Tuesday, 20 October 2026 10:21

"ሻዕቢያ ከጥፋት መንገዱ ካልተመለሰ መዘዙ ከባድ ይሆናል"

Written by 
Rate this item
(0 votes)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኤርትራው ገዥ ቡድን (ህግደፍ) የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠቀሚያ መሆኑን አቁሞ ለቀረበለት የሰላም እና የጋራ ልማት ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ የሚከተለው መዘዝ እጅግ መራራና ከባድ እንደሚሆን ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ።
ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ አገዛዙ የራሱን ሀገር እና ሕዝብ የልማት ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የቀጣናው የጥፋት ኃይሎች መናኸሪያ እና መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። "የራሱን ችግር ያልፈታ ኃይል ለሌላው ሊተርፍ አይችልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውጭ "አይዞህ ባዮች" ጥይት ከማቀበል ባለፈ የራሳቸውንም ችግር መፍታት እንደማይችሉ በመጠቆም፣ ሥርዓቱ ከልማት እና ከትብብር ይልቅ ቀጣናውን የማተራመስ አጀንዳን መምረጡ ፈጽሞ እንደማያዋጣው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
በአገዛዙ ምክንያት በኤርትራ ላይ የደረሰውን ዘመናት የተሻገረ ውድቀት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ከመገንጠሏ በፊት በንግድ እና በኢንዱስትሪ ደምቀው የነበሩት ከተሞቿ ሙሉ በሙሉ መደብዘዛቸውን አብራርተዋል። በአንድ ወቅት ከ300 በላይ ንቁ ፋብሪካዎች የነበሯትን ኤርትራን ወደ ባዶነት ከቀየረው እና ውቢቷን አስመራን አንሳ እንድትገኝ ካደረገው ሻዕቢያ ጋር መተባበር የጥፋት ጥግ መሆኑንም አመልክተዋል። የሕዝቦችን የወደፊት ተስፋ የሚያጨልመው ይህ የጥፋት መንገድ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባውም አስምረውበታል።
ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ለሰላም፣ ለትብብር እና ለጋራ ልማት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ልማትን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ መሆንን የመረጠው የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ ታቅቦ የልማት አጋር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ሻዕቢያ የውጭ ኃይሎችን ተማምኖ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ "ጆሮ ዳባ ልበስ" ብሎ በጥፋት መንገዱ የሚገፋበት ከሆነ፣ በመጨረሻ የሚከተለው መዘዝ እጅግ የከፋ እንደሚሆን በድጋሚ አሳስበዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 557 times