Monday, 16 September 2013 08:25

‘ቀይ ወጥ’ እና እንቁጣጣሼ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(1 Vote)

አዝናለሁ!
እንቁጣጣሽ ‘አመት ጠብቃ የምትመጣ ጭንቀት’ ናት - ለኔ ፡፡
‘እንቁጣጣሽ፣ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሃል፣ እንምነሽነሽ…’
የሚለውን ዘፈን ስሰማ፣ ደስታ ሳይሆን ጭንቀት ነው በደም ስሬ የሚዘዋወረው፡፡ መስከረም በጠባ ቁጥር፣ እንቁጣጣሽ ይዛብኝ የምትመጣውን ጭንቀት ማስተናገድ እጣዬ ከሆነ አመታት አልፈዋል። “እንኳን አደረሰህ!” ብሎ መልካም ምኞት እኔን አይመለከተኝም፡፡ አመታዊ ጭንቀት መጣች ብዪ ልደሰት አልችልም!! ምንም ማድረግ አልችልም፡፡
እርግጥ ድሮ ግን እንዲህ አልነበርኩም፡፡ የዛሬን አያድርገውና ድሮ ድሮ እንቁጣጣሽ በጉጉት የምጠብቃት የፍንደቃ አውዳመት ነበረች፡፡ አመት ጠብቃ ይዛው እስክትመጣ የምጓጓለት፣ የራሷ የሆነ ድምቀት ነበራት፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ ግን፣ እንቁጣጣሽ ድምቀት ትታ ጭንቀት ይዛልኝ መምጣት ጀመረች፡፡
ጊዜው 1984 ነበር፡፡
የአስራ አንድ አመት ልጅ እያለሁ ከመጣችው እንቁጣጣሽ በኋላ እየመጡ የሄዱት (ይቺኛዋን ጨምሮ) ሃያ ሁለት እንቁጣጣሾች ሁሉ፣ ለእኔ ጭንቀቶች ናቸው፡፡
አስራ አንደኛዋ እንቁጣጣሽ…
እንቁጣጣሽ… የኔ እንቁ… የኔ ፍልቅልቅ… የኔ ብዙ ብር… የኔ ብዙ ሳንቲም… የኔ መትረፍረፍ… እንቁጣጣሼ መጣች!!
ሰኔ ግም ሲል ጀምሮ በጉጉት ስናፍቃት ፣ በተስፋ ስጠብቃት ፣ ስዘጋጅላት፣ ሳቅድላት፣ መቼ በመጣች ስላት የከረምኳት እንቁጣጣሽ ደረሰች፡፡ አልነጋ ብሎ ከሚጎተተው፣ ከዚህ ዘልዛላ ሌሊት በኋላ ወደ ቤቴ ሰተት ብላ ልትገባና ብር በብር… ሳንቲም በሳንቲም ልታደርገኝ ከደጃፍ ቆማለች!!
እኔም ሆንኩ ታናናሽ እህቶቼ፣ እንቁጣጣሽ የምታመጣልንን አመታዊ ጸጋ ለመቀበል ዝግጅታችንን አጠናቀናል፡፡ በቀይ በቢጫ የደመቁ ስዕሎቻችንን ይዘን መንጋቱን እንጠባበቃለን፡፡
“የምን ስዕል ላይ ማፍጠጥ ነው?!.. አትተኙም እንዴ?” አለች እናቴ ቆጣ ብላ፡፡
“እህ!... ገና እኮ ነው… ትንሽ እንጫወት እንጂ?... ደሞ ከለር ያልቀባኋት አበባ አለች… ቀብቼ ከጨረስኩ በኋላ…” በማለት የተቃውሞ ድምጼን ማሰማት ጀመርኩ፡፡
ምናለ የእናቴን ትዕዛዝ በተቀበልኩ ኖሮ?!... ምናለ ድምጼን አጥፍቼ አልጋ ውስጥ በገባሁ ኖሮ?!... ምናለ ያንን ቀለብላባ ምላሴን የሆነ ነገር በቆረጠው ኖሮ?!
አባባ ከመኝታ ቤት ሆኖ የምለውን ሰምቶ ኖሮ፣ እንደተኮሳተረ በፒጃማ ከተፍ አለ፡፡
“ተናግሪያለሁ!... በኋላ ጉድ እንዳይፈላ!!... እንደማንም መረን አደግ፣ በየሰው ደጃፍ እየተለገባችሁ እንዳታዋርዱኝ!!... ከእኔ፣ ከናታችሁና ካጎታችሁ በቀር እንቁጣጣሽ ብላችሁ ከሌላ ሰው ፊት ብትቆሙ ጉድ ይፈላል!!...” አለ አባባ በሚያስፈራ አንደበት፡፡
“ኧረ ምን በወጣን!... እኛ ለማኝ ነን እንዴ?... ይሄው ሶስት ስዕል ብቻ ነው ያዘጋጀሁት” እህቴ አበባ የተሳለባቸውን ወረቀቶች ከፍ አድርጋ ይዛ ተናገረች። ደግነቱ አባቴ ለማጣራት አልሞከረም እንጂ፣ እኔ እንኳን ስድስት ስዕሎች ነበር ያዘጋጀሁት፡፡ የአባባን ትዕዛዝ ለማክበር ቃል ገብተን አልጋ ውስጥ ገባን፡፡
ሲነጋ…
እንቁጣጣሽን ገድ ያልኩት ከአባባ ባገኘሁት አንድ ብር ነው፡፡ እናቴም “እንቁጣጣሽ!” ብዬ የሰጠኋትን የአበባ ስዕል በአድናቆት እያየች፣ “በያመቱ ያምጣህ!” በማለት 50 ሳንቲም አሻረችኝ። ከአባባ በተሰጠን ፍቃድ መሰረት፣ ከእህቶቼ ጋር ወደ አጎታችን ቤት በማምራት አንድ አንድ ብር ተቀብለን እንደወጣን፣ እግረመንገዴን ከጋሽ ጣሴ ስሙኒ ሸቀልኩ፡፡ እማማ የሰራሽም ስልሳ ሳንቲም ለቀቁብኝ፡፡
እነ አባባ አክስቴ ቤት በግ ሊያሳርዱ እስከሚሄዱ ጠበቅኩና ከግቢያችን ሹልክ ብዬ ወጣሁ፡፡ በስማም!!... ጓደኞቼ ሁሉ ከወዲያ ወዲህ እየተራወጡ ነፍ ብር ይሸቅላሉ፡፡ እኔስ ምኔ ሞኝ ነው!?... ሮጥ ሮጥ ብዬ መስራቴን ቀጠልኩ፡፡ በስተመጨረሻ ግን ለእንቁጣጣሽ ያዘጋጀኋቸውን ስዕሎቼን ጨረስኩ፡፡ ተናደድኩ!! ምን አይነቱ ጌጃ ነኝ?... ለምንድን ነው አስር ስዕሎች ያላዘጋጀሁት?... ለሚቀጥለው ግን ሃያ ምናምን ነው የማዘጋጀው፡፡ እስከዛው ግን፣ በስዕል እጥረት ሽቀላ አያመልጠኝም፡፡ ለእናቴ የሰጠኋትን ስዕል ከሼልፉ ላይ ወስጄ ለቲቸር ጸደይ ሰጠኋትና ሽልንግ አሻረችኝ፡፡ ከዛም ከዳኒ ሁለት ስዕሎች በስሙኒ ሂሳብ ገዝቼ፣ በላይኛው ቅያስ በኩል ሄጄ እንቁጣጣሽ አልኩበት፡፡
ረፋድ ላይ…
ከመንደራችን መሃል ያለችው ጉብታ ላይ ቁጭ ብዬ፣ ያገኘሁትን ገንዘብ መቁጠር ጀመርኩ፡፡
በስማም!!... እንደዘንድሮ አይነት አሪፍ እንቁጣጣሽ አይቼ አላውቅም!!
ልጥጥ ነኝ!!
ለማስቲካና ከዳኒ ገዝቼ እንቁጣጣሽ ላልኩባቸው ተጨማሪ ሁለት ስዕሎች ያወጣሁት ወጪ ተቀናንሶ፣ ሰባት ብር ከስልሳ ሳንቲም አግኝቻለሁ!! ይህ ብር፣ በአስራ አንድ አመታት የህይወት ቆይታዬ በእጄ የያዝኩት ከፍተኛው ገንዘብ ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የራሴ ነው፡፡ እንደፈለግኩ የማደርገው የግል ገንዘቤ ነው!!
በሰባት ብር ከስልሳ ሳንቲሜ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ቀጭ ቀጭ እስክርቢቶ ልግዛ?... ቀዩዋን መነጽር ልግዛ?... ለወላጆች ቀን መንበሽበሻ ላቆየው?... አስማተኛ ሲመጣ ልይበት?... ጸጉሬን ፓንክ ልቆረጥበት? (እናቴ ነበረች የምትላጨኝ)… እየቆጠብኩ የህንድ ፊልም ልይበት?... ወይስ ምን ላድርግበት?...
ጨነቀኝ!... በጣም በጣም ጨነቀኝ!... ገንዘቤን አስራ ምናምን ጊዜ ደጋግሜ እየቆጠርኩ፣ መቶ ምናምን እቅድ ማውጣትና ማግባት ቀጠልኩ። ገንዘብ ሳገኝ እንዲህ አደርጋለሁ ስላቸው የነበሩ እቅዶቼ ሁሉ ተምታቱብኝ፡፡ ምን አይነት እዳ ነው?!
ብሬ አለመጉደሉን ለሀያ ምናምነኛ ጊዜ በመቁጠር ላይ እያለሁ የሆነ ድምጽ ሰምቼ በድንጋጤ ክው አልኩ፡፡ እርግጠኛ ነኝ አስቻለው ነው፡፡ አስቻለው የሰፈራችን ጉልቤ ነው፡፡ አምና ለመስቀል በዓል ሆያ ሆዬ ብለን ያገኘነውን ብር ቀምቶናል፡፡ ይሄ ዱርየ!... አሁንም ሊቀማኝ መጣ!
ሰባት ብር ከስልሳዪን ጭምድድ አድርጌ ይዤ ቀና ስል፣ አስቻለውን ሳይሆን ዳዊትን ከአጠገቤ ቆሞ አየሁት፡፡ ተመስገን አምላኬ!! ዳዊት ጓደኛየ ነው፡፡
“ስንት ሸቀልሽ?” አለኝ እጅ እጄን እያየ፡፡
“አንቺስ?” መልሼ ጠየኩት፡፡
“አንድ አስራ ምናምን… አንቺስ?” አለ በፍጥነት።
ትንሽ ቀናሁ፡፡ ብዙ ስእሎች ባዘጋጅ ኖሮ፣ ከዳዊት በላይ ብር አገኝ ነበር፡፡
“አስራ ምናምን” አልኩት ከእሱ ላለማነስ፡፡
“አሪፍ ነዋ!... ይበቃናል!” አለ ዳዊት ፈገግ ብሎ፡፡
“ይ… ይበቃናል… ለምኑ ነው የሚበቃን?” ኮስተር አልኩበት፡፡
“ለቀይ ወጥ ነዋ!”
የኔ ነገር!... ረስቼው ነው እንጂ፣ እንቁጣጣሽ ብለን ስንጨርስ በሽር ሱቅ ጋ ልንገናኝ ተቀጣጥረን ነበር፡፡ ዳዊት ግን ጎበዝ ነው፡፡ ገና በአንደኛው ሴሚስተር የተባባልነውን አስታውሶ መምጣቱ ደነቀኝ፡፡ ያኔ የአክስቱ ባል ከሃረር መጥቶ እያለ፣ የሆነ ሆቴል ወስዶ የጋበዘው ቀይ ወጥ እንዴት እንደሚጥም ሲነግረኝ፣ እንዴት እንደጎመጀሁ አልረሳውም፡፡ እርግጥ ያልጎመጀሁ ለመምሰል ሞክሬ ነበር፡፡
“ዴቭ ደሞ ጉረኛ ነህ!... እኛ ቤት ቀይ ወጥ ተሰርቶ የማያውቅ መሰለህ!?” አልኩት፡፡
“የሆቴል ቀይወጥ፣ እንደ ቤት ቀይ ወጥ መሰለህ እንዴ?... ብታየውኮ… በስማም!... ደሞ የአጥንቱ ብዛት!.. ካላመንከኝ ስኔፉን አሽተው?” ብሎ ቀይ ወጥ የበላበትን እጁን ጣቶች አንድ በአንድ አሸተተኝ፡፡ አቤት ሽታው!! የሆነ ተንኮለኛ ነገር አይደለ!?... ሆን ብሎ እጁን ሳይታጠብ ሳይሆን አይቀርም የመጣው። የጣቶቹ ወጥ ወጥ የሚል ሽታ ምራቄን አስዋጠኝ!!
“ተከየፍሽ አይደል?... አይዞሽ… የእንቁጣጣሽ ብር ስናገኝ፣ እናጋጭና የሆቴል ቀይ ወጥ ገዝተን እንበላለን” ብሎ አጽናናኝ፡፡ እኔም እንቁጣጣሽና ቀይወጥ የሚመጡበትን ቀን በሩቁ እያየሁ ተጽናናሁ። እርግጥ ነው… ከዛ በኋላ የሆቴል ቀይ ወጥ ስበላ ሶስት ጊዜ በህልሜ አይቻለሁ፡፡
ይሄው ከስንት ጊዜ በኋላ፣ ዳዊት ቀኑን ጠብቆ መጣና የቀይ ወጥ ቀጠሯችንን አስታወሰኝ፡፡
የጣቶቹ ሽታ ውል አለኝ፡፡ የሚጣፍጥ፣ ብዙ አጥንት ያለው የሆቴል ቀይወጥ በአይኔ ላይ ዞረ፡፡ ወፍራም ምራቅ አፌን ሞላው፡፡
እነ አባባ የአክስቴን በግ አሳርደው ሳይመለሱ፣ ቀይ ወጥ በልተን ልንመጣ ተስማማን፡፡
“ግን ቀይ ወጥ ስንት ነው?” በፍጥነት እየተራመድኩ ጠየቅኩት፡፡
“እኔ እንጃ!... ወይ አምስት ብር፣ ወይ ስድስት ብር፣ ወይ…” በግምት መለሰልኝ፡፡
ብቻ ኪሴ ቀዳዳ ሆኖ ብሬን እንዳልጥለው!... ሁለት ሱሪ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ አራት ከስልሳውን በአንዱ ሱሪዪ፣ ሶስት ብሩን በሌላኛው ሱሪዪ ኪስ አደርገው ነበር፡፡ የአንዱ ኪስ ቢጠፋ የሌላኛው ይተርፋል፡፡ አሁን ገና ገባኝ!... ቅመም ነጋዴው አባ አዘነ፣ ኬኔቴራ፣ ሸሚዝ፣ ሌላ ሸሚዝ፣ ኮት፣ ጃኬት፣ ካፖርት አድርገው ጋቢ የሚደርቡት ዝም ብለው አይደለም፡፡ ብዙ ብር ስላላቸው ነው!!
“ዴቭ…መቼም ቀይ ወጥ፣ ቢበዛ ቢበዛ ከሰባት ብር ከስልሳ አይበልጥም አይደል?...” ፈርቻለሁ፡፡
“አንተ ደግሞ!... ምን አስቦካህ?… አጋጭተን እኮ ነው እምንበላው” ኮስተር አለ፡፡
“እሱማ ነው!...” ኪሴ ቀዳዳ አለመሆኑን እየፈተሸኩ ተከተልኩት፡፡
ድልድይዋን አልፈን በታችኛው ቅያስ ስንታጠፍ፣ ድንገተኛ ስጋት ወረረኝ፡፡ ባለሁበት ቆምኩ፡፡
“የአባ ጌቴን ሆቴል ታውቀዋለህ አይደል?” አለኝ ዴቭ፡፡ መልስ ሲያጣ ዘወር ብሎ አየኝ፡፡ በፍርሃት ተውጬ ኪሴን ጨምድጄ ይዤ ቆሜያለሁ፡፡
መቼም እናቴ ባለፈው ይሄን ኪስ ጥሩ አድርጋ ሰፍታልኝ ካልሆነ ጉዴ ነው፡፡
“ምን ሆንክ?” ግራ ተጋብቶ ጠየቀኝ፡፡
“በላይኛው ቅያስ ይሻለናል፡፡ አስቻለው ካገኘን ብራችንን ይቀማናል” አልኩት፡፡
“አስቹ መታሰሩን ረሳሽው እንዴ?... አይ አንቺ ቦቅቧቃ እኮ ነሽ!” ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ምን ማለቱ ነው እሱ?!... በስንት መከራ ያገኘሁትን ገንዘብ ተቀምቼ፣ ዜሮ እንድወጣ ይፈልጋል እንዴ?... ያውም ደግሞ ቀይ ወጥ ሳልበላ…
መንገድ ቀይረን ጉዞ ቀጠልን - ወደ ቀይ ወጥ!!
በስማም!... ብር ግን እንዴት ነው የሚጨንቀው?!... ለካ አባባ ደመወዝ የሚቀበል ቀን አምሽቶ የሚመጣው፣ አስቻለው እንዳያገኘውና ብሩን እንዳይቀማው መንገድ እየቀየረ ስለሚጓዝ ነው!
“ስማ… መንከራፈፍ የለም!... ቀልጠፍ ብለን እንገባና ሳንደናበር፣ ዘና ብለን ወንበራችን ላይ ቁጭ እንላለን፡፡ ከዛ እናጨበጭባለን፡፡ ስናጨበጭብ የሆነች ንቅሴ ሴትዮ ትመጣና ‘ምን ልታዘዝ?’ ትለናለች፡፡ ያኔ ‘ቀይወጥ’ ምናምን ብለህ መንገብገብ የለም…” አለኝ ዴቭ፣ አባ ጌቴ ሆቴል አጥር ላይ ስንደርስ ወደ ጥግ ጎተት አድርጎ፡፡
‘መንገብገብ የለም’ ይለኛል እንዴ?… የምበላው ያጣሁ መሰለው እንዴ!?... የሆቴል ቀይ ወጥ ለመቅመስ ብየ እንጂ፣ አባባ ምን የመሰለ ሙክት አርዶ፣ እማማ ምን የመሰለ ጥብስና ቀይወጥ እንደሰራች አያውቅም?!
“እና ከዛ… ንቅሴዋ ሴትዮ መጥታ ‘ምን ልታዘዝ?’ ስትለን፣ እኔ ልክ አጎቴ ከሃረር የመጣ ጊዜ እንዳደረገው፣ ዘና ብዪ ‘የሚበላ ነገር ምን ምን አላችሁ?’ እላታለሁ፡፡ ከዛ… ” እያለ ረጅም ማስጠንቀቂያና መመሪያ ይሰጠኝ ጀመር፡፡
እርሙን አንድ ቀን አጎቱን ነዝንዞ ቀምሷል መሰል፣ ‘ያለኔ የሆቴል ቀይ ወጥ የሚያውቅ ሰው የለም’ ሊል አማረው፡፡
“ተከተለኝ…” ብሎኝ ከፊት እየመራኝ ወደ ሆቴሉ ግቢ ገባን፡፡
ፊትና ኋላ በመሆን ሰፊውን ግቢ አቋርጠን ወደ ዋናው በር በመጓዝ ላይ እያለን በረንዳው ላይ አንዲት ሴትዮ ከሆነ ሰውዬ ጋር ቢራ እየጠጡ አየሁ፡፡
በስማም!... ሰውዬው… ሰውዬው… ቲቸር ጌታቸው!... ጉዴ ፈላ!
የማረገውን አጥቼ ስንቀጠቀጥ፣ ሴትዮዋ በጣም እየሳቀች ዴቭን ስታየው አየኋት፡፡
“ወይ የዘንድሮ ልጆች!... ብቻ፣ እናንተም እንትን አምሯቹህ እንዳይሆን የመጣችሁት?!” አለች፡፡
“አ… አዎ!... አምሮን ነው” ዴቭ ቆም አለና መንተባተብ ጀመረ፡፡
ሴትዮዋ በሳቅ ፍርስ አለች፡፡
“ምናባክ ነው ያማረህ አንተ ውርንጭላ?” ሰውዮው ጣልቃ ገብተው ጠየቁ፡፡
ተመስጌን!... ሰውዮው ቲቸር ጌታቸው አይደሉም!
“ቀ… ቀይ ወጥ!” አልኩ ጣልቃ ገብቼ፡፡ ዴቭ ዘወር ብሎ ገላመጠኝ፡፡
“ደሞ ለቀይ ወጥ!... እናንተን ይመራችሁ እንጂ፣ በዋጋ ከተስማማን ሁሉም ነገር ሞልቷል!” ተሞላቀቀች ሴትዮዋ፡፡ ግን እኮ እውነቷን ነው!... ዋጋ ሳንስማማ ቀይወጣችንን እንክት አርገን ከበላን በኋላ፣ ‘ሀያ ብር ክፈሉ’ ብንባል ምን ይውጠናል?!
“ግ… ግን ስንት ነው?” ፈራ ተባ እያልኩ ጠየቅኩ።
ሴትዮዋ የሚያስፈራራ ሳቅ ሳቀች፡፡ ሰውየው በንዴት አፈጠጠብን፡፡
“ተራርቆ ገበያ አለ እንዴ?... ጎራ በሉና እንነጋገራ?” አለች ሳቋን ለማፈን እየሞከረች፡፡
“እኔኮ ‘ከገባን በኋላ ነው ዋጋ የምንጠይቀው’ ብዬ ነግሬው ነበር፡፡ ዝም ብሎ ይቅለበለባል!” አለ ዴቭ ዘወር ብሎ እየገላመጠኝ፡፡ ሃፍረት ተሰማኝ፡፡
ዴቭ በልበ ሙሉነት ወደፊት መራመድ ጀመረ፡፡
“ይቺን ይወዳል መንጌ!... ገና ሳትገረዙ ሸመታ ጀመራችሁ እናንተ ጉዶች?!” ሰውየው በቁጣ ገንፍሎ ብድግ አለ፡፡ ጠረጴዛው ላይ ከተደረደሩት ጠርሙሶች አንዱን ለማንሳት ሲሞክር፣ ሴትዮዋ ጣልቃ ገብታ ከለከለችው፡፡
“ለካ እናንተን ናችሁ ገበያውን ያስወደዳችሁት!... ውርንጭላ ሁሉ!” ሰውየው አምርሯል፡፡
ሴትዮዋ ተንከትክታ ስትስቅ፣ የቢራ ጠርሙስ ተንኮትኩቶ ሲወድቅ ቆሞ ማየት አይገባም፡፡
አምልጥ!... ፊታችንን አዙረን!
አቤት ሩጫ!...ዴቭን አስከትየ ሩጫዬን ስነካው፣ በአናቴ በኩል የቢራ መክፈቻ ሽው ብሎ አለፈ፡፡
ግቢውን እንዴት እንደወጣነው፣ ዋናውን አስፋልት እንዴት እንዳቋረጥነው፣ እንዴት አምልጠን ሰፈራችን እንደደረስን፣ አባቴ ‘የታባህ ነው በአመት በዓል ስትዞር የዋልከው?’ እያለ እያገላበጠ በቀበቶ ሲገርፈኝ እንዴት እንዳለቀስኩ፣ ከኪሴ በርብሮ ያገኘውን ብር ‘ከየት አመጣኸው?’ ብሎ ሲያናዝዘኝ ምን ምላሽ እንደሰጠሁት፣ ሰባት ብር ከስልሳ ሳንቲሜን በእጄ አስይዞ ሽንት ቤት ቀዳዳ ውስጥ ሲያስጥለኝ ምን እንደተሰማኝ የማውቀው ነገር የለም!!
የማውቀው ነገር ቢኖር፣ ከዚያ ወዲህ ቀይወጥና እንቁጣጣሽ ለእኔ ጭንቀት መሆናቸውን ነው፡፡

Read 3703 times