Friday, 08 December 2023 20:18

የቢኒያም ወርቁ "ትራንዚት" ትያትር ሊመረቅ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የቢኒያም ወርቁ "ትራንዚት" ትያትር ሊመረቅ ነው
የመግቢያ ዋጋ 1,000 ብር
በአይነቱ ልዩ የሆነው የቢኒያም ወርቁ "ትራንዚት" ትያትር ታሕሳስ 4/2016ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰአት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ሊመረቅ እንደሆነ አሜዜንግ ፕሮሞሽንና ኢቨንት ዛሬ ሕዳር 28/2016ዓ.ም በሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል ።
አሜዚንግ ፕሮሞሽንና ኢቨንት ዳግም እየተናነቃቃ ያለውን የሀገራችንን የመድረክ ቴአትር ወደላቀ ከፍታ ለማሻገርና የተመልካቹን ፍላጎት ለማርካት በማሰብ በሀገራችን የትወና ታሪክ በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን እጅግ ተወዳጅ የሆኑትን ተዋንያን
ሰለሞን ቦጋለ
ሳምሶን ታደሰ(ቤቢ)
* ሃና ዮሐንስ
* ሸዋፈራሁ ደሳለኝ በአንድ መድረክ የሚያሳትፍ ሲሆን የዚህ ትያትር
*ፕሮዲዩሰር= አሜዚንግ ፕሮሞሽንና ኢቨንት
*የክብር አጋር =ፀደይ ባንክ
*ደራሲና አዘጋጅ =ቢኒያም ወርቁ ነው።
የ"ትራንዚት ትያትር አጽመ-ታሪክ (SYNOPSIS) እነሆ
ካልደነገጥክ አትሰራም!
ካልሰራህ አትተባበርም!
ካልተባበርክ አታሸንፍም!
በጊዚያዊ ችግር አብሮነት ፍቅር ተስፋ እና የአላማ ጽናት ቢፈተንም እጅ ለእጅ በመያያዝ በየትኛውም መስክ አብሮ በጋራ በመቆም ሁሉንም ችግር ማሸነፍ እንደሚቻል የሚሳይ ትያትር ነው ።
የታሪክ ውቅር፤ ... የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍና የመጨረሻውን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ቱኒዝያ ለመሄድ የ12 ሰዓት ትራንዚት ጣልያን ላይ ያደርጋል፡፡ እኩል መውጣት አልያም ማሸነፍ ብድኑን ያሳልፈዋል፡፡
የትያትሩ መቼት ላይ ...
ጣልያን ላይ አራት ተጫዋቾች ከቡድኑ ተነጥለው ይጠፋሉ፡፡ ሌሎች ተጫዋቾችም ሊጠፉ እየተዘጋጁ መሆኑ ተስፋ አስቆራጭ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ከሚጠፉት ተጫዋቾች መካከል የቡድኑ አምበል ሲሳይ ረጋሳ ከቡድኑ አጥቂ መንሱር ጋር አንድ ክፍል ተጋርተዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ለስደት ምክንያት ሆነው ከአገራዊ ኃላፊነትና ከሀገር ፍቅር መስዋዕትነት ጋር በትያትሩ ይጋጠማሉ፤ ይፈተናሉ፡፡
የቡድኑ አምበል ሲሳይ ረጋሳ የቡድኑ አጥቂ መንሱር ከ40 ዓመት በፊት በአፍላ ወጣትነታቸው በፖለቲካ ስደተኝነት አውሮፓ ሄደው በሆቴል ውስጥ የፀጥታ ሠራተኛ የሆኑት ሻምበል ሺመላሽ፣ የኢኮኖሚ ስደተኛና የመንሱር የልጅነት ፍቅረኛ ንግሥት፣ በአካል መድረክ ላይ የምናያቸው ሲሆን የመንሱር ጎረቤት እርጊቲ፣ የሲሳይ አባት አቶ ረጋሳ፣ የንግሥት እናት እና አባት፣ የሻምበል የስደት ጓደኞች እንዲሁም የአዲስ አበባ አንድ አካል የሆነችው የቄራ መንደር ሕዝብ የዋናዎቹን ገፀ ባሕሪያት ያህል ሀሳባቸው፣ ሕይወታቸው፣ ፍልስፍናቸውና ትግላቸው በጥበባዊ እይታ ተተንትኖ ይቀርባል፡፡
መደምደሚያ
"ትራንዚት" ትያትር - በጥልቅ ፆታዊ ፍቅር በቤተሰብ መሰረት እና በልጆች አስተዳደግ እንዲሁም በየዘመኑ ያሉ የፖለቲካ አስተሳሰቦችና ሂደቶች በሳቅ እና ቁም ነገር እየተዋዛ የሚቀርብበት ትያትር ነው፡፡
የ"ትራንዚት ትያትር ደራሲና አዘጋጅ - ቢኒያም ወርቁ
ማነው?
በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ ትያትር ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የትያትር እና የፊልም ታሪክ ውስጥ በስፋት ከሚጠቀሱ ባለሙያዎች ይመደባል፡፡ በርካታ ፊልሞች ጽፏል፤ አዘጋጅቷል፤ በፊልሞቹም ላይ ተውኗል፡፡በተጨማሪም በትያትር ሥራዎቹም እናውቀዋለን፡፡
ደራሲና አዘጋጅ ቢኒያም ወርቁ፤ ከትያትር ሥራዎቹ መካከል ሜዳሊያ፣ የአልማዝ ቀለበት፣ ዱር ያደረ ፍቅር፣ ማን ለምን፣ ማበዴ ነው፣ መብረቅ ከበርካታ የመድረክ ሥራዎቹ መሃል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከአርባ በላይ ከሆነው የፊልም ድርሰት እና ዝግጅት ሥራዎቹ ደግሞ አዲስ ሙሽራ፣ የትሮይ ፈረስ፣ ቫኬሽን ፍሮም አሜሪካ፣ የፍቅር መንገድ፣ 7ተኛው ሰው እና ሌሎችም በየዘመናቸው የበርካታ ሸልማት ባለቤቶች ናቸው።
 
Read 880 times