Saturday, 23 February 2013 10:59

የተሰደዱ የዱር እንስሳት ነዋሪዎችን አስጨንቀዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ጠና ወረዳ የሚገኘውና ከባሌ ሰንሰለታማ ተራሮች አንዱ የሆነው ጋለማ ተራራ በመጨፍጨፉ የዱር እንስሳት ወደ ጢቾ ከተማ በመሸሻቸው ለከተማዋ ነዋሪዎች ሥጋት መፍጠራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ፡፡
እንደነዋሪዎች ገለፃ ከሆነ ተራራው እንደ ዝግባ፣ ዋንዛ፣ ኮሶ፣ ወይራ፣ አስታ ሽውሸዌ እና በመሣሰሉ አገር በቀል ዛፎች የተጠቀጠቀና ለብርቅዬ ዱር እንስሳቱ መኖሪያ የነበረ ሲሆን፤ ደኑ ለእርሻ መሬት፣ ለጣውላና ለከብቶች መዋያ ሆኖ በመጨፍጨፉ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ አጋዘን፣ የደጋ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮ፣ አቦሸማኔ ነብርና መሰል የዱር እንስሳት ተሰደው ወደ ጢቾ ከተማ በመግባታቸው የከተማው ነዋሪዎች ለስጋት መዳረጋቸውንና ሌሊት ራሳቸውን ከእንስሳቱ ሲጠብቁ እንደሚያድሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

በጤቾ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር የሆኑትና ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉት ግለሰብ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ መኖሪያቸውን በህገ-ወጥ ደን ጨፍጫፊዎች ያጡትና ወደ ከተማ ሸሽተው የገቡት የዱር እንስሳቱ ከተማ ውስጥ ሲታዩ በከብት እረኞችና በተማሪዎች እየተገደሉ ነው፡፡ “ለምሣሌ የደጋ አጋዘን ብርቅዬ በመሆኑ በ40 በሬ ይለወጣል” ያሉት መምህሩ፤ ደኑ ከመጨፍጨፉም ባሻገር የከብቶች መኖ እንዲያበቅል በሚል እሳት እንደሚለቁበትም ነግረውናል፡፡ በእሳትና በደን ጭፍጨፋው የተነሳ የተደናበሩት እንስሳቱ በጢቾ ከተማ ችግኝ ጣቢያ፣ በጢቾ አንደኛ ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኝ ጫካ፣ እና በየቤተክርስትያኑ ግቢ ተሰግስገው የሚገኙ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም ለስጋት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ 
በተለይም ስደተኛ ጦጣዎች የሰው ሳሎን ውስጥ እና ማዕድ ቤት በመግባት ምግብ በመውሰድና ዕቃ በመሰበር ማስቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡
የወረዳው የተፈጥሮ ሀብት የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሽመልስ ስበር ጉዳዩን አስመልክተው ሲናገሩ፤ ስለ እንስሳቱ መሰደድ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው ነገር ግን ተራራው ከህዝብ ብዛትና ከመሬት ጥበት ጋር በተያያዘ በሰፊው ለእርሻ ማስፋፊያ መዋሉንና በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ “በዙሪያው ሌሎች ወረዳዎች ተራራዎችን እያረሱ በመሆኑ የአንድ ጠና ወረዳን ህዝብ ማቆም አልተቻለም” ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በአሁን ሰዓት ለህዝቡ የመሬት ሠፈራ ሥራ እየተሰራ በመሆኑ ሠፈራው ሲጠናቀቅ ህዝቡ ያለው የመሬት መጠን ታውቆ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
በወረዳው ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የእንስሳት ባለሙያ አቶ ሙሴ ከድር ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ህዝብ መጨመር የተነሳ የእርሻ መሬትን ለማስፋፋትና ለጣውላ ስራ አገር በቀል ደኖች መጨፍጨፋቸውን ገልፀው፤ በዚህም ሳቢያ በውስጡ ይኖሩ የነበሩት ብርቅዬ እንስሳት ወደከተማው ገብተዋል ብለዋል፡፡ የእንስሳት ባለሙያው አክለውም፤ በተለይም ድኩላዎች በጢቾ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ፣ በቤተክርስቲያንና በመቃብር ቦታዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ “ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች ሲንጫጩ የሚደነብሩት ድኩላዎቹ በግርግር እየተገደሉ ነው” ብለዋል፡፡
ከከተማው ዳር ዳር ባለው ጫካ ውስጥ አጋዘን፣ ከርከሮና መሰል እንስሳት በመጠጋታቸው የአካባቢው ሰዎች በስጋት ውስጥ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

Read 4463 times