ቱፓክ መድረኩ ላይ ለስኑፕ ዶግ አጃቢ ሆኖ የራፕ ዘፈኖችን በመጫወት ታዳሚውን ማዝናናቱን ያወሳው ዋሽንግተን ፖስት፤ ሙከራው ታላቅ ድምፃዊያን በነበሩበት ዘመን ላልተወለዱና ህፃን ለነበሩት ሁሉ የማያውቋቸውን ታላላቅ አርቲስቶች የሚያስተዋውቅ ድንቅ ፈጠራ ብሎታል፡፡ ከዘመኑ እውቅ ራፐሮች አንዱ የሆነው ናስ ከሟቹ ቱፓክ ሻኩር ጋር ጠበኛ ቢሆንም በሆሎግራም መድረክ ላይ ለመጫወት የቻለበትን ሁኔታ በይፋ አድንቋል፡፡ ዊዝ ካሊፋ፣ ጄይዚ እና ሌሎች ዝነኛ ራፐሮቹም በፈጠራው እንደተማረኩ ተናግረዋል፡፡ በሆሎግራም ቅንብር የቱፓክ ዳግም መነሳት ዶር ድሬ እና ስኑፕ ዶግ ለራፕ ሙዚቃ ፈጠራ ዛሬም ቢሆን እየደከሙ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል ራፐሮቹ፡፡ የመድረክ ቅንብሩን “የራፐሮች ድምቀት” በሚል ርእስ አድንቆ የፃፈው “ዎል ስትሪት ጆርናል” በበኩሉ፤ ከ15 ዓመት በፊት የሞተው ቱፓክ በዚህ የቴክኖሎጂ ቅንብር መመለሱ ምናልባትም ለሌሎች ተመሳሳይ ስራዎች መነቃቃትን ይፈጥራል ብሏል - የቢትልስ የሙዚቃ ቡድን በሞት የተለያቸውን አባላቸውን ጆን ሌነን፤ የጃክሰን ወንድማማቾች ማይክል ጃክሰንን እንዲሁም ጂሚ ሄንድሪክስ፣ ዊትኒ ሂውስተንና ሌሎች ሟች ሙዚቀኞች እንደቱፓክ በሆሎግራም ቴክኖሎጂ ኮንሰርት የሚያቀርቡበት መድረክ እንደሚፈጠር በመጥቀስ፡፡
የቱፓክ ሻኩር የሆሎግራም ቅንብርን ለመስራት አራት ወራት የፈጀ ሲሆን 400ሺ ዶላር ገደማ ወጪ እንደፈጀ ተገልጿል፡፡ ቅንብሩን የሰራው ዲጅታል ዶሜን ግሩፕ የተባለ ኩባንያ ሲሆን የመድረክ ላይ ትእይንቱ በዩቲውብ መታየቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎች እንዲመለከቱት እድል ፈጥሯል ተብሏል፡፡ ኩባንያው ሌሎች የሞቱ ዝነኛ የዓለም አርቲስቶችን ሥራዎች በተመሳሳይ መንገድ ለማሰራት እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል፡፡