Administrator

Administrator

43 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቶባታል ተብሏል

          ግብጽ 43 ሚሊዮን ዶላር ያወጣችበትንና የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የግንባታ ሂደት በአየር ላይ ሆኖ እየተከታተለ መረጃ የሚሰጣትን ወታደራዊ ሳተላይት ከሁለት ሳምንት በፊት ማምጠቋን በይፋ እንደገለፀች   አህራም ኦንላይን ዘገበ፡፡
ኢጂሳት የሚል ስያሜ የተሰጠው ሳተላይቱ፤ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቁመት፣ ውሃ የመያዝ አቅምና የሚለቀውን የውሃ መጠን የተመለከቱ መረጃዎችን እየተከታተለ የሚያቀርብ እንደሆነ የገለጹት የግብጽ ብሄራዊ የሪሞት ሴንሲንግና ስፔስ ሳይንስስ ባለስልጣን ምክትል ፕሬዚደንት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ሳተላይቱ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሚከናወንበት አካባቢ በተጨማሪ፣ የአባይ ወንዝ በሚፈስባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በማተኮር፣ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ጠቃሚ ፎቶግራፎችን እያነሳ እንደሚልክ  ሰሞኑን በካይሮ በተካሄደ ሴሚናር ላይ ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ወራት ከሚቆይ የሙከራ ጊዜ በኋላ፣ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ መደበኛ ስራውን ይጀምራል የተባለው  ሳተላይቱ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከታተለ ለግብጽ ባለስልጣናት መረጃ ከማቀበል ባለፈ፤ የኮንጎ ወንዝን ተፋሰስ በመከተል በሚያነሳቸው ፎቶግራፎች፣ ወንዙን ከአባይ ጋር ለማገናኘት ታስቦ የተረቀቀውን የፕሮጀክት ሃሳብ ውጤታማነት በተመለከተ የራሱን ፍተሻ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የግብጽ መንግስት ሳተላይቱ ከሚያቀርባቸው መረጃዎች የሚያገኘው ውጤት፣ ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ዙሪያ የጀመረው ክርክር ተጠናክሮ እንዲገፋ እንደሚያደርገው ያምናል ያሉት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ግድቡን ከታለመለት የሃይል ማመንጨት ስራ ውጭ ለማዋል በኢትዮጵያ በኩል ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ቢደረጉና ጉዳዩ ወደ አለማቀፍ ግልግል የሚያመራ ከሆነም፣ የግብጽ መንግስት ይሄንኑ የሳተላይት መረጃ ለክርክሩ የህግ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጠቀምበት አል አህራም ለተባለው  ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
አል አረቢያ ድረ-ገጽ በበኩሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ የምታነሳቸውን ቅሬታዎች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማቅረብ ከወሰነች፣ ኢትዮጵያ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ባለፈው ሳምንት መናገራቸውን ዘግቧል፡፡
የግድቡ መገንባት የአባይን ወንዝ የውሃ መጠን በመቀነስ ተጎጂ ያደርገናል በሚል ተቃውሞአቸውን በተደጋጋሚ የገለፁት የግብጽ ባለስልጣናት፣ ሳተላይቱ የሚሰጣቸውን መረጃ መሰረት በማድረግ የሚደርሱበት ውጤት፣ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ክርክር ይዘውት የቆዩትን አቋም እንደሚያጠናክርላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡ የግብጽን ሳተላይት ማምጠቅ በተመለከተ፣ አንዳንድ ድረገጾች ቀደም ብለው መረጃ ያወጡ ቢሆንም፣ የአገሪቱ መንግስት ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ ሲሰጥና ድርጊቱን ሲያምን የአሁኑ የመጀመሪያው  ነው፡፡

  “ሥራቸውን በገቡት ውል መሰረት ባለመስራታቸው አሰናብተናቸዋል”- ሆቴሉ
    ከአምስት ወር በፊት ስራ የጀመረው የኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አራት የሴኩሪቲ ሰራተኞች፣መብታችንን በመጠየቃችን በማይመለከተን ጥፋት ወንጅሎ ያለማስጠንቀቂያ ከስራችን አባርሮናል ሲሉ በሆቴሉ ላይ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡ የሆቴሉ የሰው ሃይል አስተዳደር አቶ አሰፋ በየነ በበኩላቸው፤ሰራተኞቹ የተባረሩት የተሰጣቸውን ሃላፊነትና ተግባር ወደጐን በመተው በሆቴሉ ላይ ችግር በመፍጠራቸው ነው ብለዋል፡፡ እንደማንኛውም አመልካች ተወዳድሮና መስፈርቱን አሟልቶ በሴኩሪቲ ክፍል መቀጠሩን የገለፀው አቶ ሃዲስ በሪሁን፤ አማርኛህ ለሆቴሉ አይመጥንም፣ ሴት ፈትሸሃል፣ እንግዳ አቆላምጠህ ጠርተሃልና ሌሎች   የማይመስሉ ሰበቦችን በመደርደር አስተዳደሩ ከስራው እንዳሰናበተው ተናግሯል፡፡
“የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱል ሰላም ሲዮ ባሬንቶ፤ ከምሁር የማይጠበቅ ፀያፍ ንግግር ተናግረውኛል፣ የጓደኛዬን ሚስት አቆላምጬ በመጥራቴ “እሱ እስኪለቃት እየጠበቅህ ነው” በማለት ክብሬን የሚነካ ንግግር ተናግረውኛል፣ ለዚህም ምስክር አለኝ” ሲል ምሬቱን ገልጿል - አቶ ሀዲስ፡፡ “ሆቴሉ እንደማንኛውም ሰራተኛ ውል ያስገባን በቀን ለስምንት ሰዓት እንድንሰራ ቢሆንም እስከ 14 እና 16 ሰዓታት ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ ተገደን ሰርተናል” ያሉት ሰራተኞቹ፤ የህክምና ኢንሹራንስ ቢኖረንም መድሀኒት የምንገዛው በግላችን ነው፣ ከተቀጠርንበት የስራ መደብ ውጭ የማይመለከተንን ስራ ሁሉ እንሰራለን፤ በአጠቃላይ ከፍተኛ በደል ደርሶብናል ብለዋል፡፡ “ከዚህ በፊት ሆቴሉ በርካታ ሰራተኞችን በግፍ አባርሯል” የሚሉት ሰራተኞቹ፤አሁንም ሊያባርራቸው ያዘጋጃቸው እንዳሉ መረጃ አለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ በመስራት ልምድ እንዳካበተ የሚናገረው ሌላው ተሰናባች ሳሙኤል ደመመው፤ “የሴኩሪቲ ሰራተኞችን የፍተሻ ብቃት ለማረጋገጥ አንዳንድ ጊዜ ፈንጂና ቦንብን ጨምሮ መሳሪያ ታጥቆ የሚገባ እንግዳ ይላካል፣ ያንን በብቃት ፈትሾ ላገኘ የምስጋና ደብዳቤ ይሰጣል፣ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ይህን መሰል በርካታ የብቃት ማረጋገጫዎችን ስናልፍ እናመሰግናለን እንኳን አልተባልንም፣ ከስራ ለማባረር ግን በርካታ የማይመለከተኝን ታፔላ ለጥፈውብኛል” ሲል አማርሯል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ “ቡልሺት፣ ጋዴም” የሚሉ ስድቦችን ሰድበውን ሲያበቁ፣ “የትም ቦታ ብትሄዱ ምንም አታመጡም” በማለት በአገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረናል ብለዋል - ሠራተኞቹ፡፡
“በስራችን ተግተን ብንሰራም ደሞዛችን በጣም አነስተኛ ነው፣ ሰርቪስ ቻርጅ የለውም፣ የሚቀርብልን ምግብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ የብሔር ወገንተኝነት የተንሰራፋበት ድርጅት ነው” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ችግሮቹ እንዲስተካከሉ ፊርማ አሰባስበን ለሰው ሃይል አስተዳደር በማስገባታችን “ሰራተኛ አሳመፃችሁ” ተብለን ከሥራ ተፈናቅለናል ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ፕ/ር አብዱልሰላም ሲዮ ባሬንቶ፣ በመምህርነት በተለያዩ የአለም አገራት ለ37 ዓመታት ቢሰሩም ስለ ሆቴል ማኔጅመንት የሚያውቁት ነገር ስለሌለ ስራውን እያበላሹ ነው ሲሉም ሰራተኞቹ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ የሰራተኞቹን ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የሆቴሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱልሰላም ሲዮ ባሬንቶ በበኩላቸው፤ በስነ-ምግባር ጉድለት፣ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት እና መሰል ችግሮች ሰራተኞች መሰናበታቸውን እንደሰሙና ገና ሪፖርት አለማንበባቸውን ጠቁመው፣ “በሰራተኞቹና በእኔ መካከል ሌሎች በርካታ ማናጀሮች በመኖራቸው የትኞቹ እንደተሰናበቱ አላወቅሁም” በማለት ጉዳዩ  በቀጥታ የሚመለከተው የሰው ሀይል አስተዳደሩን እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የሆቴሉ የሰው ኃይል አስተዳደር አቶ አሰፋ በየነን በስልክ አግኝተን በሰጡን ምላሽ፤ ሆቴሉ አለም አቀፍ ሆቴል እንደመሆኑ በርካታ አለም አቀፍ እንግዶች እንደሚያርፉበት ጠቁመው፣ ከዚህ አንፃር የሴኩሪቲ  ስራ ከፍተኛ ጥንቃቄና ንቃት የሚጠይቅ ቢሆንም ሰራተኞቹ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው መሰናበታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ስንብቱም የተፈፀመው በገባነው ውል መሰረት ነው፤ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ደሞዝ ቅጣት ደርሰናል” ያሉት አቶ አሰፉ፤ ከሴኩሪቲ ሃላፊው በደረሰን መረጃ ጥፋታቸውን ባለማረማቸውና ባለማስተካከላቸው ተሰናብተዋል ብለዋል፡፡ የጥቅማጥቅም ጥያቄን በተመለከተም ሲናገሩ፤እንደማንኛውም ሰራተኛ ሰርቪስ ቻርጅ ይከፈላቸዋል ያሉ ሲሆን ህክምናን በተመለከተም ለዓለም ከፍተኛ ክሊኒክ ጋር በገቡት ውል መሰረት፤ሰራተኞች በክሊኒኩ አስፈላጊውን ህክምና እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ የብሄር ወገንተኝነት የተባለው ሃሰት መሆኑን የገለፁት አቶ አሰፋ፤በሆቴሉ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሀዲያ፣ ትግሬ፣ ወላይታ እና የበርካታ ብሄር ተወላጆች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ጠቁመው “እናንተም ጋ ለአቤቱታ ከመጡት ውስጥ አማራም ትግሬም ኦሮሞም አሉበት” ብለዋል፡፡
የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ ሰራተኞቹ ቀደም ሲል ይከፈላቸው እንደነበር ጠቁመው ሆቴሉ በትክክል ተከፍቶ ስራ ከጀመረ በኋላ ግን በርካታ የሰው ኃይል በመቅጠርና በሶስት ሽፍት በመደልደል ሁሉም ሰው በቀን ስምንት ሰዓት መስራት እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ስነ-ምግባር ይጎድላቸዋል፣ ከሆቴል ጋር የተገናኘ ሙያ የላቸውም በሚል የቀረበው ትችት ተቀባይነት እንደሌለው ሲያስረዱም “ዋና ስራ አስኪያጁ በአሜሪካ አገር ለ42 ዓመት ሲኖሩ ትምህርታቸው ሆቴል ስራ ላይ ነው ያተኮረው” ያሉት የሰው ኃይል አስተዳደሩ፤ በሆቴል ሙያ ዙሪያ ከፍተኛ ስልጠና እንደሚሰጡና በሆቴሉ ባለአደራ ቦርድ ብቃታቸው ታምኖበት መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ አንድ ሰራተኛ በተሰማራበት ሙያ ላይ የሚቀመጡ መስፈርቶችና ገደቦች እንዳሉ የተናገሩት አስተዳደሩ፤ “የሆቴሉ ማናጀር የሴኩሪቲ ሰራተኛው አንዲትን እንግዳ አቅፎ ሲስም አግባብ አለመሆኑን በመናገራቸው ስማቸውን ለማጥፋት መሞከር ትክክል አይደለም፣ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው በተወሰደው እርምጃ ገና ስራ ከጀመረ አምስት ወር ያልሞላውን ሆቴል ስም ለማጥፋት መሯሯጥ አግባብ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሰራተኞችን በግፍ ያባርራል፤ ሊያባርርም ተዘጋጅቷል መባሉም ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አቶ አሰፋ አስተባብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የሸራተን አዲስ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር 4ኛ አመት የምስረታ በአሉን ባለፈው ማክሰኞ በሆቴሉ ላሊበላ አዳራሽ የማህበሩ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳዊት ሣሙኤል ባደረጉት ንግግር፤ከዚህ ቀደም የሆቴሉ ሠራተኞች በአመት ለ27 ቀናት ያለ ክፍያ ማሠራትን ጨምሮ የተለያዩ በደሎች በማኔጅመንቱ ይፈፀምባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ከማህበሩ ምስረታ በኋላ ግን በሂደት ማኔጅመንቱ እና ማህበሩ እየተነጋገሩ የሠራተኛው ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡ አሁንም በርካታ ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ የፍርድ ቤት ውሣኔን የሚጠብቁ ጉዳዮችም እንዳሉ አመልክተዋል፡፡
በበአሉ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) ተወካይ አቶ ታመነ መኮንን ባደረጉት ንግግር፤ ሠራተኛው መብቱን ለማስከበር በማህበር መደራጀት ጠቀሜታ እንዳለው አሳስበው፣ የሸራተን አዲስ ሆቴል ሠራተኞች ማህበር ለአባላቱ መብት መከበር እያደረገ ያለው ትግል በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡   

*ከ2500 በላይ ህፃናት ይሳተፋሉ
የፊታችን አርብ የሚከበረውን “የአውሮፓ ቀን” ምክንያት በማድረግ የህፃናት የሩጫ ውድድር ነገ በጃንሜዳ ይካሄዳል፡፡ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽ/ቤት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ ውድድር፤ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተውጣጡ ከ2500 በላይ እድሜአቸው ከ14 አመት በታች የሆኑ ህፃናት ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
ለዘጠነኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ተካፋይ የሚሆኑት ህፃናት፤ በአራት የእድሜ ክልል ተመድበው ከአንድ እስከ ሁለት ኪሎሜትር ርቀት የሚሸፍን የሩጫ ውድድር ያካሂዳሉ፡፡ ከዚህ ውድድር ቀደም ብሎ በአለም አቀፍ ት/ቤት ህፃናት ተማሪዎች መካከል የሁለት ኪሎ ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር ይካሄዳል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽ/ቤት ይህን የህፃናት የሩጫ ውድድር የአውሮፓ ቀንን ምክንያት በማድረግ በየአመቱ የሚያዘጋጀው፤ ስፖርት ለአንድ ሀገር እድገት የሚያበረክተውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ መድረክ ወደር የለሽ ክብርና ዝና በተጐናፀፈችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መሆኑን የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽ/ቤት የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ሰሎሞን ከበደ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

የስነ ጥበብ ስራዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ አማራጭ መድረክ የመፍጠርና ለጥበብ አፍቃሪያን በተለያዩ አጋጣሚዎችና ስፍራዎች የስነ ጥበብ ስራዎችን የመመልከት፣ የማድነቅና ቁምነገር የመቅሰም ዕድል የመፍጠር አላማ ይዞ የተቋቋመው ጉራማይሌ የስነ ጥበብ ማዕከል፣ ትናንት ምሽት ተመርቆ ተከፈተ፡፡
የማዕከሉ መስራችና ዳይሬክተር አቶ ሚፍታ ዘለቀ እንደተናገሩት፤ ጉራማይሌ የስነ ጥበብ ማዕከል፣ ስነጥበባዊ ዋጋው ከፍ ያለ ማህበረሰብ የመፍጠር፣ የስነ ጥበቡን ማህበረሰብ ከሰፊው ህብረተሰብ ጋር የማቀራረብ፣ ስነ ጥበብን መሰረት ያደረገ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ብልጽግናን የመፍጠር ግብ ይዞ ነው የተቋቋመው፡፡
ትናንት ምሽት በተከናወነው የማዕከሉ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ፤ ታደሰ መስፍን፣ ደረጀ ደምሴ፣ ዘላለም ግዛው፣ ዳዊት አድነውና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ሰኣሊያን የተሳተፉበት “ጉራማይሌ - አንድ” የተሰኘ የስዕል ትርዒት ለእይታ በቅቷል፡፡

በርካታ የሀገሪቱን ተዋንያን መፍለቂያ የሆነው እና ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚገኘው “ሚያዚያ 23” አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት እያከበረ ነው፡፡  በ1956 ዓ.ም “አስፋወሰን ካሳ” በሚል መጠሪያ ሥራ የጀመረው “ሚያዚያ 23” በመጪው ሐሙስ ከጧቱ ሦስት ሰዓት በሚከናወን ደማቅ ሥነ-ሥርአት የቀድሞ ተማሪዎቹ እና ያሁኖቹ የሀገሪቱ አንጋፋና ታዋቂ ከያንያንና ጋዜጠኞች በትምህርት ቤቱ እንደሚገኙ የተናገሩት የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ጌታቸው አዋሽ፤ እነዚሁ ከያንያን ልምድና ተሞክሮአቸውን እንዲሁም ትዝታቸውን ለአሁን ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች የሚቀርቤ ሲሆን 50ኛ ዓመቱን አስመልክቶ እየተካሄደ ያለው የእግር ኳስ ውድድርም ይጠናቀቃል፡፡ ሥራ ሲጀምር ከ120 በታች ተማሪዎች የነበሩት ትምህርት ቤቱ፤ አሁን 1560 ያሕል ተማሪዎች ያሉት ሲሆን ከቀድሞ ተማሪዎቹ መካከል አርቲስት ጥላሁን ዘውገ፣ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ፣ የቶክሾው አቅራቢው ሰለሞን ሹምዬ፣ አርቲስት ግርማ ተፈራ፣ አርቲስት አለልኝ መኳንንት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኤፍኤም ጣቢያዎች ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ ሳሙዔል እንዳለ ይገኙበታል፡፡

     በሽመልስ ይፍሩ (ጤርጢዮስ ከቫቲካን) የተዘጋጀው “የተመለሱና ያልተመለሱ ጥያቄዎቼ” የተሰኘው መፅሃፍ ታትሞ እየተሸጠ ነው፡፡
መጽሃፉ፤ አንዱን ቅዱስ መጽሐፍ እያነበቡ በተለያየ ስም የተጠሩበትንና የተለያየ አቋም የያዙበትን ዐብይ ምክንያት እንደሚፈትሽ የገለፀው አዘጋጁ፤ ርዕሰ ጉዳዩም ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ሰውና ስለ ክርስቶስ ባላቸው የእምነት ግንዛቤ ላይ ብቻ የሚያተኩር ነው ብሏል፡፡
በመፅሃፉ ውስጥ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት፣ የሐዋርያዊት (በተለምዶ Only Jesus የሚባሉቱ) ቤተክርስቲያናት እና የይሖዋ ምስክሮች አገልጋዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ መጽሐፉ በ50 ብር እየተሸጠ ሲሆን በጃፋር የመጽሀፍት መደብር እየተከፋፈለ ይገኛል፡፡

  በቴዎድሮስ ኃይሉ ተፅፎ በሰለሞን ሙሄ የተዘጋጀው “አንላቀቅም” የተሰኘ ሮማንስ ኮሜዲ ፊልም፤ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ በ11 ሰዓት በአቤል ሲኒማ ይመረቃል፡፡ በቴዎድሮስ ፊልም ፕሮዳክሽን በቀረበው በዚህ ፊልም ላይ ማህደር አሰፋ፣ ሰለሞን ሙሄ፣ ሙሉዓለም ጌታቸው፣ ነብዩ ኤርሚያስ፣ ሄኖክ አለማየሁና ሌሎች አንጋፋ ባለሙያዎች እንደተሳተፉበት ታውቋል፡፡

    የተለያዩ የቢዝነስ፣ የሞቲቬሽን እና መሰል መፅሀፍት በማዘጋጀት የሚታወቁት ዶ/ር አቡሽ አያሌው፤ ያዘጋጁት “ካይዘን” የተሰኘ መፅሀፍ በትላንትናው እለት በግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል ተመርቋል፡፡ ሩቅ ምስራቃዊያን ሳይንሳዊ እውነታውን ቀድመው በመረዳት ካይዘንን ተለውጠውበታል የሚሉት ዶ/ር አቡሽ፤ ሀገራችንም ካይዘንን ተግባራዊ ካላደረገች ያሰበችው ለውጥ ላይ እንደማትደርስ በማሰብ፣ የካይዘንን ግንዛቤ በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል በመፅሀፉ ምረቃ ላይ የተለያዩ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በመፅሀፉ ዙሪያም ውይይት ተካሂዷል፡፡

    ነዋሪነታቸውን በለንደን ባደረጉት ኢ/ር ወንድሙ ነጋሽ ተፅፈው የተዘጋጁት “የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድን ነው” መፃህፍት ዛሬ ረፋድ ላይ በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ ይመረቃሉ፡፡
መፃህፍቶቹ ስሜትን ስለመቆጣጠር፣ በራስ ስለመተማመን፣ በአላማ ስለመፅናት፣ ስለ ደስታና የፍቅር ያለንን ግንዛቤ የሚያሰፉ ሲሆን “ፍቅር ምንድነው?” በሚለው መፅሀፍ ውስጥ ፍቅር ምንነትና መሰል ጉዳዮች ተዳስሰውበታል፡፡ መፃህፍቱ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ዛሬ ሲመረቁ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፀሐፊው ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ ላለፉት 15 ዓመታት በእንግሊዝ የጦር መርከቦችን ከአደን የመከላከል ሲስተም መሀንዲስ በመሆን ከመስራታቸውም በተጨማሪ በስነ-ልቦና ላይ የተመሰረቱ ተከታታይነት ያላቸው ጥናታዊ መፃህፍት በመፃፍ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የተለያዩ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርሶችና የብሔር ብሄረሰቦችን ባህልና ትውፊት በአንድ ላይ በማሰባሰብ ለማስጎብኘት የሚያስችል ነው የተባለ የባህል ማዕከል የፊታችን ሐሙስ ሊከፈት ነው፡፡
“ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል” የሚል ስያሜ የተሰጠው የባህል ማዕከል፤ ኢትዮጵያን ቀደምት ታሪኮች የሚያወሱ ቅርሶች፣ ለአገሪቱ ታሪካዊ ቦታዎች ምሳሌ የሚሆኑ ስራዎች፣ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ አሁን ድረስ ያሉ የአገሪቱ መሪዎች ምስሎችና አጫጭር ታሪኮችና ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ቤቶችን አካቶ የያዙ መሆኑ ታውቋል፡፡
የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሳቤላ በላይነሽ አባይ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ማዕከሉ ህብረተሰቡ ባህሉን በአግባቡ ለማወቅና ጎጂውን ለማስቀረት፣ ጠቃሚውን ደግሞ ለመያዝ እንዲችል የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቱሪስቶች በአንድ ጊዜ ሁሉንም አካባቢዎች ለመጎብኘት እንዲችሉ እድሉን ያመቻቸ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ቄራ ቡልጋሪያ ማዞሪያ አካባቢ የተሰራው የባህል ማዕከል፣ የፊታችን ሐሙስ በይፋ ተመርቆ እንደሚከፈትም ታውቋል፡፡