Saturday, 24 October 2015 08:35

.....ዛሬም መገለል አልቀረም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    በዚህ እትም ወደ ጅግጅጋ እና ሐረር ተጉዘን ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ በመሰራት ላይ ያለውን እንቅስቃሴና በአጠቃላይም የወላዶችን ሁኔታ ለንባብ ብለናል፡፡
በጅግጅጋ በአንድ የግል የህክምና ተቋም ውስጥ ወላዶችን ለማየት ገባን፡፡ በአንድ ክፍል አንዲት እርጉዝ ሴት በመተኛ አልጋዎች መካከል ምንጣፍ ተነጥፎላት ተኝታለች፡፡ ዙሪያዋን ቤተሰቦችዋ ከብበዋታል፡፡ እርጉዝዋ ሴት ያለችው በቤትዋ ነው ቢባል ይሻላል፡፡ ሁሉም በየፊናቸው ያወራሉ፡፡ አንድዋ ሴት የእርጉዝዋን ወገብ አንድዋ ሴት ደግሞ እግርዋን ሌላዋ ደግሞ እጅዋን ይዘው ያሻሻሉ፡፡ እርጉዝዋ ሴት ምጡ ሲመጣ እያማጠች...ምጡ ተወት ሲያደርጋት ደግሞ የእነሱን ንግግር እያደመጠች ትስቃለች፡፡ ታስጎበኘን የነበረችውን ነርስ ሁኔታውን ስንጠይቃት የሚከተለውን መልስ ነበር የሰጠችን፡፡
ጥ/    ሲ/ር ፋጡማ እነዚህ ቤተሰቦች በሆስፒታል ውስጥ ምጥ ከያዛት ሴት ጋር ምን     ያደርጋሉ?
መ/    የምታምጠው ሴት የምጡዋ ደረጃ ገና ስለሆነ ቤተሰቦችዋ ከብበዋት ምጡን እንድትረሳ     ያጫውቱአታል፡፡ ሆድዋም እንዳይባባ ዘመዶችዋ አብረዋት እንደሆኑ የምታውቅበት     መንገድ
ነው፡፡ የመውለጃ ሰአትዋ ሲደርስ ግን ከመሀከላቸው ወስደን እንድትወልድ እናደርጋለን፡፡
ጥ/ ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ የወላዶች ሁኔታ ምን ይመስላል?
መ/ እንግዲህ እዚህ ክሊኒክ ላይ ብዙ ወላዶች ይመጣሉ ቢያንስ በቀን አንድ ስድስት እና ሰባት          ሰው ይወልዳል በወር ደግሞ እስከ 90 ሰው ይወልዳል፡፡
ጥ/ እናቶች ለእርግዝና ክትትል ወደ እናንተ ሲመጡ ቫይረሱ በደማቸው የመገኘቱ ሁኔታ ምን       ይመስላል?
መ፡ ሁሉም እናቶች መጀመሪያ ሲመጡ የምክር አገልግሎት ተሰጥቷቸው ምርመራ እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ እና ሁሉም እናቶች ፍቃደኞች ናቸው፡፡ አሁን ዘጠነኛ ወር     ላይ ሁለት እናቶችን አግኝተናል አስረኛ ወር ላይ ደግሞ ሶስት እናቶችን አግኝተናል፡፡     ከዛ በኋላ ምንም አላገኘንም፡፡
ሁሉም ማለትም ቫይረሱ በደማቸው  የሚገኝ እናቶች       መድሀኒቱን ጀምረዋል፡፡ ወደፈለጉበት አካባቢ እሪፈር ተፅፎላቸው     በሄዱበትም  መድሀኒቱን ጀምረዋል፡፡ ብዙ ግዜ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ እርጉዝ     ሴቶች     አያጋጥሙም፡፡ ግን አሁን በአምስት ወይም በስድስት ወር ግዜ ስናይ ነው... ሁለት ወይም ሶስት የምናገኘው ፡፡
ጥ/ ልጆቻቸውን በሚመለከትስ እንዴት ነው ክትትል የሚያደርጉት?
መ/ ምንም ችግር የለባቸውም፡፡ እንደውም ከእራሳቸው የበለጠ ልጆቻቸው ላይ ነው ትኩረት     የሚያደርጉት፡፡ መድሀኒቱን ስናስጀምራቸው በደንብ የምክር አገልግሎት ስለምንሰጣቸው እራሳቸው የበለጠ ወደ ልጁ ነው የሚያደሉት ልጁን በደንብ ተከታትለው መድሀኒቱን እንዲወስድ ያደርጋሉ፡
ጥ/ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከሚደርሱ ችግሮች ምን ያህል ተላቀዋል?
መ አሁን ያለምንም ችግር እያዋለድናቸው ነው፡፡ በተለይም ስልጠና የወሰድን አዋላጅ     ነርሶች     የሀኪሙ እገዛ እንኳን ሳያስፈልገን ብዙ ስራዎችን እንሰራለን፡፡ እኔ ለምሳሌ...የደም     ግፊታቸው ከፍተኛ የሆኑ ፣ የደም መፍሰስ ያጋጠማቸው እናቶችን ሁሉ     በሚገባ     አዋልዳለሁ፡፡ ምክንያቱም በስልጠናው ላይ እንደዚህ አይነት ችግሮች ሲገጥሙ     ምን መደረግ እንዳለበት ተምሬያለሁ፡፡ ከፍተኛ እና ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ከሌላ ቦታ     የሚመጡ እናቶች ካልሆኑ በስተቀር በወሊድ ምክንያት እኛ ጋር የምትሞት እናት የለችም፡፡
በሐረር ጠቅላላ ሆስፒታል አንዲት እርጉዝ ሴት አንድ የአራት አመት ልጅ በእጅዋ ይዛ ከወዲያ ወዲህ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ መልኩዋ ብስል ቀይ ነው፡፡ ቁመናዋ እረዘም ያለ እና መልከ ቀና ነች፡፡
መ/    እኔ ወደእዚህ ሆስፒታል የመጣሁት ፀረ ኤችአይቪ (ኤአርቲ) ልወስድ ነው፡፡ የኤች     አይቪ ቫይረስ በደሜ ውስጥ ስላለ ዛሬም ብቻ ሳይሆን በፕሮግራም እየመጣሁ መድሀኒትም እወስዳለሁ ከሐኪም ጋርም እመካከራለሁ፡፡
ጥ/ ባለቤትሽስ?
መ/ ባለቤቴ እዚህ የለም ድሬድዋ ነው ግን እሱ ከቫይረሱ ነፃ ነው
ጥ/ ቫይረሱ በደምሽ ውስጥ መኖሩን ያወቅሽው መቼ ነው?
መ/ ከባለቤቴ ጋር ተገናኝተን ትዳር ከመመስረታችን በፊት መመርመር አለብን ተባብለን     ስንመረመር ነው ያወኩት፡፡
ጥ/ የመጀመሪያውን  ልጅ ስታረግዢ እና ስትወልጂ ምንድነው ያደረግሽው?
መ/ ያን ግዜ ትንሽ ችላ ብዬ ነበር ማለት መድሀኒት ጀምሬ ነበር ግን በጥንቃቄ ጉድለት     ምክንያት የተወሰነ ነገር ተበላሽቶብኛል
ጥ/ ምንድነው የተበላሸው?
መ/ ከወለድኩ ከስድስት ሳምንት በኋላ ለምርመራ መመለስ ነበረብኝ፡፡ ጡት መስጠቱንም     ከስድስት ወር በኋላ ማቆም ነበረብኝ፡፡ ግን በቃ ቤተሰቦች ስለሁኔታው ምንም አያውቁም     ነበር እና የዛን ግዜ ብቻዬን ነበርኩ፡፡ ለቤተሰብ የማሳወቅ ፍላጐቱም አልነበረኝም በቃ     እራሴ ባደረኩት ነገር ክፍተት ተፈጠረ፡፡
ጥ/ የኤችአይቪ ቫይረስ በልጁ ደም ውስጥ አለ?
መ/ አዎን፡፡ አለ፡፡
ጥ/ አሁን የደረስሽ እርጉዝ ነሽ፡፡ እና ካለፈው ስህተትሽ ምን ተምረሻል?
መ/ አሁን በጣም ጥንቃቄ እያደረኩ ያለፈውን ስህተት ላለመድገም እየጣርኩ ነው፡፡ እርግዝናው     ከተጀመረ ጀምሮ ክትትል እያደረኩኝ ነው፡፡ ከከተማ ወጣ ብዬ ወደ ጉርሱም ከተማ ነው     የምኖረው እና እዛ አካባቢ እንደዚህ አይነት ነገሮች በግልፅ አይነገሩም፡፡ እኔም ለዚህ ነው     ለቤተሰቦቼ ያላሳወኩት፡፡
ጥ/ በፊት ምን ነበር የምትሰሪው?
መ/ በአጠቃላይ በፊት ላይ የነበረው ህይወቴ ጥሩ አልነበረም፡፡ በቃ መዝናናት ነው መጣጣት ነ    ው እና ለሕይወቴ የማደርገው ጥንቃቄ አልነበረም ፡፡ ብቻ ጥሩ የህይወት መንገድ ላይ     አልነበርኩም፡፡ አሁን ነው ተረጋግቼ መኖር የጀመርኩት እና እንደዛ ባልሆን ኖሮ ለዚህ     እንደማልዳረግ ስለማስብ አሁን ነው የሚቆጨኝ፡፡ አሁን ግን ያለፈውን ግዜ በመርሳት የወደፊት ህይወቴን እያስተካከልኩ ነው፡፡ በፊት በጣም እታመም ነበር አሁን መድሀኒቱን መውሰድ ከጀመርኩ በኋላ ግን በጣም ጤነኛ ነኝ ብየ አስባለሁ፡፡ ምንም በሽታም አያጠቃኝም ለእራሴ በጣም እጠነቀቃለሁ፡፡
ጥ/ ልጁ መድሀኒቱን ስትሰጪው ምን ይላል?
መ፡ ለምንድነው ሁልግዜ መድሀኒት የምትሰጪኝ ይለኛል፡፡ እናቴም ለምንድነው ይህን መድሀኒት ከአመት አመት የምትሰጪው ትለኛለች፡፡ ሆዱን ስለሚያመው ወይም በተደጋጋሚ ተቅማጥ ስለሚይዘው ነው እላታለሁ እንጂ እውነቱን አልነግራትም፡፡     
ምክንያቱም ከነገርኩት ጥሩ ስሜት ላይሰማት ይችላል ፡፡ የማግለል ነገርም ሊመጣ ይችላል ብዬ ስለማሰብ እንዲሸሹኝ ስላልፈለግሁ ነው፡፡ ዛሬም መገለል አልቀረም፡፡ ልጁም ወደፊት እንዴት አድርጌ መድሀኒት እንደምሰጠው ገና ከአሁኑ እየጨነቀኝ ነው፡፡ እድሜ ሲጨምር ሊያስቸግረን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር ሐኪም     የሚነግረኝን መመሪያ ተቀብዬ እታገላለሁ፡፡
ጥ/ እንዴት ነው የወደፊት ህይወትሽን መምራት የምታስቢው?
መ/ ያው አንደኛውን ብሰሳትም ለሁለተኛው የበለጠ ጥንቃቄ አድርጌ እንደማንኛውም ጤነኛ     ሰው የደስታ ህይወት ለመኖር አስባለሁ፡፡ ከኤችአይቪም የበለጠ ብዙ በሽታዎች እንዳሉ     ሳይ ደህና እንደሆንኩ እና አንድ ቀን እግዚያብሄር ምህረቱን እንደሚሰጠኝ አስባለሁ ፡፡     ቫይረሱ በደማችን የሚገኝ ሰዎች ሳናስበው በተፈጠረ ስህተት እንደዚህ አይነት ችግሮችን     ብንፈጥርም እንደውም አሁን መድሀኒቱን በትክክል በመጠቀም እራሳችንን መጠበቅ     ግዴታ አለብን፡፡  የእግዚያብሄር ምህረት ሲታከልበት ደግሞ ምናልባት መድሀኒት     ሊገኝ ይችላል እና እራሳቸውን  የሚደብቁም ካሉ ለእራሳቸው ጥንቃቄ ማድረግ     አለባቸው፡፡ መድሀኒቱን መውሰድ ምንም የሚያመጣው     ችግር የለም ፡፡...ይሄ ያከሳል     ወይም ያሳብጣል የሚሉት ነገር በሙሉ ውሸት ነው፡፡     መድሀኒቱ በአግባቡ ምግብን     መመገብን ብቻ ነው የሚፈልገው ፡፡
ስለዚህ የተገኝውን ነገር ቤት ያፈራውን እየተመገቡ     እና ከአጓጉል ሱሶች ተላቆ እንደማንኛውም ጤነኛ ሰው መኖር እንደሚቻል የእኔ ሁኔታ     በቂ ምስክር ነው፡፡ 

Read 4320 times