በግንቦት 13 እና 20 ቀን 2003 ዓ.ም እዚሁ ጋዜጣ ላይ በታተመው በዚህ ጽሑፍ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ተክለሀዋርያት ተክለማሪያም፣ ግርማቸው ተክለሀዋርያት፣ ሀዲስ ዓለማየሁ እና በዓሉ ግርማ ከተፈተሹት ሐፍቶች መካከል ነበሩ፡፡ እንዲያም ሆኖ መነሳት ሲገባቸው ያልተነሱ ደራሲዎች በቁጥር መላቃቸው ሲከነክነን ቆይቷል፡፡ ዮሐንስ አድማሱ፣ ደበበ ሠይፉ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ አቤ ጉበኛን የመሰሉ ተንዘራፋፊ ደራሲዎች ሳይወሱ መቅረታቸው እንደ እናት ሞት እያደር መፍጀቱን አልተወንምና ዛሬ እስካለልን እንዘልቅ ዘንድ ወደድን፡፡
..አንድ ደራሲ ወደደም አልወደደ፣ አወቀም አላወቀ የሥርዓት አገልጋይ ነው.. የሚለው ካርል ማርክስ ነው፡፡ ጥበብን ተፈናጦ ከፖለቲካ ስልት ውጭ መስገር አይቻልም - እንደ ማርክስ እምነት፡፡ ጨቋኙ ወይም ተጨቋኙ በተፋጠጡበት ሁለት ጉብታዎች መካከል ለጥበብ ሰው የተዘጋጀ ..ሠርጥ.. የለም፡፡
ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ የዚያና የእዚህ ..ጉብታ.. ከመፈጠሩ አስቀድሞ ገና በድብልቅልቁ ጊዜ ውስጥ ፖለቲካዊ ሚናውን የለየ ደራሲ ነበር፡፡ የዮሐንስ አባት አቶ አድማሱ ኃይለማሪያም ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ..ኮሌጅ ገብቶ በግጥም ውድድር ውስጥ መካፈል ከጀመረ በኋላ መንገዱን ለወጠ፡፡ ስለሰው ተፈጥሮ ምርምር ላይ አትኩሮ ሲመጣ ለስቃዩም ለጉስቁልናውም ለክፋቱም መሪዎች ኃላፊነት እንዳለባቸው ተመለከተ፡፡ ባለሥልጣኖች ሰውን ሲጐዱ አየ፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ ገባ፡፡..
ዮሐንስ አድማሱ የተወለደው ደብረሊባኖስ ውስጥ መስከረም 29 ቀን 1929 ዓ.ም ነው፡፡ ልክ በአፍላ እድሜው በ1952 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብቶ ከመሰል ወጣቶች ጋር ሲቀላቀል ውይይቱ እንደ ባህል መድሃኒት ሆኖ አይነ-ጥላውን የገፈፈለት ይመስላል፡፡ ከእውነታ ጋር እርቅ የሌለው መንፈሳዊ አስተውሎቱን ትቶ አካባቢውን ቃኘ፡፡ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ ድህነት፣ በሽታ፣ ድንቁርና... ሕዝቡ ላይ ተንሰራፍቷል፡፡
አሉ ወይ በእናንተ በመቃብር አገር
የችግር ጅረት
የሚወርድባቸው ወትሮ ዘለለት
ያንከራተታቸው መኖር ጉስቁልና፣
ሰዎች ሆነው ሳሉ እንደዚህ የወጡ
ከሰዎች ጐዳና፣
በቁመና ሲኦል አካላቸው ገብቶ
ለግዴታ መኖር በከንቱ ተገዝቶ
የሚያስብላቸው ሁሉን አስተንትኖ
በፍፁም ስላጡ ኑሯቸው መንምኖ
የዮሐንስ ግጥሞች መቆርቆሩና መትከንከኑ የፈጠሩበትን ቁስሎች ማከሚያዎች ናቸው፡፡ ቁዛሜ ቢበዛባቸውም ዕጣ-ፈንታቸውን ለሁኔታዎችና ለእግዚአብሔር አሳልፈው የሰጡ አልነበሩም፡፡ ለውጥ የሚሹ፣ የጭቆና ማብቂያ ደወልነት በጠባያቸው ውስጥ ይታየል፡፡ ባህሪውም በግጥሞቹ አምሳያ እንደነበር የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ደበበ ሠይፉ ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፍ ..ዮሐንስ ባለው አመለካከት በዘመነ ኃይለሥላሴ ብዙ ሰዎች የሚያርቁት፣ እንደ እብድም የሚቆጥሩት ነበር፡፡ ያ ላሊበላ ነበር የኋላ ሥሙ፡፡ እሱም ከእምነቱ ባለማፈንገጥና አተያዩን ለማጥራት ሲታክት ለህይወቱ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሳያደርግ፣ እንደ ቀድሞ ዘመን ባለቅኔዎች ሙጭጭ ብሎ ለተግባሩ በመታመኑ፣ ሳይደላው ይህንን ሰዎች ሳያውቁለት ነው በወጣትነት እድሜው የተቀጨው፡፡..
የዮሐንስ አድማሱ ፖለቲካዊ ትግሉ ከተደብዳቢው ወገን ቆሞ እስከመደብደብ ድረስ ሰማዕታዊ ባህርይ ያለበት ነበር፡፡ የመጀመሪያ ..ዱላ.. ያረፈበት በ1955 ዓ.ም ነበር፡፡ kዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተባረረ፡፡ ለአንድ ዓመት ደሴ የሚገኘው ወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት አስተምሮ ተመለሰ፡፡ ከዚያም ወደ አሜሪካ ተጉዞ ትምህርቱን ለመቀጠል ቢሞክርም አልቻለም፡፡ በአማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ከሚታወቁት ከፕሮፌሰር ውልፍ ሌስሎው ጋር በሥርዓተ ትምህርትና በሴም ቋንቋዎች ምርመራ ዘይቤአቸው ተጋጭቶ ተመለሰ፡፡ ዳግም yዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አራተኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ በማስጠንቀቂያ ቀጠለ፡፡ ትምህርቱን ሳይጨርስ እዚያው ኮሌጅ ውስጥ የማስተማር እድል ቢገጥመውም አሁንም በማይበርድ አመፁ ሌላ ..ዱላ.. አረፈበት፡፡ ወደ ሐርማያ ኮሌጅ ተዛወረ፡፡ እዚያው እንዳለ በ38 ዓመቱ በሰኔ 1967 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
ዮሐንስ አድማሱ፤ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ..ሙሴ.. አመ ቀስቅሶ፣ ከባርነት ለማውጣት ..ቀይ ባህራቸውን.. ከሁለት ከፍሎ፣ የ..ተስፋይቱን ምድር.. በቅርስ እያየ ሳይገባ የቀረ አብዮታዊ ነብይ ነው፡፡ ..የተስፋይቱ ምድር.. ፍሬ አረረም መረረም ያጣጣመለት ገጣሚ ደበበ ሰይፉ ነበር፡፡ ..ሙሴም እጆቹን ስለጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፣ የእስራኤል ልጆች ታዘዙለት.. እንዳለ መጽሐፉ፤ ደበበ ሰይፉም በዮሐንስ አድማሱ የጥበብ መንፈስ ወደ ..ተስፋይቱ ምድር.. አምርቷል፡፡
ደበበ ሠይፉ ከዮሐንስ አድማሱ በ13 ዓመት ያንሳል፡፡ ይሁንና ይሄ የእድሜ ገመገም ሁለቱ ገጣሚዎች በመንፈስ እንዳይገናኙ እንቅፋት አልሆነባቸውም፡፡ ደበበ መለስ-ቀለስ እያለ የዮሐንስን አቋምና ግጥም በአድናቆት ቃኝቷል፡፡ ያኔ ሳይሆን አይቀርም ዮሐንስ እጆቹን በደበበ ላይ የጫነው፤ ደበበም፣ የጥበብን መንፈስ የተሞላው፤ አብዮታዊ ሕዝቦች የታዘዙለት...
..ዮሐንስ ብዕሩን ለትግል ያዋለ ሰው ነው.. ይላል ደበበ፡፡ ..በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪነትና በመምህርነት በቆየባቸው አመታት ሁሉ በብዕሩ የኃይለሥላሴን ፊውዶ ቡርዥዋ መንግሥት በኑ ተዋግቷል... በግጥሞቹ ይዘት ጭቆናንና ምዝበራን እንዲደቆስ፣ የመንፈስ የሥጋ ባርነትንና ድህነትን እንዲቃወም፣ ያለመታከት በእጅጉ የጣረ ሰው ነው፡፡ ...በይዘት ረገድ ማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ተቃርኖዎችና ፍጭቶች በግጥሞቹ ውስጥ አካቶ ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ከኢትዮጵያውያን ደራሲያን መካከል፣ አንድ ደራሲ ለማኅበረሰቡ ያለበት ግዴታ እምን ድረስ መሆን እንዳለበት እንደሱ የተገነዘበ፤ ወይም ቢገነዘብም እንደእሱ ባደባባይ ወጥቶ፣ ከጣራ አተያይ ተነስቶ የተቸ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡..
ደበበ ስለዮሐንስ ሲገል እሱ ቢሆነው እየተመኘ እንደሆን ያስታውቅበታል፡፡ አባቱን በአካሄድ፣ በአነጋገር፣ በአቀማመጥ... ለመምሰል እንደሚጥር ሕፃን ቀልቡን ሰጥቶ ተመልክቶታል፡፡ ከዚያ ባሻገር ገምግሞ ቀርነቶቹን በአብዮታዊ ወረንጦ ነቅሶ ለማውጣት ሞክሯል፡፡ የዮሐንስ የግጥም ሥራ ቀርነቶች በእድሜና በአመለካከት መጥራት እየተሟሉ እንደሚሄዱ መጠቆም የሚሻም ይመስላል፡፡ ዮሐንስ በደበበ የተተቸበት አንዱ የግጥም አዝማሚያው ..ሜታፊዚካዊ´ (ደበአካላዊ) መሆኑ ነው፡፡ ..ሜታፊዚካዊ ባለቅኔ.. ይላል ደበበ ..ሜታፊዚካዊ ባለቅኔ ሰው ምንድነው? ህይወት ምንድነች? ሞት ምንድነው? እግዚአብሔርስ ማነው? የፍቅር፣ የእምነት፣ የውበት ባህሪያቸው ምንድነው?... በሚሉና እኒህን የመሳሰሉትን ረቂቃን ጥያቄዎች በሥራዎቹ ውስጥ የሚጠይቅና የሚመልስ ሰው ነው፡፡ የዮሐንስም ቀደምት የበኩር ግጥሞቹ በዚህ ዓይነት ጥያቄዎችና መልሶች የተሞሉ ናቸው፡፡´የዮሐንስን ጉርድ ህይወት በደበበ አብዮታዊ ህይወት ላይ ብንቀጥለው ወጥነቱን ሳያጣ የአንድ ሰው የእድሜ ልክ ትግል በመምሰል ሊያደናግረን ይችላል፡፡ የማይዛነፈው ህይወታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ሥራዎቻቸውም እንደዚያው ከተምኔታዊ ሶሻሊዝም (utopian socialism) ወደ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም የመሸጋገር፤ የአንድ ሰው እድገት መለስው ሊያደናግሩ ይችላሉ፡፡ ደበበ የዮሐንስን ሥራ የሚተቸው በራሱ ቀደምት ሥራ ላይ ግለ-ሂስ እንደማካሄድ ባለ ቃና ነው፡፡ ..ያኔ ተምኔታዊ ሳለሁ.. እንደማለት፡፡ ዮሐንስም የኋለኞቹን የደበበን አብዮታዊ ግጥሞች ቢመለከት ሥራነታቸውን እንደራሱ ሥራ፣ አቋማቸውን እንደ አቋሙ ከመቀበል ዝንፍ የሚል አይመስልም፡፡ ሁለቱም በመምህሮች ላይ የተሳለቁበት ሥራዎች አሏቸው፡፡
የእርሻ ኮሌጅ ሰዎች - ሊቆቹ በሙሉ
እንደተኙ ናቸው አልተነሱም አሉ፡፡
እናንተ ዘበኞች ተግታችሁ ጠብቁ
አይታወቅምና መቼ እንደሚነቁ፤
የዮሐንስ ግጥም ነው፡፡ ዮሐንስ ይሄን ግጥም የጻፈው በ1962 ዓ.ም ነበር፡ ደበበ ሠይፉም በዚያው ተመሳሳይ አመት (1962) ..ድንቄም መምህር..ን ገጥሟል፡፡
ራሱን ሲከሽን
ሲያንቆለጳጵሰው
ማር-ወተት ሲያደርገው
ከንፈሩን ሲስመው
ሊያስተምረኝ መጥቶ፤
ብሽቅ አደረገኝ፡፡
የተረብ ጋዘና መሆኑ ሰቀቀኝ፡፡
ለጋ ጊዜዬ ላይ መሽናቱ ነደደኝ፡፡
እንዳይሰማው ፈርቶ
ልቤ አንሾካሾከ
..አስተምረኝ ባለ
ስንት ነገር አለ!..
እነዚህ ግጥሞች የጭብጥ ብቻ ሳይሆን የስሜትና የድምዳሜ ተጋሪዎች ናቸው፡፡ የዮሐንስን ግጥም ከደበበ ግጥም ስር ብንሰድረው ጥቂት የአርትኦት ሥራ ከማስፈለጉ ውጭ የስሜትና የአቋም መዛነፍ አያስቸግረንም፡፡ ከደበበ ሌሎች ሥራዎች ውስጥ ..ጥሬ ጨው..ም እንዲሁ ከዮሐንስ ..የእርሻ ኮሌጅ ሰዎች.. ጋር እንዲስማማ ሆኖ የተገጠመ ይመስላል፡፡
ፖለቲካ ለደራሲዎች የሚያዘጋጀው ..ላፋቸው ሊጥ.. ብቻ ሳይሆን ..ለወገባቸውም ፍልጥ.. ነው፡ የደበበ ሠይፉ የመጨረሻ ህይወት እንዲያ ነበር፡፡ በፖለቲካ ጉብዝናው ወቅት የሰበሰበው ..ሐብት.. የፖለቲካውን እርጅና ተከትሎ ተበትኖበታል፡፡ በኮንትራት ቅጥር ከ1965 ዓ.ም አንስቶ ለ20 ዓመታት ያገለገለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሰቀላው በመጤ ..ነፋስ.. እንደተገለበና አውላላ ላይ እንደቀረ አይቶ (ይመስላል) መጦሪያውን ለስምንት አመት ነፍጐ መጨረሻውን አክፍቶበታል፡፡ ተፈጥሯዊ በሽታው በሰው ሰራሽ ችግር ወደ ፀና ህመም ተሸጋግሮ ቆይቷል፡፡ ሚያዝያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ገና የ50 ዓመት ጐልማሳ ነበር፡፡ በፖለቲካ ያገኛቸው ክብር፣ ተሰሚነት፣ ገሳጭነት፣ ግርማ ሞገስ፣ ተከባሪነት... ከትከሻው ላይ በረው ጠፍተው ነበር፡፡ የትኛው ባለጊዜ ደራሲ ላይ አርፈው ይሆን?