ከ4 ሺህ በላይ ህፃናት 9.ሚ ብር መቆጠብ ችለዋል 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ነው
አዋጭ የገንዘብ ቁጠበና ብድር የህብረት ስራ ማህበር ቁጠባን በመሰብሰብና በቁጠባ የተገኘን ሀብት በማሳደግ ሀብቱን ወደ 2.3 ቢሊዮን ብር ማሳደጉን አስታወቀ፡፡ ከ4 ሺህ በላይ ህፃናትም ከ9 ሚ ብር በላይ እንዲቆጥቡ ማስቻሉን ማህበሩ ጠቁሟል።
አዋጭ ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ ታህሳስ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የተመሰረተበትን 15ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ስራ ማህበር መጋቢት 1998 ዓ.ም በ8 ወንዶችና በ33 ሴቶች፣ በ15 ሺህ 236 ብር ከአባላት በተሰበሰበ የቁጠባ ካፒታል፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 መቋቋሙን የአዋጭ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘሪሁን ሸለመ የገለፁ ሲሆን የሀሳቡ አመንጪና መስራችም እሳቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩን ለመመስረት የተነሱት በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ኑሮ የከበዳቸው ሰዎች እንደነበሩም የገለፁት አቶ ዘሪሁን፤ ኢኮኖሚያዊ ጫናውን ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት በሚል ምክክር ሀሳቡ ተፀንሶ ዛሬ ስኬትን የወለደ የህብረት ስራ የሆነው አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ስራ ማህበር መመስረቱን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ከ41 አባላት ወደ 62 ሺህ 522 አባላት ያደገ ሲሆን ከነዚህ መካከል 40 በመቶዎቹ ሴቶች፣73 በመቶዎቹ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ18-34 ዓመት የሆኑ ወጣቶችን ያቀፈ እንደሆነም አቶ ዘሪሁን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አብራርተዋል፡፡
ማህበሩ የቁጠባ መጠኑን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደገ ሲሆን ከአባላቱ ብቻ ቁጠባን በመሰብሰብ የሀብቱን መጠን ከ15 ሺህ 236 ብር ወደ 2.3 ቢሊዮን ብር ማሳደጉን ተናግረዋል፡፡
አዋጭ ከዚህም በተጨማሪ የቁጠባ አይነቱን ከአንድ ወደ 8 በማሳደግ የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል እንዲያድግ ከማድረጉም በላይ ቁጠባ በህጻናትም ዘንድ እንዲሰርፅ በማድረግ በሰራው ከፍተኛ ስራ 4 ሺህ 410 ህጻናት 9ሚ ብር እንዲቆጥቡ ማድረግ መቻሉንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
አዋጭ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ ከቁጠባ ቀጥሎ የብድር አገልግሎት አንዱ ሲሆን ማህበሩን ሲጀምሩ የአብዛኛው አባላት ችግር መሰረታዊ የቤት ዕቃዎችን ማሟላት እንደነበር የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በአባላት የሚጠየቁ እንደ አንሶላ፣ብርድ ልብስ ፈረሱላ በርበሬ፣ቴሌቪዥን፣ፍሪጅ፣ዳቦ መጋገሪያ እንደነበሩ አስታውሰቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ለአንድ አባል እስከ 2.ሚ ብር ድረስ ማበደር በመጀመሩ ከ16 ሺህ የሚበልጡ አባላት ከ2.8 ቢ ብር በላይ ብድር ወስደው 1 ሺህ 680 አባላት የቤት ባለቤት፣2 ሺህ 318 አባላት መኪና ገዝተው የተለያዩ የትራንስፖርት ዘርፎች ላይ መሰማራታቸውን 4 ሺህ 448 አባላት የንግድ ስራ ውስጥ መግባታቸውንና 199 አባላት ደግሞ በተበደሩት ብር ከ2ኛ እስከ 3ኛ ዲግሪ መማር መቻላቸው ተገልጿል፡፡
አዋጭ ዋነኛ የሀገር የህዝብ ጠላት የሆነውን ድህነትን በመዋጋት የሚደረገውን ርብርብ በማገዝ በሰጠው 2.8 ቢሊዮን ብር ብድር፣ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉ ተብራርቷል፡፡
ህብረት ሥራ ማህበሩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 103 ሚ. ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ የተገለፀ ሲሆን 30 በመቶ መጠባበቂያ እንዲሁም 5 በመቶ ለማህበራዊ አገልግሎት ቀንሶ በአባልነት አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ለቆዩ አባላት በአንድ እጣ 30.7 በመቶ የትርፍ ክፍፍል መስጠቱንና ይህም አንዳንድ ትልልቅ ባንኮች ከሚሰጡት የትርፍ ክፍፍል የተሻለ ስለመሆኑም ሀላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡ከህብረት ስራ ማህበሩ መርሆች አንዱ “አንዱ ለሌሎች ማሰብ” የሚል ሲሆን ለ200 ህጻናት የት/ቤት ክፍያ በመሸፈን፣ ለ50 አረጋውያን የጤና መድህን ዋስትና በመክፈል፣የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና የመጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ በህልውና ዘመቻው ለቆሰሉ የሰራዊቱ አባላት 250 ሺህ ብር የሚያወጣ የአካል ድጋፍ መለገሳቸውንም ሃከላፊዎቹ ተናግረዋል። ዛሬም ሁሉም አባላት ደም በመለገስ ግማሽ ሚ ብር ከአባላትና ከሰራተኞች በመሰብሰብ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
አንድ ሰው የአዋጭ አባል ለመሆን ሁለት ዕጣዎችን በ2 ሺህ ብር በመግዛትና 1 ሺህ 600 ብር ለመመዝገቢያ በመክፈል እንዲሁም 400 ብር በየወሩ በመቆጠብ ወደ እድገት ማማ መውጣት የሚችል ሲሆን አባል ሆኖ ሲበደር ደግሞ ለወንዶች 13.5፣ ለሴቶች 13 በመቶ ወለድ እንደሚከፍልና ይህም ከየትኛውም አበዳሪ ተቋማት ያነሰ የወለድ መጠን ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋም በአሁኑ ሰዓት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ የሚመጡበት፣በአዲስ አበባ 10፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ አራት በድምሩ 14 ቅርንጫፎች ያሉት ከመሆኑም አልፎ በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ባገኘው ፈቃድ በሁሉም ክልሎች የሚሰራ ከሀገራችን አልፎ የዓለም አቀፍ የህብረት ስራና የአፍሪካ ቁጠባና ብድር ኮንፌደሬሽን የመጀመሪያው አባል በመሆን ሀገራችንን የወከለ ተቋም መሆን መቻሉ ተገልጿል፡፡
በአገራችን ካሉት 20 ሺህ የቁጠባና ብድር ተቋሞች ለቁጠባው ከሚያደርጉት 5 በመቶ የቁጠባና ብድር አስተዋጽኦ አዋጭ 1 በመቶውን አበርክቶ መሸፈን የቻለ ትልቅ ተቋም መሆኑም ተገልጿል፡፡
Sunday, 02 January 2022 20:13
“አዋጭ” ቁጠባና ብድር ተቋም ሀብቱን ወደ 2.3 ቢ. ብር ማሳደጉን ገለፀ
Written by ናፍቆት ዮሴፍ
Published in
ዜና