Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 November 2011 14:17

SPAIN

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“መዝናናት፣ መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት!” - ጓድ ሌኒን
እስፓኝ በጣም ከሚገርሙኝና ከሚነሽጡኝ አገሮች አንዱ ነው፡፡ Renaissance ከሚባለው ዘመን እንጀምራለን፡ በሌሎቹ የኤውሮፓ አገሮች እነ ሼክስፒር፣ እነ Leonardo da Vinci, እነ Michelangelo Buonarotti, እነ El Greko በቀሉ፡፡
በእስፓኝ ከበቀሉት አርቲስቶች አንዱ Lope de Vega የሚባል ፀሀፌ ተውኔት ነው፡፡ እንግዲህ ሼክስፒር አርባ አምስት ተውኔት ፅፎ አይደለ እንደዚህ አለም ሁሉ ያፈቀረው? ሎፔ ደ ቬጋ ደግሞ አንድ ሺ አምስት መቶ ተውኔት ፃፈ! እና “ብታምኑም ባታምኑም” እያንዳንዱ ተውኔት እንከን የማይወጣለት Masterpiece ነው ይባላል፡፡ (እንግድያው ምነው አንድ ተውኔት እንኳ በእንግሊዝኛ ትርጉም አልደረሰንም? ምስጢር፡፡)

… የአብዛኛው አገር ዋና ከተማ መሀል አደባባይ ላይ የሚታየው ሀውልት የንጉስ ወይም የጀግና ጦረኛ ነው፡፡ Madrid ዋነኛ አደባባይ ግን ልዩ ነው፡፡ Don Quixote በኮሳሳ ፈረሱ Rosinante እየሰገረ፣ ባለ ሙያውና የልብ ጓደኛው Sancho Panza በጐኑ ሲራመድ ያሳያል፡፡ 
እዚህ ላይ ስለ ደራሲና ስለ ድርሰት ሌብነት አንድ ነጥብ እናወሳለን፡፡ Miguel Cervantes Saavedra የፃፈው ልቦለድ ዋና ገፀ ባህሪ አንድ ከሲታ እብድ Knight ነው፡፡ Knight ማለት ለተጠቁና ለተጨነቁ አቅመ-ቢስ ሰዎች የሚዋጋላቸውና መብታቸውን የሚያስከብርላቸው ነው፡፡ Knights የነበሩት የዶን ኪሾት አያቶች ዘመን ከድቷቸው ስለሄደ እየደኸዩ መጥተው፣ ዶን ኪሾት በድህነቱ ላይ ድህነት ደረበ፡፡
ልቦለዱ ከምእራፍ ወደ ምእራፍ እያሳቀቀን፣ ውስጥ ውስጡን ግን ስለ አገሩ ታሪክ፣ ሀይማኖት እና ባህል ይፈላሰፋል፡፡ ገበያውን ተቆጣጠረው፣ ማለትም best Seller ሆነ፡፡
ሴንቫንቴስ ልቦለዱ መጨረሻ ላይ “ተፈፀመ” ብሎ ፅፎ ነበር፡፡ አንድ ሌባ “ዶን ኪሾት ቅፅ ሁለት” ብሎ አንድ ልቦለድ በሴርቫንቴስ ስም አሳተመ፡፡ ተራውን ገበያውን ተቆጣጠረ፡፡
Cervantes ተናደደ፣ ወኔው ተቀሰቀሰ፡፡ የራሱን Original “ዶን ኪሾት ቅፅ ሁለት” ፃፈ፡፡ መግቢያው ላይ ሌባውን ደራሲ አጋልጦ፣ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርጎ፣ በሚያስቅ ምፀት አብጠለጠለው፡፡ መፅሀፉ ገበያውን ተቆጣጠረው፡፡
አንባቢዎች ሌባውን ደራሲ አመሰገኑት፡፡ እሱ ባይሰርቅ ኖሮ እውነተኛው “ዶን ኪሾት ቅፅ ሁለት” አይፈጠርም ነበራ! ምቀኛ አታሳጣኝ! ይባላል በንዲህ አይነት ጊዜ፡፡ …
… ከዚያ ዘመን የስፓኝ ታላቅ ሰአልያን ሁሉ ዝነኛው Francisco Goya ይባላል፡፡ ስሙ Inquisition ከሚባለው ዘግናኝ ሀይማኖታዊ ስርአት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ፣ የአመጣጡ ታሪክ እነሆ ባጭሩ፡፡
የሮማዊት ካቶሊካዊት ጳጳሳት በአንድ ዘመን (በመቶዎች አመታት የሚቆጠር) የኤውሮፓ መንግስታት በቁጥጥራቸው ስር ነበሩ፡፡ በሀይማኖት በሚያዝዘው አስራት ስም ሰበብ ፈጥረው፣ ሊከፍለው ይችላል ብለው የገመቱትን “ግብር” እንዲከፍል ያዙታል፡፡ ይከፍላታል!
ለራሴ በቂ ገንዘብ ስለሌለኝ ልከፍል አልችልም ያለ እንደሆነ፣ ጳጳሱ ለዚያ አገር ህዝብ የሚከተለውን ያውጃሉ “ይህ ንጉስ በጥፋቱና በሀጢአቱ ምክንያት ከዙፋኑ ወርዶአል፡፡ በምትኩ ወንድሙ እገሌ ይነግሳል”
ይህ ስልጣን የሀዋርያው ጴጥሮስ ወራሽ ለሚባሉ ተከታታይ ጳጳሳት ትልቅ ፈተና ሆነባቸው፣ አልቻሉትም ወደቁ፡፡ የቤተክህነት አገልጋይ ሲባል፣ ከዲያቆን እስከ ጳጳስ ደናግል ናቸው (ማለት ከሴት ጋር ፆታዊ ግንኙነት የላቸውም)
እነዚህ ጳጳሳት ግን ይህን ዋነኛ ህግ ጥሰው በይፋ እቁባት ያስቀምጡ ነበር፡፡ አንዳንዶችም ልጅ ይወልዱ ነበር!
በዚህ ሁሉ አሳፋሪ ጋጠወጥነት መሀል Martin Luther ተከሰተ፡፡ ሀቀኛና ምሁር መነኩሴ ነበር፡፡ አንድ ሰንበት ጧት ምእመናን ከመግቢያው በር ጐን ማርቲን ሉተር የፃፈውን አነበቡ፡፡
የጳጳሳቱን በወንጀልና በሀጢአት መጨማለቅ በዘጠና አምስት አንቀፅ ይዘረዝራል፡፡ ማንበብና መፃፍ የሚችሉት ቃል በቃል እየገለበጡ ለሚያምኑዋቸው ዘመዶችና ወዳጆች ላኩት፡፡ ተቀባዮቹ ተራቸውን እየገለበጡ ለዘመድ ወዳጆቻቸው አስተላለፉት፡፡ እነዚያም እንደዚሁ፡፡
እንዲህ እየተባዛ ኤውሮፓን በሙሉ አዳረሰ! አሁን ሌላውን እንዝለልና “ወደ ገደለው እንምጣ” በታሪክ፣ በባህል እና በዘር ስለሚለያዩ፣ ደቡቦቹ አገሮች Catholic እንደሆኑ ሲቀሩ፣ ሰሜኖቹ Protestant ሆኑ፡ እንቅስቃሴው እንዲህ የተሰየመው Luther ጳጳሱን ምእመናኑ ፊት የኰነነበት ፅሁፍ “I Protest” ብሎ ስለሚጀምር ነው፡፡ እንጂ የሉተር አላማ ክርስትናን ለመከፋፈል አልነበረም፡፡
ማርቲን ሉተር “እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጥሮ ብዙ ተባዙ ብሎ አዘዘን እንጂ ድንግል ሁኑ ብሎ አዝዞ አያውቅም” ባይ ነው፡፡ እሱ ራሱም አግብቶ ሶስት ወልዷል፡፡
የማርቲን ሉተር አመፅና ውጤቱ ካቶሊክ ቤተ ክህነትን አስበረገገ፡፡ ከሉተር የተረፈችውን ካቶሊክነት ሌላ አመፀኛ ተነስቶ እንደገና እንዳይከፋፍላት ለመጠበቅ ሲሉ Inquisition የተባለውን የውን ቅዠት ፈለሰፉ፡፡ አንድ ሰው ከጓደኞቹ ጋር ሲጨዋወት ስለ ሀይማኖት አጠራጣሪ ነገር ከመሰላቸው፣ አንዳቸው ወደ Inquisition ቢሮ ሄዶ ስሙንና የተናገረውን ነገር ያሳብቅበታል፡፡ ምስክርም አያስፈልግ፣ ያሳባቂው ስምም አይጠየቅ፡፡
አንድ እሁድ ረፋድ ላይ (ማለት ከቅዳሴ በኋላ) ተከሳሹ ህዝቡ ክሱንና ፍርዱን ለመስማት ወደ ተሰበሰበበት አደባባይ ይጠራል፡፡ (በርካታ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ይመጣሉ)
Inqusitor (መርማሪ) ክሱን ያነብለትና “አጥፍተሀል?” ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ጥፋቱን አምኖ “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው፡፡ አይለምደኝም፡፡ ይፍቱኝ አባቴ” ይላል፡፡ ፆም ፀሎት እና ለድሆች ምፅዋት፣ እና ለቤተክርስትያን መባ ይታዘዛል፡፡ በቃ!
ሴጣን አሳስቶኝ አይደለም፣ እምነቴ ነው ብሎ ድርቅ ለማለት ከደፈረ ግን፣ ለዚሁ ጉዳይ የተዘጋጀው ደመራ ይለኮስና፣ ሰውየው በስነ ስርአት ከተረገመና ስሙ ከክርስትያን መዝገብ ከተሰረዘ በኋላ ይቃጠላል፡፡
ታሪክ የመዘገባቸውን ሁለት ዝነኛ ሰዎች ክስና ፍርድ ለናሙና ያህል እነሆ፡፡ በታዋቂነታቸዉ ምክንያት በተራ Inquisition አልተመረመሩም፡፡ ዳኛቸው The Grand Inquisitor ራሱ ሆነ፡፡ ለመላው ህዝበ ክርስትያን ትምህርት የሚሰጥ ምርመራ ይሆናል፡፡
አንዱ ተከሳሽ Galileo Galilei ነበር፡፡ አይናችንም ኦሪት ዘፍጥረትም ፀሀይ ምድርን ትዞራለች ብለው እያረጋገጡልን እያለ፣ ይሄ ሳይንቲስት ነኝ ባይ ጋሊሊዮ ምድር ናት ፀሀይን የምትዞራት ብሎ በፅሁፍ አስፍሮ አሰራጨ፡፡
ወንጀሉና ሀጢአቱ ከተነገረው በኋላ “ታምናለህ ወይስ ትክዳለህ?” ተጠየቀ
“አምናለሁ፣ የተከበሩ ዳኛ ሆይ፡፡ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው፡፡”
ለቤተ ክርስትያን የተወሰነ ወርቅ፣ ለነዳያን ምፅዋት፣ ለሙታን ምህረት ፀሎት የሚበራ ብዙ ሻማ ለፍርድ ቤት እንዲያስገባ ታዘዘ፣ ይፍቱኝ አባቴ አለ፣ ሀጢአቱ ተሰረየለት፡፡
ተሰናብቶ ሲሄድ፣ ያጀቡትን ወዳጆቹን “እንድያም ሆኖ፣ ምድሪቱ ፀሀይ መዞርዋን እንደቀጠለች ነው” አላቸው፡፡ እና ከዚያ በኋላ በርካታ ሳይንሳዊ ህግጋትን አገኘ (discover አደረገ)
ሌላው ተከሳሽ Giordano Bruno በስፋትና በጥልቀት እየተፈላሰፈ፣ እና እንደ ማርቲን ሉተር ፅፎ እያሰራጨ ለዘመኑ ምሁራን መሪ ብርሀን ስለሆነ የInqusition ባለስልጣናት (እና ጳጳሱ) እንደ ትልቅ አደጋ ይቆጥሩት ነበር፡፡
ጋሊሊዮ ምድር ናት ፀሀይን የምትዞራት ማለቱ አነሰና ይሄ እብድ ፈላስፋ ምን ይላል? ፀሀዮችና ፕላኔቶች ቁጥራቸው መጀመርያም የለው፣ ማለቅያም የለው፡፡ እዚያ infinity ውስጥ ልክ ቁርጥ የኛን አለም የሚመስሉ ብዙ ናቸው፡ ወዘተ፡፡ ሀሳቦቹ ለተከተላቸው አእምሮ አስፈሪ ጫካ ቢሆኑም ቅሉ፣ ከጫካው መውጣት አያስመኝም፡፡
እምነት ክህደት ተጠየቀ፡፡ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው ብሎ፣ ለስነ ስርአት ያህል ጥቂት ቅጣት ተቀብሎ ቢሄድ እሱም ዳኛውም ተገላገሉ ነበር፡፡ ጂዮርዳኖ ብሩኖ ግን የዋዛ ሰው አልነበረም፡፡ ይህ ታሪካዊ ትእይንት ፍልስፍናውን የሚያሰራጭበት አይነተኛ መድረክ እንዲሆን አቀደ፡፡ የምትናገረው አለህ ወይ ሲሉት፡-
“Inquisition ስላስጠራኝ አመሰግናለሁ፡፡ እስከ ዛሬ ፅፌ ያሰራጨሁት ሁሉ ሀቅ ነው፡፡ ይህን በማለቴ ታቃጥሉኛላችሁ፡፡ ይሄ ደመራችሁ ግን ስጋዬን እያቃጠለ እምነቶቼን ለመጪዎች ትውልዶች የሚያበራላቸው ችቦ ነው፡፡ ስትገድሉኝ፣ እስከ ዛሬ የዘራሁዋቸው ሀቆች ስር ሰደው ይለመልማሉ፡፡” ሳይንሳዊ ሀቅ ነው፣ አንጠራጠርም! …
… አሁን ወደ ሰአሊ ፍራንሲስኮ ጎያ እንመለስ፡፡ ወደ Studio Goya እየመጡ እሱ አቋቋም አቀማመጣቸውን ካስተካከለ በኋላ ለሰአታት ሳይንቀሳቀሱ “ደርቀው” ይቆያሉ፡፡
አንድ ቀን የመጣችው የልኡላን ዘር የሆነች ኮረዳ ግን እንዳያት ልቡን ማረከችው፡፡ በኋላ ስትነግረው እሷም እንዳየችው ነበር ፍቅር የያዛት፡፡ እጅግ በተዋበ አለባበስዋ ሲስላት ታላቅ የጥበብ ስራ ሆነች፡፡
“ለኔም የእድሜ ልክ እሴት ያለው ንብረት ይሆነኛል፣ አንቺም ስእሉ አልቆ ስታዪው ምንኛ የቆንጆ ቆንጆ እንቁ እንደሆንሽ እንዲገለፅልሽ፣ ራቁትሽን ልሳልሽ”
“ሁለታችንንም Inquisition ይበላናል”
“የፍቅር አምላክ ይጠብቀናል፡፡ ለብሰሽ አጊጠሽ የሰራሁት ስእል ቤታችሁ ተሰቅሎ አገር ያየዋል፡፡ ራቁትሽን ግን አንቺ በሌለሽበት በምናብ ብርሀን አይቼሽ የፈጠርኩት ነው፣ አንቺ አንዳች ጥፋት የለብሽም”
“እሺ እንግድያው” አለች፡፡ ያ ስእል (Maja Desnuda) በጥበብነቱ ከነሞና ሊዛ ጋር ይፈረጃል ይባላል፡፡ Inquisition እየተምጰረጰረ እስኪያልፍና የታሪክ ቅዠት ነበር ብለው እንደ ተረት እስኪያወሩት ድረስ ከሰአሊው በቀር ማንም ሰው አይቶት አያውቅም ይባላል፡፡
ከዚች ሽሽግ ስእል እኩል የታወቀ የጐያ ስእል አለ፡፡ Black ink በሚባለው በጣም ጥቁር ቀለም የተፈጠረ ነው፡፡
አንዲት ችጋር ያቀጠናት ሴት ተሰቅሎ ከሞተ ሬሳ አፍ ላይ ወርቅ ጥርሱን እየነቀለች ነው፡፡ እና ሙዋቹ እንዳያያት ወደዚያ ማዶ ትመለከታለች፡፡
ይህ ስእል የሰው ልጅን እጣ - ፈንታ አንዱን ገጽታ ጠልቆ ያሳያል ይባላል፡፡ Viva Francisco Goya!...
…አብዛኛው ሰው “እስፓኝ” የሚለውን ስም ሲሰማ “Bull Fight” የሚባለውን ስፖርት ያስታውሳል፡፡ አዋቂዎች እንደሚሉት ደግሞ “Bull fighting” ከትያትር ወይም ከስእል እኩል የሚያስደንቅ ጥበብ ነው፡፡ የሚመስጥ ጥበብ ከመሆኑ የተነሳ፣ በሬውና ስፖርተኛው ሲፋለሙ፣ ሰውየው እንስሳውን ለአንድ እስከ ሁለት ሰአት ሙሉ እጅግ በሚዘገንን ጭካኔ ካጐሳቆለው በኋላ ነው (ሰዎች torch ከሚደረጉት አያንስም)
እንድያም ሆኖ ጥበቡ ከመላቁ የተነሳ፣ በሬውም ከስፖርተኛው እኩል ይመሰገናል ወይም ይነቀፋል፡፡ ጐበዝ በሬ ከሆነ ሲሞት ከገዳዩ እኩል ይጨበጨብለታል፡፡ ጀግና ኮርማ ከሆነ ሰውየውን ወግቶ ይገድለዋል፡፡
(ልቦለድ ማንበብ የምታዘወትሩ አንባብያን ሳትኖሩ አትቀሩም በሚል፣ እነሆ ታሪካዊ መረጃ፡፡ የኖቤል ሽልማት አሸናፊው Earnest Hemingway ባለሙያዎቹ ያመሰገኑት Bull Fighter ነበር፡፡ Death in the Afternoon የተባለው ልቦለዱ ዋና ገፀባህሪ በመጨረሻ ተወግቶ የሚሞት Bull Fighter ነው - ከሰአት በኋላ ነው የስፖርቱ ሰአት፡፡)
…Captain Christopher Columbus ያገኘውን አዲስ አለም ኤውሮፓውያን መንግስታት እየተሻሙ ሲይዙ፣ Pizzaro የሚባለው በመርከቦች ፈረሰኛና እግረኛ ሰራዊት ጭኖ Mexico ደረሰ፡፡
ይህ ሰው ከመምጣቱ ከብዙ ሺ አመታት በፊት (ይላሉ Aztec የሚባሉት ሚክሲካውያን) ምንም አይነት ስልጣኔ ስለሌለ ሰዎች በየጐሳቸው እንደ ከብት በመንጋ በሚኖሩበት ጨለማ ዘመን አምላካቸው Quetzalcoatle ጐበኛቸው፡፡ ስላሳዘኑት ስልጣኔን ፈጠረላቸው፡፡ ካስተማራቸው የስልጣኔ ዘርፎች በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ስንጠቅስ በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ያስፈልገናልና ነው እንጂ አምላካቸው ግን ሁሉንም ዘርፍ ያስጨበጣቸው እኩል አቀናጅቶ ጊዜንና ሁኔታዎችን እያሰባጠረ ነበር፡፡ (እንደ Symphony Orchestra ዝያሜ)
ጭቃ እያዩ፣ የታተመበትን የሰው እግርም፣ የእንስሳ ኮቴም ሲያስተውሉት፣ እንደሚደርቅ ስለሚያውቁ የጭቃ እቃዎችን መስራት ይጀምራሉ፡፡ አመታት እስኪያልፉ፣ አንዳቸው በፀሐይ የደረቀውን ጭቃ በእሳት ይጠብሰዋል (ትጠብሰዋለች) የገል ስራ ጥበብ ተወለደ
ጥጥ ወይም ተመሳሳዩን አይታ ስትነካካው፣ ስትበጣጥሰው፣ ክር የመስራት ሀሳብ ይመጣባታል፡፡ ክሩን መግመድ ይከተላል፡፡ አእምሮና እጅ ስለማያርፍ፣ ስራ ከመፍታት በክርም በገመድም እየተጫወቱ እያለ፣ አንዷ genius ከቁጥዛልቆአትል ህልም ወይ ራእይ ይላክላትና፣ አብረዋት የሚኖሩት በአድናቆታቸው እያበረታቷት፣ በሀሳብም እያገዙዋት ሽመና ተፈጠረ፡፡ “ውጣ የቆዳ ልብስ ግባ የጥጥ መጐናፀፍያ”
እንዲህ በመሳሰሉ ሂደቶች የስልጣኔ ዘርፎች ሁሉ ተገኙና መሰረት ያዙ፡፡ ከዚያ በኋላ እነሱ መገንባቱን ቀጠሉበት፡፡ ወይም አምላካቸው የቀደደላቸውን ፈር እየተከተሉ ማረሱን ቀጠሉበት፡፡
ቁጥዛልኮአትል የመጣበትን ለሰው ስልጣኔ የማስተማር አላማ ካሳካ በኋላ ሲሰናበታቸው “በርቱ” አላቸው “ስልጣኔ የሚባለውን ትምህርት በሚገባ ስታጠናቅቁ፣ ተመልሼ ወደሚቀጥለው የእድገት ደረጃ እመራችኋለሁ” ብሏቸው ነበር፡፡ ከዚህ ስንቀጥል የታሪካችንን ውል የሚያስጨብጠን መረጃ (Information) እነሆ :-
የአዝቴክ ህዝብ እንስሳትን አለመደ እንጂ በፈረስ የመቀመጥ ሃሳብ መጥቶለት አያውቅም፡፡ ከስፓኝ ተጭነው የመጡት የፒዛሮ ወታደሮች ደግሞ እግረኞችም ፈረሰኞችም ናቸው፡፡ ስለዚህ አገሬው ፈረሰኞቹ ሲመጡ ሲያይ ባራት እግር የሚሄዱ፤ ከወገባቸው በላይ ሁለት ራስ ያበቀሉ የቁጥዛልኮአትል አጃቢዎች መሰሉት፡፡
ህዝቡ ሊቀበላቸው ሊያስተናግዳቸው ከየአቅጣጫው እየሮጠ መጣ፡፡ የፒዛሮ ጀግኖች ወንድ/ሴት፣ ህፃን አሮጊት ሳይሉ ጨፈጨፉት፡፡
ሊቀበላቸው እየመጣ የነበረው ንጉስ Montezuma ጭራቅ መሆናቸውን ሲሰማ ተመለሰ፡፡ ሰራዊቱን ክተት አለ፡፡ ሀይለኛ ጦርነት ሆነ፡፡ ንጉስ ተማረከ፡፡
ፒዛሮ ዋና አመጣጡ ዝነኛውን የሞንቴዙማ የወርቅ ክምችት ለመዝረፍ ነበር፡፡ አምጣ ሲለው ሞንቴዙማ “ለሱ እንደመጣህ ገና አማልክት አለመሆናችሁን እንደገባኝ ነው ያወቅኩት፡፡ በውጊያም እንደማልችልህ እያወቅኩ ነው የገጠምኩህ፡፡ በሰላም መገበሩን ክብሬ አይፈቅድም፡፡ ዳሩ አንተ ይሄ ሊገባህ አይችልም፤ ወርቅ የራበው ጅብ ነህ እንጂ ሰው እንኳን አይደለህም”
ፒዛሮ “ታመጣታለህ” ብሎ እስረኛውን “tourch አደረገው” ማለት በልዩ ልዩ ዘዴ (ጣቱን በመስበር፣ ፍም ገላው ላይ ላፍታ ማጣበቅ ወዘተ) አሰቃየው፡፡
“የኔስ ስቃይ ስትገድለኝ ያበቃል” አለው ሞንቴዙማ፣ በአፀፋው እኔ እድሜ ልክህን ቁጭት ፀፀት እያንገበገበህ እንድትኖር የሚያስገድድህን የነብስ ቁስል እተክልብሃለሁ”
“ከየት አምጥተህ”
“ከዚህ” አለው ጭንቅላቱን እያሳየ “ያለውጊያ ከመሰለፌ በፊት ሰባት ሳጥን ሙሉ ወርቅ በሰባት ግድግዳ ወታደር አሸክሜ ጫካ ወስጄ ቀበርኩት፡፡ እና አንተም ሌሎች ጅቦችም እንደቋመጣችሁ እንድትቀሩ ብዬ ሰባቱንም ተሸካሚዎች አስገደልኳቸው፣ የወርቁ ምስጢር ለዘላለም ታሸገ፡፡ በል ምን ትሆን”
የንጉስ ሞንቴዙማ ካንሰር ፒዛሮን እስከ እለተ ሞቱ እንዳሰቃየው ተስፋ እናረጋለን…
…የስፓኝ ኮሎኒያሊስት የጦር መሪዎችና አገረ ገዢዎች፣ በደረሱበት/የቅኝ አገሩን ቤተመቅደሳትና ሌሎች የስልጣን መለያ እሴት ያላቸው ስራዎችን አፈራረሱ፣ ማፍረስ ያልቻሉትን አቃጠሉ፣ ለማቃጠል ያቃታቸውን ለወደፊት Archaeology ጥናት ተውት፡፡ (ዛሬ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ስራዎች UNESCO (World Heritage site ብሎ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ እንደ አክሱም ሀውልቶች እንደ ላሊበላ ቤተክርስትያናት)
ቅኝ ግዛቶችዋን እንደጠቃሚ ንብረት ሳይሆን እንደ ጠላት ገንዘብ ስለደመሰሰቻቸው ስምዋ ከኮሎኒያሊስቶቹ አገሮች ሁሉ ግምኛ የከፋ ነው፡፡
…አዲሱን አለም እንደየአቅማቸው ከተቀራመቱት በኋላ፣ ማናለብኝ ሲሉ የነበሩት ሃያላን እርስ በርስ በጥርጣሬ መመዛዘን ጀመሩ፡፡ ቀጥሎ ማን ነው Super Power በሚል እስፓኝና እንግሊዝ መፋጠጥ ጀመሩ፡፡
እስፓኝ ጠላትዋን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጨፍለቅ Armada (የታጠቀው) ብላ የሰየመችውን fleet (የብዙ መርከብ ሰራዊት) መገንባት ጀመረች፡፡
በዚህን ጊዜ francis Drake የሚሉት ጃዊሳ (Pirate) በውቅያኖስ እንደ ልቡ ይዘዋወር ነበር፡ አንድ መርከብ ሳይሆን፣ ሶስት መርከብ አብረው ስለሚቀዝፉ፣ ያገኛትን መርከብ ይከብባታል፡፡ ትዘረፋለች፡፡ የእንግሊዝ መርከብ ከሆነች ግን ሶስቱ መርከቦች አጅበው አደጋ እማይደርስባት አካባቢ ድረስ ያጅቡዋታል፡፡ ከዚያ ወደ ጃዊሳ ሙያቸው ይመለሳሉ፡፡
ፍራንሲስ ድሬክ ስሙ እየገነነ ሄደ፡፡ አንድ ቀን ንግስት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊት አስጠርታ “ስለምትፈጽመው ሀገር ወዳድ ጀብዱ ሰምተናል፣ ቀጥልበት፡፡ የተያዝክ እንደሆነ ግን ለጊዜው እንግሊዝ ነው ብለን እንድንደግፍህ ሁኔታዎች አይፈቅዱም” ብላ አሰናበተችው፡፡
አንድ ቀን ማለዳ ላይ የድሬክ መርከቦች አርማዳው ወደሚገነባበት ወደብ መጥተው፣ አምስቱን መርከብ በእሳት አጋይተው፣ አንዳች ጉዳት ሳትደርስባቸው አመለጡ፡፡
ንግስት ኤልሳቤጥ አስጠራችው፡፡ የደስ ደስ Sir Francis ተብሎ በደማቅ ስነስርአት የማእረግ እድገት ከተሰጠው በኋላ ንግስቲቱ Admiral of the Royal Navy (የባህር ጦር ጠቅላይ አዛዥ) አድርጋ ሾመችው፡፡ …
…በስፓኝ ወደብ የወደሙት መርከቦችም ተተኩ፣ አርማዳውም ተጠናቀቀ፡፡ ወደ ኢንግላንድ ቀዘፈ፡የእንግሊዝ የጦር መርከቦች Calais ወደብ ዙሪያ ሲጠብቁ፣ እንመልሳቸዋለን የሚል ብዙ ተስፋ አልነበራቸውም፡፡
አርማዳው ብቅ ባለበት ሰአት Sir Francis ድንኳኑ ውስጥ ከጓደኛው ጋር Chess እየተጫወተ ነበር፡፡
መልክተኛ እየሮጠ መጥቶ “አርማዳው ደረሰ” አላቸው፡፡
ጓደኛው ብድግ ሲል፣ ሰር ፍራንሲስ “ቁጭ በል” አለው “ጨዋታችንን ጨርሰን እንደርስባቸዋለን” አለው፡፡
ጨዋታው አልቆ ወጥተው ሲያዩ፣ የእንግሊዝ ጠባቂ ታቦት ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተዋጋላቸው ይመስላል፡፡ ሀይለኛ ማእበል ተነሳ፡፡ የአርማዳውን መርከቦች እያንገላታ ከጥቅም ውጪ አደረጋቸው፡፡ አነስ ያሉት የእንግሊዝ መርከቦች ግን የለመዱት አይነት ማእበልም ስለሆነ፣ ብዙ ጉዳት ሳያደርስባቸው አለፈ፡፡
እስፓኝ ቅስምዋ ተሰበረ፡፡ እንግሊዞች “Rule Britannia, Britania rule the waves!” እያሉ እየዘፈኑ፣ ውቅያኖሶቹን ተቆጣጠሩ፡፡ ከዘመናት በኋላ ናፖሊዮን ቦናፖርት ኢንግላንድን ለመውረር የጦር መርከቦቹን ሲልክ የእንግሊዝ የባህር ሀይል Trafalgar ወደብ አጠገብ “ድባቅ መታው”
የተከበራችሁ አንባብያን፣ እስፓኝ በአዲሱ አለም ህዝቦች ላይ ለፈፀመችው ግፍ እንግሊዝ አይቀጡት ቅጣት ቀጣቻት አያስብልም? ነገሩ ግን “ማሞ ሌላ መታወቅያው ሌላ” ነው፡፡ ምክንያቱም እስፓኝም እንግሊዝም ሰዎች አይደሉም፡፡ ፒዛሮ እና ፍራንሲስ ድሬክ እንኳን ሊዋጉ ቀርቶ ጭራሹን አይተዋወቁም፡፡
እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

 

Read 4279 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:24