Saturday, 04 July 2015 10:53

የፌስቡክ ጸሃፊያን በመጽሐፍት እየመጡ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በፌስቡክ  ለአመታት የተለያዩ ጽሁፎችን በማቅረብ የሚታወቁ ጸሃፊያን በጋራና በተናጠል ያሳተሟቸውን የግጥም፣ የአጫጭር ልቦለዶችና የወጎች ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ እያበቁ ነው፡፡
የአምስት ገጣሚያንን ስራዎች ያሰባሰበው “መስቀል አደባባይ” የተሰኘ የግጥም መድበል ባለፈው ማክሰኞ ገበያ ላይ የዋለ  ሲሆን፣ በፌስቡክ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂሶችንና ወጎችን በማቅረብ ተወዳጅነትን ያተረፈችው  ህይወት እምሻውም “ባርቾ”በሚል ርዕስ  የአጫጭር ልቦለዶችና የወጎች ስብስብ መጽሃፍ አሳትማለች፡፡
በግጥም መድበሉ የአሌክስ አብርሃም፣ ዩሃንስ ሃብተ ማርያም፣ ረድኤት ተረፈ፣ ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ እና ፈቃዱ ጌታቸው ግጥሞች የተካተቱ ሲሆን፣ ገጣሚያኑ እያንዳንዳቸው አስር ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡ 150  ገጾች ያሉት የግጥም መድበሉ፣ በ45 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡
የግጥም ስራዎቹን በማሰባሰብ ለህትመት ያበቃው ገጣሚና ደራሲ አሌክስ አብርሃም በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፣ መስቀል አደባባይ በቀጣይም በቅጽ ተከፋፍሎ ለህትመት የሚበቃ ሲሆን፣ በፌስቡክም ሆነ በተለያዩ መድረኮች የሚታወቁ ወጣትና አንጋፋ ጸሃፊያንን የግጥም፣ የወግና የልቦለድ ስራዎችን የሚያካትት ይሆናል፡፡ የመስቀል አደባባይ ሁለተኛ ቅጽ ዝግጅት በከፊል መጠናቀቁንም አሌክስ አብርሃም ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ወጎችን፣ አጫጭር ልቦለዶችንና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጣጥፎችን  በፌስቡክ በስፋት በማቅረብ የምትታወቀውና በርካታ ተከታዮችን ያፈራችው ህይወት እምሻው፣ የመጀመሪያ ስራዋ የሆነውን ባርቾ የተሰኘ የወጎችና የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ፣ ለህትመት አብቅታለች፡፡ 31 ወጎችን፣ 8 ልቦለዶችንና 13 የመሸጋገሪያ አጫጭር ልቦለዶችን ያካተተውና 256 ገጾች ያሉት መጽሃፉ፣ የመሸጫ ዋጋው 60 ብር እንደሆነ ደራሲዋ ለአዲስ አድማስ የገለጸች ሲሆን የፊታችን ሐሙስ  በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚመረቅ ተናግራለች፡፡
በዕለቱ ከ11፤30 ሰኣት ጀምሮ በሚካሄደው የምረቃ ስነስርዓት ላይ በመጽሃፉ ከተካተቱት ታሪኮች አንዱ በአጭር ድራማ መልክ ለታዳሚዎች የሚቀርብ ሲሆን፣ የሙዚቃና የግጥም ስራዎችም ይቀርባሉ፡፡
ፌስቡክ ለበርካታ ወጣትና አንጋፋ ጸሃፍያን ስራዎቻቸውን ለአንባቢ ለማድረስ ሁነኛ አማራጭ እየሆነ የመጣ ሲሆን በማህበራዊ ድረገጹ ላይ በመጻፍ የሚታወቁ በርካቶችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስራዎቻቸውን በመጽሃፍ መልክ እያሳተሙ በስፋት ለንባብ ማብቃት ጀምረዋል፡፡
በፌስቡክ ከሚታወቁና ከዚህ ቀደም ስራዎቻቸውን ለህትመት ካበቁ ጸሃፊያን መካከል፣ አሌክስ አብርሃም፣ በረከት በላይነህ፣ ሮማን ተወልደ ብርሃን፣ ዮሃንስ ሞላ፣ ሃብታሙ ስዩም፣ ቢኒያም ሃብታሙ፣ ትዕግስት አለምነህ፣ ሄለን ካሳ፣ ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ፣ ሜሮን አባተ፣ ብሩክታዊት ጎሳዬ፣ ስመኝ ታደሰ እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

Read 2318 times