Saturday, 05 August 2023 11:38

ዳገት ጨርሶ---

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(2 votes)

የአንድ እግር ጫማ ከጥቅም ውጭ ቢሆን የሁለቱም እግር ጫማ ይጣላል። አዎ! የአንደኛው መጥፋት ሌላውንም ይዞ ይጠፋል። መንግሥትና ሕዝብ የአንድ ሰው የግራና ቀኝ ጫማዎች ናቸው። ለዚህም አንዱ ከጥቅም ውጭ ከሆነ አገርን ማሰብ ይከብዳል። ምሣሌዬ የራቀ ይመስላል። ከባልና ሚስት አንዱ መሐን ቢሆን ልጅ መውለድ እንደማይቻል ኹሉ ከገዢና ተገዢ አንዱ መሐን ከሆነ የሚጠበቅ ፍሬ አይኖርም።
እማ ብርቄ ክፉኛ ታመሙ።
ጎረቤት መክሯቸው ጸበል ሊኼዱ ስንቅ ቋጠሩ። ከኮቸሮው፣ ከቆሎው በየዓይነት አዘገጃጅተው ለመኼድ አንድ ቀን ሲቀራቸው  ፈሩ።
«ለምን ይቀራሉ ?» አሏቸው ጎረቤቶች
«ልጄን ለማን ሰጥቼ?»
«አባቷስ?»
«ሴት ልጅ ለአባት አደራ መስጠት እየቀረ ነው» ብላ ወደ ቤት ገባች። ምን ታድርግ ልጁን የሚደፍር አባት በዝቷል። ለመሆኑ በዚህ ዘመን አገርን ለማን አደራ ይሰጧታል?
ሰይጣን ከአለቅነቱ ሲጣል በሰው ልጆች ሆድ ውስጥ ነው የወደቀው የሚለን ጋሼ ስብሐት፣ ይህ ቢገባው አይደለ?_ሆድ አምላካችን ሆኗል። በሊታዎች አገር የአባቶቻችን አደራ ናት ሲሉኝ  ሳቄ ይቀድመኛል። የአደራ እቃ እንኳን ሊነኩት ዞረው ሊያዩትም የሚያፍሩት እንደሆነ ከወላጆቼ ተምሪያለሁ።
አሐዱ...
(ከእማ ጥሩነሽ ቤት ብሔርተኛ  መጠጦችን ጠጣሁ _ጂንና ጃንቦን። መቀ˙ላቀል አይወዱም ኖሯል (ለሞቅታ እንጅ) ግን ቀላቀልኳቸው። ወደ ሆዴ ገብተው አይጠርጉ ጥርጊያ ጠረጉኝ። መቀላቀልን ለምን አልፈለጉም? ብዬ አልተመራመርኩም። ለምን? ከኑሯችን ተማርኩታ።
አሲድን ውኃ ላይ ቢጨምሩት ይቻላል። ውኃን ወደ አሲድ ቢቃጡ ግን ትርፉ አደጋ ነው። ለመቀላቀልም «ከማን...ወደ ማን» የሚለው እሳቤ ይገታናል፤ እንደ አገርም። አለፍ ስንል አራት ሲደመር አምስት ዘጠኝ ፤ አምስት ሲደመር አራትም እንዲሁ ዘጠኝ። በመደመር ጊዜ ቁጥሮች ቦታ ቢቀያየሩ ውጤቱ አይዛባም። የመደ˙መር ዘመን ሰዎች ግን ቦታ መቀያየርን ለሞት መንደርደሪያ ሲያደርጉት አይና እንባ ይተናነቀኛል።
ክልኤቱ...
ብዙ የስካር ታሪክ አለኝ ፤የምሰክረው ስለሰከረ ገፀ-ባሕርይ ልጽፍ እንጅ የመጠጥ ፍቅር ኖሮኝ አይደለም። ሰክሬ በወጣሁ ጊዜ ደብረወርቅ ሕንጻ ሁለት ሆኖ ይታየኛል፤ መንገድ ላይ የተኮለኮሉ ሰዎችም በእጥፍ ጨምረው ይታዩኛል። ሁለቱ ...አራት ፤ አራቱ...ስምንት ይሆናሉ። ለካ የሰከረ ይጨምራል። እርስበርሳችን ላለመቀናነስ ሁላችንም እንስከር እንዴ?
ሠለስቱ...
ግዑዛን እንኳ ጠላትን ተደግፈው ይኖራሉ። ጥቀስ ቢሉኝ ጋን እላለሁ፤ጠጠር ይደግፈዋላ። ይህ ጠጠር ከጋን ማስደገፊዬነት ቢርቅ በሆነ ሰው እጅ ገብቶ ጋንን መስበሩ አይቀርም ነበር። ነገር ግን ጋን ብልጥ ነው፡፡ ጠላቱ ጠጠርን ተደግፎ ይኖራል። «እንዳያማ ጥራው ፤እንዳይበላ ግፋው»ን ጋን ችሎበታል። ጠላት ሁሌ ጠላት አይደለም። ማዕበል ለንሥር ጠላቱ ነው። ዳሩ ማዕበሉን ተጠቅሞ መክነፉ ችግርን እንደ መፍትሔ መጠቀምን ለመጠቆም ነው። በቡጢ ጀርባውን የተመታው እውቁ ሯጭ   የመታውን መቼ ዞሮ ወቀሰ?_አንገቱን አስግጎ ቀደሞ አሳፈረው እንጅ! በፍቅር መያዝ እያለ፤ለምን ጠላት የሚመስላችሁን ወይም የሆናችሁን ማሳደድ ላይ ተጠመዳችሁ?... ጩቤ ለአፎት ጠላቱ ነው፤ዳሩ እቅፍ ድግፍ አድርጎ ያኖረዋል። በጉያ ውስጥ ያሉት ሁሉ ጥሩ ላይሆኑ ቢችሉ እንደ አመል ...እንደ አመል።
እያረፋችሁ።
ቃሉ ቅኔ ፤ማረፍን ፈላጊም እኔ።
ከእውነት ትክሻ የሚለካካ ተረት...
እየተቃጠለ ላለው ጨጓራ ወተት ...እስከመቼ?።
«አንዱ የካምፓስ ተማሪ ዊድ አጭሶ ክላስ ገብቶ ከተማሪዎች ኋላ መቀመጥ። ከዛን ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ፡፡ ተማሪዎች ምን ሆነ ብለው ማባባል። «ሁላችሁም አኩርፋችሁኝ አይደል ፊታችሁን አዙራችሁብኝ የተቀመጣችሁ» ማለት። ክፍሉ በሳቅ ዶፍ መሙላት።»
ዛሬ እሱን መስያለሁ።
የገባሁባት ሰማያዊ ታክሲ ውስጥ ከኋላ ወንበር ተቀምጬ፤ «ለምን ፊታቸውን አዞሩብኝ?» ብዬ  እያሰብኩ ነው። አሥራ ኹለት ሰው መያዟን መዘገብኩ ፤ግን ደስ አላለኝም። ከአሥራ ሁለቱ ውስጥ የቱ ይሆን ይሁዳ? እያለኝ ነበር ውስጤ። አጠገቤ ያለው ወጣት ልጅ ጫማ ይሸታል። ውኃ ስለማትኖር ይሆናል ብዬ ደንታ አላልኩትም።
መንገዱ ረጅም ነው፤በዛ ላይ ዳገት።
መኪናዋ አልማዟ ተበልቷል። ሆዷን በምን እንደደለለው ባላውቅም ጉልበቷ በዳገት ለግሟል። ሹፌሩ የእኛን ነፍስ በእጁ ይዞ ጫት ይቀነጥባል። አናደደኝ። ቀስ ብዬ ተስቤ ፌስታሉን ወደ ኋላ አሸሸሁበት። እየነዳ እጁን ወደ ጎን ሰድዶ አጣ።«ጫቴስ?»አይባል ሆኖበት...ስሜቱን ዋጥ አደረገው።
ከኋላ ወንበር መቀመጥ ጥቅም አለው።
የሁሉንም ሰው ጀርባ ማየት ይቻላል፤ከራስ ጀርባ በስተቀር።
አንዳንድ ሰዎች ወደ’ኔ ዞር ዞር አሉ። አንገታቸው የተሰራ አዎ! ለመዞር ነው።ዳሩ «ዞሮ ማየት» በፍካሬው ቢሆን ነበራ። ተናገርኳቸው። እናንተ የእፍኝት ልጆች...አዩኝ ደም በጎረሰ ዓይናቸው።
የልብ የልቤን ማውራት ቀጠልኩ።
መኪነዋ እድሳት ትሻለች። በተለይ መሪዋ!..(ገና ንግግሬን  ሳልጨርስ ፖለቲካ አደረጉት)።
ናቅኳቸው ።
የአንዳንዱን ሰው ተፈጥሮ መረዳት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የድመት ተፈጥሮ መቧጨር፣የውሻ መናከስ ፣የእባብ ተፈጥሮ መናደፍ ነው። ድመትን ተንኩሎ ስለ ቡጭሪያ፣ውሻን ነክቶ ስለ ንክሻ፣እባብን ተቃልዶ ስለ ንድፊያ ማውራት ጅልነት ነው። አምነን የምንቀበላቸው የሰው ባሕርያት አሉ። ለዛም ነው መንገድ ሳልጀምር ረዳቱ ሒሳብ ሲለኝ ዝም ያልኩት። ሁላችንም ገና ላልኼድንበት መንገድ ቀብድ ከፋዮች ነን።
ከኋላዬ አቧራ ይርመሰመሳል።
ወዳጄ ነበር ማለት ነው፤ ጠላት ቢሆን በፊቴ በመጣ። አያት አያትና ዓለም ታሳዝነኛለች። ወደ ተስፋ ልጽፍ ያልኩ እንደሁ ጽሑፌ ያጥራል፤ወደ ትዝታ ስመድር ነው የሚረዝመው። ፊታችንን ዘላለማዊ ጉም ከልሎታል። «ስለመሻገራችን» እንጅ ስለሚገጥመን አዲስ ትዕይንት ዝግጁ አይደለንም። ከጦርነት ተሻግረው ረሃብን ካገኙት መሻገር ምንድን ነበረ? ከድጡ ወደ ማጡ አኗኗር፣ የሙሾ ግጥሞች መበራከት ይከተላሉ።
እያወራን ነው የምናልቀው።
ብዙ ለፍልፌ ተሳፋሪዎች  ፈገግ ሲሉ  ገረመኝ። ለካ የሚያስቅ ነገር አይለዩም። አውቃለሁ  ንግግሬ ይመራ˙ል(በሰሙም በወርቁም)፤ መድኃኒትም መራራ ነውና በዚህ እጽናናለሁ። የማለዳ ደውል ጠባቂዎች ነን። «የምትመለስበት ለነፍሴም ቀን አላት» እስከመቼ ይደገም? አልጋውም ተኝውን መልቀቅ ትቷል።
ስለ ዳገቱ ብዙ  አወራኋቸው ፤ስለ መሪውም። አንዳንድ ቦታ ፍሬን ይይዛሉ። እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ዓይነት።
«ዳገቱ ላይ አትዛል ጉልበቴ
ከተራራው ጫፍ ፍቅር ናት እርስቴ»ን ከፈተልኝ። ተስፋ...ተስፋ ብቻ። ይኼን የሰነፍ አምላክ ተስፋን እጠለዋለሁ። ዳገቱ ማለቅ አልቆበታል፤መድረስ ድራሽ አባቱ ጠፍቷል። ይኼን አቀበት ጨርሶ ወራጅ አለ እለዋለሁ ደጋግሜ፤ ዳሩ በየት በኩል።
መሪውን ጨብጦ ይወዛወዛል።
ያረጀ መኪናውን በአቀበቱ ይጎትታል።
ከኋላ ትልቅ የማናፋት ድምፅ አለ። ብዙ ተመሳሳይ መኪኖች ቀድመውን ሲከንፉ አያለሁ። ቀድመን ጉዞ ጀምረን አርፍደን እንድንደርስ ማን ፈረደብን? ተሳፋሪዎች በየመንገዱ በተስፋ መቁረጥ እንዲወርዱ ለምን ይሆናል?_ወያላው የቀልድ አይደለም፤በመልስ ይኮረኩማል።
«ዳገቱ ላይ አትዛል ጉልበቴ»ን፣«ጎዳናው ጎዳናው»ን፣ሄድ መለስ»ን...አልያም ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድን፣ እላፊ መንገደኞችን፣ወደ መንገድ ሰዎችን...አንዱን እንኳ በቴፕህ ሳታጫውትልን የቀረህ ለምን ይሆን? ...አልኩት ስፈራ ስቸር።
«የመኪናዬን ዜማ አልሰማህም?» ነበር ያለኝ።ጆሮዬ ቆመ። የመኪናዋ እሪታ ዜማ ፈጥሯል። ዳገቱ እሷንም አሰልችቷት ይሆናል።
«ዳገት ጨርሶ» በጭራሽ የለም።
ዳገቱ ዘላለማዊ መንገድ መስሏል።እንደ ህልም አይጨብጡት፣ እንደ ጉም አይዘግኑት፣ እንደ ምኞት አይሆኑት ዓይነት።
መኪናዋ ባትደርስም፣አቀበቱን ባናልፈውም። የኔ ልፍለፋ ቀጥሏል...
ሞት ደሃን ብቻ የሚገድል ቢሆን ኖሮ ይቺ አገር ደሃ ሰው አይኖራትም፣ ደሃም አትሆንም ነበር አልኩት አጠገቤ የተቀመጠውን። ሳቀብኝ። ምናልባት ሐሳቤን ንቆታል አልያም ሐሳቤ ስሜቱን አ’ኮለታል። ደሃን በመግደል ድህነትን ማጥፋት እንዳይቻል አውቃለሁ። በተለይ እዚች አገር ላይ ይኼን መሞከር ውጤቱ ኗሪ ማጣት ነው። እንዲሁ ቀባጥር ቢለኝ። ዳገቱንም ይቺ ተፍታፋ መኪና ልትወጣው ባለመቻሏ ነው። ቀልዴን አምርሮ...«ለምን ይኼን ሐሳብ ይዘህ አንተ ሃብታም አልሆንክም?»ብሎኝ  ወገቤ  ተያዘ። አይ !...አይ ሃብት አጠራቅሜ ለሞት ከምገብር ብዬ ነው አልኩታ።
በወሬ’ችን መሐል ሌላም ሰው ወረደ። ከፈለገው ደርሷል አልያም ፍላጎቱን ገድቧል_ታድሎ። ጥበቃን መቀነስ ለዚህ ዳገት ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ ታየኝ። እንደ ሲሲፈስ አይደርሱትን መታገል እምብዛም ነው ፋይዳው።
 ሌሎች ቀሪ አሥር ተሳፋሪዎች እንደ በገና ክር ተወጥራችሁ ከእኔ ጋር ትቆያታላችሁ አልኳቸው።
በገናን ታውቁት የል፤ተወጥሮ የሚገረፈው። በግርፋቱ ዜማ የሚፈጥረው። በለቅሶ ዜማው ሰው መንፈሱን የሚያድስበት። እንደዛ እንሆናለና። የዳገቷ ምሬታችን ለሌሎች ሐሴት ከሆነ ምን ይደረጋል።
በመሐል...
ሰዓቴ ቢጠፋ በምን ላገኘው እችላለሁ? ብዬ ተጨነቅሁ፡፡ መኪናዋ ውስጥ አንድ ጽሑፍ ሳገላብጥ ጸጥ እንድል መከረኝ። ጸጥ ባልኩ ሰዓት፣ የሰዓቱን ድምጽ እንደምሰማ እርግጠኛ ሆንኩ። ዝም አላልንም እንጅ እንኳን የእኛ ዳገቱ የረዘመብን ሰዎች የሰቆቃ ድምጽ ይቅርና ደላን የሚሉትም ሰዎች ሙሾ ይሰማን ነበር። ለማንኛውም ቃል ቀብድ ነውና...ዳገት ጨርሶ ወራጅ አለ። እስከዛው Comedy is sex ( ቀላጁ አድማጩን የማስደሰት ኃላፊነት አለበት) እንዲል ትሬቨር ኖህ፣ ሹፌር ሆይ ዳገቱ ባያልቅም እኛ ተሳፋሪዎችህን ማስደሰት ቀጥል።

Read 632 times