Saturday, 04 July 2015 10:49

ወሲብ እና የወሲብ አብዮቱ ጣጣዎች

Written by  ጤርጢዮስ- ከቫቲካን
Rate this item
(44 votes)

    መረን የወጣ የፍትወት ልማድና አፈንጋጭ ወሲባዊ ልምምድ እጅግ የቆየ የማህበረሰብ ልማድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሶዶማውያን የቀለጡበት፣ ጥንታውያኑ ግሪኮች የኖሩበት፣ ለሮማውያኑም ውድቀት እንደ ምክንያት ተደርጎ የሚዘከርለት ነው። የፍቅር ግንኙነት አካል ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በበጎም ሆነ በመጥፎ ጎኑ እንደ ፍትወት/ወሲብ የተነገረለት የለም። ይህንኑ በሚመስል ርዕሰ ጉዳይ ላይ አንድ የአገራችን ምሁር “አውሬ ያለ ጫካ አይኖርም!” እንዳሉትም ከገንዘብና ከሥልጣን ጥማት በትይዩ የብዙ አውሬነቶች መፈልፈያው ጫካ በሰው ልጅ የፍትወት ፍላጎት ውስጥ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በማህበረሰባችን ዘንድ ስለ ወሲብ መነጋገር ማለት በአመዛኙ ስለ “ባለጌ ነገር” እንደማውራት ይቆጠራል፡፡ ሆኖም ገና ከአፍላነት እድሜ አንስቶ ወሲብን በቀልድና በጫወታ መካከል ጣል የሚያደርግ ሰው ሲገኝ ጆሮ መስጠትና ነቅቶ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡
   የጋብቻና የሥነ ወሲብ አማካሪው ቲም ላሃዬ፤ “በጊዜያችን ወሲብ ከፍቅር ሙሉ በሙሉ ተነጥሏል፣ ከፍ ተደርጓልም፣ ወሲብ ከፍቅር በፊት መምጣቱ የተለመደ ሆኗል” ይላሉ፡፡ “አንድ ግንኙነት የሚጀምረው ወይም የሚቋጨው በወሲብ ነው” የሚሉት ቲም ላሃዬ፤ “ወሲብ ልክ እንደ ቴኒስ ጨዋታ ከአንድ ከሚያውቁት ሰው ጋር የሚፈፀም ሆኗል፤ከፍቅር ይልቅ አፅንኦት የሚሰጠው ለወሲብ ነው፡፡ እንዴት ‹ጥሩ› ሆኖ እንደተፈጸመና አስደሳችነቱ የሚለካው በእርካታው መጠን ነው” የሚሉት ላሃዬ፤ ወሲብ የፍቅር ግንኙነት አካል እንጂ ብቻውን ተነጥሎ የሚመነዘር ርካሽ ነገር ያለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ “ወሲብ መልካምና አስደሳች የሚሆነው ግልፅነት፣ መተማመን፣ ጓደኝነትና ፍቅር ሲኖር ብቻ ነው፤አርኪ ወሲብ ምን አይነት እንደሆነ የሚያውቁ ሰዎች የብልቶች መገናኘትና ከእርካታ ጫፍ መድረስ ብቻቸውን በቂ እንዳልሆኑ ይገነዘባሉ” ይላሉ፡፡
በሰለጠኑት አገሮች ጤናማው የወሲብ መረዳት ምን መምሰል እንዳለበት የሚመክሩ ብዙ መፅሐፍት  ተፅፈዋል፡፡ በዚህች በእኛዋም አገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሞከሩ ያሉና ይበል የሚያሰኙ ሥራዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ዕድሉን አግኝቼ  በተካፈልኩባቸው አንድ፣ሦስት ያህል አውደ ጥናቶች ላይ ስለ ጉዳዩ የተደረጉ ውይይቶችን ባደመጥኩበት ጊዜም ‹‹ለካስ ወሲብ ብልግና የሚሆነው ባለጌ ሰው ሲያወራው ነው›› አሰኝተውኛል፡፡ ከነዚያ መካካል አንዱን ብጠቅስ ከጥቂት ዓመታት በፊት “የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ተማሪዎች ህብረት” (ኢቫሱ)፤ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ ተማሪዎች አዘጋጅቶት በነበረው አውደ ጥናት ላይ ታድሜ ነበር፡፡ እጅግ የሚገርሙና በስታቲስቲክስ የተደገፉ መረጃዎችን ያደመጥኩትም እዚያው ነው፡፡
በወቅቱ የወጣቶቹ የአፍላ ዘመን ግፊቶች ይበልጡኑ እንዲጋጋል አስተዋጽኦ ካላቸው የመገናኛ አውታሮች የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ማህበራዊው ድረ-ገፅ ስለመሆኑ በአውደ ጥናቱ ላይ ሲነገር አድምጬያለሁ። በዚህና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በእውቀትና በእምነት ላይ የተመሠረቱ ሰፊና ጥልቅ ትንተናዎች ሲሰጡ ሰምቼ ብርቱ መደመም ውስጥ ገብቼም ነበር፡፡ በበቀደም ዕለታው የኦባማና የምክር ቤታቸው የውሳኔ አዋጅ መደንገጥ የሚገባኝን ያህል ያልደነገጥኩትም ነገሮች ወዴት እያመሩ እንዳሉ የሚያመላክቱ ብዙ መረጃዎች ቀደም ብለውም መሬቱ ላይ ስለነበሩ ነው፡፡ ውሳኔው በእውነት ላይ ማላገጥ ቢሆንም መልካም አቀባበል እንድናደርግለት ግን ቀደም ብሎ ጭንቅላታችን ላይ አዚሙ ሲደረግ ቆይቷል! አንዳንድ የአውሮፓና የአሜሪካ ቤተ ክርስቲያናት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ተቀብለው በመድረኮቻቸው ላይ ማጋባትና ቡራኬ ሰጥተው መሸኘት ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ በእነዚህ አገሮች የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን መንቀፍ የሰውን ሰብዓዊ መብት በመንካት ወንጀል የሚያስከስስ ከሆነም ቆይቷል፡፡
 እናም በዚያ የወሲብ ጣጣዎችና መፍትሔዎቹ ላይ ለመምከር ታድሞ ለነበረው ጉባኤ፤ “ወሲባዊ ተፈጥሮን መረዳት” በሚል ርዕስ ንግግር ያደረጉት አቶ ንጉሴ ቡልቻ፣ ቀደም ብለው በቀውሱ ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ከገቡበት ፈተና ለማውጣት መኬድ ስላለበት መንገድ ሲያወሱ፤  “የወሲብ ሃሳብ ገና ከጨቅላነት ዕድሜ አንስቶ የሚጀምር በመሆኑ ጉዳዩ የማይመለክተው ሰው የለም” ካሉ በኋላ ይልቁንም ካለፉት 40 ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ በተቀሰቀሰው የወሲብ አብዮት ምክንያት ብዙዎች ነጋ ጠባ ይህንኑ ብቻ እያውጠነጠኑ ውለው እንዲያድሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ይኸው አብዮት መቀጣጠሉን ባለማቆሙ ወጣቶቻችን ነገሩ ካመጣባቸው ወጥመድና የጎንዮሽ ጠንቆቹ ይላቀቁ ዘንድ ብዙ ምክር፣ከብዙ ፍቅር ጋር ሊለገሳቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ “ወጣቶቻችን ልቦና ውስጥ ለሚፈጠሩ ወሲብ ተኮር ጥያቄዎች ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በቅጡ ለመምከር እንደህ ዓይነቱ ፕሮግራም መዘጋጀቱ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው” ያሉት አቶ ንጉሴ፤አንድ/አንዲት ወጣት አእምሮ ውስጥ “ከጋብቻ በፊት ወሲብ ብፈጽምስ?”፣ “ከተመሳሳይ ጾታዬ ጋር የወሲብ ፍላጎት ቢያድርብኝስ?”፣ “ሳልፈልገው የመጣብኝን ጽንስ ባስወጣውስ?”፣ “ስለ ወሲብ የተጻፉ ጽሁፎችን ለማንብብ ብገፋፋስ”፣”ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችንና ፊልሞችን የመመልከት ፍላጎት ቢያድርብኝስ?” ለሚሉና የመሳሳሰሉት ጥያቄዎች በዋናነት መለኮታዊ ምላሾቻቸውን ማቅረብ የሚገባም ቢሆን እነዚህን ለመሳሰሉት የወጣቶች ግርታን የተሞሉ ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜ በእውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ፍቅር፣ ርህራሄና ብልሃት ያልተለየው አቀራራብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡  
ብልህ መካሪ አያሳጣን!
በአገራችን “መካሪ አያሣጣህ!” የሚል የምርቃት ቃል አለ፡፡ እነሆ ከላይ በተዘረዘረው መልኩ መልካም መካሪና ዘካሪ የሚያገኙ ወጣቶችም ዕድለኞች ናቸው። በወጣትነት ዘመን ላይ ከሚከሰተው ጠንካራ የወሲብ ፍላጎትና የአቻ ግፊት ባሻገር በዚህ ዘመን ላሉ ወጣቶችና ታዳጊዎች ብርቱ ፈተና የሆነው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው መስፋፋትና እኩዩም ሆነ ሰናይ መረጃዎች በቀላሉ የመገኘታቸው ጉዳይ ነው፡፡  የብዙዎች አፍላ ወጣቶቻችን አካላዊ ስሜት ገደቡን ጥሶ ወደ ተሳሳተ ተግባር እንዲገቡ እያደረገ ያለውም በዚሁ ቴክኖሎጂ በኩል እየሾለኩ የሚመጡት የተሳሳቱ መረጃዎች ናቸው። ዛሬ ላይ የብዙ ወጣቶችና ታዳጊ ልጆች መካሪና ዘካሪዎችም እነዚሁ ናቸው፡፡ በተለይም በዚህ ቴክኖሎጂ አንድ ፈርጅ ውስጥ ተፈጥሯዊ ግፊቶቻቸውን በቀላልና ርካሽ በሆነ መንገድ እንዲያሰክኑት የሚያበረታቱ ትምህርቶችን የሚያገኙባቸው ብዙ ሀዲዶች ተዘርግተውላቸዋል፡፡ የአፍላነት ዘመን ፍላጎቶቻቸውን ግለት ተግነው ግዳያቸውን ሊጥሉ ባደቡ ብዙ አዳኞችም ተከብበዋል፡፡    
የዛሬ አምስት ወይም ስድስት ዓመት ገደማ አሁን በህትመት ላይ የሌለችው የ”አዲስ ነገር” ጸሃፊ አህመድ ሰልማን፤ ምስል ከሳች በሆነው ግሩም አጻጻፉ “የታዳጊዎቹ ኢሮዬቲክ ፓርቲ” በሚል ርዕስ ይዞት የወጣው ዘገባ በወቅቱ ብዙ ወላጆችን ያስደነገጠና ያሸማቀቀ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ሁሉን ቃል በቃል ላሰፍረው ባልችልም ከብዙ በጥቂቱ ግን የሚከተለውን ይመስላል፡፡ 12ኛን ክፍል ማጠናቀቃቸውን ምክንያት ያደረጉ አዲስ አበባ የሚገኘው “ናዝሬት ትምህርት ቤት” ታዳጊ ሴት ተማሪዎች ቦሌ መዲሃኒዓለም አካባቢ በሚገኝ አንድ “ላውንጅ” ውስጥ ፓርቲ አዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህ ታዳጊ ሴት ልጆች በፓርቲያቸው ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ያደረጉላቸው ወንድ ታዳጊዎች ደግሞ “ቅዱስ ዮሴፍ” እና “ካቴድራል” በመባል በሚታወቁት ሁለት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ እኩያዎቻቸው ናቸው፡፡
የጋዜጣው ዘጋቢ በሥፍራው ተገኝቶ እንደተመለከተው፣ አብዛኞቹ ልጃገረዶች የለበሷቸው ልብሶች ሰውነታቸውን አጋልጠው የሚያሳዩ፣ ለብሰውም “ራቁታቸውን” እንደሆኑ እንዲሰማን የሚያደርጉ ስለመሆናቸው ይገልጻል፡፡ ሆቴሉ ደጃፍ ላይ ቆመው ለክብር እንግዶቻቸው የ”እንኳን ደህና መጣችሁ” አቀባበል የሚያደርጉት ጥቂት ታዳጊ ቆነጃጅት እድሜያቸውን በማይመጥኑ አልባሳት ተሸላልመው የመጡ ወንድ እንግዶቻቸውን ወደ ውስጥ የሚሸኟቸው ከንፈሮቻቸውን እየሣሙ መሆኑም ፈጽሞ ያልተለመደና ዕንግዳ ነገር ነበር፡፡ እንደ ጋዜጣው ዘጋቢው እማኝነት ከሆነ፣ አንድ ታዳጊ ወንድ ወደ ውስጥ ከመዝለቁ በፊት በአማካኝ የሦስት ልጃገረዶችን ከንፈር የመሣም ዕድል ነበረው፡፡
እነሆ ፓርቲው እየተጋለለ በሄደ ሰዓት ታዳጊዎቹ ደስታቸውን በዳንስ፣ ሲጋራ በማጨስና አልኮል በመጎንጨት የሚያጣጥሙት ከመሆኑ አልፎ በየጥጋጥጉ ይካሄዱ የነበሩት ትእይንቶች ዘጋቢውን “የት ነው ያለሁት?” የሚያሰኙ ነበሩ፡፡ ዘግየት ብሎም በዚያ “ጫካ” ውስጥ በእነዚያ ታዳጊዎች መካከል ይኖራል ብሎ ያልገመተውን ሌላም ነገር ተመልክቷል። ይኸውም ልዩ ክፍያ በሚጠይቀው የላውንጁ ሌላኛ ጓዳ ውስጥ ለዚያው ተግባር ተብሎ መድረኩ መሃል በተተከለ ምሰሶ ላይ ራቁቷን እየሾረችና የተለያዩ ወሲብ ቀስቃሽ እንቅስቃሴዎችን እያሳየች የታዳጊዎቹን አቅል የምታስት ሴትም ተዘጋጅታ ነበር፡፡ እንግዲህ፣ እንዲህ ባለው የአፍላነት እድሜ በዚህ ዓይነቱ ልምምድ ውስጥ ለመገኘት ትምህርቱ የተቀሰመበት ቦታና ሁኔታ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ለእነዚህ ታዳጊዎች ድርጊት መነሻ የሆኑ መረጃዎች በአመዛኙ የሚገኙትም ፖርኖግራፊክ (ወሲብ ቀስቃሽ) የሆኑ መልእክቶችን በያዙ ድረ-ገጾች፣ መጽሔቶችና ፊልሞች መሆኑም አጠያያቂ አይደለም፡፡
በዚህ ዘመን ከትልልቆቹ ባልተናነሰ ሁኔታ ትንንሾቹም ልጆች ገብተው የሚጠፉበት ጥቅጥቁ ጫካ ፖርኖግራፊ መሆኑ ከታወቀ ሰነባብቷል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነኝ ሁለተኛው ማሳያዬም ምናልባት ከሁለት ዓመት በፊት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በመታሰቢያ ካሳዬ ተጽፎ ያነበብኩት የሁለት ታዳጊ ወንድም እና እህት ታሪክ ነው፡፡ የእነዚህ ታዳጊ ልጆች ወላጆች በሥራ የተጠመዱና አብዛኛውን ጊዜ ቤታቸው የማይገኙ ባተሌዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ልጆቻቸው ሰርክ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እንጂ ሌላ ነገር የማያውቁ ጨዋዎች አድርገው ነው የሚቆጥሯቸው፡፡ በሌላም በኩል አደራ በሰጧት የቤት ሠራተኛቸው ላይ እምነታቸውን ጥለው በዚያም እረፍት ሲሰማቸው ቆይቷል፡፡ ከዕለታቱ በአንደኛው ቀን የተፈጠረው አስደንጋጭ ክስተት ግን ነገር ዓለሙን ሁሉ አደበላለቀው፡፡
ከክስተቱ በኋላ የቤት ሠራተኛዋ ለፖሊስ በሠጠችው ቃል፣ ልጆቹ ሁልጊዜም ቤት በሚውሉበት ወቅት አቅራቢያቸው ከሚገኝ ቪዲዮ ቤት እየተከራዩ የሚያመጧቸው ፊልሞች እንደነበሩ ገልጻ፣ፊልሞቹ ጤናማ ያልሆኑ ትዕይንቶችን የያዙ መሆናቸውን ግን በጭራሽ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡ ያቺ ምስኪን የቤት ሠራተኛ ሁሉም ነገር የተገለጠላት ከዕለታቱ በአንደኛው ቀን ከዚህ ቀደም ሰምታው የማታውቀውን የጩኸት ድምፅ ሰምታ ልጆቹ ወደነበሩበት ክፍል በገባችበት ሰዓትና የወንዱን ልጅ የተራቆተ ሰውነት፣ መርበትበትና ድንጋጤ  ከሴቷም ልጅ የመራቢያ አካል አካባቢ የሚፈሠውን ደም ባየችበት ቅጽበት ነው፡፡ ያኔም የድረሱልኝ እሪታዋን ታቀልጠዋለች፡፡ የልጆቹ የኋላ ታሪክ ከተጠና በኋላ ዘግይታ የሰማችው ሀቅ ለካስ እነዚያ የአደራ ልጆቿ በፀጥታ ተውጠው ሲኮመኩሙ የሚውሉት የወሲብ ፊልም ኖሯል፡፡ ያን ዕለትም ቢሆን  ድንገት እህትና ወንድም መሆናቸውን አስረስቶ በዚያ አይነቱ ፈተና ውስጥ እንዲወድቁ የገፋፋቸው እሱው ነበር፡፡
ሌላም የባሰ ነገር በማህበረሰባችን ውስጥ ሰፍኗል!
ዳንኤል ክብረት ሰኔ 2005 ዓ.ም ላይ በወጣው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት፤ “ወላጆች፡-ሁለት ጉዳዮች አሉኝ” በሚል ርዕስ ያሰፈረው ጽሁፍ ሌላም የባሰ ነገር በማህበረሰባችን ውስጥ እየሰፈነ መምጣቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ “ባለፈው ሰሞን አንዲት እናት ወደ ቢሮዬ መጥተው እንዲህ አወጉኝ፡፡” የሚለን ዳንኤል ክብረት፤ተጠቃሽዋ እናት የነገሩትን እንዲህ ይተርክልናል፡- “ልጄ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅና የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የማይበት ጠባይ ግራ የሚያጋባኝ እየሆነ ተቸግሬ ነበር፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ የእኔን ሽቱ ይቀባል፡፡ እኔም ይሄን ሳይ የልጅ ነገር አድርጌ ትቼው ነበር፡፡ በኋላ ግን ከሌላው ነገር ጋር ሲደመርብኝ ነው ግራ የተጋባሁት፡፡ ፀጉሩን እንደ ሴቶች ማስተኛት ይፈልጋል፡፡ ጥብቅ ያለ ሱሪ ካልገዛሺልኝ ይለኛል፡፡ አንድ ቀን ትምህርት ቤት አድርሼው መኪናዬን አዙሬ ልመለስ ስል ከኋላ ያለውን መኪና እንዳልነካው ዞር አልኩ፡፡ ያን ጊዜ ያየሁትን ነገር ዓይኔ ሊያምን አልቻለም፡፡ ከሌላ አንድ ወንድ ልጅ ጋር ከንፈር ለከንፈር ሲሳሳሙ አየኋቸው፡፡ ከኋላ የነበረው መኪና በጡሩምባ እየጮኸብኝ እንኳ የማየውን ተጠራጥሬ ለረዥም ሰዓት ፈዝዤ ነበር፡፡” የሚሉት እኚህ እናት፤አንድ ሁነኛ ሰው ካማከሩ በኋላ ያደረጉትን ደግሞ እንዲህ ሲሉ ለዳንኤል ያወጉታል፡-
“አንድ ቀን አባቱ ወደ መዝናኛ ቦታ እንዲወስደው ነገርኩትና እኔ እቃዎቹን መፈተሸ ጀመርኩ፡፡ ያኔ ነው የልጄን ጉዳይ በጥልቀት የተረዳሁት፡፡ እኔ ያልገዛሁለትን አንድ ቀይ ቲሸርት አገኘሁ፡፡ ቲሸርቱ ላይ በእንግሊዝኛ “I am a gay” የሚል ተጽፎበታል። እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ አልጋው ላይ ተቀምጬ ለረዥም ሰዓት አለቀስኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ልጄን እንዳጣሁት ገባኝ፡፡ ልጄን እንደማላውቀው ገባኝ። ልጄና እኔ በተለያዩ መንገዶች እየተጓዝን መሆኑ ገባኝ።” በማለት የደረሰባቸውን ጠሊቅ ሀዘን ያጫውቱታል። የዳንኤል ክብረት ጽሁፍ ጭብጥም ቢሆን “ወላጆች ሆይ ልጆቻችሁን ምን ያህል ታውቋቸዋላችሁ?” የሚል ከንካኝ ጥያቄ በመጠየቅ ወላጆችን ማንቃት ነበር፡፡ ነገሩን በእንጥልጥል ላለመተው ያህል ግን እኚያ እናት በብዙ ብልሃት ልጃቸውን አግባብተው እውነቱን እንዲነግራቸው በጠየቁት ሰዓት ልጁ፤ “እማዬ እኔኮ ጌይ ሆኛለሁ!” እንዳላቸው፣እነርሱ ትምህርት ቤት እንደዚያ የሆኑ ብዙ ልጆች ስለመኖራቸው፣” I am a gay” የሚል ቲሸርት እንደሚለብሱ፣አንድ አይነት ማስቲካ እንደሚያኝኩ፣ በዕረፍት ሰዓታቸው ላይ አንድ ጓደኛቸው (ይኸውም የልጃቸውን ከንፈር ሲስም ያዩት መሆኑን ልብ ይሏል) በሞባይሉ የጌይ ፊልሞችን እየጫነ እየመጣ እንደሚያሳያቸው፣ ይህንን የምታደርግለት እናቱ እንደሆነች፣ አባቱም ሁሌ ሲሸኘው ከንፈሩን እንደሚስመው… ሁሉንም ዝርዝር አድርጎ እንደነገራቸው ለዳንኤል ገልጸውለታል፡፡  
 እየበረታ የመጣው የወላጆች ሥጋት
ለእኔ ደግሞ ቀጣዩን መረጃ ያቀበለችኝ አንዲት ስለ ልጆቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሠርክ በመጨነቅ ላይ ያለች እናት ናት፡፡ ይህች እህቴ ዘጠኝ ወራት በሆዷ ተሸክማና አምጣ የወለደቻቸው ሦስት እንቦቃቅላዎቿ የዚህ ክፉ ዘመን እኩይ ልምምዶች ሰለባ እንዳይሆኑባት በመስጋት ገና ከአሁኑ እንደምን እንደ ቆቅ ነቅታ እንደምትጠባበቃቸው የነገረችኝ ዕለት በሥጋቷ ሳይሆን ጥበቃ በምታደርግበት ስልት ከት ከት ብዬ ስቄያለሁ። (ያልተነካ… እንዲሉ) በአንፃሩም በዚህ ዘመን ያሉ ወላጆች ሸክም እንደምን እየከበደ እንደመጣ አመላክቶኝ ከልቤ አዝኛለሁ፡፡
የዚህችን እህት የወትሮ ሥጋት ይበልጡኑ ያባባሰው ጉዳይ እንድመለከተው ባዋሰችኝ DVD ውስጥ ይገኛል፡፡ DVDው አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የተከናወነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዐውደ ጥናት ተቀርጾ የተቀመጠበት የመረጃ ማኖሪያ ቋት ነው፡፡ DVDውን ላፕቶፔ ውስጥ ጨምሬ መዝግቦ የያዛቸውን ትዕይንቶች ስመለከት፣ አሁን በዚህ ጋዜጣ ላይ ልጽፋቸው የማልችላቸውን ጨምሮ ብዙ የሚገራርሙ የዘመናችንን ነውረኛ ታሪኮች ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ ዶ/ር ስዩም አንቶኒዮስ፣ “ማየት” ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ትስስርና ትውልዱ ከፊልም ጋር እንዴት እንደተቆራኘ ሲያስረዱ፤ “seeing is actually doing when it comes to how our brains work” የሚለውንና ማየት የድርጊትን ያህል ስለሚሆንበት ሁኔታ የሚያብራራውን አንድ በቅርቡ ይፋ የተደረገን የሳይንሳዊ ምርምር ግኝት ዋቢ አድርገዋል፡፡
“የዘመኑ ልጆች የፊልም ልጆች ናቸው” ያሉት ዶክተሩ አክለውም “ልጆቻችን ከእኛ ከወላጆቻቸው ይልቅ ቅርበታቸው ከፊልም ጋር ስለሆነ አስተሳሰባቸውን የምንቀርጸው እኛ ሣንሆን በፊልም ውስጥ የሚመለከቷቸው ገፀ ባህሪያት ናቸው” ይላሉ፡፡ በሰከንዶች ሽርፍራፊ ውስጥ በልጆች አይን በኩል ወደ አእምሯቸው የሚዘልቁ ትዕይንቶች ለዘመናት የማይረሱ ትውስታዎች ሆነው እንደሚዘልቁም ሌሎች ሳይንሳዊ ዋቢዎችን በመጥቀስም አስረድተዋል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዐውደ ጥናቱ በዋናነት ካተኮረባቸው ጉዳዮች መካከል የተመሳሳይ ጾታ ወሲባዊ ፍላጎትና ፖርኖግራፊ ዋነኞቹ ነበሩ፡፡  
አንድ ሰው የፖርኖግራፊ ሱሰኛ ለመሆን የሚያበቃው የዕይታ ጊዜ የአንድ ሴኮንድ 1/3ኛ እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር ስዩም፤ ልጆች ለሚመለከቷቸው የፊልም ትእይንቶች ወላጆች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ “በዚህ ዘመን ልጆቻችን የሚያነቧቸው መጽሔቶች አስደንጋጭ ናቸው” ያሉት ዶክተሩ፣ ብዙ ታዳጊ ልጆች ወሲባዊ ምስልን በግልፅ የሚያሣዩ ገፆች ያሏቸውን እንደ  “Play boy” የመሳሰሉትን  መጽሔቶች መዋዋስ ከጀመሩ መሰነባበታቸውን ጠቅሰው ዛሬ ላይ እንዲህ ዓይነት ፖርኖግራፊክ የሆኑ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን በስልኮቻቸው መቀባበል በእነርሱ ዘንድ ትልቅ ነገር አለመሆኑንም በታላቅ የሀዘኔታ መንፈስ ገልጸዋል፡፡
“ኢንተርኔት ዋናው የልጆቻችን መጥፊያ መንገድ ሆኗል!” ያሉት ዶ/ር ስዩም፤ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ምንም እንኳ በራሱ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የመገናኛ አውታርና የብዙ እውቀቶች ማግኛ ድልድይ ቢሆንም አብዛኞቹ ልጆች ግን በአመዛኙ የሚጠቀሙበት ለመጥፊያቸው የሚሆነውን ፖርኖግራፊ ለመመልከቻነት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ “እኛው ራሣችን በውድ ዋጋ ገዝተን በምንሰጣቸው የእጅ ስልኮቻቸው በቀላሉ ዘው ብለው የሚገቡበት የመረጃ መረብ (ጫካ) በሚዘገንን ሁኔታ ለህፃናት ተብለው ወደሚዘጋጁ የፖርኖግራፊ ሳይቶች ነው” ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ በአንድ ት/ቤት  የሆነውን ታሪክ በምሳሌነት ሲያወሱም፣ አንድ ታዳጊ ልጅ በሞባይሉ ላይ ጭኖ ያመጣውን የህፃናት ፖርኖግራፊ ሌሎች አራት ጓደኞቹን ጠርቶ እያሣያቸው ሣለ ድንገት የደረሠባቸው መምህር እንዳጫወታቸው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ስዩም “አዲሱ ሃይማኖት” ብለው የሚጠሩት ፌስ ቡክ  የተሰኘው ማህበራዊ ድረ ገፅም ቢሆን ብዙ ወጣቶች በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ ሳይሳለሙት የማይውሉት ጣኦት እየሆነ መምጣቱን ገልፀው፣ ድረ ገፁ በራሱ ያለው ጠቀሜታ  ባይታበልም በቀን አምስትና ስድስት  ሰዓት እዚያ ላይ ተጥዶ የሚዋልበት ምክንያት ግን በአመዛኙ ሌላ መልክ ያለው እንደሆነ አመላክተዋል። “ፌስ ቡክ ላይ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ተመልክቼ አውቃለሁ፡፡” ያሉት ዶክተሩ፤ ሆኖም ከተጠቃሚዎቹ አብዛኛዎቹ ነገሩን የሚጠቀሙበት ለወሬና ለፖርኖግራፊ መቀባበያነት እንደሆነ አውስተዋል፡፡ “Daily mirror”  የተሰኘው ታዋቂ መጽሔት እ.ኤ.አ በ2012 “sex” የሚለውን ቁልፍ ቃል በመጫን  ቀዳሚ እንደሆኑ ከጠቀሷቸው አገሮች መካከል (Top of nation in sex search in Google) ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ሥፍራ መያዟም የገባንበትን ቀውስ አመላካች አድርገው አቅርበውታል፡፡  
“እንዲያምን አድርገው!”
ማንኛውም የፈጠራ ሥራ መመዘን ያለበት በውስጡ ከያዘው መልእክት አንፃር መሆን እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በገሃዱ ዓለም እውነታዎች የበለጠ ጎልተው ከሚታዩበት የጥበብ ዘርፍ አንደኛውም ፊልም ነው። እንደየሁኔታው በዚያ ውስጥ የሰዎች እምነት፣ ባህል፣ የአስተሳሰብ ሥርዓትና የህይወት ፍልስፍና ይንፀባረቃል፡፡ ፊልም እንደ ሌሎች የኪነ ጥብብ ፈርጆች ሁሉ ማህበራዊ እሴቶች የሚጎሉበት አሊያም እንደ ገለባ ቀለው የሚታዩበት መስክ ነው፡፡ ከዛሬው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማደግና መንሠራፋት የተነሣ፣ ከየትኛውም ዘመን ይልቅ የተለያየ ባህልና እምነት ያላቸውን ህዝቦች በአንድ ዓይነት የአመለካከትና የስሜት ቦይ ውስጥ እንዲፈስሱ ከሚገደዱባቸው መሣሪያዎች ዋነኛው ፊልም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ይህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ መንጋነት ለሰናይ ዓላማ ሆኖ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ አሳዛኙ ግን ተቃራኒው መሆኑ ነው፡፡ ዴቪድ ሪስማን የተሰኘ አሜሪካዊ የሥነ - ህብረተሰብ ባለሙያ ይህን አስመልክቶ ሲፅፍ፤ “የሃያኛው ምዕተ ዓመት ግለሰቦች ህይወትን የጠሉ፣ ዓላማ የሌላቸው፣የመወስን ድፍረት የጎዳላቸው፣ ተጨባጭ እውነታን ለመገምገም የማይችሉና የሰጧቸውን ሁሉ በዘፈቀደ የሚቀበሉ ህያው አሻንጉሊቶች ናቸው” ማለቱም እውነታውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ የአሜሪካ ህዝብ የሚመራው ከነጩ ቤት (ኋይት ሃውስ) በሚወጣው ህግ ሣይሆን በሆሊዉድ ምናብ ስለመሆኑ መነገሩም ያለ ምክንያት ዓይደለም፡፡ ሰሞነኛውም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ህጋዊነትም ቢሆን ከነጩ ቤት ይነገር እንጂ ምንጩ ሆሊ ዉድ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡
በፊልሞች ውስጥ የሚንፀበራቀው ሃሳብ ነው። ከታሪኩም ቢሆን ሠፊውን ቦታ የሚይዘው ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ የማይጨበጥ ቢሆንም ተጨባጭ ነገሮችን በውስጣችን ይፈጥራል፡፡ የሰው ልጅ ሃሳብና ገሃዳዊው ዓለም የተቆራኙ በመሆናቸው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሁሉ በፊልም ውስጥ ስለ ሚመለከቷቸው ታሪኮችና ጭብጦች ተገቢውን ጥንቃቄና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያው በላይነህ አቡኔ “ፈርጥ” በተሰኘች የኪነ ጥበብ መጽሔት ላይ (1995) “ሆሊውድ አዝናኝ ኢንዱስትሪ ወይስ…?” በሚለው ጥርጣሬ አዘል ፅሁፉ፤ ፊልም የዘመናችን ኃያልና ተወዳዳሪ የሌለው የጥበብ ዘርፍ እንደሆነ ጠቅሶ፣ ለአንድ የፊልም ዝግጅት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦች ለምን እንደተራ ነገር እንደሚወጡ መጠየቅ የብልህ ሰው ጥያቄ መሆኑን ይገልፃል፡፡ “አዝናኝ” ከሚባሉት ፊልሞች በስተጀርባ ያለውን “ስውር አጀንዳ” ወይም “ርዕዮተ ዓለማዊ” ተልዕኮ መፈተሽና መመርመር እንደሚገባም ይመክራል፡፡
በላይነህ አቡኔ በዚህ ጽሁፉ፤ “የሆሊዉድ ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ሶፕ-ኦፔራዎችን በተናጠል ወስዶ በጥልቀት የሚፈትሻቸው ንቁ ተመልካች ቢኖር፣ ከዚያ የሚገነዘበው ሀቅ ፊልሞችም ሆኑ ድራማዎቹ የሠሪዎቻቸውን መደባዊ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቁ፣ የሥርዐተ ጾታንና ፖለቲካዊ ተፅእኖዎችን የተላበሱ መሆናቸውን ያውቃል፡፡”
በማለት ገልጾ፣ የሰጡንን ሁሉ እንደወረደ የምንቀበል መሆን እንደሌለብን ያስጠነቅቃል፡፡ እንደ እርሱ እምነት ፈንጆች፤ “Make believed” ወይም “እንደሚታመን አድርገው!” በሚሉት በዚህ ጥበብ በኩል ዓላማቸው እንዲተላለፍላቸው የፈለጉትን መልእክት ሁሉ ለሌሎች አስመስሎ ማሳየትና ማሳመን በመሆኑ፣ ያንን የምር ማጤን ብልህነት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የሳይንስ ልብ ወለድ ጸሐፊው ብሬድበሪ ያለውን ጠቅሶም እንዲህ አይነቶቹን ፕሮፓጋንዳዎች ለመቃወም ያልተዘጋጀ ማህበረሰብ እውነተኛውን ጦርነት በቴሌቪዥን ሳይሆን ገሃድ በሆነ የጦር ሜዳ ሊያየው እንደሚችል ያስጠነቅቃል፡፡  

Read 40648 times