Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62

አስቴር ፊልም ፕሮዳክሽን አጫጭር የአማርኛ ልቦለድ ድርሰቶችን ወደ ፊልም ሊቀይር መሆኑን አስታወቀ፡፡ የፕሮዳክሽኑ ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ይገረም ደጀኔ ..የትሮይ ፈረስ.. በአጭር ልቦለድ ላይ ተመሥርቶ የተሰራ ፊልም ሲመረቅ ሌሎች መሰል ፊልሞች ለመሥራት እየተንቀሳቀስን ነው፣ የሦስቱ ቀረፃ በመጪው ወር ይጀመራል ብሏል፡፡

ፈረንሳይ ለጋስዮን በተለምዶ ብረት ድልድይ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው ዛጐል ቤተመፃህፍት አዲስ ወርሃዊ የልጆች ሥነ ሁፋዊ ዝግጅት ጀመረ፡፡ የድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት ሥነ ሁፋዊ ዝግጅቱ በሌሎች ዘርፍ የሚገኙ ባለሙያዎች ለልጆች በሚሆን መልኩ በየወሩ ልምድ የሚያካፍሉበት ሲሆን ልጆች ዘወትር እሁድ በቤተ መፃህፍቱ በነፃ ያነባሉ፡፡

ኢትዮጵያዊው የፊልም ባለሙያ ዮሐንስ ፈለቀ ከስመ ጥሩ የስፔን ፊልም አዘጋጅ ቤንቱራ ዱረል ጋር ያዘጋጀው ባለ 35 ሺህ ዩሮ በጀት ፊልም በሚቀጥለው ሳምንት  በባርሴሎና ቴሌቪዥን የሚታይ ሲሆን በዚህ ሳምንት በቱርክ አንካራ በተጀመረው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል እየተሳተፈ ነው፡፡ በጐዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ሕይወት ላይ ተመስርቶ “The Hidden Smile” በሚል የእንግሊዝኛ ርእስ የተሰራው ፊልም የእንግሊዝኛና የስፓኞል መግለጫ (Subtitle) አለው፡፡ የዘጠና ደቂቃው ባለ ሦስት ክፍል  ፊልም ሁለት ክፍል ተሰርቶ ተጠናቋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በኪነጥበቡና በፖለቲካው ዘርፍ ጉልህ ሚና ያላቸው ባለሙያዎች 2003 ዓ.ምን እንዴት እንዳሳለፉትና በ2004 ለአገራቸው የሚመኙትን ተናግረዋል፡፡ አብዛኞቹ አርቲስቶች ባሳለፍነው ዓመት የጥበቡ ዘርፍ እንዳደገ ቢስማሙም እየናረ የመጣው የኑሮ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ጠቅሰው የተሻለ ዘመን እንዲመጣ ተመኝተዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በበኩላቸው ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው እያደር መቀነሱንና ዲሞክራሲያዊ ሂደቱ መቀጨጩን ይገልጻሉ፡፡ የፖለቲካውን ዕጣ ፈንታ ለመተንበይም ተቸግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ በተለይ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በህዝቦች መካከል መግባባትና መነቃቃት እንደፈጠረ ገልጾ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ግብዓት የመሰብሰብ ሥራ እንዳከናወነ ይገልጻል፡፡ በ2004 ዓ.ም. ተቃዋሚዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው አርቲስቶቹንና ፖለቲከኞቹን አነጋግራ የአዲስ ዓመት መልዕክታቸውን እንደሚከተለው አቅርባለች፡፡

ዓለምአቀፍ የአፍሪካ ደራስያን ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄዱና ሐፍቱ የሀገራችንን የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ሥፍራዎች መጎብኘታቸው የዓመቱ የዘርፉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የአንጋፋ ሐፍትን ለምሳሌ የጋሽ ፀጋዬን እና የአብዬ መንግሥቱን ሥራዎች ማሳተሙ ሌላው ስኬት ነው፡፡ ለደራስያኑ ጉባኤ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዋና ሐፊነቴ፣ በአስተባባሪነት የራሴን አስተዋዖ አድርጌአለሁ፡፡ በወረቀት ዋጋ መናር በርካታ ሥራዎች አለመቅረባቸው የቀረቡትም በኑሮ ውድነት የተጠበቀውን ያህል ገዢ አለማግኘታቸው ዓመቱን አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ በግል ሕይወቴ ከማፈቅራት እሌኒ መስፍን ጋር ጋብቻ መፈፀሜ እጅጉን አስደስቶኛል፡፡ አምና በዚህ ወቅት አርቲስት ፀሐይ ዮሐንስ ያለውን ደግሜ ልዋስና 2004 ዓ.ም የንባብ ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
እንዳለጌታ ከበደ
ደራሲ

የ..ሰው ለሰው.. ተከታታይ የቴሌቭዢን ድራማ መጀመርና ከሰለሞን ቦጋለ ጋር የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የክብር አምባሳደር መባላችን፣ ከዓመቱ አስደሳች አጋጣሚዎቼ ተጠቃሽ ነው፡፡ የቴሌቪዢን ድራማው ባተሌ ስላደረገኝ ከእነሙሉዓለም ጋር ልሠራ የነበረው ፊልም፣ አመለጠኝ ከምላቸው አሳዛኝ ገጠመኜ አንዱ ነው፡፡ የአባይ ግድብ ጉዳይ ከሀገሪቱ ትልቅ አጀንዳዎች ይሰለፋል፡፡ 2004 ዓ.ም መተሳሰባችንን አዳብረን አኩሪ ባህሎቻችንን የምንጠብቅበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
ሰለሞን ዓለሙ ፈለቀ
አርቲስት

ባሳለፍነው ዓመት ብዙ አዳዲስ ሙያተኞች በመምጣታቸው ፊልም ቤቶች ከውጭ ፊልሞች ይልቅ ለሀገር ውስጥ ፊልሞች በራቸውን እየከፈቱ ነው፡፡ ከኋላዬ የመጡትን በማበረታታትና በማድነቅ ጥሩ መንገድ የማሳየት፣ ባህል ጠብቀው ሀገር ወዳድ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታዬንም ቀጥዬበታለሁ፡፡ የቲቢ በሽታን ለመከላከል የተሰጠኝ ኃላፊነት ከ2003 ዓ.ም የደስታ ምንጮቼ አንዱ ነው፡፡ ብዙ መሥራት በሚችሉበት ዕድሜ ድንገት ያሸለቡ ሞያተኞች ያሳዝኑኛል፡፡ 2004 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚደሰቱበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም

ያለፈውን 2003 ዓ.ም ከሙዚቃ ኢንዱስትሪው አንፃር እንዴት እንዳለፈ ስገመግመው፤ አድማጩ ጥራት ያለውን ሥራ የሚመርጥበት ጊዜ በመሆኑ የሙዚቃ ሞያውም አድማጩም ያደገበት ነው፡፡ ነገር ግን የቅጂ መብት ጥሰት በየቦታው በመንሠራፋቱ እና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች አጠቃላይ ኢንዱስትሪው ማደግ በሚገባው መጠን ሊያድግ አልቻለም፡፡ ከሞያው አንፃር እያበረከትኩ ያለሁትን አስተዋጽኦ በሚመለከት ከተጠየኩ ለ2004 ዓ.ም መግቢያ አዲስ የሙዚቃ አልበም አበረክታለሁ ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እና ከቅጂ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አዲስ ዓመትን ተሻግረዋል፡፡ ከዓመቱ በአንዱ ወር ግን እነዚህ አዳዲስ ሥራዎቼን ለሕዝብ ጆሮ አደርሳለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡  በሌላ በኩል ክለብ ውስጥም በሙዚቃው ዘርፍ በርካታ ጥሩ ነገሮችን ለመሥራት እየጣርኩ ነው፡፡  በ2003 ዓ.ም ቀን በቀን ጤነኛ ሆኜ ማሳለፌ አስደሳች ትውስታዬ ነው፡፡ ቴሌቭዥን በከፈትኩ ቁጥር የምሠማው የዓለም አለመረጋጋትና ችግር እንዲሁም በኢትዮጵያ የተከሰተው የኑሮ ውድነት 2003ን በአስቸጋሪነቱ የሚያስታውሱኝ ክስተቶች ናቸው፡፡ 2004 ዓ.ም እርስ በእርስ መዋደድ ያለባት፤ ሰላም የበዛባት፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት እመኛለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም አዲስ ዓመት፡፡
ሸዋንዳኝ ኃይሉ
ድምፃዊ

የሙዚቃ ሙያው አድጓል፤ ጥሩ ባንዶች እየተቋቋሙ ነው፡፡ ቀደም ሲል በኪቦርድ ብቻ ይሠራ የነበረው አሁን  በቡድን በደንብ የሚጫወቱትን ሳይ ደስ ይለኛል፡፡ ገና ብዙ ነገሮች ቢቀሩትም መንግሥት በቅጂ መብት ዙሪያ ያደረገው ጥበቃ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ በግሌ ለሞያው አስተዋጽኦ እያደረኩ ነው፡፡ ለአዲሱ ዓመት ..የበረሀ ስደተኛ.. የሚል ነጠላ ዜማ ለቅቄያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ቴዲ አፍሮ ተጨምሮበት ዘፈኑን አሳድገን ክራር እና ማሲንቆ ጨምረን እንዲያስጨፍር አድርገን፣ በቆንጆ ሁኔታ ሁለት ሆነን ሠርተነዋል፡፡ ለብዙ ዘመን ሁለት ሰው መሥራት ቆሞ ነበር፤ አሁን ግን ከታላቁ ከማከብረው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ጋር ሠርቻለሁ፡፡ በ2003 ዓ.ም በኖርንበት አሜሪካ የደረሰው የተፈጥሮ አደጋ፤ ባልተለመደበት በቨርጂኒያና በዲሲ መድረሱ ያስፈራል፡፡ በሀገራችን የሚታየው የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት በጣም ያስከፋል፡፡ አስደሳቹ በአገራችን መንገድ እና በርካታ ቤቶች መሠራታቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ እግዚአብሔር የቀደሳት፤ ሕዝቡ አብሮ ተዛዝሎ እና ተቃቅፎ የሚኖርባት አገር ናት፡፡ እኔም በ2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ ስራ አጥ የማይኖርባት፤ የትምህርት ቤት ጥራት የሚያድግባት፤ የተማረ ሥራ ሠርቶ የሚኖርባት አገር እንድሆን እመኝላታለሁ፡፡
ኩኩ ሰብስቤ
ድምፃዊ

በ2003 ዓ.ም ጥበብ አድጓል አላደገም የሚለውን ለመናገር ብዙ ነገሮች ያስፈልጋል፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው በርካታ ፊልሞች በመሠራታቸው ከሆነ፣ በብዙ መንገድ በርካታ ፊልሞች እየወጡ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ሙያው ትኩረት እየተሰጠው እያደገ መሆኑን እናያለን፡፡ ተዋናዩ የተሻለ ነገር የሚያሳይና ተዋናዩን ያከበረም ነው፡፡ ይሄንን ዕድገት ለማስቀጠል በበኩሌ እኔ ፕሮዲዩስ የማደርገው የራሴ ድርሰት ለማቅረብ፣ ከጓደኞቼ ጋር አዲስ ፊልም ለማበርከት እየተሯሯጥኩ ነው፡፡ በአገሪቱ ተከሰተ የምለው አስደሳችና አስቸጋሪ ለይቼ የማየው የተለየ ነገር የለም፡፡ በ2004 ዓ.ም መልካም ወሬ የሚወራባት፤ ሰው አብሮ ተባብሮ በቀናነት የሚተያይባት፤ ሁሉም የሥራውን ፍሬ የሚያገኝበት፤ የተሻለ ለውጥ የምናይበት ሀገር እንድትሆን እመኛለሁ፡፡
ሜሮን ጌትነት
ገጣሚ እና ተዋናይ