Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62

ኢትዮጵያዊቷ ሞዴልና በጎ አድራጊ ሊያ ከበደ “ብላክ ጎልድ” በተሰኘው ፊልም ላይ ከአንቶኒዮ ባንድራስ ጋር እንደምትተውን ተገለፀ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ  በኳታር በሚደረግ በ”3ኛው ዶሃ ትሬቤካ” ፊልም ፌስቲቫል ላይ በሚመረቀው “ብላክ ጎልድ” ፊልም ላይ ሊያ ከበደ አይሻ የተባለች ባርያ ገፀ-ባህርይን ወክላ ትጫወታለች፡፡ ፊልሙ 55 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን ቀረፃው በቱኒዚያና በኳታር እንደተከናወነ ታውቋል፡፡ ከ80 ዓመት በፊት ስለነበሩ ሁለት የአረብ ኢምሮች ሽኩቻ የሚተርከው “ብላክ ጎልድ”፤ በኳታር ያለውን የሲኒማ ስራ እንቅስቃሴ ያሟሙቃል ያለው ገልፍ ኒውስ፤ አምና “ዴዘርት ፍላወር”  በተሰኘው  ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ ሆና የተደነቀችው ሊያ፤ በሙያው ስኬታማ እየሆነች መምጣቷን ገልጿል፡፡

በሊባኖስ የምትኖረው ራሄል ዘገየ  “ቤይሩት” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያውያን የስደት ኑሮ ላይ ያተኮረ ፊልም እየሰራች መሆኑን ከታድያስ ድረ ገፅ ጋር ባደረገችው ቃለምምልስ ተናገረች፡፡ ፊልሙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሚደርስባቸው የጉልበት ብዝበዛ፣ ፆታዊና ሰብአዊ  ጥቃቶችና ሌሎች በደሎች ዙርያ ያውጠነጥናል ብላለች፡፡ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምስራቅ  በሚደርስባቸው በደል ልቤ ይቃጠላል ያለችው ራሄል፤ በሃያ ዓመቷ በሊባኖስ በቤት ሰራተኛነት ለመስራት ከአገሯ መሰደዷን ትናገራለች፡፡

“60 ሻማ” የሐዋሳ ኪነጥበብ ወዳጆች በየወሩ ዝግጅቱን እያቀረበ እስከ 2003 ዓ.ም መጨረሻ 33 ሻማ የለኮሰ ሲሆን 34ኛዋ ኪነጥበባዊ ሻማ ነገ በኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ትለኮሳለች፡፡ በከተማይቱ ቤተሰብ መምሪያ አዳራሽ በክብር እንግድነት በመገኘት ልምዱን የሚያጋራው ፀሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ነው፡፡

በፊልም ጥበብ ዙርያ ላለፉት አምስት አመታት ባለሙያዎችን ልምድ ሲያቀሳስም የቆየው አላቲኖስ የፊልም ሰሪዎች ማህበር፤ “የተዋናይ ግሩም ኤርምያስ የአተዋወን ብልሃት” የሚል የጥናት ወረቀት ሊያቀርብ ነው፡፡ የጥናት ወረቀቱ የሚቀርበው በሩስያ የሳይንስና የባህል ማእከል ፑሽኪን አዳራሽ በመጪው ሐሙስ ከቀኑ 11 ሰዓት ነው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ አንጋፋው የኢትዮጵያ የፊልም ባለሙያ ሚሼል ፓፓታኪስ ከትናንት ወዲያ ምሽት በፑሽኪን አዳራሽ ልምዳቸውን አጋርተዋል፡፡

Saturday, 08 October 2011 10:15

መፃሕፍት ይመረቃሉ

የሬዲዮ ፋና ኦሮምኛ ቋንቋ አገልግሎት ባልደረባ በሆነው ጋዜጠኛ ኪዳኑ ዘለቀ ለንባብ የበቁ ሁለት የኦሮምኛ መፃሕፍት ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ቦሌ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር አዳራሽ ይመረቃሉ፡፡ በዚሁ ወር ከማተሚያ ቤት የወጡት የጋዜጠኛ ኪዳኑ መፃሕፍት ለመጀመርያ ጊዜ በኦሮምኛ የታተመው “ቆሳ ገገባር” የቀልድ መጽሐፍ እና “ኮቲ ሞኮሚቲ” የግጥም መፃሕፍት መሆናቸውን ምረቃውን ያሰናዳው ሱቢ ፕሮሞሽን ለአዲስ አድማስ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የጀርመን የባህል ማእከል ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ “Rap poetry” ሙዚቃዊ ግጥም እንደሚያቀርብ ገለፀ፡፡ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የማዕከሉ አዳራሽ የሚቀርበው ዝግጅት ግጥሞች፣ ቀረርቶ፣ ፉከራና ሽለላ ከፋቡላ ጥበባት ጋር የሚቀርቡበት ሲሆን ሰዓሊያን የሚቀርበውን ሙዚቃና ግጥም በማዳመጥ ብቻ የቅብ ስዕል እንዲሰሩ ተደርጐ በዚያው ምሽት ከሙዚቃ ዝግጅቱ በመቀጠል ለእይታ ይበቃል፡፡ ዝግጅቱ የኢትዮጵያንና የጀርመንን የባህል ግንኙነት እንደሚያጠናክር የባህል ማዕከሉ ገልጿል፡፡ ይህ በእዚህ እንዳለ ዕሮብ ጥቅምት ምሽት 12፡30 በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ኪነጥበባዊ ዝግጅት ይቀርባል፡፡ በገጣሚ አበባው መላኩ፣ ሜሮን ጌትነት፣ እንዳለጌታ ከበደ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ምስራቅ ተረፈ ከመለከት ባንድ ጋር የግጥም ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ የመግቢያ ዋጋ 50 ብር ነው፡፡

“ጥሪ አይቀበልም” እና “የማልተኛው” ፊልሞች ዛሬ እና ነገ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ይመረቃሉ፡፡
“ጥሪ አይቀበልም” በዩሊያን ተክለማርያም የተፃፈ ሲሆን በሚሊዮን ስዩም ተዘጋጅቶ ፕሮዱዩስ ተደርጓል፡፡ በ99 ደቂቃ ልብ አንጠልጣይ ፊልሙ ላይ መስፍን ኃይለኢየሱስ (ጠጆ)፣ ፊዮሪ ኃይሌ፣ ኤልሳቤጥ ጌታቸው (ቀጮ)፣ ሚካኤል ታምሬ፣ ዳንኤል ወንድወሰን እና እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠቀቅ አንድ አመት ከስድስት ወር የፈጀ ሲሆን ከሥራ የተፈናቀሉ ወጣቶች በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚያደርጉትን ውጣ ውረድ ያሳያል፡፡

ከ8 ዓመት በፊት የተሰራ የኮሜዲ ስራው እንደ አዲስ ስራ መውጣቱን የገለፀው ኮሜድያን ክበበው ገዳ፤ ሕዝቡ በእኔ ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽር ስለሆነ ሕዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ አለ፡፡ ረቡዕ ጧት በሐርመኒ ሆቴል በሀበአብ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት አማካይነት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ከ8 ዓመት በፊት በ45 ሺህ ብር የሸጥኩት ለዚያን ጊዜ የሚሆን ኮሜዲ ያኔ መውጣት ሲገባው አሁን መውጣቱ በአዲሱ ስራዬ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ያለው ኮሜዲያኑ፣ አዲሱ ስራም በዚሁ ምክንያት አልወጣም ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት እኔን ሳያማክር በ1995 ዓ.ም. የገዛውን ስራዬን ለመሸጥ ሲነሳና አዲሱን ስራዬን ለመጠቀም ሲወስን በተመልካቹ ዘንድ ከሚፈጥረው ስሜትና ትርጉም አንጻር ሊጠነቀቅና እኔንም ሊያማክር፣ ቢያንስ ሊያሳውቀኝ ይገባ ነበር ብሏል፡፡ “ኤሌክትራ ቢያማክረኝ በአሮጌው ምትክ አሁን የስራዬን እድገት የሚገልጽ አዲስ ስራ እሰጠው ነበር” ሲል ተናግሯል፡፡ እስከ መቼ በኮሜዲያንነት እንደሚቀጥል የተጠየቀው ኮሜዲያን ክበበው ገዳ፤ ዕድሜ ልኩን ኮሜዲያን ሆኖ መቆየት እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡

ሁለት መቶ ሃምሳ መቀመጫዎች ያሉት አዲስ ሲኒማ ቤት በጎንደር ከተማ ተከፈተ፡፡ በከተማዋ ፒያሳ አካባቢ የተከፈተው “ደስታ ሲኒማ ቤት” ከፊልም ማሳያነት በተጨማሪ ለስብሰባ አገልግሎት ይውላል፡፡ በምንትዋብ አርት ፕሮሞሽን እና በአንድ ባለሀብት ትብብር የተከፈተው “ይኼው” ሲኒማ ቤት ከ10 ቀን በኋላ በይፋ ስራ ይጀምራል፡፡

ለንደን ሊጓዙ አንድ ሌሊት ብቻ የቀራቸው ወጣቶች በመሸኛ ድግሳቸው ላይ የሚገጥማቸውን ፈተና ለመወጣት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያሳየው “ዕጣ ፈለግ” የተሰኘ ትያትር መታየት ሊጀምር ነው፡፡ ትያትሩን የጻፈው ጋዜጠኛ ዘካርያስ ብርሃኑ ሲሆን፤ ረቡዕ ከቀኑ 11 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር የሚጀመረውንና ደራሲው ከታጠቅ ነጋሽ ጋር ያዘጋጁትን ትያትር ሐረገወይን እሸቱ፣ ታጠቅ ነጋሽ፣ መስከረም ኪዳኔ፣ ሀረጓ እንድሪስ፣ ዘካሪያስ ብርሃኑ፣ ወርቅነህ ማሞ እና ጌጤ ታደሰ ይተውኑበታል፡፡