Friday, 08 March 2024 17:36

ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን 6ኛ ዓመት በድምቀት አከበረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዳሸን ባንክ ሸሪክ የተሰኘ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን 6ኛ ዓመት ባከበረበት ዕለት ከደንበኞች በበጎ አደራጎት ፈንድ በአደራ የሰበሰበውን 12.5 ሚሊዮን ብር ለ18 አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለገሰ፡፡  

ዳሸን ባንክ በሚሰጠዉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ብቻ አሁን ላይ ከ1 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፤ይህንንም በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች አክብሯል፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ ለባንኩ አመኔታቸውን ለሰጡ ደንበኞች ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ወደፊትም ለላቀ ስኬት የሸሪዓህ መርህን በመከተል አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶቸን እንደሚያቀርብ ገልፀዋል፡፡

አቶ አስፋው አክለውም፤ በአደራ የተሰጣቸውን ገንዘብ የተረከቡ 18 አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች የማህበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ በሚያስችሉ ስራዎች ላይ እንዲያውሉት አደራ ብለዋል፡፡ በቀጣይም ባንኩ እነኚህንም ሆነ መሰል ሌሎች ተቋማትን የማህበረሰቡን ችግሮች በዘላቂነት በሚፈቱ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚሻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዳሸን ባንክ፤ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአንድ መስኮት መስጠት የጀመረው አገልግሎት አድጎ ዛሬ ላይ ከ70 በላይ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሚሰጡ ቅርንጫፎች እንዲሁም ከ800 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች ደግሞ በመስኮት ለደንበኞቹ የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከደንበኞቹም ከ9.5 ቢሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ከ6 ቢሊየን ብር በላይ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ፋይናንስ አድርጓል፡፡

ባንኩ ከወለድ-ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚጠይቀውን ሙያዊና ሸሪዓዊ ስነ-ምግባር ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ረገድ እ.ኤ.አ ህዳር 28 ቀን 2023 በባህሬን ማናማ በተካሄደው 9ኛው የኢስላሚክ ሪቴል ባንክ ሽልማት ላይ ጠንካራው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚሰጥ ባንክ (The strongest Islamik Retail Banking Window in Ethiopia 2025) በሚል ተቀማጭነቱ ሎንዶን በሚገኘውና  በፋይናንስ ዘርፍ ጥናትና ምርምር በሚሰራዉ  ኬምብሪጅ አይ ኤፍ ኤ(Cambridge IFA) የተሰኘ ተቋም ሽልማት አግኝቷል፡፡ ባንኩን ለዚህ ሽልማት ካበቁት መሰፈርቶች አንዱ  ጠንካራ የሸሪዓህ አስተዳደር ማዕቀፍ በመተግበሩ ነው፡፡

ባንኩ በአለም አቀፍ ደረጃ የእስላማዊ ፋይናንስ ተቋማትን የሂሳብ፣ ኦዲትና ሸሪዓህ መስፈርቶችን የሚያወጣው ተቋም (AAOIFI) ቋሚ አባል የሆነ፣ በኢትዮጳያ ብቸኛው የፋይናንስ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡

Read 603 times