Saturday, 15 July 2023 20:37

“እንካን የማያውቅ አምጣን ማን አስተማረው!?”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በአይሁድ አፈ-ታሪክ አንድ ተረት አለ፡፡
እየተሳሰቡ አብረው የሚኖሩ አራት እንስሳት ነበሩ፡፡ እነሱም አንዲት ብልህ የጥንቸል ግልገል፤ ተኩላ፤ ዝንጀሮና የዱር ድመት ናቸው፡፡ ጥንቸሏ ገና ግልገል ትሁን እንጂ ብስል በመሆኗ ትክክለኛ አኗኗር ማለት ምን እንደሆነ ሁሌ ታስረዳቸው ነበር፡፡
አንድ ቀን ጥንቸሏ፤ “ነገ የፆም ቀን ነው፡፡ እኛ ምንም መመገብ የለብንም፡፡ በአንፃሩ ግን ለደሀ የሚበላ ነገር መመፅወት አለብን፡፡ ይህን ማድረግ ትችላላችሁ?” ስትል ጠየቀች።
ሌሎቹ ሦስቱ የሚበላ ነገር ሲፈልጉ ውለው አግኝተው መጡ፡፡ ጥንቸሏ ግን ከሳር በስተቀር ምንም ያገኘችው ምግብ አልነበረም፤ “ለማኝ ሳር አይበላም፡፡ እንግዲህ እኔ ምን ልመፀወት ነው?” ስትል አሰበች፤ ተጨነቀች፡፡ በመጨረሻ ግን፤ “በቃ ለማኝ ካጋጠመኝ ራሴን አሳልፌ እሰጠዋለሁ” ብላ ወሰነች፡፡
በድንገት የአማልክቱ ሁሉ ኃያል ነው የሚባለው የእንስሳት ፈጣሪ ወደ እሷ መጣ። ጥንቸሏ የገባችውን ቃል ሰምቷታል፡፡ ስለዚህ ሊፈትናት ፈለገ፡፡ የአማልክቶች አምላክ ነውና፣ ራሱን በፍጥነት ወደ አንድ ለማኝ ለወጠ፡፡ ከዚያም የሚበላ ነገር ይመፀውቱት ዘንድ ጠየቀ፡፡
ተኩላው፡- “ጥቂት ስጋ አግኝቻለሁ፤ እሱን ልመፅውትህ” አለው፡፡ ለማኙም አመሰግኖ፤ “ስመለስ እወስደዋለሁ” ብሎ ወደ ዝንጀሮው ሄደ፡፡ ዝንጀሮም ከዛፍ ያገኘውን ፍሬ እንደሚሰጠው ገለፀ፡፡ ለማኙም፤ “አመሰግናለሁ ቆይቼ እመለሳለሁ” ብሎ ወደ ዱር ድመት አመራ፡፡ የዱር ድመት ከጫካ ያገኘውን የአንድ የታረደ በሬ ትራፊ ሊሰጠው እንደሚችል ገለፀለት፡፡ ለማኙ ሦስቱንም አመሰገናቸው፡፡
“የሦስታችሁም ምፅዋት ይቀመጥልኝ፤ ተመልሼ መጥቼ እወስደዋለሁ” አለና ወደ ጥንቸሏ ሄደ፡፡ ጥንቸሊቱ ግን ምንም የምትመፀውተው አልነበራትም፡፡ ለድሀ እንዲመፀውቱ ስታስተምር የነበረችው ደግሞ እሷው ራሷ ናት፡፡ ስለዚህ እንዲህ አለችው፡
“ለማኝ ሆይ፣ እኔ ምንም የምመፀውተው ምግብ የለኝም፡፡ ያለኝ አማራጭ ራሴኑ አሳልፌ መስጠት ነው፡፡ እኔን ልትበላኝ ትችላለህ፡፡ እርግጥ ‘አትግደል‘ የሚል ህግ እንዳለ አውቃለሁ። ስለዚህ ልትገድለኝ አትችልምና አንድ ዘዴ ልንገርህ፡፡ እሳት አያይዝ፡፡ ከዚያ ለእኔ መመሪያ ስጠኝ። ዘልዬ እሳቱ ውስጥ እገባለሁ፡፡ በተቃጠልኩ ጊዜ የተጠበሰ ስጋዬ መልካም ምግብ ይሆንልሃል” አለችው፡፡
ለማኙም የተሸፈነ አምላክ ነውና ችሎታ ስላለው ወዲያውኑ እሳት ፈጠረ፡፡ ለጥንቸሏም “እሳቱ ተዘጋጅቷል” ሲል አስታወቃት፡፡ ጥንቸሊቱም ምናልባት ከቆዳዋ ውስጥ የተሸሸጉ ጥቃቅን ነብሳት ካሉ አብረዋት እንዳይቃጠሉ መጀመሪያ ቆዳዋን አራገፈች፡፡ ከዚያም ዘላ እሳቱ ውስጥ ጥልቅ አለች፡፡
የሚገርመው ግን እሳቱ አላቃጠላትም፡፡ ምክንያቱም ያ በለማኝ የተመሰለ አምላክ የሰራው የማያቃጥል አርቴፌሻል እሳት ስለነበረ ነው፡፡ እንዲህም አላት፤
“ጥንቸል ሆይ፤ እኔ እመገብ ዘንድ ያለሽን ሁሉ ሰጠሽኝ፡፡ ህይወትሽን ጭምር ለገስሽኝ። ከዚህ የበለጠ ምንም ስጦታ አይገኝም፡፡ ከሁሉም ያንቺ ስጦታ ትልቅ ነው፡፡ እኔ የአማልክቶች አምላክ ነኝ፡፡ ለደግነትሽ ውለታ ካሳ ይሆንሽ ዘንድ ጉልበተኛ አውሬዎችም ሆኑ ሰዎች እንዳያጠቁሽ ፈጣን-ሯጭ እንድትሆኚ አደርጋለሁ፡፡” ብሏት ተሰወረ፡፡ ጥንቸል ፈጣን-ሯጭ የሆነችው ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው ይባላል፡፡
*** ***
ቃሉን የሚያከብር ምንም ቢሆን የማታ ማታ ዋጋውን አያጣም፡፡ ቃሉን የሚያከብር መሪ፤ አለቃ፤ ኃላፊ ወይም ዜጋ ማግኘት መታደል ነው፡፡ እንደ እኛ ባለች የማህበራዊም ሆነ የፖለቲካዊ ሽግግር ውሽንፍርና ነፋስ ከአሰርት አሰርት በማይለያት አገር ውስጥ እጅግ የተለመደ ነገር ቢኖር ቃል-መግባት ነው፡፡ በየዘመኑ መሪዎች ቃል ይገባሉ፡፡ ቃሉ ካልተፈፀመ ህዝቦች ትዝብት ይፈፅማሉ፡፡ በአብዛኞቹ ቃል - የሚገቡት በመፈክር መልክ ነው፡፡ “ከምንወድደውና ከሚወደን ህዝባችን የምናስቀድመው ምንም ነገር አይኖርም።”…”የሀገር ልማትና የህዝብ እድገት ተቀዳሚ አደራችን ነው…” “እስከ መጨረሻው አንድ ሰው ድረስ እንታገላለን፡፡”… “ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናለብሳታለን!”… “ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር እናውላለን!”…”ከእንግዲህ ርሀብ፣ ድንቁርና ድህነት የምናይባት ሀገር አትኖረንም”…
…“አንድ ጥይት የማይተኮስባትና ሰላም የሰፈነባት አገር ነው ከእንግዲህ የሚኖረን…” …“በቀን ሦስቴ የምንመገብበትን ሁኔታ እንፈጥራለን”… “የአገርን ጉዳይ ለድርድር አናቀርብም…”…”ከልማት የምናስቀድመው ነገር አይኖርም…” “ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር ይሰፍናል…”።
 “ከእንግዲህ ሳናጣራ አናስርም!”፤ “ኢትዮጵያ አትፈርስም”፤ “ለልጆቻችን የበለጸገች አገር ነው የምናስረክበው” “ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን እንፈጥራለን“ ወዘተ… ቃል-መግባት፣ ቃል-መግባት፣ አሁንም ቃል መግባት፡፡ ተግባሩ የት ድረስ ነው? በተጨባጭ ምን ያህል አራመደን? ከገባነው ቃል አንፃር ወዴት እያመራን ነው? የማይጠየቁ፣ የማይመረመሩ፤ ሌላው ቀርቶ በወጉ በታሪክ መልክ እንኳ የማይፃፉ ጥያቄዎች፡፡ ተገብተው ያልተፈፀሙ ቃል-ኪዳኖች፣ የትላንቱን እንድናወግዝ እንደሚያደርጉን ሁሉ፣ እኛንም ለውግዘት ሊዳርጉን ለመጪው ዘመን እንደሚያመቻቹን ማስተዋል ይኖርብናል። አዲስ ዕቅድ ስናወጣ፣ አዳዲስ ሹማምንት ስንመርጥ፣ “የኔን ዘፈን ያዜመ የኔ አጋር ነው” ብለን መሆን የለበትም፡፡ ሰው ለውጥ ካላመጣ፤ አላማው፣ ፕሮግራሙ፤ የግምገማ ስርዓቱ አይለወጥም፡፡ ያ ለውጥ ከሌለ ደግሞ አገር ካለችበት ፈቀቅ አትልም፡፡ ግዙፍ ተስፋዎችን ተክለናል ብለን፤ ሰፋፊ ህልሞችን በሰፋፊ ማሳ ላይ ዘርተናል ብለን፤ አንዳችንም የተግባር እመርታ ካላሳየን፣ “የተማመኑበት ቢላዋ ይሰበራል” ይሆናል መጨረሻችን፡፡
ነቢብ ወገቢር እንዲሉ ቃል ከተግባር ካልተዋሃደ ወይ ማታለል፤ ወይ መደለል አሊያም የእለት ጭንቅን በጮሌነት ለማለፍ መሞከር ነው፡፡ በየስብሰባው የሚታየው የአንድ ሰሞን ውጣ ውረድና ሹም ሽር፣ የለውጥ ምልክት ሳይሆን “የፕወዛ” ፈሊጥ (reshuffling style) እንዳይሆን ከተፈለገ፣ በምወስደው እርምጃና በማደርገው ግምገማ አገር ምን ያህል ትራመዳለች፤ ምን ያህል የሰው ኃይል አጣለሁ? ምን ያህል ሀቀኛ አስተያየት ሰብስቤያለሁ… ማለት ያሻል፡፡ አለበለዚያ ስልጣንም እንደሽርክና ኩባንያ “የካዚኖ ቁማር ነው” እንዳይባል ያሰጋል። እንደ ፈረንጆቹ አባባል “who guards the guards” (ጠባቂዎቹን ራሳቸውንስ ማን ይጠብቃቸዋል?) ማለት ያባት ነው። የትላንት ገምጋሚ የዛሬ ተገምጋሚ የሚሆንበት፣ “አሳሪው ሲታሰር ታሳሪው ሲፈታ” አይነት አካሄድ ተፈጥሮአዊ  ሂደት እስኪመስል ድረስ መደጋገሙ የጤና አይደለም ብሎ ማሰብ አግባብ ነው፡፡
ከአለቆችና ከፖለቲካ መሪዎች ሙገሣን ለማግኘት ብቻ ላላመኑበት ፅላት መስገድ፣ በማያውቁት ዘፈን መደነስ፣ በማይረዱት ፅንስ-ሀሳብ ግነን በሉኝ ማለት፣ ከጊዜያዊ ጭብጨባ ባሻገር ረብ-ያለው ፍሬ እንደማይኖር ለማየት፤ ደግሞ ሌላ የዓመት መዝጊያ ሪፖርት መጠበቅ አያስፈልግም። በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ገና ከዐይነ-ውሃው ለመለየት ይቻላልና፡፡
ከቶውንም “ያሞገሷት ምራት አማቷ ፊት ራቁቷን ትጨፍራለች” የሚለውን ተረት ልብ ማለት ለአሞጋሽም ለተሞጋሽም ትልቅ ቁም ነገር አለው፡፡ ለታዛቢ ደግሞ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
ከቶውንም “ማንም በዚህ መንገድ ከመጣ ጠብ የለንም፤ ችግር የለብንም” የምንልባቸው ብዙዎች ጉዳዮች ጠብም ችግርም የሚሆኑት ውለው አድረው መሆኑን አለመርሳት ይኖርብናል። ወዲህ በቢሮክራሲው ቀይ ሽረሪት-ድር (red-tape) ሲተበተቡ፤ ወዲህም በሙስና ሲገዘገዙ ያኔ ነው ጉዱ! አንድም፣ ከምናቀልላቸው በላይ ሊወሳሰቡ እንደሚችሉ፣ አንድም ደሞ፣ ‘እኔ ፈቃጅና ሰጪ፣ አንተ ለማኝና ተቀባይ ነህ፣ የሚል ትርጓሜ ይኖረው ይሆን?’ ወደሚል መደምደሚያ እንዳያመሩ መጠንቀቅ፣ አካሄድን ማወቅ ነው፡፡
“አንዴ ካፍ የወጣን ነገር፣ ለምን አልኩት ብሎ ማለት
ለማለት ብቻ ማለት!”
የተባለውን አስታውሶ ከመናገር በፊት ልብንም ሀሳብንም ማጥራት ደግ ነው። መንግስት ከህዝብ ብዙ መጠበቁን የመናገሩን ያህል፤ ህዝብም ከዚያ ጋር ታሳቢ የሚሆነውን መብቱን፣ ነፃነቱን፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን፣ የምግብ ዋስትናውን፣ ማህበራዊ ጥበቃውን፣ የትምህርትና የስራ እድሉን፣ ከረሃብ መላቀቁን፣ የልማት መሬት ካለአድልዎ ማግኘቱን፣ በልማትና በ“ህገወጥነት“ ሰበብ ከመኖሪያው አለመፈናቀሉን፣ ወዘተ ይጠብቃል፡፡
የፓርቲ ሹማምንት በተቀያየሩ፣ የቢሮ ኃላፊዎች በተበወዙ፣ መመሪያ በተዥጎደጎደና እቅድ-ነዳፊው እንቅልፍ ባጣ ቁጥር፤ ህዝብ አዲስ መና ሊወርድልኝ ነው ማለቱ አይቀሬ ነው። እንደ ጥንቸሏ ራሱን አሳልፎ የመስጠትን ያህል ቁርጠኝነትና ተግባራዊ ልባምነት ሳይኖር፣ አዳዲስ ቃል-ኪዳንና አዳዲስ መፈክር፤ በአዳዲስ ማህደር ብናኖር፤ የህዝብን ተሳትፎና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በጠየቅን ጊዜ “እንካን የማያውቅ አምጣን ማን አስተማረው” መባል አይቀርልንም። አምጡ እንጂ እንኩ አላልንምና! በቅጡና በጊዜ መረዳት የሚገባን  አንድ ቡጥ ቁም-ነገር፣ ፈተናችን ጥንቸሏ እንደገባችበት አርቴፊሻል እሳት ዓይነት ብቻ ሳይሆን የእውነት ወላፈንም እንዳለበት ነው፡፡

Read 1814 times