Saturday, 03 August 2013 10:19

በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ቃሲም ፊጤ ፍ/ቤት ቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

እስከ ሐምሌ 30 ክስ ይመሠረትባቸዋል
ከመሬት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፌደራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲፈለጉ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቃሲም ፊጤ በቁጥጥር ስር ውለው በትናንትናው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ፡፡ የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ክሱን እስከ ሐምሌ 30 እንዲያቀርብ ታዟል፡፡ 

የፌደራሉ የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአቶ ቃሲም ፊጤ በተጨማሪ ቀደም ብሎ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው የአስተዳደሩ የመሬት ልማት ቡድን መሪ አቶ በቀለ ገብሬ እና የዚሁ ክፍል ኦፊሰር አቶ ገብረየሱስ ኪዳኔ ላይ ምርመራ እያከናወነ የቆየ ሲሆን ከትላንት በስቲያ አቶ ቃሲም ፊጤን በቁጥጥር ስር አውሎ ትናንት ፍ/ቤት ካቀረበ በኋላ፣ የሶስቱም ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በአንድ መዝገብ መታየት ስላለበት ክስ የመመስረቻ ቀጠሮ እንዲሰጠው ብቻ ጠይቋል፡፡
አቶ ቃሲም ፊጤ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፍ/ቤቱ በንባብ ያሰማ ሲሆን የክሱ ፍሬ ሃሳብ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ወረዳ 17ቀበሌ 03 ውስጥ የሚገኝን ንብረትነቱ የኢንጅነር ግርማ አፈወርቅ የሆነን 500 ካሬ ሜትር ቦታ በመመሳጠር ለሌላ ግለሰብ እንዲሰጥ በማድረግና በዚህም ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በግል ተበዳይ ላይ አድርሰዋል የሚል ነው፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ የተጠርጣሪዎቹን ቃል መቀበሉንና መረጃዎችንም ማሰባሰቡን በመግለጽ የክስ መመስረቻ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ቃሲም በበኩላቸው፤ ጉዳዩ በማጣራት ሂደት ላይ ሆኖ አመት እንዳለፈው በማስታወስ እሳቸው ውጭ ሃገር ስልጠና ላይ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡ “ወደ ውጭ የሄድኩት ጉዳዩን እያወቅሁ ነው” ያሉት ተጠርጣሪው፤ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
በዋስትና ጥያቄው ላይ መርማሪው ያላቸውን አስተያየት ሲጠየቁም፤ ክሱ ሲቀርብ የሚጠቀሰው አንቀጽ ከባድ ስለሆነ የዋስትና መብቱን እቃወማለሁ ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ባስተላለፈው ትዕዛዝ፤ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ባለመቀበል ኮሚሽኑ እስከ ሐምሌ 30/2005 ክሱን እንዲያቀርብ አዟል፡፡

Read 54850 times