Saturday, 09 February 2013 12:00

ግርማ በዳዳ - ከጅማ እስከ ደቡብ አፍሪካ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

“ዓሳ አጠምዳለሁ ብለህ ዛፍ ላይ አትውጣ”

ደላላው መጀመሪያ ላይ ሰማኒያ ሺ ብር እንዲከፍለው የጠየቀው ግርማ በዳዳ፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሄድ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደነበረው ስለተገነዘበ ነበር፡፡ በግርማ አይኖች ላይ እንደ አንዳች ነገር የሚንቦገቦገውን ከፍተኛ የጉጉት ስሜት በተረዳ ጊዜ ነው ግርማን ገና ከመጣዱ እንደሚግል ትንሽዬ ጀበና የቆጠረው፡፡ ግርማ ግን በቀላሉ እጅ ሳይሰጥ እስከመጨረሻው ድረስ ከደላላው ጋር በፅናት መከራከር በመቻሉ፤ የማታ ማታ አምስት ሺ ብር ለማስቀነስ ቻለ፡፡ 

እንደ እውነቱ ከሆነ ግርማ ከተሰማራበት የስራ መስክና ከሚያንቀሳቅሰው የገንዘብ መጠን አኳያ ሲታይ፤የአምስት ሺ ብር ቅናሽ ማግኘት ቀላል የሚባል የድርድር ውጤት አልነበረም፡፡ ትልቁ ችግር ግን ሰባ አምስት ሺ ብሩንስ ቢሆን እንዴት ማግኘት ይቻላል የሚለው ነበር፡፡ ለዚህም ነው ግርማ ሲበር ወደ ቤቱ በመሄድ ያለ የሌለ ገንዘቡን ካስቀመጠበት አውጥቶ መቁጠር የጀመረው፡፡ ሆኖም ግን ከሀምሳ አንድ ሺ ብር ከፍ ሊልለት አልቻለም፡፡ በእጁ ላይ ካለው ገንዘብ በተጨማሪ ሃያ አራት ሺ ብር እንደሚያስፈልገው ሲረዳ አናቱ ላይ ከፍተኛ የማቃጠል አይነት ስሜት ተሠማው፤አፍንጫውንም የነሰረው መሰለው፡፡
“ሃያ አራት ሺ ብር አሁን ከየት ነው የማመጣው?” ግርማ በከፍተኛ ጭንቀት ተወጥሮ ማሰብ ጀመረ፡፡ “አባዬንና ወንድሞቼን ልጠይቅ ወይስ ጓደኞቼን?” በጠባቡዋ የኪዮስኩ ወለል ላይ በጀርባው ተንጋሎ ማውጣትና ማውረድ ጀመረ፡፡
በኋላ ግን ከሁሉም የሚቀርበውን ጓደኛውን ኑረዲን አባቡልጉን ለማማከር በመወሰን ጉዳዩን አጫወተው፡፡
ኑረዲን የጓደኛውን ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሄድ ጠንካራ ፍላጐትና እቅድ ካዳመጠ በኋላ የሰጠው መልስ “ትናንሽ ጀልባዎች ከወደቡ በእጅጉ መራቅ የለባቸውም፡፡” የሚል ነበር፡፡
በቂ ገንዘብና ጥሪት ሳይኖርህ ትልቅና ምናልባትም አደገኛ ነገር ውስጥ ለመግባት አትድፈር ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ ግርማ ግን ከማንም በላይ ቅርብ ከሆነው ጓደኛው እንዲህ አይነት መልስ አገኛለሁ ብሎ ስላልገመተ በድንጋጤ ክው እንዳለ ወደሌላኛው ጓደኛው ዘንድ አመራ፡፡
ከዚህኛው ጓደኛው ያገኘውም መልስ ከመጀመሪያው የተለየ አልነበረም፡፡ ደግነቱ የዚህኛው መልስ እንደ መጀመሪያው አላስደነገጠውም፡፡ “ያለህን ሀብት ለደላላ ከፍለህ ወደማታውቀው ሀገር ከምትሰደድ ይልቅ እዚሁ ባገርህ ላይ እየሰራህ ብትኖር ይሻልሃል፡፡ አሳ አጠምዳለሁ ብለህ ዛፍ ላይ አትውጣ” ነበር ያለው ይኸኛው ጓደኛው፡፡ “ከሌሎች አንዳች ነገር እንዲደረግላቸው የማይጠብቁ ብፁአን ናቸው አይናደዱምና” የሚባለው ያለ ነገር እንዳልሆነ ግርማ ገብቶት ተገረመ፡፡
ግርማ ሁለቱ ጓደኞቹ የሰጡትን መልስ ለአበበች የነገራት የተጐዳው ስሜቱ በመጠኑም ቢሆን ከተረጋጋ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር፡፡ አበበች እንደሚያገባት ደጋግሞ ቃል የገባላት ሳይሆን ደጋግሞ የነገራት የአራት አመት ፍቅረኛው ናት፡፡
እርሷ ይህ የደቡብ አፍሪካ የስደት ጉዞ ከሞቀው ፍቅራቸው እንደሚለያያቸውና የወደፊቱን የትዳራቸውን ነገር አጠራጣሪ እንደሚያደርገው በሚገባ ስላወቀች ከመጠን በላይ ጠልታዋለች፡፡ ይሁን እንጂ ልቧ በከፍተኛ ቅሬታና ስጋት ቢኮማተርም፤ ይህንን መራራ ስሜት በከፍተኛ ግብግብ በልቧ አምቃ በመያዝ እንደሁለቱ ጓደኞቹ ካሰበው የደቡብ አፍሪካ ጉዞ እንዲቀር ልትመክረውና ልትገፋፋው ጨርሶ አልደፈረችም፡፡
ይህን ያላደረገችው ከልቧ ፍላጐት ሳይኖራት ቀርቶ ግን አልነበረም፡፡ በግርማ ላይ በግልጽ ይነበብና ይታይ የነበረውን እንዲህ ነው ተብሎ በቃል ሊገለጽ የማይችል ከፍተኛ ጉጉትና ቁርጠኝነት በቀላሉ መስበርም ሆነ ማስቀየር እንደማይቻል በደንብ በመረዳቷ እንጂ፡፡
በእነኛ ወሳኝ ቀናቶች ግርማ የሃያ አራት ሺ ብሩ ነገር ክፉኛ ቢያስጨንቀውም ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ በወሰነው ቁርጠኛ አቋሙ እንደፀና ነው፡፡ ያኔ ግርማ በእርግጥም ቺዝ ወይም የፈረንጅ አይብ ሆኖ ነበር፡፡ ቺዝ ደግሞ የሰው ልጅ ከሚመገባቸው የምግብ አይነቶች ውስጥ ማዋሃድ የማይችለው ራሱን ብቻ ነው፡፡
በእነኛ በበርካታ ትዕይንቶች በተሞሉ ቀናቶች የግርማ ዋነኛ ጭንቀት የነበረው ከፍቅረኛውና ከመላ ቤተሰቦቹ ከመለያየቱ ይልቅ ደላላው የጠየቀውን ሰባ አምስት ሺ ብር አሟልቶ መክፈል መቻሉ የነበረውን ያህል አበበችም ከግርማ ጋር ከመለያየቷ በተጨማሪ ክፉኛ ዕረፍት የነሳት ከግርማ ጋር ወደ ደቡብ አፍሪካ አብራው የምትሄድ ሴት ትኖር ይሆን የሚለው ነበር፡፡ አበበች በመጠኑም ቢሆን ረጋ ማለትና ከቀልቧ መሆን የቻለችው አብራው የምትሄድ ሴት እንደሌለች ካረጋገጠች በኋላ ነው፡፡
ከግርማ ጋር የመለያየቷንም ነገር ሆነ ደቡብ አፍሪካ ስለሚጠብቀው የስደት ህይወት እያሰበች መብሰልሰሏ አልቀረም በኋላ ላይ ግን “አንበሳም እኮ በስዕል እንደሚታየው በእውኑ አያስፈራም ይባላል፡፡ ለዚያውም ደግሞ የሰውን ልጅ እጣፈንታ የሚወስነው አንድዬ እንጂ ሰው አይደል!” እያለች ራሷን ታፅናና ገባች፡፡ ከዚያም ግርማን ወደ ማፅናናት ገባች፡፡ “የአለማችንን ታላላቅ ውቅያኖሶችና ክፍለ አለማትን የመሠረቱት እኮ ትናንሽ የውሃ ነጠብጣቦችና ደቃቅ አሸዋዎች ናቸው” በማለትም አበረታችው፡፡ ኧረ ምን ማበርታት ብቻ---- የጐደለውን ሃያ አራት ሺ ብር ደቡብ አፍሪካ ሄዶ በሁለትና በሶስት ወር ውስጥ ሰርቶ መክፈል እንደሚችል በመግለፅ “እባካችሁ አበድሩት” እያለች ብድር አፈላልጋለታለች፡፡
ግርማ አባቱንና ሁለት ወንድሞቹን ሃያ አራት ሺ ብር እንዲሰጡት ጠይቆ ማግኘት እንደማይችል ካረጋገጠ በኋላ ነው ፊቱን ወደሌላ አማራጭ ያዞረው፡፡ የሃያ አራት ሺ ብሩ ነገር እልባት አግኝቶ የተጠየቀውን ሰባ አምስት ሺ ብር ለደላላው መክፈል የቻለው ጉዳዩ ከተጀመረ ከአንድ ወር በኋላ ሲሆን ያኔ በሱቁ ውስጥ ሰባራ ስንጥር ሳይቀር ተሸጦ አልቆ ነበር፡፡
ደላላው የጠየቀውን ገንዘብ ማሟላት እንደቻለ እላዩ ላይ እንደ መርግ ተጭኖት የነበረው ከባድ ሸክም ድንገት በኖ ሲጠፋለትና ምኞቱና ጉጉቱ ሲሰምርለት ታይቶት የተሰማው ደስታ ዲካ የለሽ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን ይህን መጠን የለሽ ደስታውን በመጠኑም ቢሆን የሚያደበዝዝ ነገር ተፈጠረ፡፡ ደላላው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያስገባውን ቪዛ ለማግኘት የሰጠው የሁለት ሳምንት ቀጠሮ ነበር፡፡ የደላላው ቀጠሮ በሁለት ሳምንት ብቻ ሊያጥርለት የቻለውም ፓስፖርት ስለነበረው ነው፡፡
ከሁለት አመት በፊት ጓደኞቹ ሲያወጡ አይቶ ያወጣው ፓስፖርት አሁን በእጅጉ ጠቀመው፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የደላላውን ክፍያ ለማሟላት ድፍን አንድ ወር ሙሉ ከሮጠውና ከባዘነው ይልቅ ለግርማ መቸውንም ጊዜ ሊወጣው የማይችል እጅግ ከባድ ፈተና የሆነበት ቪዛውን ለማግኘት ደላላው የሰጠውን የሁለት ሳምንት ቀጠሮ መጠበቅ ነበር፡፡ ሁለቱ ሳምንታት የሁለት አመታት ሳይሆን የምጽአት ቀንን ያህል ረዘሙበት፡፡ ትዕግስት አልባነቱ ከእንቅልፍ እጦቱ ጋር ተደምሮ ያለአመሉ በጣም ነጭናጫና በውሃ ቀጠነ የሚበሳጭ ልጅ ሆኖ አረፈው፡፡
የግርማን አዲስ አመል ያስተዋሉት የሰፈሩ ሰዎች፤ “እድሜ ልኩን ታውሮ የኖረ ሰው አይኖችህ ነገ ይበራሉ ሲባል ዛሬን እንዴት ብዬ አድሬ” አለ በማለት ተርተውበታል፡፡ ሌሊቱ የፈለገውን ያህል ቢረዝም መንጋቱ ግን አይቀርም እየተባለ እንደሚነገረው ሁሉ፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ ደላላው የግርማን የደቡብ አፍሪካ መግቢያ ቪዛ የተመታበት ፓስፖርት ይዞ በቀጠሯቸው መሠረት ከግርማ ኪዮስክ ፊት ለፊት በምትገኝ ትንሽዬ ካፌ በረንዳ ላይ ተገናኙ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 2381 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 15:51