Sunday, 28 April 2024 21:09

የፖለቲካ ሹመኞች በሙያተኞች ላይ በሚያሳድሩት ጫና የመንግስት ሥራ እየተደናቀፈ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የፖለቲካ ሹመኞች በሙያተኞች ላይ በሚያሳድሩት ጫና የመንግሥት ሥራ እየተደናቀፈ ነው ሲሉ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎቹ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ። በብዙዎቹ የመንግስት መ/ቤቶች ሃላፊዎች ሥልጣን ላይ የሚቀመጡት በፖለቲካ ታማኝነት እንጂ በዕውቀትና በብቃት ባለመሆኑ በሙያተኞች ላይ የሚያሳድሩት ጫና ሥራውንም ባለሙያውንም እየጎዳው መሆኑንም ያስረዳሉ። እየጎዳው ነው ተብሏል፡፡
በአንድ የመንግስት መ/ቤት ውስጥ በከፍተኛ ኤክስፐርትነት የሚሰሩት ግሩም ኤሊያስ (ዶ/ር) የተባሉ ግለሰብ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በመ/ቤቱ ውስጥ  በከፍተኛ ኤክስፐርትነት ቢቀጠሩም፣ በሃላፊነት የተመደበው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የፖለቲካ ሹመኛ በመሆኑ ሙያተኞች ሥራቸውን በቅጡ መስራት አልቻሉም ብለዋል።
እንደ ኤክስፐርቱ ገለፃ፣ ለሀገር ይጠቅማል ብለን የምናጠናው ጥናት፣ የምናቅደው ስትራቴጂክ ዕቅድ በሙሉ በዋና ስራ አስፈጻሚው ውድቅ ይደረጋል። የተሻለ ሀሳብ አይቀርብም፣ የተለፋበት ጥናትና እቅድ መና ይቀራል፡፡ እኛ ግን ከፍተኛ ደሞዝ እየተከፈለን ቀጥለናል። ይህ ደግሞ ህሊና ላለው ሰው ከባድ ነው ብለዋል፤ ግሩም ኤልያስ (ዶ/ር)።
ለደህንነታቸው ሲሉ የመስሪያ ቤታቸው ስም እንዳይጠቀስ የፈለጉት እኚህ ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ በሥራ ባልደረቦቻቸው ዘንድ በማያምኑበት ጉዳይ ሁሉ ከአለቃቸው በመቃወም የሚታወቁ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ከአንዴም ሶስት ጊዜ በዲሲፕሊን ጥሰት የደሞዝ ቅጣት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከደረጃ ዝቅ የመደረግ ዕጣ ፈንታ እንደገጠማቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
ግሩም ኤርምያስ ላለፉት ዓመታት ሲሰሩ በቆዩበት መስሪያ ቤት፣ ሥራቸውን በብቃትና በትጋት ከሚሰሩ ኤክስፐርቶች  ይልቅ ለበላይ አካል ወሬ የሚያቀብሉና የሚላላኩ፣  የመስሪያ ቤቱ “ቁንጮ ሰራተኞች” ተብለው ይሸለማሉ፣ ደሞዛቸው ያድጋል ይመነደጋል፤ የደረጃ እድገትም ያገኛሉ መንግስት ይህን፤ አገርንም ህዝብንም የሚጎዳና እድገትን የሚጎትት የፖለቲካ ሹመኞች ፈላጭ ቆራጭነት በጊዜ ማስተካከል ካልቻለ፣ አገር ወደፊት መራመድ አትችልም ብለዋል። እርሳቸው በሙያቸው አገር ማገልገል ስላለባቸው ወደ ግል ተቋማት እያማተሩ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ሌላው በኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ ባለሙያነት የሚሰራው ዘሪሁን አማን (ስሙ ተቀይሯል) የተባለ ወጣት ኤክስፐርት በበኩሉ፤ ከደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን ይዞ ወደ ሀገሩ መመለሱን ይናገራል። በለውጡ ሰሞን በኢትዮ ቴሌኮም የተቀጠረው ይሄው  ወጣት ባለሙያ፤ ለውጡ የመጣ ሰሞን የነበረውን ተስፋና የለውጡ መንግስት ሥልጣን በያዘ ሰሞን በአገሪቱ የተስተዋለውን መነቃቃት በመተማመን ሀገሩን ለማገልገል ወጣትነቱን፣ ትኩስ ጉልበቱንና እውቀቱን ይዞ ወደዚህ መስሪያ ቤት መግባቱን ገልጿል።
በተለይ የመሥሪያ ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ከተሾመች በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም ብዙ ፈጣን ለውጦችን እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን  ማስተዋወቁን የሚናገረው ወጣቱ፤ ከሃላፊዋ ስር ያሉ የፖለቲካ ሹመኞች ግን ተቋሙ የበለጠ እድገት እንዳያስመዘግብ ሙያተኞች ላይ የሚያሳድሩት ጫና ከፍተኛ ነው ይላል በምሬት። “ለሙያውና ለቴክኖሎጂው ያለኝን ቅርበትና የውጪ ተሞክሮዎችን በመጠቀም ተቋሙ የሌላው አገር ቴሌኮሙኒኬሽን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሌት ተቀን የማደርገው ጥረት ለአለቃዬ ምቾት አይሰጠውም፣ ያለው ወጣቱ፤ ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ ይህም በሀገሬ በሙያዬና በአጠቃላይ ባለው በሁኔታ መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እያስገባኝ ነው ብሏል።
ወጣቱ አክሎም፤ ቢያንስ የፖለቲካ ሹመኞች የፖለቲካ ታማኝነታቸው እንዳለ ሆኖ ለሚመሩት መስሪያ ቤትና የስራ ጠባይ ቢቻል ሙያውን የተማሩና በዘርፉ እውቀት ያላቸው፣ ካልተቻለ ተቀራራቢ ሙያ ውስጥ ያሉ ቢሆኑ አገርን ከዘርፈ ብዙ ችግር መታደግ ስለሚችል መንግስት ጉዳዩን ያስብበት ጥሪ አቅርቧል።

Read 1099 times