Saturday, 20 April 2013 11:35

በከሰል ጭስ ምክንያት ሁለት ሰዎች ታፍነው ሞቱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

በአዲስ አበባ ለም ሆቴል በሚባለው አካባቢ ተመስገን ጠጅ ቤት የሚሰሩ ሙሉቀን ጠንክር እና አበበ ጄዛ የተባሉ ወጣቶች ትናንት በከሰል ጭስ ታፍነው ሞተው ተገኙ፡፡ በእንግድነት ማምሻውን ወደ ሟቾቹ ዘንድ የመጣና ማንነቱ ያልታወቀ ሌላ ወጣት በጠና ታሞ ሚኒሊክ ሆስፒታል የሚገኝ ሲሆን በአደኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን የፖሊስ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ወጣቶቹ እንደሌላው ጊዜ ስራቸውን ሲከውኑ አምሽተው የምሽቱን ቅዝቃዜ ለመከላከል ከሰል አቀጣጥለው በማስገባት በራቸውን ዘግተው እንደተኙ ከጠጅ ቤቱ ባለቤቶች ያኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አደጋ ይገጥማቸዋል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ወጣቶቹ እንደተለመደው በሰዓታቸው እንዲነሱ ቢጠበቁም አልሆነም፡፡ የጠጅ ቤቱ ባለቤቶች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ፖሊስ መስኮት ሰብሮ ሲገባ ነው፡፡

ሁለቱ የጠጅ ቤቱ ሠራተኞች ሞተው የተገኙት፡፡ በእንግድነት የመጣው ሶስተኛው ወጣት ራሱን ስቶና ተዝለፍልፎ እንደተገኘ ፖሊስ ጠቅሶ፤ በአፋጣኝ ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና እየደረገለት ነው፡፡ በአካባቢው ህዝብ ተከቦ ከነበረው ጠጅ ቤት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦች የሁለቱን ሟቾች አስከሬኖች ለምርመራ ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል በመኪና ጭነው ወስደዋል፡፡ ተመልክተናል፡፡ የሟች አበበ ጄዛ የአጐት ልጅ የሆነው ጐሣዬ ሀለቱ እንደነገረን፣ ሟች አበበ ወደ ጠጅ ቤቱ ለስራ የገባው በቅርብ ጊዜ ሲሆን የ28 ዓመት ወጣት ነው፡፡ የ23 ዓመቱ ሙሉቀን ጠንክርን ታላቅ ወንድም አግኝተን ልናናግረው ብንሞክርም በከፍተኛ ለቅሶና ጩኸት ላይ ስለነበረ ሊያናግረን ባለመቻሉ ተጨማሪ መረጃ ስለወጣቱ ማግኘት አልቻልንም ይሁን እንጂ የጠጅ ቤቱ ባለቤቶች እንደገለፁት ጠጅ ቤቱ ከተከፈተ ከአንድ አመት በላይ የሆነው ሲሆን፣ ወጣቱ ሙሉቀን ጠጅ ቤቱ ሲከፈት ጀምሮ ይሰራ እንደበር፣ አበበ ጄዛ ግን በቅርቡ ስራ መጀመሩን ገልፀውልናል፡፡

የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ አበበ እንደናገሩት ከሰልን በቂ ንፁህ አየር በሌለበትና በተዘጋ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ እጅግ አደገኛ መሆኑን ገልፀው፤ ካርቦሞን ኦክሳይድ የተባለው ጋዝ ለሞት የሚዳርግ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ “በተለይም አሁን የክረምት ወቅት በመቃረቡ የከሰል ተጠቃሚው ቁጥር ይበዛል” ያሉት ዶ/ር ዮሐንስ አበበ፣ ከሰል ተጠቃሚዎች በተለይም ማታ ማታ ከሰል በደንብ ሳይቀጣጠል አስገብተው በር መዝጋትና መተኛት እንደሌባቸው ይመክራሉ፡፡ ከሰል እቤት መግባት ካለበትም ጥቁሩ አልቆ በደንብ ሲቀላና ጭሱ ሲወጣ መሆን እንዳለበት አስታውሰው “ይህም ቢሆን በር ባይዘጋ ይመረጣል” ሲሉ ዶክተሩ አሳስበዋል፡፡

Read 2737 times