልጆች አሏቸው፡፡

ጳጳሳት የፓትርያርኩን የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ማሻሻያ ቅድመ ኹኔታ አልተቀበሉትም
‹‹ቅድመ ኹኔታው የማኅበሩን አገልግሎት የሚያቀጭጭና በሒደትም የሚያስቆም ነው›› /ታዛቢዎች/

የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅን እንደ አንድ አጀንዳ የያዘው የዘንድሮው የሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ጉባኤ ከረቂቁ ጋር በተያያዘ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል በተፈጠረ ፍጥጫ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
የፍጥጫው መንሥኤ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሠየመው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴ ያዘጋጀው የማሻሻያ ረቂቅ በዝርዝር ከመታየቱ አስቀድሞ ፓትርያርኩ ለውይይቱ እንደ ቅድመ ኹኔታ ያቀረቧቸው ነጥቦች በአብዛኛው የጉባኤው አባላት የገጠመው ተቃውሞ እንደኾነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የቅ/ሲኖዶሱን ስብሰባ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩት ፓትርያርኩ፤ በአጀንዳው ላይ የሚካሔደውን ውይይት ቀጣይነት ይወስናል በሚል ካቀረቧቸው ቅድመ ኹኔታዎች ውስጥ÷ ለአጥኚ ኮሚቴው መመሪያ የሰጡባቸው ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› አንድም ሳይቀነሱ በደንቡ እንዲካተቱና ረቂቁ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከጸደቀ በኋላ እንዲታይ የሚሉ እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ አስቀምጠዋቸዋል በተባሉት ነጥቦች ስምምነት ላይ ከተደረሰ ስብሰባው ሊቀጥል እንደሚችል በመጥቀስ፣ ኃይለ ቃልም ተማኅፅኖም በተቀላቀለበት አኳኋን መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
ይኹንና የሚበዙት ሊቃነ ጳጳሳት በቀጥታ እንደተቃወሟቸው፣ የተቀሩትም ድጋፍ ከመስጠት እንደተቆጠቡ ታውቋል፡፡ ፍጥጫው ቀጥሎ አቡነ ማትያስ ‹‹አቋሜ ይኽው ነው፤›› በሚል አጀንዳውን መዝጋታቸውን ሲያስታውቁም፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ እንዲህ ተብሎ የሚተው አይደለም፤›› በሚል ከኹሉም ሊቃነ ጳጳሳት ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ምንጮች ይገልፃሉ፡፡
የቅ/ሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባ የሚካሔደው ምልዓተ ጉባኤው ከጅምሩ ተስማምቶ ባጸደቃቸው የመነጋገርያ አጀንዳዎች መሠረት እንደኾነ በሊቃነ ጳጳሳቱ ተቃውሞ ተጠቅሷል፡፡
የማኅበሩ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ እንዲቀርብ ከታዘዘበት ከጥቅምት 2005 ዓ.ም. ጀምሮ እየተንከባለለ ለኹለት ዓመታት መዘግየቱን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ የተጓተተው አጀንዳ ‹‹የማኅበሩን አገልግሎት ያቀጭጫሉ፣ በሒደትም ያስቆማሉ›› በሚል በተተቹት የፓትርያርኩ ቅድመ ኹኔታዎች ሊዘጋ እንደማይችልና ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ ቅ/ሲኖዶሱ ሊወያይበት እንደሚገባ በአጽንዖት በመናገራቸው፣ ጉዳዩ ሳይቋጭ ለቀጣዩ ቀን በይደር ተላልፏል፡፡
አጀንዳው ሰኞ፣ ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ጥዋት መታየት ሲጀምር፣ አጥኚ ኮሚቴው በ37 አንቀጾችና በ34 ገጾች አሻሽሎ ያዘጋጀው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብና የኮሚቴው ቃለ ጉባኤ በንባብ መሰማቱም ታውቋል፡፡ ፓትርያርኩ ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› በሚል ራሱን በቻለ ርእስ በደንቡ እንዲካተት ለአጥኚ ኮሚቴው ጥብቅ መመሪያ የሰጡበት ባለ24 አንቀጽ ሰነድም አብሮ እንዲነበብላቸው መጠየቃቸው የመጀመሪያው ቀን የፍጥጫ መነሻ እንደነበር ታውቋል፡፡
በ24 አንቀጾችና በአምስት ገጾች የተዘረዘሩት የፓትርያርኩ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች÷ በአባላቱ በጎ ፈቃድ ተቋቁሞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኘውን ማኅበር፤ ከሕገ ተፈጥሮው ውጭ የሚያደርግ፣ በቅ/ሲኖዶሱ ፈቃድ ከሚመራበት ደንብ በተፃራሪ ተቋማዊ ህልውናውን፣ የአመራር ምርጫውን፣ የአባላት አያያዙንና የሥራ ቦታውን ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥና አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ፣ በአርኣያነት የሚጠቀሰውን የፋይናንስ አሠራሩን ወደ ኋላ የሚጎትት መኾኑን እንደተረዱ ያብራሩ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፣ ‹‹ቀጣዩ ቀንም የከበደ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ፡፡
በይደር የተያዘው አጀንዳ በቀጣዩ ቀን ማክሰኞ ጥዋት ተጀምሮ ለግማሽ ቀን የቀጠለ ቢኾንም ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያውን በዝርዝር ለመመልከት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡
‹‹ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ ያስቀመጧቸውን ነጥቦችና በአጀንዳው ቀጣይነት ላይ የያዙትን አቋም አልቀየሩም፤ ሊቃነ ጳጳሳቱም ባጸደቅነው አጀንዳ መሠረት ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር ያለብን የሠየምነው አጥኚ ኮሚቴ አዘጋጅቶ ባቀረበው ረቂቅ ላይ ነው፤ መካተት ያለበት ነገር ካለም ማኅበሩን በሚያሠራ መልኩ እያገናዘብን በሒደት እናየዋለን እንጂ አጀንዳው በቅድመ ኹኔታ መታሰር የለበትም በሚል ለማስረዳት ጣሩ፤ በመጨረሻም ፓትርያርኩ “እንግዲያውስ ስብሰባውን ለመምራት አልችልም” በማለታቸው የስብሰባው መቋጫ ኾኗል፤›› ይላሉ- ሒደቱን ለአዲስ አድማስ የገለጹ የስብሰባው ምንጮች፡፡
የማኅበሩ ደንብ በመጀመሪያ ረድፍ ከሰፈሩት የቅ/ሲኖዶሱ መነጋገርያ ነጥቦች አንዱ እንደነበር ያስተዋሉ ሌሎች የስብሰባው ተከታታዮች በበኩላቸው፤ አጀንዳው ከቅደም ተከተሉ ወጥቶ እየተገፋ በመጨረሻ መነሣቱ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ይህ ዓይነቱ አለመግባባት ሊነሣ እንደሚችል ጠቋሚ ነበር ብለዋል፡፡  
ተከታታዮቹ አክለውም፣ ፓትርያርኩ ስብሰባውን ለመምራት ፈቃደኛ ባይኾኑም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በተደነገገው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ ምልዓተ ጉባኤው በማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያዎች ላይ የጀመረውን ውይይት ቀጥሎ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚችልባቸው አግባቦች እንደነበሩ ገልጸው፣ ቅ/ሲኖዶሱ በግለጫው የመጨረሻው አጀንዳው ባደረገው የማኅበሩ ደንብ ላይ “ውይይት ተደርጎበታል” ከማለት በስተቀር ስብሰባውን የቋጨበት አኳኋን ያልተለመደና አደናጋሪ ነው ብለዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የዘመኑን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ አደራጅቶ ማንነቱን የሚያውቅበትንና በግብረ ገብ የሚታነፅበትን ትምህርተ ሃይማኖት ከማስተማር ባሻገር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት አገልግሎታቸውን በብቃት የሚወጡበትን ኹለገብ ሞያዊ ድጋፍ የመስጠት ሓላፊነት እንዳለበት በደንብ አጥኚ ኮሚቴው ማሻሻያ ረቂቅ ላይ መስፈሩ ታውቋል፡፡
ይኹንና ‹‹ጥበቃና ጥንቃቄ›› በሚል ፓትርያርኩ እንደ መመሪያ ያቀረቧቸው ድንጋጌዎችና ግዴታዎች እንዲሁም ከልዩ ጽ/ቤታቸው ማኅበሩን አስመልክቶ በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎች የማኅበሩን አገልግሎት የማቀጨጭ፣ በሒደትም አዳክሞ የማስቆም ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡
የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ፣ ቅ/ሲኖዶሱ የማኅበሩ ደንብ እንዲሻሻል ግንቦት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ÷ ማኅበሩ ከጊዜው ጋር የሚሔድ፣ አገልግሎቱና አደረጃጀቱ የደረሰበትን ስፋትና ዕድገት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ልማት የሚጠቅም ድርጅታዊ መዋቅር እንደሚያስፈልገው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አምስት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገለልተኛ የሕግ ባለሞያዎችና የማኅበሩ አባላት በታከሉበት አጥኚ ኮሚቴ የጋራ ጥናት የተዘጋጀ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም. በበጎ ፈቃድ በተሰበሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተመሠረተው ማኅበሩ፤ እየተመራ ያለው ቅ/ሲኖዶስ በ1994 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ አሻሽሎ በሰጠው መተዳደርያ ደንብ ሲኾን አሁን የተሻሻለው ረቂቅ ተመርምሮ ባለመጽደቁ በነባሩ ደንብ እየተመራ ለመቀጠል እንደሚገደድ ተመልክቷል፡፡

በ800 ሜትር ሳይሸነፍ 15 ወራት አልፈዋል
ዘንድሮ ለዳይመንድ ሊግ ድል ለሃትሪክ ተጠብቋል
አዲስ የዓለም ሪከርድ እንደሚያስመዘግብ ግምት ተሰጥቶታል

አትሌት መሃመድ አማን ባለፉት 15 ወራት በሮጠባቸው የ800 ውድድሮች አልተሸነፈም፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት ላለፉት 30 ዓመታት በረጅም ርቀት ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ አትሌቶችን በማፍራት ትታወቅ ነበር፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት ግን በ20 ዓመቱ የዓለማችን የመካከለኛ ርቀት ምርጥ ሯጭ  ኮርታለች፡፡ አትሌት መሃመድ የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ዝና በአዲስ ምዕራፍ ቀይሶታል፡፡
ዘንድሮ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ ምርጥ ብቃት ያሳያሉ ተብለው ከተጠበቁ ምርጥ አትሌቶች አንዱ የሆነው መሃመድ በዚህ የውድድር ዘመን የ800 ሜትር የዓለም ሪከርድን ሊሰብር እንደሚችል በመገመትም ላይ ነው፡፡  በእርግጥም በርቀት አይነቱ  የዓለም ንጉስ ለመባል የሚቀረው ሪከርዱን መስበር ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች አትሌቱ አሁን በያዘው ብቃት ከቀጠለ ዘንድሮ ባይሳካለት እንኳን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚኖሩት ልምዶች የዓለም ሪከርድን የሚያሻሽልበት ብቃት ላይ እንደሚያደርሱት እየመሰከሩ ናቸው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የ2014  የዳይመንድ ሊግ ውድድር በኳታር ዶሃ ሲጀመር አንፀባራቂ ከነበሩ አትሌቶች ዋናው የነበረው አትሌት መሃመድ አማን፤ በወቅቱ በ800 ሜትር ውድድር ሲያሸንፍ ያሳየው አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት ከፍተኛ አድናቆት አጉርፎለታል፡፡ እንደውም አንዳንድ ዘገባዎች ‹‹ሱፕር አትሌት›› ብለው አግንነውታል፡፡ ይሁንና አትሌቱ ከ2013 አጋማሽ ጀምሮ በተሳተፈባቸው የ800 ሜትር ውድድሮች ሳይሸነፍ ለመቆየቱ በቂ ምክንያት በማቅረብ የሚከራከሩ አልጠፉም፡፡ በእነዚህ ተከራካሪዎች መሃመድ አማን የሚቀናቀነው የጠፋው በተለይ የርቀቱ ሁለት ምርጥ አትሌቶች ጋር ባለመገናኘቱ ነው የሚል ማስረጃ ይቀርባል፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ለንደን ኦሎምፒክ ላይ የዓለምን ሪከርድ ያስመዘገበው የ25 ዓመቱ ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ በጉዳት ከውድድር ከራቀ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡ ሌላው ምርጥ አትሌት እና በእድሜው እኩያው የሆነው ደግሞ የቦትስዋናው ኒጄል አሞስ ሲሆን እሱም በጉዳት ከውድድር እንደራቀ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ዘንድሮ በከፍተኛ ጉጉት ከሚጠበቁ ትንቅንቆች ዋንኛው መሃመድ አማን ፤ ኒጄል አሞስ እና ዴቪድ ሩዲሻ የሚገናኙበት የ800 ሜትር  ፍጥጫ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ ሶስቱ አትሌቶች በዳይመንድ ሊግ መገናኘታቸው እየተጠበቀ ሲሆን በተለይ ከሳምንት በኋላ በአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን፤ የሚደረገው የፕሮፎንታይኔ ክላሲክስ ላይ ከተገናኙ አስገራሚ ፉክክር እንደሚኖራቸው   ተገምቷል፡፡ የ800 ሜትር የዓለም ሪከርድ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በኦፊሴላዊ ደረጃ መመዝገብ የተጀመረው በ1952 እኤአ ነው፡፡ የመጀመርያው ሪከርድ በአሜሪካዊው አትሌት ቴድ ሜሪንዴዝ በ1.51 ደቂቃዎች የተመዘገበ ሲሆን ከዚሁ ሪኮርድ በኋላ 24 ጊዜ ሰዓቱ ሲሻሻል በርካታ እንግሊዛዊያንና አሜካዊያን አስተዋኝኦ ነበራቸው፡፡ ከ2008 ጀምሮ የተመዘገቡ ሦስት ሪኮርዶችን ማስመዝገብ የቻለው ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ ሲሆን የወቅቱ ሪከርድ ከ2 ዓመት በፊት በለንደን ኦሎምፒክ  በ1 ደቂቃ ከ41.54 ሰኮንዶች ያስመዘገበው ነው፡፡ አትሌት መሃመድ አማን ዘንድሮ በርቀቱ ሪከርድ ለመስበር  ፍላጐት እንዳለው በይፋ የተናገረው ነገር ባይኖርም የራሱን ምርጥ ሰዓት ወይንም የኢትዮጵያን ሪከርድ ለ7ኛ ጊዜ ለማሻሻል ያስባል፡፡ 800 ሜትርን ከ1.40 ደቂቃ በታች እንደሚገባም ያምናል፡፡

ምርጥ ሰዓቶቹ- በ800 ሜትር 1፡42.37 ቤልጅዬም ብራሰልስ  በ2013 እኤአ የተመዘገበ ሰዓት ሲሆን የኢትዮጵያ ሪከርድ ነው፡፡ በ800 ሜትር የኢትዮጵያ ሪከርድን ለስድስት ጊዜያት አሻሽሏል፡፡ በ1500 ሜትር 3፡43.52 ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን በ1 ማይል ያለው ምርጥ ሰዓት ደግሞ 3፡57.14 ነው፡፡
ወቅታዊ ደረጃው- በኦልአትሌቲትክስ ድረገፅ ዘንድሮ በ800 ሜትር በ1405 ነጥብ የዓለም አንደኛ አትሌት ሲሆን በሁሉም የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች በተመሳሳይ ነጥብ ከዓለም 8ኛ ነው፡፡ በዓለም የ800 ሜትር የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ 9ኛ ነው፡፡
ማኔጅመንት እና ስፖንሰር -የትጥቅ ስፖንሰሩ ናይኪ ሲሆን፤ ከ2009 እኤአ ጀምሮ ኤሊት ስፖርትስ ማኔጅመንት ኢንተርናሽናል ESMI በመታቀፍ እየሰራ ነው፡፡
አስደናቂ ድሎቹ- አሁን በጉዳት ላይ የሚገኘው የኬንያው አትሌት ዴቪድ ሩዲሻ የ800 ሜትር የዓለም ሪከርድን ለስድስት ጊዜያት አሻሽሏል፡፡ ግዙፉ አትሌት በሩጫ ዘመኑ ካደረጋቸው 47 ውድድሮች 45ቱን አሸንፏል፡፡ የተሸነፈባቸው ሁለት ውድድሮች የመሃመድ አማን ሁለት አስደናቂ ድሎች ናቸው፡፡ የመጀመርያው በ2011 እኤአ ላይ በጣሊያኗ ከተማ ሬቲ ያሸነፈበት ሲሆን በወቅቱ ዴቪድ ሩዲሻ ለመጀመርያ ጊዜ የተሸነፈው ከ34 ተከታታይ ድሎች በኋላ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በ2012 እኤአ ላይ በዙሪክ የተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሲሆን በዚህ ወሳኝ ትንቅንቅ ለመጀመርያ ጊዜ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫን ያሸነፈበት ነበር፡፡

ባርሴሎና ለሊዮኔል ሜሲ ሰሞኑን በሰጠው አዲስ የኮንትራት ውል  ተጨዋቹን የዓለማችን ውዱ  ተከፋይ አድርጎታል፡፡ እስከ 2018 በኑካምፕ ለማቆየት በፈጸመው ስምምነት በየዓመቱ 16.3 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፍለዋል፡፡ 20 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 27 ሚሊዮን ዶላር ወይም 580 ሚሊዮን ብር  ማለት ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ ሰሞን 27 ዓመቱን የሚደፍነው ሜሲ ባለፉት 11 ዓመታት ከባርሴሎና ጋር ለ8ኛ ጊዜ የኮንትራት ውል እና ማራዘሚያዎች መፈራረሙ ነው፡፡
የባርሴሎና የምንግዜም ከፍተኛ አግቢ ሲሆን በ425 ጨዋታዎች 354 ጎሎችን አግብቷል፡፡ 6 የላሊጋ፤ 3 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ 2 የኮፓ ዴላሬይ እና ሌሎች በድምሩ 21 ዋንጫዎችን አግኝቷል፡፡
በአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ  እስከ 73 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኘው  ክርስትያኖ ሮናልዶ ይበልጠዋል፡፡ የሜሲ 65 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
 ለሊዮኔል ሜሲ እስከ 250 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ይጠራል፡፡

በእግር ኳስ ዓመታዊ ትርፍ 2.8 ቢሊዮን ዶላር የአዲዳስ 1.9 ቢሊዮን ዶላር የናይኪ
አዲዳስና ናይኪ ዓለም ዋንጫው ገና ወራት ሲቀሩት በገበያ ዘመቻቸው ከባድ ትንቅንቅ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በእግር ኳሱ የማልያ ትጥቅ አቅራቢነት ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ያንቀሳቅሳሉ፡፡ በከፍተኛ የቴክኖሎጂ እገዛ የተመረጡ ታኬታዎችና ማልያዎችን በማቅረብ ፉክክራቸውን ያጧጡፋሉ፡፡
ናይኪ ለዓለም ዋንጫው ያቀረበው ታኬታ የቅርጫት ኳስና የሩጫ ጫማዎች የተሰሩባቸውን ቴክኖሎጂ አጣምሮ የያዘው “ማጂስታ” ነው፡፡ ኢኒዬስታና ማርዮ ጎትዜ በዚህ ታኬታ አሠራር ላይ የሃሳብ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የናይኪ “ማጂስታ” ታኬታ ዋጋ 275 ዶላር ነው፡፡ አዲዳስም “አዲዜሮ ኤፍ50” በሚል ስያሜ በሊዮኔል ሜሲ የሚተዋወቁትን የታኬታ ምርቶች ለዓለም ዋንጫው ይዞ ቀርቧል፡፡ የገበያ ዋጋቸው 270 ዶላር አካባቢ ነው፡፡የዓለም ዋንጫዋን ኳስ “ብራዙካ” ያቀረበውም አዲዳስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ በዓለም ገበያ 17% ድርሻ የያዘውና 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ያስመዘገበው የአሜሪካው ናይኪ ነው፡፡ የጀርመኑ ኩባንያ አዲዳስ በ12% የገበያ ድርሻ እና በ20 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ይከተለዋል፡፡
አዲዳስ  ከዓለም ዋንጫ ውድድሮች እና በአጠቃላይ በእግር ኳስ ስፖርት የቅርብ አጋር ሆኖ ሲሰራ ከ66 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአንፃሩ ናይኪ ከዓለም ዋንጫ እና ከእግር ኳስ ስፖርት ጋር መንቀሳቀስ ከጀመረ ገና 20 ዓመቱ ነው፡፡
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ናይኪ የ10 ብሔራዊ ቡድኖችን ትጥቅ ሲያቀርብ የአዲዳስ 9 ናቸው፡፡ ፑማ ለ8 ብሔራዊ ቡድኖች ትጥቅ በማቅረብ 3ኛ ደረጃ አለው፡፡  
የዓለም ኮከብ ተጨዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ የናይኪ ታኬታዎች ዋና አምባሣደር ሲሆን የብራዚልና የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ ትጥቅ ከሚወስዱት ይጠቀሳሉ፡፡  የስፔንና የጀርመን ብሔራዊ ቡድኖች ደግሞ የአዲዳስ ዋና ደንበኞች ሆነው ሲጠቀሱ በፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ለ4 ጊዜያት የተመረጠው ሊዩኔል ሜሲ የአዲዳስ ትጥቆች ዋና አምባሳደር ነው፡፡ ፡፡
በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች በቀጠለው የሁለቱ ኩባንያዎች ዘመቻ ናይኪ ብልጫ ሲኖረው 36 ሚሊዮን የፌስ ቡክ ወዳጆች፣ እንዲሁም 8.8 ቢሊዮን የትዊተር ተከታታዮች በማስመዝገቡ ነው፡፡ አዲዳስ 17 ሚሊዮን የፌስ ቡክ ወዳጆች እና 9.4 ሚሊዮን የትዊተር ተከታታዮች አሉት፡፡

የዓለማችን የረጅም ርቀት ምርጥ አትሌቶች የሆኑት  ቀነኒሣ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በጐዳና ላይ ሩጫዎች ስኬታማ እየሆኑ ናቸው፡፡  ባለፈው ሳምንት  በእንግሊዝ በተካሄደው የቡፓ ግሬት ማንቸስተር ራን በ10 ኪ.ሜ የጐዳና ላይ ሩጫ በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በወንዶች ምድብ ያሸነፈው ርቀቱን በ28.23 ደቂቃዎች በመሸፈን ነበር፡፡ የዓለም ማራቶን ሪኮርድ ባለቤቱን ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ በ5 ሰኮንዶች በመቅደም አስከትሎት ገብቷል፡፡ ይህ ውጤት  ሁለቱ አትሌቶች ለመጀመርያ  በማራቶን የሚገናኙበትን ሁኔታ አጓጊነት ጨምሮታል፡፡ ዊልሰን ኪንሳንግ በ2013 አጋማሽ ላይ በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ  የዓለም ሪከርድን ያስመዘገበ ነው፡፡ ከወር በፊት ቀነኒሳ የመጀመርያ ማራቶኑን በፓሪስ ሮጦ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግቦ ሲያሸንፍ በዚያው ሰሞን ዊልሰን ኪፕሳንግም በለንደን ማራቶን በተመሳሳይ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግቦ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ከዊልሰን ኪፕሳንግ ጋር በማራቶን መሮጥ ፍላጎት እንዳለውም የሰጠው፡፡ ከቡፓ ግሬት ማንችስተር ራን በኋላ ቀነኒሳ በሰጠው አስተያየት አሁን ትኩረቱ ወደ ትራክ ውድድሮች መመለስ እንደሆነ ገልፆ፤ በተለይ በ10ሺ ሜትር አንድ ውድድር ማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ርቀቱን በ32 ደቂቃ ከ20 ሰኮንዶች በመሸፈን አሸንፋለች፡፡ ጥሩነሽ  በቡፓ ግሬት ማንችስተር ራን ዘንድሮ ያሸነፈችው ለሁለተኛ ግዜ  ሲሆን አምና ውድድሩን ስታሸንፍ በ30.49 ደቂቃዎች በሆነ ጊዜ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግባ ነበር ፡፡
ከወር በፊት በፓሪስ እና ለንደን በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች የመጀመርያ ማራቶናቸውን የሮጡት ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ አጀማመራቸው ስኬታማ እነደሆነ ያመለከቱ መረጃዎች፤ በሚቀጥሉት ዓመታት በሁለቱም ፆታዎች የተያዙ የዓለም ማራቶን ሪከርዶችን ለመስበር ግንባር ቀደም እጩዎች ስለመሆናቸውም ግምት ሰጥተዋል፡፡ የመጀመርያ ማራቶኑን በፓሪስ የሮጠው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የቦታውን ሪከርድ ካሸነፈ በኋላ ያሳየው ብቃት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊሰብር እንደሚችል ያመለክታል በሚል በርካታ ዘገባዎች አውስተውለታል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ የፓሪስ ማራቶንን ሲያሸንፍ ርቀቱን የሸፈነበት 2 ሰአት ከ05 ደቂቃ ከ4 ሰኮንዶች ነበር፡፡ በረጅም ርቀት 5 የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም 3 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ያሏት ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ከወር በፊት በለንደን የመጀመርያ ማራቶን ውድድሯን  በሁለት ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ54 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በሶስተኛ ደረጃ ጨርሳለች፡፡ ይሄው የጥሩነሽ ሰዓት በማራቶን የመጀመርያ ሩጫ ከተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች በሶስተኛ ደረጃ ተመዝግቧል፡፡