Saturday, 01 July 2023 00:00

ድሃ እስኪለብስ ሸንጎ ይበተናል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሰባት ወንድ ልጆች የነበሯቸው አንድ ባለፀጋ ነበሩ፡፡ ከሰባቱ ልጆች ትልቅዬው ነበር ብልህ፡፡ ለሰባቱም መሬት ገዝተው ሰጥተዋቸዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን የጨመሩላቸው ነገር የለም፡፡ ይልቁንም በየጊዜው ግብር እያስገበሩ የሩቅም የቅርብም ዘመድ- አዝማድና ጎረቤቱን ሁሉ እየጠሩ ፈንጠዝያ ያደርጉ ነበር፡፡ የቅርብ ወዳጆቻቸው፤ “ተው አይሆንም፤ ገንዘብህን የትም ለማንም አትዝራ፤ ለልጆችህ አቆይላቸው” ሲሏቸው፤
“የለም ለልጆቼ መሬት ገዝቼ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ቢያውቁ ይወቁበት፡፡ እኔ የራሴን ሀብትና ንብረት ነው ለድግስ ያዋልኩት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን የነበረኝን ወርቅ ከአንዳቸው መሬት ውስጥ ቀብሬዋለሁና አንዱ ያገኘዋል፡፡” አሉ፡፡
ሰነባብቶ አባትየው ሞቱ፡፡ ልጆቹ ለኑዛዜው ተጣደፉ፡፡ እንደ ጠበቁት ኑዛዜው ተነበበ፡፡ ኑዛዜው፡-
“ከሰባቱ ልጆቼ በአንደኛው መሬት ውስጥ ወርቅ አኑሬያለሁ፤ ከሳጥኔ ውስጥም በብራና ተፅፎ የተቀመጠ ገንዘብ አስቀምጫለሁ” ይላል፡፡
ልጆቹ ኑዛዜው ከፈሰሰ በኋላ በኑዛዜው መሰረት ሳጥኑን ከፍተው ቢያዩ አንድ የተጠቀለለ የብራና ቁራጭ አገኙ፡፡ በብራናው ላይ የሚከተለው ፅህፈት አለበት፡፡
“ራስህን ይብረደው
እግርህን ይሙቀው
ለልጆቼ ይህን አውርሻለሁ” የሚል ነው፡፡ የዚህን ፅሁፍ ፍቺ የሚያውቅ ሰው በድፍን አገር አልተገኘም፡፡ በኋላ ግን አንድ እዚህ ግባ የማይሉት ተማሪ ፍቺውን ተናገረ፡፡ በተማሪው ፍቺም መሰረት፡-
“እራስህን ይብረደው ማለት፤ በራስ የገባ ህመም ይገላል ማለት ነው፡፡
“እግርህን ይሙቀው ማለት በእግር የገባ ህመም ስንኩል ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳያጋጥምህ አድርግ ማለት ነው” ሲል ፈታው፡፡ አገሬውም አደነቀው፡፡  ልጆቹ ግን ሳጥን ውስጥ ምንም ወርቅ ባለመገኘቱ በጣም ከፋቸው፡፡
አንጋፋው ልጅ የአባቱ ብልሃት ገብቶታል፡፡
“እንግዲህ በአባታችን ቃል መሰረት መሬት እንቆፍርና አንዳችን ዘንድ የተቀበረው ገንዘብ ይገኝ ይሆናል” ተባባሉ፡፡ የሰባቱም ተቆፈረ፡፡ አንዲት እንክብል ወርቅ አልተገኘችም፡፡ ተናደዱ፡፡ ከማጣታቸው ይልቅ ድካማቸው አሳዘናቸው፡፡
“እንግዲህ እዚህ ምድር ላይ ምን ተረፈን፤ ምንስ አለን? ለቀን ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ” ተባባሉ፡፡
 አንጋፋው ወንድማቸው ግን የአባቱ ብልሃት ስለገባው እዚያው ቀረ፡፡ ሲቆፍሩ የተባበራቸው ልምሰላቸው ብሎ እንጂ ነገሩ በቁፋሮ እንደማይሆን ገብቶታል፡፡ የነገ ህይወቱ በምን እንደሚመራ በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ቆይቷል፡፡
ወንድሞቹ ሁሉ ወደ ሌላ አገር ተሰደው በየጌታው ቤት ሎሌነት አደሩ፡፡ የአባቱ ብልሃት የዘለቀው ልባሙ አንጋፋው ልጅ ግን ወንድሞቹ ቆፍረውት የሄዱት መሬት ላይ ወቅቱን ጠብቆ እህል ዘራበት፡፡ አዝመራው አማረ፡፡ በቀጠለውም አመት እንዲሁ አደረገ፡፡ ሃብት በሃብት ሆነ፡፡ አባትየው “ከምድራችሁ ወርቅ ቀብሬአለሁ” ማለታቸው ይሄ ነበር ትርጉሙ፡፡ ጉዳዩ ገብቶት ስራውን ስለሰራ የገበሬ ሁሉ ንጉስ ሆነ፡፡ ከሱ ገንዘብ የማይበደር ሰው የለምና ወሬው በየአገሩ ተስፋፋ፡፡
ወንድሞቹ በቅምጥል ስላደጉ በሄዱበት ሎሌነት መስራቱ አልሆንላቸው አለ፡፡ መከራ በመከራ ላይ ተደራረበባቸው፡፡ ስለዚህ መከሩ፡፡ “እዚህ ተቀምጠን የምንፈይደው ነገር የለም፡፡ ወደ ወንድማችን ዘንድ ሄደን እናዋየው“ ተባባሉ፡፡ ተጎሰቋቁለው፣ ከሰውነት ጎዳና ወጥተው ወደ ወንድማቸው ተመልሰው መጡ፡፡ ጨርሶ ሊለያቸው አልቻለም፡፡ ማንነታቸውን ሲነግሩት አለቀሰ፡፡ ምግብ እንዲበሉ መጠጥም እንዲጠጡ አደረገ፡፡ ወደየ መሬታቸው መልሶ እልቅናቸውን ዳግም አፀናላቸው፡፡ እድሜ ለብልሁ ወንድማቸው፣ ኮርተው ደስ ብሎአቸው ኖሩ፡፡ መከራ ቀጥቅጧቸዋልና ያለ አንዳች ዋልጌነት፣ ያለ አንዳች ዋዛ ፈዛዛ ስራ ይሰሩ ጀመር፡፡ ሰው አከበራቸው፡፡ ጎረቤት ፈራቸው፡፡ የአባታቸውም ምክር ለመላው አገሪቱ ተባዛ፡፡
***
እውነትም በራስ የገባ ብርድ ይገላል፡፡ ራስ ያጣ ህብረተሰብ መንግስት፣ ፓርቲ፣ ድርጅት ወዘተ … እንደሙት እንደበድን የሚቆጠር ነው፡፡ ከሌላው የሰውነት ክፍላችን ይልቅ ራሳችን የተራቆተ ለታ፣ ራሳችንን የበረደን ለታ፣ አለቀልን ማለት ነው፡፡ አመራር አጣን ማለት ነው፡፡ መሪ የለንም ማለት ነው፡፡ አቅጣጫ ጠቋሚ የለንም ማለት ነው፡፡ በዚሁ አይነት እግራችንን ካልሞቀንም ጅማታችን ይኮማተራል፡፡ ሰንካላና መራመድ የማንችል መሆናችን ነውና ጉዞአችን በአጭር የተቀጨ እንሆናለን፡፡ ሁሌም በራስ ከሚገባ ብርድና ሙቀት ከተለየው እግር ይሰውረን ዘንድ ሳናሰልስ ለራሳችን ቃል ልንገባ፣ መልካም ምኞት ልንመኝ ይገባል፡፡
ከአባትም መልካም አባት ቁራጭ ብራና ያወርሳል፡፡ ብራናም ቢሉ የእውነት ሰብል ሊመረትበት  የሚችል ሁነኛው አዱኛ፣ ሰፊ አዝመራ ነው፡፡ ከሀብት ይልቅ የሃብት ማግኛውን ሰረገላ ቁልፍ የሚያወርስ አባት ያሻናል፣ ይሻለናል፡፡ ምድራችን ውስጥ ወርቅ የሚቀብር፣ ለነገ እድገታችን የሚያስብ አንጋፋ ሰው ያስፈልገናል፡፡
ሁሌም ሎሌነት ከማደር፣ የሰው ፊት ከማየት፤ ያልተቀጣ ያልተቆነጠጠ ከመሆን፣ ለስደት ከመዳረግ፣ ይሰውረን፡፡ … ሁሌም ቅርስና ውርሱን የሚመረምር በራሱ የሚተማመን ትውልድ እንድናፈራ በፅናት የምንጣጣር ዜጎች መሆን አለብን፡፡
ተሳስተን ለመከራ ተዳርገን ከሆነም መክረን፣ ዘክረን፣ ተወያይተን አቅጣጫችንን የሳትንበትን ነጥብ እናይ ዘንድ፤ ቆም መለስ ብለን ታሪካችንን፣ ጉዞአችንን፣ ዱካችንን እንድናይ ልብና ልቡና ይስጠን፡፡ ወደ ኢትዮጵያዊነታችን፣ ወደ ህብረታችን መልሶ እራሳችንን እንድንመራ የሚያደርግ መሪ፣ አለቃ፣ አጋር፣ ወንድም እንዲኖረን የምንመርጠውን ሁሉ እንደ ንስር በነቃ አይን ለማየት የምንችልበት ሁኔታ ለማምጣት መጣጣር ይኖርብናል፡፡
ልብ ለልብ፣ አዕምሮ ለአዕምሮ፣ ቋንቋ ለቋንቋ የማንጠፋፋበት፤ የምንደማመጥበት፣ አዲስ  ሃሳብ የምንቀበልበት የሰለጠነ መድረክ ይፈጠር ዘንድ ጠባቡ እንዲሰፋ፣ አምባገነኑ እንዲገራ፣ ጥጋበኛው እንዲበርድለት፣ አመፀኛው እንዲገታ፣ ለእኔ ብቻ ባዩ እንዲያጋራ፣ እምቢተኛው እንዲጨምት፣ ጥፋተኛው እንዲተጋ፣ ሃሞት - የለሹ እንዲጀግን፣ ሞራለ-ቢሱ እንዲፀና መሃይሙ እንዲማር  ዘመኑን በቀና ልቦና ማየትና ዝግጁ መሆን ይገባናል፡፡
እንደ መስቀል ወፍ በአመት አንዴ የምናቅደውን እቅድ የምንመራበትን ፖሊሲ፣ የምንቀይሰውን ርእዮት ደግመን ደጋግመን የምናስተውልበት ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡
ሁሌም አምስቱን ህዋሶቻችንን በሚገባ እናንቃቸው፡፡ አይናችን በቅጡ ይይ፤ ጆሯችን በተገቢው መጠን ይከፈት ምላሳችን ሀቅ ይልመድ፡፡ አፍንጫችን መአዛ ይለይ፤ እጃችን መጨበጥ ይወቅ፡፡ ከአምስቱ ህዋሶቻችን የሚያመልጥ አንዳችም የሃገር ጉዳይ የለም፡፡ አለበለዚያ “ደሃ እስኪለብስ ሸንጎ ይበተናል” (እንዲል ወላይታ)፤ የምንይዝ የምንለቀው እንደጠፋን ዘመን እንደ ዋዛ ይነጉዳል፡፡ በራሳችን ብርድ የሚገባው ያኔ ነው፡፡

Read 2199 times