Saturday, 09 March 2013 11:50

አብቹን ምን በላው? ላሊበላንስ ማን ቀበረው?

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(1 Vote)

(ካለፈው የቀጠለ) ባለፈው ሳምንት በዚሁ ርዕስ ስለ አብቹ ማንነት፣ የት ተወልዶ የት እንዳደገ፣ ገና የ16 ዓመት ጉብል ሳለ ስለፈፀመው ተዓምራዊ ጀብዱ፣ በንጉሡና በራሶች ዘንድ ስጋት ሆኖ ስለመታየቱ፣ የጣሊያኖችንም ሆን የባንዳዎችን ቅስም እየሰበረ ወደፊት ስለመገስገሱ፣ ከማይጨው ሽንፈት በኋላም የሚወደውን አለቃውንና ጓደኛውን ደጃዝማች አበራን እና ሁለት ወዶ ዘማች ፈረንጆችን (አንደኛው የአብቹን ታሪክ በመጠኑም ቢሆን የጻፈውን አዶልፍ ፓርለሳክ ነው) ተሰናብቶ በጥቁር ፈረሱ ላይ ሆኖ፣ ከሁለት የጦር ሜዳ ጀግኖቹ (ጀኔራል ወርቁና ጀኔራል ሃብቶም) ጋር ቁልቁል ወደ ዓባይ ሸለቆ ሽምጥ መጋለቡን ገልጬ ነበር በቀጠሮ የተለየኋችሁ፡፡ ቀጣዩን ክፍል እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡ ከቅስም ሰባሪው የማይጨው ሽንፈት በኋላ፣ንጉሡና ምርጥ አሽከሮቻቸው ወደ አውሮፓ በባቡር ሲኮበልሉ መጀመሪያም የፋሽስቶችን አረር በደረቱ እየመከተ የሀገርን ክብር ለማስጠበቅ የተዋደቀው ምስኪን ድምር ህዝብ ግን የሚያሰባስበው አላገኘም፡፡

በመሆኑም በአግባቡ የተደራጀውንና በዘመናዊ ትጥቅ ጡንቻውን ያፈረጠመውን የጠላት ኃይል በተናጠል መመከት አልቻለም፡፡ የኋላ ኋላ ግን ምንም እንኳ ንጉሡ ሜዳ ላይ በትነውት ቢፈረጥጡም፣ ምንም እንኳ አቅሙ ደካማ መሆኑን አሳምሮ ቢያውቅም፤ አያት ቅድመ አያቶቹ በባዕድ ተገዝተው አያውቁምና “አሜን” ብሎ መገዛት የሞት ሞት ሆኖ ታየው፡፡ ስለሆነም በየአካባቢው የጐበዝ አለቆችን እየመረጡ ከጣሊያን ጋር ፊትለፊት መጋፈጡን በቁርጠኝነትና በፍጹም ጽናት ተያያዘው፡፡ አብቹም ለተመሳሳይ ዓላማ ጃርሶ ወረደ፡፡

ከዚያስ? ሃሳቡ ተሳክቶለት በለመደው የጀግንነት ወኔ ጣሊያንን ተፋለመ? ተፋልሞስ ለድል በቃ? ወይስ በጠላት አረር ከሆነ፣ ከማይታወቅ ቦታ ወድቆ የጆቢራ ራት ሆነ? ወይስ መንግስት ቂም ቋጥሮ ቆይቶ እንደነበላይ ዘለቀ በድብቅ ቀበረው? ለፈፀመው ጀብዱስ ከድል በኋላ መንግሥት ምን ወሮታ ከፈለው? በአብቹና መሰል አርበኞች ለዘውድ የበቁት ንጉሥ እንዴት ረሱት? በአስጨናቂዎቹ የጦርነት ወቅቶች “እሰሩት! ገንዙት!” ሲሉ የነበሩ ልዑላን ራሶች ከድል በኋላ እንዴት ስሙ እንኳ ትዝ አላለቸውም? አምባራዶምም ሆነ ማይጨውና መቀሌ አካባቢ በተካሄዱ ውጊያዎች ላይ በዘግናኝ ሁኔታ ያለቁት ምስኪን ዜጐች ቀድሞውንም በሥርዓት ስላልተመዘገቡና ስለማይታወቁ፣ ስማቸው በወርቅ ቀለም አለመጻፉ ላያስደንቅ ይችል ይሆናል፡፡

ሆኖም አገራቸውና ቤተሰባቸው እንዲሁም ታሪክ በነሲብ ሲያወሳቸው ይኖራል፡፡ ግን አብቹ እንዴት ይረሳል? በወዶ ዘማችነት ከራስ ካሳ ጦር ጋር ዘምቶ የነበረው ቸኮዝሎባኪያዊው አዶልፍ ፓርለሳክ እንኳ ከዚያ ሁሉ ሠራዊት መሃል እንደ አብቹ በህሊናው ታትሞበት የቀረ ምርጥ ጦረኛ ያለ አይመስልም፡፡ በዚያ አስከፊ ሰዓት እንዲህ ዓይነት ተዓምር የሠራ የ16 ዓመት ጉብል መኖሩን የነገረንም እሱ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ስለማይጨው ጦርነት ጽፈዋል፡፡ ብዙ የመጻፋቸውን ያህል የንጉሡንና የራሶችን “እንከን አልባ” ታሪክ ሊነግሩን ደከሙ እንጂ እንዲህ እንደ አብቹ ያሉ ሳተናዎችን ታሪክ እየመዘዙ አላሳዩንም፡፡ ይልቁንም “ንጉሡ ወደ አውሮፓ የሄዱት ሸሽተው ሳይሆን የተባበሩትን መንግሥታት (ሌግ ኦፍ ኔሽን) እርዳታ ለማግኘት ነው” የሚል ስብከት ደጋግመው ይነግሩንና የትየለሌ ኢትዮጵያውያን በመርዝ ጋዝ እየተጠበሱ አምስት ዓመት ሙሉ ፍዳቸውን አይተው ያስመዘገቡትን ድል ለንጉሡ በገጸበረከትነት ያቀርባሉ፡፡ “ፀሐዩ ንጉሠ ነገሥት በድል አድራጊነት መጡ” እያሉም ድሉን በኪሳቸው ውስጥ ይዘው የመጡ በማስመሰል ከኬኩ ላይ ክሬሙን እንዲልሱ ያደርጓቸዋል፡፡ በመሠረቱ እንዲህ ዓይነቱ ዘገባ ስህተት ሳይሆን ክህደት ይመስለኛል፡፡ በጣሊያን የመርዝ ጋዝ በየበረሃው አካሉ እንደ ቅጠል ረግፎ የቀረው፣ በወንድሙ ሬሣ ላይ እየተራመደ የሀገሩን ጠላት አናዝዞ ለድል የበቃው አርበኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ንጉሡ አይደሉም፡፡ ንጉሡማ አውሮፓ ውስጥ ከቤተሰባቸውና ከምርጥ አሽከሮቻቸው ጋር የሞቀ ኑሮ እየኖሩ ነበር፡፡ ጦርነት ደግሞ በርቀት መቆጣጠሪያ ሊካሄድ የሚችል ቀላል ጨዋታ (ጌም) አይደለም፡፡ እንዴት አርጐ ነው ታዲያ ድል ከአውሮፓ ያውም ከእንግሊዝ ይዘውልን የሚመጡት? ቀድሞ ነገር ጣሊያን የወረረችንኮ የእንግሊዝን ሙሉ ድጋፍ አግኝታ ነው፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዳጅና ጠላትን ሳይለይ አውሮፓን ስላመሳቀለው፣ ጣሊያንም በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የእንግሊዝን ጥቅም የሚነካ ተግባር በመፈፀሟ ነው ፊት የተዟዟሩት፡፡ ያም ሆኖ ድሉ የተገኘው አብቹን በመሰሉ ቆፍጣና ጀግኖች መራራ ትግልና መስዋዕትነት እንጂ ከእንግሊዝ ወይም ከንጉሡ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡

ንጉሡ በእንግሊዞች አጃቢነት ገና መንገድ ላይ ሳሉኮ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጣሊያንን አርበድብደው መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የደሙላትን፣ በርካታ ወገኖቻቸውን ጭዳ ያደረጉላትንና ምንጊዜም ተዋርዳ የማታውቀውን ሰንደቅ ዓላማቸውን አውለብልበዋል፡፡ ይህ ቀን በደርግ ዘመን በክብር ሲታሰብ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ ግን ቀኑን ወደሚያዝያ 27 ቀይሮታል፡፡ ቀኑ ደግሞ ንጉሡ አዲስ አበባ የገቡበት ነው፡፡ ግን ለምን? ትክክለኛው የድል ቀን አርበኞች የገቡበት ነው፡፡ ሚያዝያ 27 ማለት ንጉሡ ሳያስቡት ተገፍትረው ያጡትን ዙፋን መልሰው ያገኙበት እንጂ እንደ አጼ ቴዎድሮስ፣ እንደ አፄ ዮሐንስ ወይም እንደ አጼ ምኒሊክ ጦራቸውን መርተው፣ በጀግንነት ተዋግተው ለድል ያበቁበት ዕለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ጣሊያን አዲስ አበባን የተቆጣጠረችበትና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አዋርዳ የራስዋን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ያውለበለበችበት ዕለት ነው፡፡

ስለዚህ የምናከብረው የማንን የድል ዕለት ለማስታወስ ይሆን? የጣሊያንን ወይስ…? ለነገሩ ይህኛው ሃሳብ በጠለፋ ገባ እንጂ የጽሑፌ ዓላማ ብሔራዊው አርበኛ አብቹ ከማይጨው የሽንፈት መልስ በኋላ የት እንደገባ መጠየቅና የላሊበላን ታሪክ ቀባሪዎች ለማወቅ መትጋት ነው፡፡ አምስት የፍዳ ዓመታት በገድል ከተፈፀሙ በኋላ ንጉሡ “በድል አድራጊነት” ሳይሆን በእንግሊዞች አጃቢነትና በጀግኖቻችን ድል አድራጊነት ወደ ሥልጣን ሲመለሱ በብዛት ይሾሙና ይሸልሙ የነበሩት ለዘውድ ያበቋቸውን የቁርጥ ቀን ጀግኖች ሳይሆን የወገኑን አንገት እንደ ጐመን ያስቀነጠሰ ባንዳንና ስደተኛውን ነበር፡፡ አንዳንዶችን እንዲያውም ማዕረጋቸውን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውንም በመሪር ግፍ ነጥቀዋቸዋል፡፡ ከህይወታቸውም ከማዕረጋቸውም በላይ ታሪካቸውን የተነጠቁት ደግሞ እጅግ የሚያሳዝኑ ናቸው፡፡ እንዴት ታሪክ ይገደላል? ስለአብቹም ሆነ አምባራዶም ላይ በተካሄደው ዘግናኝ ጦርነት ተዓምር ስለሰሩት ጀግኖች የነገሩን ቼኮዝሎባኪያዊው አዶልፍ ፓርለሳክና ኪውባዊው ኮሎኔል ዴል ባዬ ብቻ ናቸው፡፡ “ሐበሽስካ ኦዲየሳ” የተሰኘው የታሪክ መጽሐፍ ወደ አማርኛ እስከ ተመለሰበት 1989 ድረስ አብቹ የሚባል ጀግና ስለመፈጠሩም የሚያውቅ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ እውነተኛ ጀግኖች በመብራት በሚታሰሱበት በዚያ ዘግናኝ ወቅት ተዓምር የሚመስል ጀብዱ እየፈፀመ ጣሊያንን ሲያርበደብድ የነበረ ጀግና፣ የመከራው ጊዜ ሲያልፍ ስሙ እንኳ ለምን ተረሳ? የሚገርም ጉዳይ ነው፡፡

የጃጀ የመከላከል ሃሳብ ለነበራቸው ጁጁዎች ባለመታዘዙ ሹመት ሽልማቱ ይቅርበት፤ ግዴለም፡፡ ግን እንዴት በስህተት እንኳ ስሙ አይነሳም? የሃገራችን ታሪክ ጸሐፊዎችስ (በተለይ ስለማይጨው ዘመቻ የጻፉና በግንባሩ የነበሩ) ለምን ንፉግ ሆኑ? አብቹኮ ህይወቱን አልነፈገንም፡፡ አብቹ ከጣሊያን ጋር ሲዋጋ በአንዱ የሃገሩ ሸለቆ ውስጥ ወድቆ ያገሩ አሞራ በልቶታል፤ ወይም “እሰሩት ገንዙት” ሲሉ የነበሩ ወግ ጠራቂ መኳንንት አስገድለውታል፤ ወይም ድምጹን አጥፍቶ ኖሮ በህመም ሞቷል፤ ወይም ዕድለኛ ከሆነ ዛሬ የዘጠና ሶስት ዓመት አዛውንት ሆኖ ትውልዱንም ዘመኑንም ይታዘባል፡፡ ለነገሩ ሰውን ገድሎም ሆነ በቁሙ መቅበር አዲስ ነገር አይደለም ግን ታሪክን እንዴት መቅበር ይቻላል? አብቹን የመሰለ ብሔራዊ አርበኛ ታሪክስ ከምን ዓይነት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ቢቀበር ነው ፍንጩ እንኳ የታጣው? ለነገሩ ታሪክን መቅበር የዳበረ ልምድ ያለን ይመስለኛል፡፡

እንኳን የአብቹን የአንድ ፍሬ ልጅ (ግን ወኔ ሙሉ ጀግና) ታሪክ የዓለም ማህበረሰብ “… ቅርሴ ነው” ብሎ በክብር የመዘገበው የላሊበላ ታሪክስ መች በቅጡ ይታወቃል? የሚታወቀው “ላሊበላ የሚባል የተቀደሰ ንጉሥ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ከድንጋይ ሠራው” የሚል ነው፤ በቃ፡፡ ግን መጀመሪያ እንዴት ሃሳቡን አፈለቀው? ወይም እኒያን አይነት ተዓምረኛ ቤተክርስቲያኖችን ለመሥራት ያነሳሳው ሰበብ ምን ነበር? የዚያ ዓይነት ድንጋይ በአካባቢው እንደሚገኝ በምን ተገነዘበ? የከርሰ ምድር መመርመሪያ ቴክኖሎጂ በወቅቱ ነበር? በእርግጥ በመጥረቢያ ነበር የሠራው? በመጥረቢያ ከሰራውስ ለምን ምልክቱ ቤተ ጊዮርጊስ ላይ አልታየም? ድንጋዩን እንደ እንጨት አለስልሶ የሚጠርብ መሳሪያስ ምን ዓይነት ነው? ድንጋዩ ሲጠረብ (በተለይ ማዕዘን አካባቢ) ለምን አንድ ቦታ ላይ እንኳ አይሸረፍም? እጅግ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱና ተገቢው መልስ ሊሰጥባቸው ይገባ ነበር፡፡ ትክክለኛውን መልስ መስጠት የሚቻለው ግን ትክክለኛ ታሪኩ ሲገኝ ነው፡፡ የዚያ ግዙፍ ተግባር ባለቤት (የላሊበላ) ታሪክ የት ተቀበረ? በምን ያህል ጥልቀት ተቀበረ? ማን ቀበረው? ለምን? እጅግ የሚገርም ጉዳይ ነው፡፡

ከእሱ በፊት የኖሩት የአክሱም ነገሥታት ዝርዝር ታሪክ ሲጻፍና ሲተነተን፤ ሌላው ቀርቶ በጦርነት ድል ያደረጓቸው ህዝቦች፣ የወጉት ሀገር፣ ያደሱት ዕልቂት መጠን፣ ወዘተ በሰፊው ሲነገርና ሲዘከር የላሊበላና ቤተሰቦቹ ትክክለኛ ታሪክ እንዴት ተዳፍኖ ቀረ? ለማን ጥቅም? ለምን ዓላማ? ይህ ዓይነት ቅጥራት የሚፈፀመው ምን አልባት “ከሰሎሞን ዘር የወጣን እኛ እንጂ የላሊበላ ዘር አይደለም” በሚሉ ግብዝ ጸሐፊዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ግንኮ በዚያው ግብዝ ሥራቸውም ቢሆን የላሊበላን ዘር (በእናቱ በኩል ገረድ ቢያደርጉትም) አባታቸው ሰሎሞን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ታዲያ ያን የመሰለ ድንቅ ጥበብ ለዓለም ያስተማረውን ጀግና ታሪክ መቅበር ለምን አስፈለገ? ታሪክ መቅበር የጀመርነው በላሊበላ ሳይሆን ይቀራል? በላሊበላ ዘውድ ወራሾችና በ “ሰሎሞናዊው” ይኩኖአምላክ መሃል የከረረ፣ የመረረ ውጊያ ሳይካሄድ በአባ ተክለሃይማኖትና በአባ ኢየሱስ ሞዐ ፖለቲካዊ ጥበብ ሥልጣን ወደ ሸዋ መሻገሩን ብዙዎች ጽፈዋል፡፡ ለከፈሉት ፖለቲካዊ ውለታም ለአባ ተክለ ሃይማኖት የዕጩጌነት፣ ለአባ ኢየሱስ ሞዐ ደግሞ የዓቃቤ ሰዓትነት ክብር ከይኩኖአምላክ ተቸሮአቸዋል፡፡

በሽግግሩ ወቅትም ሆነ በኋላ ላሊበላ ላይ ብቻ ያተኮረ የውጭ ወራሪ አልተነሳም፡፡ ታዲያ ምን መዓት ወረደና ታሪኩን ቀበረው? ምን አልባት ወርቃማውን የላሊበላ ታሪክና ጥበብ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የቀበሩት ተንኮልን ማደሪያቸው ያደረጉ እበላ ባይ ደባትር ሊሆኑ ይችላሉ - የሚያፎደፉዱላቸው ነገሥታት ከላሊበላ የተሻለ ሳይሆን ጫፉ ጋ የሚደርስ ተግባር ማከናወን ስለማይችሉ፡፡ የጀግናውን አብቹን ታሪክ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የቀበሩትም የእነሱ የልጅ ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እናም እባካችሁ የጀግናውን አብቹንም ሆነ የላሊበላን ምሉዕ ታሪክ ያያችሁ ና ወዲህ በሉኝ! ከታሪክ ቀባሪዎች ይሰውረን፡፡

Read 1238 times