Sunday, 17 September 2023 20:27

“የአሬራ ጥጋብ የሚመጣውን ክረምት ያስረሳል”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 አንድ የአይሁዶች አፈ-ታሪክ አለ፡፡
አንድ ኃይለኛ የመርሳት ችግር የነበረበት አይሁዳዊ ነበር፡፡ ከመርሳቱ ብዛት ማታ አውልቆት የተኛውን ልብስና ጫማ የት እንዳስቀመጠ እንኳ አያስታውስም፡፡ ልብስና ጫማውን ያስቀመጠበትን ቦታ ሲፈልግ ሁልጊዜ የጸሎት ሰዓቱ ይረፍድበታል፡፡ በፀሎት ቦታ የሚሰጠውን የቶራ ትምህርትም ጠዋት ተምሮ ማታ ይረሳዋል፡፡ እሱ ግን ከሌሎች ጓደኞቹ የተሻለ የተረዳው ይመስለዋል፡፡ “የእናንተን እውቀት ማነስ ምንም ላግዘው እንደማልችል ሁሉ፤ የእኔንም አዋቂነት ምንም ላደርገው አልችልም” እያለ ጉራውን ይነዛባቸዋል፡፡
አንድ ቀን ጠዋት ሲነሳ ልብሱን፣ ጫማዉንና ባርሜጣውን የት እንዳደረገው ጨርሶ ስለጠፋው ጠዋቱን በሙሉ እሱኑ ሲፈልግ ዋለ፡፡ ትምህርትም አመለጠው፡፡ በዚህ ምክንያት “ሁለተኛ እንዳልረሳ ዘዴ መፍጠር አለብኝ” ሲል አሰበ፡፡ ይህም ሁሌ ማታ ማታ ሲተኛ የትኛውን ልብሱን የት እንዳስቀመጠ፣ ባርኔጣውን፣ ጫማውን ወዘተ የት እንደሚያደርገው በወረቀት መዝግቦ ሊያስቀምጥ ወሰነ፡፡ በዚህ መሰረት “ኮቴ ከበሩ ጀርባ ነው፣ ሱሪዬ ወንበሩ ላይ ነው” እያለ ሁሉንም ዘርዝሮ መዘገበ፡፡
በመጨረሻም አልጋው ላይ ወጣና እንደቀልድ “እኔ ደሞ አልጋው ላይ ነኝ” ብሎ ፃፈና፣ ከትራሱ ስር አስቀምጦ ተኛ፡፡
ጠዋት ሲነሳ ወረቀቷን አውጥቶ በዝርዝሩ መሰረት ሁሉንም በየቦታው አገኘው፡፡ ከፃፈው ዝርዝር ውስጥ አንድ የመጨረሻ መስመር ግን አለ፤ “እኔ ደሞ አልጋው ላይ ነኝ” ይላል፡፡
አልጋው ላይ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሄዶ አየ፡፡ እሱ የለም፡፡ መኝታ ቤቱ ውስጥ በየስርቻ ሳይቀር ዞሮ አየ፡፡ ነገር ግን ራሱን ሊያገኝ አልቻለም፡፡
“እኔ ጠፍቻለሁ ማለት ነው” አለና ከቤቱ ወጥቶ ጮኸ፡፡ “ትላንት ማታ አልጋዬ ላይ መተኛቴንስ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ዛሬ ግን የለሁም!”
ይህን ሲናገር የሰሙ ጎረቤቶቹ፤ “ትክክል ነሃ፡፡ በእርግጥ አልጋህ ላይ የለህም፡፡ ምክንያቱም አንተ እዚህ ከእኛ ጋር ነው ያለኸው፡፡” አሉና ሳቁበት፡፡
“የምለው አልገባችሁም ማለት ነው፡፡ በዝርዝሬ ላይ’ኮ ተጽፌያለሁ” አለና ወረቀቷን አውጥቶ አሳያቸው፡፡
“ጅል አትሁን አንተ ሰው፡፡ አጉል ጭንቀት ውስጥም አትግባ፡፡ ይልቅ ወደ ቤትህ ግባ” አለው አንደኛው ጎረቤቱ፡፡
“ራሴን ሳላገኝማ ወደቤቴ ልገባ አልችልም”
“እያየንህ፣ እያዋራንህ እንዴት ጠፍቻለሁ ትላለህ? መኖርህን እያየን’ኮ ነው” አሉት ሁሉም፡፡ እሱ ግን ሊሰማቸው ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
በመጨረሻም አንድ ሰውዬ በጣም ተቆጥቶ፤ “አንተ ደደብ ሰውዬ፤ እዚህ መሆንህንና አለመሆንህን አሁኑኑ አረጋግጥልሀለሁ፡፡” ብሎ በመጥረጊያ ይቆነድደው ጀመር፡፡
“ኧረ በጣም አሳመምከኝ ጎበዝ!” ሲል ጮኸ፡፡
“አሁን ይሰማሀል፤ አይደል?” ሲል ጠየቀው፡፡
“በጣም ይሰማኛል እንጂ”
“የሚያምህ እዚሁ በመሆንህ ነው፡፡ የመታሁትም አንተን በመሆኑ ነው፡፡ አንተኑ ራስህኑ፡፡ አንተ እንዳልከው ግን ጠፍተህ ቢሆን ኖሮ ህመሙ ሊሰማህ አይችልም ነበር፡፡ አይደለም እንዴ?”
 “እውነትህን ነው፡፡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እንዴት እንዳደረግኸው ባላውቅም እራሴን እንዳገኝ አድርገኸኛል፡፡ ምናልባት እኔ የተሻልኩ ሰው አልሆን ይሆናል፡፡” ሲል ራሱን ዝቅ ማድረግ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ የማስታወስ ችሎታውም እየተመለሰለት መጣ፡፡
***
ሁሉን ነገር የማውቅ እኔ ነኝ፤ ከማንም ሰው እኔ እሻላለሁ፤ የማለት አባዜ ክፉ እርግማን ነው፡፡ ክፉ መገበዝ ነው፡፡ የማታ ማታ ራስን ጭምር ወደ ማጣት ያመራል፡፡ ራስን ለመፈለግ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ጊዜ ከረፈደና ከመሸ በኋላ እራስን ማግኘት ዘበት ይሆናል፡፡ ይህንን መገንዘብ የጉዳዮች ሁሉ ቁልፍ ነው፡፡ ወረቀት በያዘው፣ አዋጅ በደነገገው፣ ፖሊሲ በቀረፀው፣ የትውስታ መዝገብ ቢደረደር፣ ቢገመገም ዋናው ራስ የጠፋ እስኪመስል ድረስ የግራ - መጋባትና የመወነባበድ ጣጣ ውስጥ መግባት አይቀሬ ይሆናል። ትላንት ያሉትን እንዳላሉ መሟገት፣ ትላንት ያመኑበትን በጭራሽ ዛሬ አላውቀውም ብሎ መሸምጠጥ ቀድሞውኑ ራስን ከመገበዝ የሚመነጩ ህፀፆች ናቸው፡፡ ራስን ዋርካ አሳክሎ ማየት መጨረሻው ጉቶ ማከልን መረዳት ይሆናል፡፡ ይህም የታደለና ልቡናውን የሰጠው ሰው ከተገኘ ነው፡፡ እንዲያመው እየተደረገ መኖሩን እንዲያውቅ የሚገደድ ራሱ የጠፋበት ኃላፊ፣ ባለሥልጣን ወይም መሪ ለሀገርና ለህዝብ ችግር እንጂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ወደዚህ አሰቃቂ ሂደት መድረስም ባንድ ስር እንደተንጠለጠለ ዛፍ የሰቀቀን አፋፍ ላይ መንጠልጠል ይሆናል፡፡
“አድረህ እይ፣ አሳድረህም እይ” እንዲሉ አስቀድሞ ታላቅነትን ከመለፈፍ ይልቅ የራስን ሚዛን ለማወቅ የሚረዳው ለራስ ጊዜ መስጠት ነው፡፡  መብሰል አለመብሰልን በጥሞና መለካት ነው፡፡ የ”አሜን ባይ” መብዛት የትክክልነት ማረጋገጫ አለመሆኑን ማጤን ነው፡፡ እኔ ያወጣሁት መርህ ትክክል ነውና ተቀበል ከማለት በፊት አንተስ ምን ይመስልሃል? ብሎ ለሌላው ሀሳብ እድል መስጠት ብልህነት ነው፡፡ ምናልባት ንጋት ላይ የቀናን መስሎ የታየን ነገር ረፋዱ ላይ ወይ ማምሻው ላይ መለወጥ አለመለወጡን በሚገባ አስተውሎ “ለአንድ ወቅት የሰጠሁት መፍትሄ መልካም ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ዘዴ ለዚህኛው ወቅት ላይሆን ይችላል” ብሎ መጠራጠር ያባት ነው፡፡ የትላንት ጣዕም ዛሬ ቃናው መለወጥ አለመለወጡን ማጣራት እጅግ ወሳኝነት አለው፡፡ “ነብር ሲያረጅ አነር ይወልዳል” ይሏልና ከሀሳብ ማርጀት፣ ከፖሊሲ ማርጀት፣ ከፕሮግራም መጣረስ ጋር የሚመጡትን ከሁኔታዎች ጋር የማይጣጣሙ እምነቶች አላየሁም አልሰማሁም ብሎ የዱሮውን ሃሳብ እኝኝ ብሎ መያዝ ተገቢ አይደለም፡፡ አገርና ዓለም ተቀበለውም አልተቀበለውም እኔ ያሰብኩት ጋ ካልደረስኩ ፍሬን አልይዝም - አንዳች የሚያቆመኝ ኃይልም ሊኖር አይችልም ብሎ ግትርነትን ማወጅ፣ ካፈርኩ አይመልሰኝ እንጂ ሌላ ፍሬ የምናፈራበት መላ አይደለም፡፡
የተመኘነው፤ ያለምነው ያቀድነውና የተለምነው ሁሉ ሙሉ በሙሉ ላይሳካ ይችላል ከሚለው እሳቤ ጀምሮ ከመሰረቱስ ሙሉ በሙሉ ስህተት ቢሆን እስከ ማለት ድረስ ለማሰላሰል ዝግጁና ደፋር መሆን ተገቢ ነው፡፡ ያማረውና የተሳካው ሁሉ የእኔ ድካም ፍሬ፣ የተሳሳተውና የተበላሸው ሁሉ የጠላቴ ሴራ ውጤት፤ ብሎ መፈረጅ የኋላ ኋላ ራሱ እንደጠፋበት ሰው መደነጋገርንና በአደባባይ “ራሴን አፋልጉኝ” ማለትን ያስከትላል፡፡
ከቶውንም የሌሎችን ድካም ለራስ ማድረግ ከአንድ ጀንበር በላይ ሊሸሸግ የሚችል ነገር አይደለም። “ያላረባ ልኳንዳ አራጅ ዐይን የሆነውን ብልት ይበላል” እንደሚባለው በሌሎች ጥናት መኩራራት፤ በሌሎች ሪፖርት ላይ ፈርሞ ብቻ መመስገን፤ በሌሎች ጫንቃ የተሰራን ስራ የእኔ ነው ማለት፤ ለሥራም፤ ለእድገትም፣ ለራስም ደግ አይደለም፡፡ አድሮ ያጋልጣልና!
በሲቪል ሰርቪስ መርሆዎች መሻሻል ብቻ መልካም አስተዳደር አይመጣም፡፡ ሰው ይፈልጋል፡፡ መርሆዎችን ከልቡ ሊተገብር የቆመ ሰው ይፈልጋል፡፡ ፍትሕ ርትዕ የሰፈነባት አገርን የሚያመላክት በርካታ አቅጣጫ ሊነደፍ ይችላል፡፡ ግን የወረቀት ስራ ብቻ ነው፡፡ ሰው ይፈልጋል፡፡ በትላንቱ አባያ በሬ አዲስ መሬት ልረስብህ ቢሉት ትርፉ ጅራፍ ማጮህ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ወደ ባህልነት ሊቀየር አንድ ሀሙስ የቀረው ሙሰኝነት ምንም ያህል የጠበቁ አናቅጽትና ህግጋት ቢጠቀሱለት፤ ተግባራዊ ትርጓሜ የሚሰጣቸው እጁን የታጠበና ልቡን ያፀዳ ሰው ብቻ ነው፡፡
አለበለዚያ “የወረት ውሻ ስሟ ትደነቂያለሽ ነው” ከሚባለው ፈሊጥ የዘለለ ነገር አይገኝም፡፡ በእርግጥም በተጎሰመው ነጋሪት፣ በተላለፈው አዋጅ፣ በብራና በተከተበው ህግና መመሪያ ጥናቱን ያስጠናውን ክፍል ለማስደሰት ይቻላል፡፡ ተግባሩ ግን ከፍተኛ የሰው ኃይልና ልባዊ ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲኖር የማድረግን ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ተልዕኮ ነው፡፡ የሃገራችን የዘወትር ህመም፤ ያማረ እቅድና እንከን - አልባ የተባለ የወረቀት ስራ በተነደፈ ቁጥር፤ የተፃፈው ሊቀደድ እንደሚችል የታቀደው ሽባ ሆኖ ሊቀር እንደሚችል ዘንግቶ፣ ከአፍ አፍ እየተቀባበሉ በየመዋቅሩ አሸንዳ የድል ብስራት መለፈፍ፣ ነገ ያለአንዳች ተግባር በነባቤ - ቃልነት ብቻ ሊቀር እንደሚችልና ለከፋ ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችል አለመገንዘብና ተዘናግቶ ማዘናጋት ነው፡፡ “የአሬራ ጥጋብ የሚመጣውን ክረምት ያስረሳል” እንደሚባለው መሆኑ ነው!



Read 1332 times