Saturday, 23 June 2012 07:04

የታክሲ ላይ ድራማ

Written by  ምግባር ተካ
Rate this item
(3 votes)

“መጨረሻ እሰጦታለሁ” ብሎ ሳይሰጠኝ በመቅረቡ በጣም ተናደድኩ፡፡ “ምን ዓይነቱ ገብጋባና ቋጣሪ ነህ? ለ20 ሳንቲም ብለህ ትንጨረጨራለህ?” አላችሁኝ? አዎ! እንዳላችሁት ይሁንላችቸሁ - ገብጋባ፣ ቋጣሪ፣ …ነኝ፡፡

በቅርቡ ነው - 12 ቀን ገደማ፡፡ በካዛንቺስ የታክሲ ረዳቶች “በአቋራጭ በአዲሱ በሲግናል መገናኛ” እያሉ በሚጠሩት መንገድ ወደ ሰፈሬ እየሄድኩ ነበር፡፡ ልማድ ሆኖብኝ ምግብ ቤትም ሆነ ታክሲ ላይ አስቀድሞ መክፈል እወዳለሁ፡ ከየት አመጣሁት መሰላችሁ? “ሂሳብ በቅድሚያ” ከሚሉ አገልግሎት ሰጪዎች፡፡ ታዲያ ያንን ለምጄ በቅድሚያ ካልከፈልኩ፣ ዕዳ ያለብኝ ያህል ይሰማኛል፡፡

አስቀድሞ መክፈል ጥቅም አለው፡ ታክሲው አገልግሎት እየሰጠኝ ነው፡፡ ለተጠቀምኩበት አገልግሎት ደግሞ ተገቢውን ሂሳብ መክፈል ግዴታዬም ነው፡፡ ታዲያ ረዳቱ፤ “እዚህ ጋ፣ እዚያ ጥግ፣ …” ወይም ጋቢና ከሆንኩም ትከሻዬን እየነካ “ሂሳብ” እስኪለኝ መጠበቅ የለብኝም - አስቀድሜ እከፍላለሁ፡፡

ታክሲ ላይ፣ ሂሳብ ሳይጠየቁ መክፈል ሥልጣኔ ነው - መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ኅብረተሰብ ተግባር፡፡ ረዳቱ “ሂሳብ” እያለ ሲጠይቅ ምን እያለ እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላችሁ? “እናንተ መብታችሁን እንጂ ግዴታችሁን የማታውቁ ሰዎች! ለሰጠኋችሁ አገልግሎት ሂሳቤን ስጡኝ …” እያለ ነው፡ የእናንተን አላውቅም እንጂ እኔ የምረዳው እንደዚያ ነው፡፡

አንዳንዱ ታዲያ ካልጐተጐቱት ሂሳብ አይከፍልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኔ እየከፈልኩ እያየ ከጐኔ የተቀመጠ ሰው በግል እስኪጠየቅ ድረስ መጠበቅ ግርም ይለኛል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ “ሂሳብ” ሲባል ምላሽ አይሰጥም፡ በሐሳብ የተዋጠ ወይም ቃሉ የተሰነዘረው ለእሱ እንዳልሆነ በመምሰል ዝም ይላል፡፡ ልጅ በድጋሚ አበክሮ ሲጠይቅ የባነነ በመምሰል “እኔን ነው እንዴ የምትለው?” በማለት ይጠይቃል - መክፈል ግዴታው ያልሆነ ይመስል፡፡

አንድ ቀን ያየሁትን ላጫውታችሁ፡ ሰውዬው አለባበሱ ያማረ፤ ጥሩ ሥራና ገቢ ያለው የተማረና ሥልጣኔ የገባው፤ … ይመስላል፡፡

የተቀመጠው መጨረሻ ካሉት ወንበሮች ፊት ባለው ረድፍ ጥግ ነው፡፡ ረዳቱ ልጅ ከሁሉም ተሳፋሪ ሂሳብ ተቀብሎ እሱ ብቻ ስለቀረ፤ “ሂሳብ” በማለት ጠየቀው፡፡ ሰውዬውም “እኔን ነው?” አለ፡፡ ልጁም “አዎ!” ሂሳብ ስጡኝ ሲል መለሰ፡፡ ሰውዬው እርጋታ በተሞላው አነጋገር ጀነን ብሎ “አብረን አይደል እንዴ የምንሄደው? ምን አስቸኮለህ?” በማለት ጠየቀው፡፡ ልጁም፤ “እርስዎ ብቻ ነው የቀሩት” አለው፡፡

“እሺ! ሂሳብ ስንት ነው?” አለው፡፡ ነገረው፡፡ አሁንም ፍፁም እርጋታ በተሞላው አነጋገር “ውይ! ለዚች ነው እንዴ?” ብሎ ሰጠው፡፡ መክፈል እንዳለበት እያወቀ እንዲህ ዓይነት ንትርክ ውስጥ መግባት ምን አመጣው?

አንድ ቀን ያስተዋልኩት ደግም ለየት ያለ ነው፡፡ ጊዜው ሩቅ ቢሆንም ከታክሲ ትዝብቶቼ አንዱ ነው፡፡ ከሾፌሩ ጐን የተቀመጠው ደልደል ያለ ሰው፤ በንዴት ጦፎና ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ የስድብና የእርግማኑን መዓት ያወርዳል፡፡ ትኩረቴ ወደ ሌላ ስለነበርና ምን እንደተፈጠረ ስላላወቅሁ፣ ከጐኔ የተቀመጠችውን ሴት “ምን ተፈጠረ?” አልኳት፡፡ “ዝም ብሎ ነው ባክህ፡፡ ረዳቱ ትከሻውን ነክቶ ሂሳብ ስላለው ነው” አለችኝ፡ የሰውዬው ሁኔታ ያልተለመደ ስለነበር፤ ሁሉም ሰው በአንክሮ ያዳምጠው ነበር፡ “…እኔ ለራሴ ትከሻዬን ሲነኩኝ አልወድም - አመል አለብኝ፡፡ ዝም ብሎ ሂሳቡን አምጣ አይለኝም እንዴ? …” እያለ ስድቡን ቀጠለ፡፡ ይታያችሁ ልጁ፤ ሰውዬው አመል እንዳለበት አያውቅም፡፡ ሌላም ጊዜ እንደሚያደርገው ትከሻውን ነክቶ ጠየቀው፡፡ ምኑ ላይ ነው የልጁ ጥፋት፡፡ አስቀድሞ ከፍሎ ቢሆን ኖሮ ችግሩ አይፈጠርም ነበር፡፡

ሌሎችም አሉ፡፡ በተለይ ሦስት፣ አራት፣ … ወጣቶች ከሆኑ፣ ሌላው ተሳፋሪ ሲከፍል፣ እነሱ የባጥ የቆጡን እየቀደዱ መሳቅ ነው፡ ረዳቱ፤ “ሂሳብ” ሲላቸው አይሰሙትም፡ ድምፁን ከፍ አድርጐ “ሂሳብ” ሲላቸው አንዱ “ቀስ በል አንተ! ምን ያስጮህሃል? ቀስ ብለን ስንወርድ ይከፈልሃል” ይላል፡፡ የተቀሩት ሐሳቡን ደግፈው አንዳንድ ቃል ከወረወሩ በኋላ ሳቃቸውን ይለቃሉ፡፡ እዚህ ላይ ሁሉንም ተሳፋሪ፣ ሁሉንም ወጣት እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ እንዲያውም በጣም ጥሩ በሆነ ሥነ ምግባር ወደ ቦርሳና ኪሳቸው የሚገቡ በጣም በርካቶች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ቀን የሰማሁትን ልንገራችሁ፡፡

ረዳቱ፣ ሂሳብ ሰብስቦ ሳይጨርስ፣ መስኮት ከፍቶ መጥራት ጀመረ፡፡ ታክሲው ጉዞ ሲጀምር ልጁ ወደ ሂሳብ መሰብሰቡ ሳይመለስ ቀረ፡፡ በዚህ ጊዜ በ20ዎቹ መጨረሻ የሚገመት ወጣት ጠርቶት “እንካ ሂሳብ” አለው፡፡ ረዳቱ ዝም ብሎ የቆመው ከሁሉም ተሳፋሪ የተቀበለ መስሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ወጣቱ በታማኝነት ጠርቶ ስለሰጠው “ምናለ ሁሉም እንዳንተ ሳይጠየቅ በከፈለ!”

አይ የእኔ ነገር! የጀመርኩላችሁን ሳልነግራችሁ ወደ ሌላ ችግር ገባሁ አይደል! ይቅርታ! አሁን ልጨርስላችሁ፡፡ የዚያን ዕለት ከሾፌሩ ጐን ነበር የተቀመጥኩት፡፡ አስቀድሞ የመክፈል “አባዜ” አለብኝ ብያችሁ የለ? ትንሽ ሜትሮች እንደተጓዝን 3 ብር ሰጥቼው መልስ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ከጐኔ የነበረውም ወጣት፣ እኔ ስሰጥ አይቶ ከብዙ ብሮች መካከል አምስት ብር አውጥቶ ሰጠው - ሳይጠየቅ፡ ረዳቱ ወዲያውኑ 2 ብር ሰጥቶት ኋላ ከተቀመጡት ለመሰብሰብ ዞረ፡፡

20 ሳንቲም መልስ ነበረኝ፡፡ ሳንቲም ስለሌለው ይሆናል፤ ከሁሉም ሰብስቦ ሲያበቃ ይሰጠኛል በማለት ጠበቅሁ፡፡ ልጁ ግን እኔንም ከጐኔ የነበረውን ወጣትም ዝም አለን፡፡ ልጠይቅ ብዬ ምን አስቸኮለኝ? ብዬ ችላ አልኩኝ፡፡ መውረጃዬ ሲቃረብ “መልስ አለኝ፤ መውረጃዬ ደርሷል” አልኩት፡፡ “ፋዘር፤ ሳንቲም ስለሌለኝ ነው፤ ሲወርዱ እሰጦታለሁ” ብሎ አረጋጋኝ፡፡ መውረጃችን ስንደርስ እኔም ወጣቱም መልሳችንን ሳንቀበል ወረድን፡፡ መልሴን ሳልቀበል መውረዴ ትዝ ያለኝ ሌላ ታክሲ ውስጥ ገብቼ ሂሳብ ለመክፈል ስዘጋጅ ነው፡፡

ታዳያ፤ “መጨረሻ እሰጦታለሁ” ብሎ ሳይሰጠኝ በመቅረቡ በጣም ተናደድኩ፡ “ምን ዓይነቱ ገብጋባና ቋጣሪ ነህ? ለ20 ሳንቲም ብለህ ትንጨረጨራለህ?” አላችሁኝ? አዎ! እንዳላችሁት ይሁንላችሁ - ገብጋባ፣ ቋጣሪ፣ …ነኝ፡፡ ቆዩ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፡፡ በዘንድሮ የኑሮ ውድነት 20 ሳንቲም ቀላል ነው እንዴ? 4 ጊዜ 20 ተጠራቅሞ’ኮ ነው 80 የሚሆነው፡ እውነቱን ለመናገር የተናደድኩት በሳንቲሙ አይደለም፤ “መጨረሻ ስንደርስ መንዝሬ እሰጦታለሁ” ብሎ ስላታለለኝ ነው፡፡ እኔን በጣም ያሳሰበኝና ብዕሬን እንዳነሳ የገፋፋኝ ግን ኅብረተሰባችን ወዴት እየሄደ ነው? የሚለው ነው፡፡

እኔ በታክሲ ረዳቶች ስታለል የበቀደሙ የመጀመሪያ አይደለም - ብዙ ጊዜ ተታልያለሁ፡፡ በቅርብም ሆነ ራቅ ባለው ጊዜ ብዙ ተጭበርብሬአለሁ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ጋቢና ተቀምጬ 10 እና 50 ብር ሰጥቼ መልስ ሳልቀበል ወርጃለሁ፡፡ ጋቢና ተቀምጣችሁ ወደ ኋላ 10፣50፣ … ብር አትስጡ - እንደእኔ ልትረሱ ትችላላችሁ፡፡ ከሁሉም አንድ የማልረሳው ትዝታ አለኝ፡፡ ድሮ ነው - የታክሲ ዋጋ ከአንድ ብር በታች በነበረበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ የራሴን ሂሳብ ከፍዬ መልስ አልተቀበልኩም፡፡ አንዲት ሴት ወርዳ፣ ረዳቱን “መልሴን ስጠኝ” ትለዋለች፡፡ ልጁ ሳንቲም አልነበረውም፤ በጣም ተጨነቀ፡፡ “እባካችሁ ሳንቲም ካላችሁ ተባበሩኝ” እያለ ተማፀነ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የልጁን ጭንቀት አይተው ወደ ኪሳቸው ገቡ፡፡ እኔ ቀድሜ 60 ሳንቲም ሰጠሁት፡፡ አሟልቶ ሰጣትና ሴትዮዋ ሄደች፡፡ እኔም መውረጃዬ ሲደርስ፣ መልሴንና ያበደርኩትን 60 ሳንቲም ሳልቀበል ወረድኩ፤ ልጁም አስታውሶ አልሰጠኝም፡፡ ያ ድርጊት እስከ ዛሬ ይቆጨኛል - መልስ ባለመቀበሌ ሳይሆን ቸግሮት ያበደርኩትን ሳንቲም ሳይሰጠኝ በመሄዱ፡፡

የታክሲ ረዳቶች ብዙ ጊዜ ዱርዬ፣ አታላዮች፣  ጨካኝ፣ ለተሳፋሪ ግድ የሌላቸውና የሚያንጓጥጡ፣ … ተደርገው ቢገለፁም፤ ከዚህ በተቃራኒው ጨዋ፣ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ሰው አክባሪ፤ … የሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ 5፣10፣20፣25፣ … ሳንቲም ጐድሎ ሲሰጣቸው፣ ሳያቅማሙ ይቀበላሉ፡፡ በተለይ ክፍያን በተመለከተ እውነቱን ከነገሯቸው ጣጣ የላቸውም፤ በነፃ ሁሉ ያሳፍራሉ፡፡ መልስ ሳይቀበል ዕቃ ረስቶ፣ … የሚወርድ ካለ፤ አስታውሰውና ጠርተው የሚሰጡ በርካቶች መሆናቸውን እመሰክራለሁ፡፡

ሌላው የታክሲ ድራማ እኔና ጓደኛዬ “የኢትዮጵያ ክፋት” የምንለው ነው፡፡ በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት አለ፡፡ ታዲያ ብዙ ሰው ተሰብስቦ ትራንስፖርት ሲጠብቅ አንድ ታክሲ ብትመጣ፤ ሰው የሚራኮተው፣ የሚንገላታው፣ የሚጐዳው ወድቆ የሚቆስለው፣ ኪስና ቦርሳው የሌላ ሲሳይ የሚሆነው፣ … በሰዓቱ ሥራ ለመግባት ወይም ወደ ቤቱ ለመሄድ ሳይሆን ክፋት ነው፡፡

እንዴት ለክፋት ነው ትላለህ? ምን ዓይነቱ ጨካኝ ብትሆን ነው በደግነትና በሩህሩህነቱ የሚታወቀውን ኢትዮጵያዊ “ክፉ ነው” የምትለው? ሊባል ይችላል፡፡ ለቃሉ አጠቃቀም አማራጭ ስላጣሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በተግባር የሚታየው ግን እንደዚያ ስለሆነብኝ ነው፡፡

ከሚጋፉት ሰዎች መካከል ጠንካራ ሆኖ ወይም ዕድል ቀንቶት ወደ ታክሲ የገባ ሰው የሚያስደስተው ትራንስፖርት ማግኘቱ ሳይሆን ሌላውን ገፈታትሮ መቅደሙ ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን አንድ ተሳፋሪ ተንደርድሮ እንደገባ፣ ጥግ ያለው ወንበር ላይ መቀመጥ ሲገባው፣ ከወዲህ ያለው ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ ወደ ኋላ ተንጋሎ ወደ ጐን ተጣምሞ “ቅርብ ነው የምወርደው” እያለ፣ ሌሎች ከኋላ ያለውን ወንበር እንዳይዙ መንገድ ይዘጋል፡፡ ይኼ የሚካድ ነው?

ረፋድ ላይም ሆነ ከሰዓት በኋላ ታክሲዎች ተሳፋሪ አጥተው በጥሪ ጉሮሮአቸው ሲደርቅ፣ ታክሲው ባዶ ሆኖ ቀድሞ የገባ ሰው ድርጊትም ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዛኛው ተሳፋሪ ጫፍ ላይ ይቀመጥና ሌላ ሰው ሲመጣ፣ ወደ ኋላ ተንጋሎና ተጣምሞ “እለፍ” ይላል፡፡ ይኼ ውሸት ነው?

እዚህ ላይ “ልክ አይደለህም፤ first come, first serve” ነው፤ (ቀድሞ የመጣ ቀድሞ የመምረጥ ወይም የመጠቀም ዕድል አለው እንደማለት ነው) የሚል የነጮች አባባል አለ ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ መሠረተ ሐሳቡን እቀበላለሁ፡፡ እኔ እንደገባኝ አባባሉ ቀድሞ የመጣ የተሻለውን ምቹና ጠቃሚ ነገር መምረጥ ይችላል ማለት ይመስለኛል፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡ ታክሲ አቀማመጥን ያየን እንደሆነ መጀመሪያ ገብቶ የጠርዙን መቀመጫ የያዘው ሰው ያለበትን ሁኔታ በአይነ-ኅሊና እናስተውል፡፡ ወደ ኋላ ተንጋሎና ተጣምሞ “እለፍ” ይላል፡፡ መተላለፊያው ጠባብ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ሁለት እግር እንደ ልብ ማሳለፍ አይችልም፡፡ እለፍ የተባለው የተቀመጠውን ሰው እግር እየታከከ፣ ጫማ እየረገጠ፣ … እየተደናቀፈ ያልፋል፡፡

ታዲያ ይኼ ምኑ ነው ምቾት? መጣመሙ? ወደ ኋላ መንጋለሉ? መጨናነቁ? መጣበቡ? … እኔ እንዲህ ዓይነት ምቾት አይገባኝም፡፡ ይልቅስ እንደገባ ጥግ ካለው ወንበር ላይ ቢቀመጥ አንዳች እንግልት ሳይደርስበት ካሰበበት ይደርሳል ነው የምለው፡፡ ይኼ ችግር “ክፋት” እንጂ ከምን መጣ?

ሌላው ሰበብ በጥግ በኩል ከተቀመጥኩ ፀሐይ ያገኘኛል የሚል ነው፡፡ በእርግጥ በየዋህነት ከታየ አባባሉ እውነት ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የ”ክፋቱ” ድርጊት፣ በክረምትና ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በምሽትም አይቆምም፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ “ቅርብ ነው የምወርደው” የሚለው ነው፡፡ ልብ በሉ! እንዲያ ሲል የሰማችሁት ሰው፤ እየተጣመመ ሰው ሲያስገባና ሲያስወጣ ታያላችሁ፡፡ ቀድሞ የተቀመጠው፤ ሌላው የት እንደሚወርድ አውቆ ነው “ቅርብ ነው የምወርደው” የሚለው? ይኼን ክፋት እንጂ ምን ትሉታላችሁ?

ሞቅ ያለ ጨዋታ የያዙ ጓደኛማቾች፤ ባዶ ታክሲ ውስጥ ቢገቡ ጐን ለጐን አይቀመጡም፡፡ አንድ መደዳ ባሉ ሁለት ወንበሮች ጐን ለጐን አይቀመጡም፡፡ በሁለት መደዳ ባሉ ሁለት የጠርዝ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ሌላ ተሳፋሪ ሲመጣ እንደተለመደው ተጣምመው “እለፍ” ይላሉ፡፡ ኋላና ፊት ተጣምሞ ከማውራት ጐን ለጐን ተቀምጦ መጫወት አይሻልም? መልሱን ለእናንተ ትቻለሁ፡፡

በአንድ ወቅት ከጓደኛዬ ጋር ከሳሪስ ስንመጣ የታዘብነውን ለጫውታችሁ፡፡ ታክሲዋ ልትሞላ አንድ ሰው ብቻ ነው የሚጐድላት፡፡ ሾፌሩ እዚያው ነበር መሙላት የፈለገው፡፡ እኛ “ኧረ ረፈደብን አንድ ሰው ነው የቀረህ ንዳው እንጂ፡- … እያልን ስለተነጫነጭንበት ሞተሩን አስነስቶ ጉዞ ጀመርን፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ አንድ ወፍራም ዘንካታ ሴት ምልክት አሳይተው አስቆሙ፡፡ በ30ዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ ጐልማሳ፣ ጠርዙ ወንበር ላይ ተቀምጦ ስለነበር እንደተለመደው ተጣሞና ተንጋሎ “እለፉ” አላቸው፡፡

ታዲያ እኒያ ወፍራም አዛውንት እንዴት ሆነው ይለፉ? ጭንቅ ሆነ፡፡ “እሺ!” ብለው አፍንጫውን አንዳች በሚያህለው መቀመጫቸውን እየታከኩ ትግል ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ምንም ያህል መንቀሳቀስ አልቻሉም፡ ይኼኔ፤ “ኧረ አፈኑኝ’ኮ” እያለ ጮኸ፡ እሳቸውም ጭንቀቱ ተሰምቷቸው “ምን ላድርግ ልጄ? ወድጄ መለሰህ? ቸግሮኝ ነው” አሉት፡፡ እኔና ጓደኛዬ ተያይተን ፈገግታ ተለዋወጥን፡፡

ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩ ተሳፋሪዎችም በጐልማሳው ድርጊት ደስተኛ እንዳልሆኑ ያስታውቃል፡፡ አንዱ “እንዲህ ከመሆን ቀድሞውኑ ምን ነበረበት ጠጋ ብለህ ብታስቀምጣቸው ኖሮ?” አለ፡፡ ሌላም ድምፅ ተከተለ፡፡ “አሁንም በምንም ዓይነት መንገድ ማለፍ አይችሉም፡፡ ምናለ ተነስተህ ብታሳልፋቸው?” አለ፡፡ ያን ጊዜ እንደምንም ብሎ በተጣመመበት በኩል ቁና እየተነፈሰ ተንሸራቶ ከወንበር ሲወርድ፣ እሳቸውም አልፈው ተቀመጡና ጉዞው ቀጠለ፡፡ ታዲያ ይህን የመሰለውን ድርጊት ምን ትሉታላችሁ? ደግነት? እኔ ግን “የሐበሻ ክፋት” ከማለት በስተቀር ምንም ትርጉም አላገኘሁበትም፡፡

ይህ ተግባር የሚፈፀመው ልጅ፣ ወጣት፣ ጐልማሳ፣ አረጋዊ፣ ሴት፣ ወንድ ሳይባል በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ እኔ በተለይ የዚህ የወገብ መጣመም አስግቶኛል፡፡ እነዚህ የተሠራንባቸውን ጂኖች አሉ አይደል… ሳይንቲስቶች አዳብቴሽን የተባለ ዘዴ የማንጠቀምባቸውን ትተው የምንጠቀምበት መንገድ እንደሚላመዱ ይነግሩናል፡፡ ስለዚህ ወደፊት ታክሲ ተጠቃሚዎች ሽንጠ ጠማማ ልጅ ሊወልዱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ፡፡

ሌላው የታክሲና አውቶቡስ ላይ ድራማ ምንዛሪ ነው፡፡ አንዱ ደረቱን ነፍቶ መቶ ብር አውጥቶ ይሰጣል፡፡ የታክሲው ረዳት ፊቱን ቅጭም አድርጐ “ኧረ የለንም ይፈልጉ” ይላል፡፡ ባለ መቶ ብሩም መልሶ “ፈልግ እንጂ! እኔ ከየት አመጣለሁ? ስለሌለኝ አይደል እንዴ እሱን የሰጠሁህ?” ይላል፡፡ ልጁም “ምንም አልሠራሁም፤ ገና ከጋራዥ መውጣቴ ነው” ይላል፡፡ ባለ ብሩም “ፈልግ ፈልግ መመንዘር’ኮ ሥራህ ነው፡፡ እኔ ከየት አመጣለሁ? የለኝም ብያለሁ” ይላል፡፡ ከተሳፋሪው መኻል ዝርዝር ያለው፣ “አትጣሉ እኔ እመነዝርላችኋለሁ” ይልና ያለመግባባቱን ያበርዳል፡፡

ለነገሩ እኛ’ኮ ነን ዝርዝር ይዘን መሳፈር ያለብን፡ ለምን መሰላችሁ? ታክሲ የማጓጓዝ እንጂ እንደ ባንክ የምንዛሪ አገልግሎት መስጠት አይጠበቅበትም፡፡ ለምሳሌ ከተሳፋሪው አብዛኛው ወይም ግማሹ መቶ ብር ቢሰጥ ረዳቱ ለዚያ ሁሉ ሰው ምንዛሪ ከየት ያመጣል? ሊኖረው አይችልም፡፡ ትናንት የሠራውስ? እንዳይባል ያንንማ ለባለንብረቱ አስረክቧል፤ የለውም፡፡ ስለዚህ እኛ ነን ዝርዝር ብሮችና ሳንቲም ማዘጋጀት ያለብን፡፡ ድሮ አንድ ባለ ላዳ ታክሲ ሾፌር ያለኝ ነገር አይረሳኝም፡ “ቅድም ባንክ ቤት ገብቼ 50 ብር መነዘርኩ፡ አራት ሰዎች አስር፣ አስር ብር ሠጡኝና መለስኩላቸው፡ አሁን የተሳፈራችሁት አስር አስር ብር ብትሰጡኝ ከየት አመጣለሁ? እንደዚያ ከሆነማ ባንክ ቤት ሆንኩ ማለት ነው” ያለው ትዝ ይለኛል፡፡ እኔ በባስም እሄዳለሁ፤ እንዳገኘሁት ነው የምሳፈረው፡ አንድ ቀን በአውቶቡስ ተሳፍሬ አንድ ሰው መቶ  ብር ሰጥቶ “ትኬት ቁረጪልኝ” አለ “ዝርዝር የለኝም” ስትል ነገረችው፡ “ሥራሽ አይደለም?” እኔ ልፈልግልሽ ነው እንዴ?” በማለት በስድብ ይሞልጫት ገባ፡፡ በዚህ ጊዜ አጠገቤ የነበረ ሰው “በውጭ አገር’ኮ አውቶቡስ የምትሳፈረው ቅንስናሽ ብሮችና ሳንቲሞች ይዘህ ነው፡፡ እዚያ ቲኬት የሚቆርጥልህ ሰው የለም - ራስህ ነህ የምትቆርጠው፡፡ ስለዚህ ቅንስናሽ ሳንቲሞችና ብሮች መያዝ አለብህ፡፡ እኛ መች ይሆን የምንሠለጥነው?” አለ፡፡ እኔም የሰውዬውን ሐሳብ ስለምጋራ፣ በታክሲም ሆነ በአውቶቡስ ስንሳፈር ዝርዝር ብሮችና ሳንቲም ብንይዝ የሥልጣኔ ምልክት ነው እላለሁ፡፡

ሌላው ችግራችን ምን መሰላችሁ? በድህነት ስለሾቅን ይመስለኛል፡፡ መጨናነቅ እንወዳለን፡፡ አንድ ነገር ስናደርግ ካልተገፋፋንና ካልተጨናነቅን በስተቀር የሚሆን አይመስለንም - በዳቦው፣ በዘይቱ፣ በስንዴው፣ … በሁሉም ሰልፍና ግፊያ ለምደናላ!  አንድ አውቶቡስ 30-40 ሰዎች ማስቀመጥ ይችላል፡፡ አውቶቡስ ሲመጣ ከ5 ወይም 10 የማይበልጡ ሰዎች ለመግባት ሲሽቀዳደሙ አይታችሁ አታውቁም? ካላጋጠማችሁ ለማየት ሞክሩ፡፡ በነገራችን ላይ ሰሞኑን ሜክሲኮ አካባቢ ያየሁት ነገር ደስ ብሎኛል፡፡ ቡናና ሻይ ልማት ጽ/ቤት ፊት-ለፊት ታክሲዎች ይቆማሉ፡፡ ታዲያ ሰሞኑን የቦሌ ታክሲዎች እጥረት አለ፡፡ ስለዚህ ጧት ጧት በርካታ ሰው ታክሲ ጥበቃ ይንገላታል፡፡ 10 እና 15 ደቂቃ ታክሲ ሲጠብቅ የቆየ ሰው እያለ፣ አንድ ታክሲ ስትመጣ ገና እቦታው የደረሰ ወጣት በጉልበት ተጋፍቶ ይገባል፡፡ ጉልበት የሌላቸው አቅመ ደካሞች፣ ልጆች፣ አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡሮች ቆሞ መዋል ነው፡፡ ታዲያ የአካባቢው ተራ አስከባሪዎች ምን አደረጉ መሰላችሁ? ሰውን እንደ አመጣጡ ያሰልፋሉ፡፡ ከዚያም አንድ ታክሲ ስትመጣ 12 ሰው ቆጥረው ተሳፈሩ ይላሉ፡፡ የቀሩት ደግሞ እንደ ተሰለፉ ሌላ ታክሲ ይጠብቃሉ፡፡ ወደ ሰልፍ መመለሳችን ባይደገፍም ጊዜያዊ መፍትሄነቱ አይነቀፍም፡፡ ዘላቂው መፍትሄ ግን ይሄ አይደለም - በቂ ሚኒባስ ማቅረብ ነው!

 

 

Read 9897 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 11:21