ድንገት ድምፁን በሙሉ ማን አጠፋው? ዛሬ ምን ተገኘና ከተማው አንድ ላይ እረጭ አለ? ትላንት ልጽፍ ነው ብዬ ስቀመጥ…አለሙ አንድ ላይ ተነስቶ ሲጮህብኝ አልነበር? እነዛ ዘመናቸው ሳይደርስ በእኔ ትውልድ ላይ ተለጥፈው የተወለዱ ህፃናት እሪ እያሉ ቤቴን ሲዞሩት… ጐረቤቴ ያለው ሰው በፆም ሆዱ በፍስክ ምኞቱ እየጮኸ ሲያደነቁረኝ አልነበረም…ዛሬ ታዲያ ሁለተኛ አልፅፍም ብዬ ምዬ፣ ብዕሬን በድራፍት ውጬ ከሰፈሬ በጣም ርቄ በተቀመጥኩበት--- ጭጭታው ከየት መጣ?
ድምፁ እንደተቀነሰ ቴሌቪዥን ከተማው ያለ ድምጽ ከፊቴ ይንቀሳቀሳል፡፡ ችኩልነቱን በስክነት የቀየረው በደንብ እንዳስተውለውና እንድፅፈው ነው አይደል? የፈለገ ብታምርም አልጽፍህም፡፡ ትላንት ሳባብልህ አሻፈረኝ ብለኸኛል፡፡ ሳሰላስል አናቴ ላይ ባዶ ሙቀጫ አስቀምጠህ ወቅጠህብኛል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ቢያምርብህም፣ ሰክነህ መፃፍ ብትሻም እኔ አልተባበርህም፡፡
አድባሪቷ ዛሬ መጥታለች፡፡ እና ምን ላድርግልሽ? ትላንት ስጠብቅሽ፣ ብዕሬን በሰም ወልውዬ ልቦናዬን ለሩቅ ምናኔ መትሬ፣ ጥሞናን ስሻ ጠፍተሽ፣ ዛሬ ለጩኸት የክት ረብሸኛነቴን ለብሼ ብወጣ ጭጭ ብለሽ መጣሽብኝ። ዛሬ ለጠብ ዝግጁ ነኝ፡፡ ለመናደድ ነው ቀጠሮ የያዝኩት፡፡ የትላንቱ ቀን እስቲ ወንድ ዛሬ ይምጣ!...
እየው…እዛ ማዶ አንዱ መዶሻ ይቃጣና የተቃጣበትን ሚስማር ይዶሸዋል፡፡ ግን ድምጽ እንዲያወጣ በሃይል ይቃጣና ሚስማሩ አናት ጋር ሲቀርብ ቀስ ብሎ ያሳርፋል። ደግሞ ቀና ይልና እኔን ያየኛል፡፡ በአይኑ ያባብለኛል። የፈለገ ብትለሳለስ አልጽፍህም! አለቀ… ይልቅስ አንተኛው ድራፍት ድገመኝ፡፡ አዎ አስተናጋጁ እንዲሰማ ጠረጴዛውን በደንብ አድርጌ እነርተዋለሁ፡፡ የብርጭቆው እጀታ እስኪረግፍ፡፡
ለምንድነው ይኼ ጠረጴዛ እንደ እስፖንጅ ስደልቀው ትሙክ የሚለው፡፡ አራት ድራፍት ነው የጠጣኸው ሲለኝ (በጆሮዬ ተጠግቶ በሹክሹክታ)…እኔ እየጮሁኩ ሁለት ነው ብዬ ክርክር መፍጠር ፈልጌአለሁ፡፡ አበሳ የሚያመጣ ክርክር፡፡ ብርጭቆ አወራውሮ የሚያፈናክት አይነት ክርክር፡፡
ለምንድነው የጠጣሁትን ቀንሼ ስከራከረው “ይሁንልህ” ብሎ ሸብረክ ከማለት ባላነሰ ተስማምቶ የሚሄደው፡፡ ቀስ ብዬ ብርጭቆውን ገፍቼ መሬቱ ላይ ብጥለው ፀጥታው ይበጠበጣል፡፡ ፀጥታውን ለማጥፋት ስል የብርጭቆውን ዋጋ ተደብድቤ ብከፍል ይቀለኛል፡፡ እልህ ይዞኛል፤ ትላንት እንደ በጠበጡኝ… ዛሬ በተራቸው ጩኸትን መቅመስ አለባቸው፡፡
አድባሪቷ መጥታ ከእኔ ጋር ተቀምጣለች። እንደማላውቃት ያላየሁዋት ብመስልም አይቻታለሁ። ውበቷን አሰማምራ፣ መቶ አምፖሏን አብርታ ነው የመጣችው፡፡ መጽሐፍ፣ ወረቀት እና ውድ እስኪርብቶ ገዝታልኝ መጥታለች። እየተቁለጨለጨች አይን አይኔን ታየኛለች፡፡ የለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ባቷን ያሳያል፡፡ በጣም ለመፃፍ የሚያጓጓ ባት ነው፡፡ እየፃፍኩ ብገልበው ውስጥ ሱሪዋን አገኘዋለሁ፡፡ እየፃፍኩ ባወልቀው በጣም የሚያረካ ድርሰት ሆና ነው የመጣችው፡፡ ግን የፈለገ ቢዮንሴን ብትመስል ዛሬ አልጽፋትም። ሌላ ፀሐፊ ጋ ትሂድ፡፡ ግን አሳምሬ አውቃለሁ፤ የኔይቱ አድባር ሌላ ማንም ጋ መሄድ እንደማትችል። ወይንስ ትችላለች?! ትላንት የት ነበር የሄደችው? ማንን ተኝታ ነው የመጣችው፡፡
ድንገት ቅናት በልቤ ውስጥ ተደመረ፡፡ የመስቀል ደመራ፡፡ ግን ደመራው ፀጥ ያለ ነው። እሳት ይንቀለቀላል እንጂ ድምጽ አያወጣም!...ለዚህች ቀልቃላ አድባር… በቅናት ነዶ መንቀልቀል አያስፈልግም፡፡ “ለምን እንደሄድሽ አልቀረሽም? የሄድሽው ደራሲ እንደምትፈልጊው አላደረገሽም? ነካክቶ ተወሽ?” አልኳት፡፡ ግን ምላሴ ላይ ዘይት ማን እንደቀባኝ አላውቅም፤ ቃላቶቼ እያሟለጩ ትርጉም ሳይሰጡ ተዝረክርከው ቀሩ፡፡
“እ” አለችኝ እግሯን ፈትታ እያጣመረች፡፡ ፈትታ ስታስረው በብልጭታ የውስጥ ሱሪዋ ቀለም ይታየኛል። በጥቁር ከሰል ላይ በደንብ የተርገበገበ ቀይ ፍም ያየሁ መሰለኝ፡፡ ሰክሬአለሁ መሰለኝ፤ የአንደበቴ መቋጠሪያው ላልቷል፡፡ የፊኛዬ መቋጠሪያ ግን በደንብ ይሰራል፡፡ ፊኛዬ ተወጥሯል፡፡ ግን ዛሬ አልጽፍም ብያለሁ፡፡ መቋጠሪያዬ ይሰራል፡፡ ዛሬም ነገም አልጽፍም፡፡ እሷም ሌላ ዘንድ ትሂድ…
እኔም ራሴን መግዛት በቅጡ ልልመድበት። እንደው በጥበብ ፍቅር ስም በሷ ገላ ላይ ሰርክ የማልሰለች ኮርማ ሆኜ አርፌአለሁ፡፡ ከተማው እኔ ለእሷ ላለኝ ፍቅር ብሎ ፀጥ ቢልም እኔ ግን እሷን አልጽፍም፡፡ ወረቀት ላይ እሷን በመተኛት እድሜዬን አባከንኩ፡፡ እሷም ወይ ልጅ አልወለደች እንዲሁ ወረቀት እና ቀለም ማልፋት ብቻ፡፡
መጋባት እና ልጅ መውለድ ወይንም መለያየት። ይሄው ነው መፍትሔው፡፡ አንድ ቀን ጩኸት ሌላ ቀን ፀጥታ እያፈራረቁ ግራ መጋባት ከእንግዲህ አይሰራም። በአፌ ከምናገረው ይበልጥ የማስበውን ማድመጥ ትችላለች አድባርዬ አድባሪቱ፡፡ እግሯን መከፋፈት ትታ ቀሚሷን ወደ ታች እየሳበች ረዥም ቀሚስ አደረገችው፡፡ ኩርምት ብላ ማሰብ ያዘች፡፡
“እኔን ካገባህ እድሜ ልክ ፀጥታ እና ጥሞናን ታገኛለህ፡፡ ግን እድሜ ልክህን ደሀ ነው የምትሆነው…ይሄንን አውቀህ ከተቀበልክ መጋባት እንችላለን” አለችኝ፡፡
በፊት በጣም እርግጠኛ ነበርኩ - እቺን ሴት ማግባት ስለመፈለጌ፡፡ አሁን ግን ድንገት ጥርጣሬ ገባኝ፡፡ ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ፤ ግን ከማታስተማምን አድባር ጋር ተጋብቼ፣ በአንድ ሴት መወሰን መቻሌን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
“ላስብበት” አልኳት፡፡
ቀጠሮ ሰጥታኝ መጽሐፍቷን እና መፃፊያ ቁሳቁሷን ይዛ ወጣች፡፡ ስትወጣ ቅር አለኝ፡፡ ቀደም ብዬ በእልህ የዋጥኩት እስክሪብቶም ደረቴን እየፋቀ ቃር ለቀቀብኝ። እሷ ስትወጣ ድንገት ከተማው ዛሬ መሆኑ ቀርቶ ትላንት ሆነ፡፡ ፀጥታው በጫጫታ ተተካ፡፡ እንደ እያሪኮ በጩኸት ፈረሰ፡፡ የብርጭቆዎቹ ኳኳታ ጆሮዬን ሰብረው ገቡ። ብርጭቆዎች መዶሻ ሆኑ፡፡ ወሬዎች እንደሚስማር የሰውን ብቸኝነት ከቡድን ወሬዎች ጋር ወስደው መስፋት ጀመሩ፡፡ ድምፆች ሲጐሉ የእኔ ድምጽ ደግሞ ውጪውን ፈርቶ አልወጣም አለ፡፡ ብርጭቆውን በቀስታ ማንሳት ጀመርኩ፡፡ የራሴ ልብ ምት መሸሸጊያ አሳጣኝ፡፡ ከሰፈሬ በጣም ብርቅም ጐረቤቶቼ የሚወቅጡት ሙቀጫ ጐልቶ የተቀመጥኩበት ቦታ ድረስ እየጮኸ መጣ፡፡
አድባሪቱ ከመሄዷ በፊት ላስቆማት ወጣሁኝ። ጠረኗን ተከትዬ፣ የዱካዋን ፊደሎች አሽትቼ፣ ቆማ ገላዋን ለአላፊ አግዳሚ ወደምታስጐበኝበት የመንገድ መብራት ስደርስ ዋጋ እየተደራደረች አገኘሁዋት፡፡ ሌላ ፀጥታን ፈላጊ አባብሎ ሊወስዳት ነው፡፡ ገና አጠገቧ ከመድረሴ…አካባቢውን በውበት ሞልታዋለች፡፡ የመንገዱን መብራት ጨረቃ አድርጋዋለች፡፡ አስፋልቱ አረንጓዴ መስክ መስሏል። የማስታወቂያ ሰሌዳ ቋሚዎቹ እንደ ሰንበሌጥ ይወዛወዛሉ፡፡
ልታስተምረኝ የፈለገችው ነገር ገባኝ፡፡ ያለ እሷ መኖር አልችልም፡፡ ከሁለታችን ኩርፊያ ጉዳቱ የሚያደላው በእኔ ላይ ነው፡፡ ሊቀድመኝ ከሚያባብልብኝ ሰው እጅ አስጥዬ አቀፍኳት፡፡ ብዙም አልተግደረደረችም፡፡ ተሳመችልኝ። ተመልሶ ፀጥታ በአለም ላይ ሰፈነ፡፡ ወደ ቤቴ…እና ቤታችን ከንፋስ በቸኮለ አከናነፍ ደረስን፡፡
አልጋውን ጠረጴዛ አድርጌ አዘጋጀሁት፡፡ አንሶላውን በወረቀት ለወጥኩኝ፡፡ እንደማትጠገብ አድርጌ.. ቶሎ እንዳታልቅ… ሌሊቱን አክላ እንድትቆይ አድርጌ ቀስ በቀስ እየገለጽኩ እስኪነጋ ስፅፋት አደርኩኝ፡፡
Saturday, 04 July 2015 10:51
እንደ እያሪኮ
Written by ሌሊሣ ግርማ
Published in
ጥበብ