Sunday, 03 September 2023 21:10

ሥልጣን በማን እጅ ቢሆን ይሻላል? እያጣላ አስቸግሯል።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 ዐዋቂዎችና ታዋቂ ሰዎች ለመረጡት? ዕጣ ለደረሰው? ሕዝብ ለጮኸለት? ወይስ በጦር ሜዳ?
“ምን ዓይነትና ምን ያህል ሥልጣን ለምን አገልግሎት?” ብለን ካልጠየቅን ግን፣ የሥልጣን መወጣጫው ዕጣ ወይም ምርጫ  ቢሆን ልዩነት የለውም።
መጽሐፈ ሳሙኤል፣ የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ ማን እንደሆነ ይነግረናል። ሳኦል ይባላል። ለንግሥና እንዴት እንደተመረጠ የሚገልጹ ሦስት ትረካዎችን በተከታታይ ያስነብበናል። የመጀመሪያውን  እንመልከት።
እንግዲህ፣… እንደ ዳኛና እንደ ሃይማኖት መሪ ሆኖ ሲሰራ የነበረው ሳሜኤል ሸምግሏል። የየአካባቢው ታዋቂ ሰዎች ተሰብስበው መጡና፣ ንጉሥ እንፈልጋለን አሉት።
ዳኝነት የሚሰጥና አገርን ከወረራ የሚከላከል  ንጉሥ ሊኖረን ይገባል። እንደ ሌሎች ሕዝቦች እኛም እናንግሥ ብለው ጠየቁት።
ሳሙኤል ተናደደባቸው።
ንጉሥ አንዴ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ወደ ባርነት ሊያወርዳቸው እንደሚችል ነገራቸው።
ልጆቻችሁን ለጦርነት ይወስዳል፤ ሴቶችን አገልጋይ ያደርጋቸዋል። ከንብረታችሁ እያፈሰ ይወስዳል አላቸው።
የአገሬው ሰዎች ይህን ሰምተዋል። እንመልከት። ግን ንጉሥ ይቅርብን አላሉም። በዚህም ሳሙኤል ተበሳጭቷል። ግን ሌላ አማራጭ አልታየውም።
አስጠንቅቃቸው፤ ከዚያም አንግሥላቸው ተብሎ ከእግዚሄር እንደተነገረው ትረካው ይገልጻል። ከዚያስ?  እግዚሄር ለሳሙኤል እንዲህ ይለዋል።
“ነገ በዚህች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድልሃለሁ። የሕዝቤን (መከራ) ተመልክቻለሁና ልቅሶአቸውም ወደ እኔ ደርሷልና፣ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ። ሕዝቤንም ያድናል… (1 ሳሙ 9፡ 16)።
ንጉሥ እንፈልጋለን የሚለው ጥያቄ፣ በአንድ በኩል እንደ ሌሎች ሕዝቦች “የንጉሥ ባለቤት” የመሆን ጉጉት ይመስላል። የማንገሥ አምሮት ኃይለኛ ነው። አንዱን ትቶ ሌላውን የማንገሥ ሥልጣን የአንዲት ቀን ሥልጣን ናት። ግን ብዙ ሰዎች ያችን ሥልጣን ይፈልጓታል። “ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ነው” ይሉባታል። ባሻቸው ጊዜ ማንገስ ብቻ ሳይሆን መሻር እንደሚችሉ የሚያስቡ ሰዎች ምን ያህል ባለሥልጣንነት ስሜት እንደሚኮፈሱ ይታያችሁ። የሕዝብ የማንገሥ አምሮት ማለት እንዳሻቸው የመሾምና የመሻር ገደብ የለሽ የሕዝብ ሥልጣን ማት ነው። እንዲህ ዓይነት የሥልጣን  ጥም በጣም መጥፎ የአምባገነንነት መንገድ እንደሆነ አይባቸውም። አምባገነን ንጉሥ ይመጣላቸዋል።
በሌላ በኩል ግን፣ የማንገሥ ፍላጎት የሕልውና ጉዳይ ነው። በወረራ ተቸግረዋል። ሰላም አጥተዋል። ማልቀሳቸውም ለዚህ ነው። መንግሥት እንፈልጋለን ለማለት ነው። ለንግሥና የተመረጠው አለቃ እስራኤልን ከወረራ እንደሚያድን እግዚሄር ለሳሙኤል እንደገለጸለትም ተተርኳል።
ከንግሥና ጋር ወይም ከመንግሥት ጋር አብረው የሚመጡ አደጋዎችስ? ማንኛውም የመንግሥት ዐይነት ሁሌም በዜጎችና በአገር ላይ አደጋ ሊያመጣ ይችላል። እናም አስጠንቅቃቸው ተብሏል።
በአጭሩ፣ የመንግሥት አገልግሎት ከነአደጋው ነው።
መንግስት አስተማማኝ የጥበቃ ዘብ ነው፤ አምባገነን ዘራፊም ይሆናል።
የመንግሥት ትክክለኛ አገልግሎትና ኃላፊነት፣ ሕይወትንና ንብረትን መጠበቅ፣ አገርንና ድንበርን ከጥቃት መከላከል፣  ሕግንና ሥርዓትን አክብሮ ማስከበር ነው ።
የሚነግሠው ኃላፊነትን ለመሸከም…
ሥልጣን የሚያገኘውም ከነገደቡ ከሆነ…
ጦር ኃይል የሚያደራጀው ሕግና ሥርዓትን አክብሮ ለማስከበር ከሆነ…
ኃላፊነቱንና ስራውን እንዳያጓድል…
ሥልጣኑን ደግሞ ከልኩ እንዳያሳልፍ የመቆጣጠሪያ  ዘዴ ከተፈጠረ…
መንግሥት አስተማማኝ የጥበቃ ሰራተኛ ይሆናል።
በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ የማዘዝ ሳይሆን… የእያንዳንዱን ሰው ሕይወትና ንብረት ከጥቃት የመጠበቅ ሥልጣን ይኖረዋል። የጥበቃ ዘብ ይሆናል።
ለጥበቃ ስራ ማንን እንዴት እንቅጠር? የሚለው ጥያቄ ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ እንዳልሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል። ዋናው ጥያቄ መንግሥት የጥበቃ ሰራተኛ መሆን አለበት? ወይስ የሕይወታችን፣ የንብረታችን አዛዥ ይሁን? የሚል ጥያቄ ነው።
ሥልጣንን ያለ ኃላፊነት አግበስብሶ፣ የጦር ኃይልን ያለ ሕግና ሥርዓት ይዞ መረን የተለቀቀ መንግሥት፣ ከሌሎች ወንጀለኞች ሁሉ የከፋ ገዳይና ዘራፊ ይሆናል። ይህ ማለት ግን ‘መንግሥት ይቅርብን’ ለማለት አይደለም። ከመንግሥት አስፈላጊነት ጎን ለጎን አደገኛነቱንም መገንዘብና አስቀድሞ መጠንቀቅ ነው መፍትሔው።
ንጉሥ አንግሥላቸው (መንግሥት ያቋቁሙ)። ከወረራ ሊያድናቸው ይችላል።
ነገር ግን ከንግሥና ወይም ከመንግሥት ጋር አብረው ሊመጡ የሚችሉ የዝርፊያና የባርነት አደጋዎችንም ንገራቸው፤ በጽሑፍ አስቀምጥላቸው… የሚል ነው የትረካው መልእክት።
በዛሬ ቋንቋ እንግለጸው ከተባለ…
የአምባገነንነት አደጋዎችን አስተምራቸው። መንግሥት የሰዎችን ሕይወትና ንብረት እንዲያከብር፣ ለሕግና ለሥርዓት ተገዢ እንዲሆን የሕገ መንግሥት መነሻ ሐሳብ አዘጋጅላቸው… እንደማለት ይመስላል።
ሳሙኤል ባይጥመውም፣ አሻፈረኝ አላለም። በእግዚሄር ተገልጦለት ሳኦልን ለንግሥና ይቀባዋል (የሳኦል አናት ላይ ቅባት አፈሰሰለት)። ምን ቀረ? ክብረ በዓል ያስፈልጋል። “ንግሥና በዕጣ” የሚመጣው እዚህ ላይ ነው።
የዘረኝነት በሽታ መፍትሔ ካልተበጀለት አገርን ይበትናል።
ሳሙኤል፣ “በዓለ ሢመት” ወይም የንግሥ ሥነ ሥርዓት ለማካሄድ ሕዝቡን ሰበሰበ።
አስገራሚው ነገር፣ ሳሙኤል ሳኦልን ወደ መድረክ አላወጣውም። “ይሄውላችሁ ንጉሣችሁ” ብሎ ለሕዝቡ አልተናገረም። ለሳኦል ዘውድ አልደፋለትም። ከሳኦል ጋር እንዳልተገናኘና ምንም እንዳልተፈጠረ ሆኗል- ሳሙኤል። ከእገሌ ነገድ አነገሥክብን የሚል የዘረኝነት ውዝግብ እንዳይመጣበት አስቦ ሊሆን ይችላል።
ሳሙኤል…ንጉስ ለመሠየም ምርጫ ማካሄድ ጀመረ። ምርጫው ደግሞ በዕጣ ነው።
ለየክልሉ ወይም ለየነገዱ ዕጣ ተጣለ።  ለየነገዱ? ይሄ በጎሳ የመቧደንና ዘር የመቁጠር አባዜ፣ አስቸጋሪ ነው። መቼስ ምን ይደረግ? ሳሙኤል ዕጣ በማውጣት የዘረኝነት ጣጣዎችን ለመሸወድ መሞከሩ፣ ሌላ መፍትሔ ባያገኝ ነው። ፍቱን መድሃኒት ሁነኛ መፍትሔ እንደይማሆን ወደፊት ይታያል። እስራአኤል ተከፋፍላ ለምዕተ ዓመታት ሰላም ያጣችው ለምን ሆነና? የይሁዳ ነገድ፣ የቢኒያም ነገድ፣ የሌዊ ነገድ… ምናምን በሚል ሰበብ ነው። ለጊዜው ግን፣ ችግሩን በዕጣ መሸወድ ይቻላል።
ዕጣው ለቢኒያም ነገድ ደረሰ። እንደ ማጣሪያ ነው። በሁለተኛው ዙር ደግሞ  ከቢኒያም አገር ለተለያዩ ጎሳዎች  እንደገና ዕጣ ወጣ። ከዚያም ወደ ግለሰቦች ወደ ፍጻሜው ተሸጋገረ።
የመጨረሻው ዕጣ ተጣለ።
ንግሥና በዕጣ ለሳኦል ደረሰ (ሳሙ 10፡ 20-21)።
ዕጣ በጥንት ዘመን እንደ ታማኝ ፈራጅ ታመንበት ነበር። የዕጣ ዳኝነት የማያዳላ ዳኝነት ነው ይባል ነበር። ‘ኋላ ቀርነት ነው’ ብለን ነገሩን ለማናናቅ እንቸኩል ይሆናል። ነገር ግን፣ ‘ትክክለኛ የዳኝነት ዘዴ’ ሊሆን እንደሚችል አትርሱ። የዕቁብ ዕጣ አንድ ምሳሌ ነው። ለነገሩ…
የፖለቲካ ምርጫዎችስ በዕጣ ቢሆኑ ምን ችግር አለው? ያልተሞከረ እንዳይመስላችሁ! በግሪክ የዲሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ መሪዎችን በዕጣ መምረጥ የተለመደ አሰራር ነበር።
የዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃና የስራ ልምድ መመዘኛዎች ይኖራሉ። እነዚህን የብቃት ደረጃዎች የሚያሟሉና ወንጀል ሰርተው የማያውቁ ሰዎች ለምርጫ መወዳደር ይችላሉ።
ዕጣ ውስጥ ይገባሉ። ያለ አድልዎ ዕጣ ይዳኛቸዋል። የሥልጣን ሽኩቻና ንትርክ፣ ብሽሽቅና ጥላቻ፣ ሤራና የመጠፋፋት ዘመቻ… በአጠቃላይ የፖለቲካ ቁማር ለመቀነስ አይረዳም? ምናልባት ጊዜያዊ እፎይታ ሊያመጣ ይችላል። ነገር ግን መፍትሔ አይሆንም። ለምን ቢባል…
መንግሥት ኃላፊነቱን ትቶ የሥልጣን ገደቡን ጥሶ በዘፈቀደ እንዳሰኘው መሆን ከቻለ፣ ሥልጣን የያዘበት የምርጫ አሰራር ምንም ሆነ ምን ብዙም ልዩነት የለውም። መንግሥት እንዳሰኘው መሆን የቻለ ጊዜ አስፈሪው አደጋ በእውን ተከሠተ ማለት ነውና።
ለዚህም ነው ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ የመንግሥት ትክክለኛ ስራና የሥልጣን ገደቡ ላይ ያተኮረ መሆን ያለበት።
የሆነ ሆኖ፣ ሳኦል በዕጣ ለንጉሥነት እንደተመረጠ ትረካው ይነግረናል። ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የመጡ ሰዎች ከነጓዛቸው በተሰበሰቡበት በዓለ ሢመት ላይ፣ የሳኦል ስም ተጠራ። በአካባቢው የለም። ሳኦል ማን ነው? ሳኦል የት ነው? ወዴት ገባ? በቁሳቁስ ተከልሎ በዕቃዎች መሐል ተደብቆ ተገኘ። ከንግሥና ለማምለጥ አስቦ ነው?
ፖለቲካ ከእልፍ የሰው ዐይነት ጋር እያገናኘ የማስተቃቀፍና የማላተም ባሕርይ ስላለው፣ እጅግ ካልተጠነቀቁ በቀር የግል ሕይወትን ያስረሳል። ከእኔነት መንፈስ ጋር ያራርቃል። ነፍስን የመንጠቅ ክፉ ኃይል አለው። ሳኦል ከንግሥና ለመሸሽ ቢሞክር አይገርምም። በተለይ የፖለቲካ ዝንባሌ ለሌለው ሰው ፖለቲካ ቢቀርበት ይሻለዋል።
በዕቃዎች መሐል ተሸሽጎ ከንግሥና ለማምለጥ መሞከር ግን ከልብ አይመስልም። ለወጉ ያህል ከሆነ እሺ። በጨዋ ወግ ‘እኔ ማን ነኝና ነው ንጉሥ የምሆነው?’ ብሎ ለመግደርደር ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ወጉ ተሟልቷል። ሳኦል ወዲያውኑ እዚያው ተገኘ።
ለሕዝቡም ታየ። ከሕዝቡ ሁሉ በቁመት ይበልጣል።
ሳሙኤልም በሳኦል ቁመና የተደሰተ ይመስላል። ለተሰብሳቢዎቹም ተናገረ።
“ከሕዝቡ ሁሉ እርሱን የሚመስል እንደሌለ እግዚሄር የመረጠውን ታያላችሁን? አላቸው።
ሕዝቡም ሁሉ ‘ንጉሥ ሕያው ይሁን’ እያሉ እልልታ አደረጉ (1 ሳሙ 10፡ 24)።
የሃይማኖታዊው መጽሐፍ አተራረክ ውስጥ፣ “ሕዝብ ሁሉ” ማለት እያንዳንዱ ሰው ሁሉ ማለት ሊሆን ይችላል። ብዙ ሰው፣ አብዛኛው ተሰብሳቢ እንደማለት ይሆናል። እንደዘወትር አነጋገርና እንደ ልማዳዊ አባባል ልንቆትረው እንችላለን።
እና ሳኦል  ለንግሥና ዕጣ ሲደርሰው፣  ገሚሶቹ ተደስተዋል። ንጉሡን ወደውታል። ለነገሩ ‘ሺ ዓመት ይንገሥ’ ብሎ መጮኽ የተለመደ ወግ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። አሳልፈው አስተርፈው የዘላለም ሕልውናን ተመኝተውለታል። ዘላለም እንደማይይኖር፣ ሺ ዓመት እንደማይነግሥ ይታወቃል። ‘ሹመትህ ይጽና፣ ዕድሜህ ይርዘም’ የሚል ምኞትንና ምርቃትን የሚገልጽ ምሳሌያዊ አባባል ነው።
በጥሬው ቃል በቃል ለሚያምኑበት ሰዎች ደግሞ የዘወትር መፈክራቸው ይሆናል። ንግሥናው ለሺ ዓመታት ከአባት ወደ ልጅ ይተላለፋል ብለው ይተረጉሙታል። ወይም ንጉሡ ዘላለማዊ አምላክ ነው ብለው ያምኑበታል።
ንጉሥ ይመጣል፣ ይሄዳል፤ አገር ጸንቶ ይቀጥላል የሚል ትርጉምም ይኖረዋል። ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ይመረጣሉ፣ ይወርዳሉ፡፡ መንግሥት ግን እንደጸና ይኖራል። ሊቀ መንበር ሥልጣን ይወስዳል፤ ይነጥቁታል፤ ፖርቲው ግን ዕድሜውን ያራዝማል…
የሺህ ዓመት ምኞት፣…በተለይ በአስቸጋሪ የለውጥ ጊዜ ላይ፣ ራስን ለማጽናናት ሊያገለግል ይችላል። አገርና መንግሥት ወይም ሕግና ሥርዓት፣ ተቋማትና ባህሎች ለሺ ዓመታት ይቀጥላሉ የሚል መልእክት ያስተላልፋል።
ሳኦል ሲነግሥም፣ “ሕያው ይሁን” በማለት ብዙ ሰዎች እልል ብለዋል።
የተቃወሙም ግን ነበሩ። ለንጉሥነት የሚመጥን ሆኖ ስላልታያቸው፣ ‘ሳኦል አይንገሥብን’ ብለው እንደተናገሩ ትረካው ይጠቁመናል።
ገሚሱ ሕዝብ በእልልታ ንግሥናውን ማጽደቁ አይገርምም።
መንግሥት ትክክለኛ አገልግሎቶችን ሊያከናውን ይችላል።
‘የወደድነው መንግሥት ሥልጣን ከያዘ እላፊ ጥቅም እናገኛለን፤ ያልፈልናል’ ብለው የሚያስቡም ይኖራሉ።
ገሚሱ ሕዝብ  ሳኦል አይንገሥብን ብሎ መቃወሙም አይገርምም።
መንግሥት አደገኛ ሊሆን ይችላል።
‘ያልወደድነው መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ያልቅልናል’ ብለው ቢሰጉ አይፈረድባቸውም።
መንግሥት ትክክለኛ አገልግሎቶቹን ቢያጎድል፣ እላፊ ሥልጣን ለራሱ ቢጨምር ምን ማድረግ ይችላሉ? ስራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ለመቆጣጠርና ሥልጣኑን ለመገደብ ከወዲሁ አስተማማኝ ዘዴ አልፈጠሩም።
በዓለ ሢመቱ ሳሙኤል እንዳሰበው በሥርዓቱ ተሟልቶ የተጠናቀቀ አይመስልም። እንዴት እንደተቋጨ ትረካው አይነግረንም። ሕዝቡ ወደየ አገሩ እንደተበታተነ ይገልጽልናል።
ሳኦልም ወደ መኖሪያ መንደሩ ሄደ። ወደ እርሻ ስራው ተመለሰ። ንግሥናው የጸደቀለት ሹመቱ የጸናለት አይመስልም።
ከወር በኋላ ሌላ አጋጣሚ ተከሠተ። ከጎረቤት አገር ንጉሥ ጋር ጸብ ተፈጠረ። ጦርነት መጣ። ሳኦል በመሪነት ዘመተ። ድል አደረገ። ያኔ የሕዝብ ፍቅር አገኘ።
ፍቅራቸውም ልክ አልነበረውም።
የሳኦልን ንግሥና የሚቃወም ሰው ሁሉ መሞት አለበት ብለው ዐወጁ። በሳኦል ስም እንገድላለን ብለው ፎከሩ። ይህን የሚናገሩት ለሳሙኤል ነው። የሚያረጋጋቸው ግን ሳኦል ነው።
ሕዝቡም ለሳሙኤል፣ ‘ሳኦል አይንገሥብን ያሉ እነማን ናቸው?’ አውጧቸውና እንግደላቸው አሉት።
ሳኦልም፣ ዛሬ እግዚሄር ለእስራኤል ማዳንን አድርጓልና ዛሬ አንድ ሰው አይሞትም አለ።
ሳሙኤልም ሕዝቡን፣ ኑ ወደ ጌልገላ እንሂድ። በዚያም መንግሥቱን እናድስ አላቸው።
በእግዚሄር ፊትም በጌልጌላ አነገሡት (1 ሳሙ 11፡ 12-15)።
ጦርነት የመንግሥት ስራ ነው።  የድክመት ምልክትም ነው።  
የመጀመሪያው የንግሥና ሙከራ አልተሳካም ነበር። በዕጣ ለንጉሥነት የተመረጠ ጊዜ እልል ተብሎለታል። ግን ከእልልታ አላለፈም። ጦርነት ሲመጣ ግን ሳኦል በውጊያ ላይ ብቃቱን አስመሰከረ። ጦርነት ደግሞ የመንግሥት ስራ ነው። ግን የድክመት ምልክት ነው።
ወታደራዊ ብቃት ያስፈልጋል። ነገር ግን ወራሪና ጸብ ፈላጊ መሆን የለበትም።
እንዲያውም ጦርነት የዘወትር ስራ እንዳይሆን አስተማማኝ ዘዴ መፍጠርና ሰላምን ማስፈን የመንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ነው። ሰላምን የመሰለ ነገር የለም ብሎ መዘመር አለበት። የሰላም መዝሙር ሁልጊዜ ሰላምን ያሰፍናል ማለት እንዳልሆነ ግን ይታወቃል።
በአንድ በኩል መንግሥት ዜጎችን የሚያስጨንቅ ክፉ አምባገነን እንዳይሆን ሥልጣኑን የሚገድብ ሥርዓት እየገነቡ ወደ ሥልጡን ፖለቲካ መጓዝ ያስፈልጋል። የሰላም መንገድ ነውና የጦርነት ሰበቦችን ለማምከን ይረዳል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለሰላም ዝማሬ ጆሮ የሌላቸው፣ ‘የፍጻሜው ጦርነት ነው’ ብለው የሚፎክሩ ወረራዎችንና ዓመፀኞችን ማክሸፍ፣ ጦርነትንና ሥርዓት አልበኝነትን ከሩቁ ማስቀረት አለበት።
እንዲህም ሆኖ፣ መተንፈሻና መፈናፈኛ የማይሰጥ፣ ቀን ከሌት የሚጨፈጭፍና የሚያሰቃይ አምባገነን ሲበረታ፣ ከጦርነት ውጭ ሌላ አማራጭ ሊጠፋ ይችላል።
ወራሪዎችና ዓመፀኞች ገፍተው ከመጡም ጉዳቶችን ለመቀነስና በአጭር ለመግታት፣ ሌላ አማራጭ ከሌለ… ያኔ ጦርነት የግድ ይሆናል። የመንግሥት ኃላፊነት ነው።
ሳኦል ይህን የመንግሥት ስራ በብቃት አከናውኖ አሳይቷል። በዚሁ አጋጣሚም የሕዝብ ፍቅር አግኝቷል። ሹመቱ ታድሶለታል። ንግሥናው በተሟላ ሥርዓት ተፈጽሟል። እስከ መቼ ይዘልቃል? እንየዋ!
አንደኛ ነገር፣ የሕዝብ ፍቅር እንደ አውሎ ነፋስ…ዛሬ እዚህ ነው። ነገ እዚያ ነው። የሕዝብ ጩኸት ዛሬ ለተቃውሞ ነው። ነገ ለፍቅር ነው።  እንደ ተለዋዋጭ ሕልም ነው።
ሁለተኛ ነገር፣ ጦርነት አሳሳች ነው። ጦርነት የድክመት ምልክት እንደሆነ ብዙ ሰው ይረሳዋል።
ብቃትን ገንብቶ፣ ሁነኛ ዘዴ ፈጥሮ ጦርነትን ከሩቁ ማስቀረት ነው ዋናው ቁምነገር። አስተማማኝ ሰላም ይኖራል ማለት ነው። የመንግሥትንና የአገርን ብቃት ያሳያል። ይህ ካልተሳካ ግን የአገርና የመንግሥት ድክመት ከየአቅጣጫው ጦርነትን የሚጋብዝ ሰበብ ይሆናል።
አሳዛኙ ነገር፣ በጦርነት ድል ያደረጉና የሕዝብ ድጋፍ ያገኙ ባለሥልጣናት የጦርነትን አሳሳችነት ይዘነጉታል። ጦርነት የድክመት ምልክት መሆኑን ይረሳሉ። በቀላሉ ወደ ስህተትና ወደ ጥፋት ይገባሉ። ከጦርነት አንዳች ትርፍ የሚያገኙ ይመስላቸዋል። በጊዜያዊ ስሜት ሕዝብን ለማነሣሣትና ለማሰባሰብ ይጠቅማቸው ይሆናል። እየዋለ ሲያድር ግን፣ ሕይወትን፣ አካልንና ንብረትን ብቻ ሳይሆን፣ ሥነ ምግባርን፣ የጨዋነት ባህልንና የሰብዕና ክብርን ጭምር የሚያሳጣ እርግማን ይሆናል። ሲሆንም አይተናል።
በእርግጥ፣ የጦርነትን ክፋት በእውን ለማስተዋልና እውነታውን ለመገንዘብ ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ። በጦርነት ዓለም ውስጥ ገብተው ሌላ ነገር ላለማየት በጭስ ተከልለው ከአንድ ውጊያ ሌላ ውጊያ ይወልዳሉ። ሥልጣናቸውን ከሥራቸው መንጭቆ እስኪወስድባቸው ድረስ እውነታው እንዳይገለጥላቸው ዐይናቸውን ይጨፍናሉ።
የድክመት ምልክት ነውና፣ ሥልጣናቸውን የሚያሳጣ ጦርነት፣ ለሌላ ሰው የሥልጣን መሰላል ይሆንለታል።
እንደተለመደው ሳኦል ጦርነት ላይ ነበር።  አሁን ግን እንደሌላው ጊዜ አይደለም። ፈጣን ድል አላገኘም። ከአርባ ቀናት ጭንቀት በኋላ ድል የቀናው በዳዊት ብርታት ነው። የዳዊትን  ጎልያድን አሸንፎ ጣለ፤ ድል ተገኘ።
ሳኦል ጦርነቱን በድል ቢያጠናቅቅም፣ ድክመቱን የሚያጋልጥ ሆኖበታል። ዳዊት ድንገት ባለ ዝና የሆነውም በዚሁ ጦርነት ነው። የኋላ ኋላም በሽምቅ ጦርነት ንግሥናን ከሳኦል ይወስዳል።
አሳዣኙ ነገር፣ ዳዊትም በተራው ሥልጣን ከያዘ በኋላ ጦርነትን ከሩቁ ለማስቀረትና በአጭር ለመግታት አልቻለም። የራሱ ልጆች ሳይቀሩ አምጸውበታል።

Read 1005 times