Saturday, 12 October 2013 13:34

ዋልያዎቹን እንደማውቃቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(23 votes)

ዋልያዎቹ በሚል ቅፅል ስያሜያቸው የገነኑት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት ከዓለም ዋንጫ ቢያንስ በ180 ደቂቃዎች ርቀት ላይ ናቸው፡፡ ከስምንት ወራት በኋላ በብራዚል አስተናጋጅነት ለሚደረገው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ዋልያዎቹ ከናይጄርያዎቹ ንስሮች ጋር ይገናኛሉ፡፡ የመጀመርያው ጨዋታ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም ይደረጋል፡፡ ለመሆኑ ከዋልያዎቹ አንዳንዶቹ ከናይጄርያ ጋር ስለሚፋለሙበት ጨዋታቸው ምን ብለዋል?…ማንነታቸው እና የግል ባህርያቸው እንዴት ይገለፃል? በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የምትታወቀው ኑራ ኢማም ስለዋልያዎቹ የምታውቃቸውን እውነታዎች፤ በተለይ በቅርብ የሚያውቋቸውን እማኝነት እና አስተያየታቸውን አሰባስባ የሚከተለውን ፅሁፍ ለስፖርት አድማስ አቅርባለች፡፡
ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አብረዋቸው በስራ ያሳለፉ ሰዎች በቅድሚያ የሚያነሱት ነገር አለ ቀልደኛነታቸው…በትልልቅ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ የሚጠቀሟቸው አነጋገሮች ፈገግታን ያጭራሉ ብለውም ጋዜጠኞች ይመሰክሩላቸዋል፡፡አሰልጣኝ ሰውነት ለተጨዋቾች በሚያወጡላቸው ቅጽል ስሞችም ይታወቃሉ። ለምሳሌ ከቀደሙት የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አንዱ የነበረውን የቀድሞ የኒያላ፣ ቅ.ጊዮርጊስና የደደቢት ተጫዋች መንግስቱ አሰፋን…ማሲንቆ የሚለውን ያወጡለት ናቸው። በዋልያዎቹ ወሳኝ ሚና ካላቸው ተጨዋቾች አንዱ ለሆነው ለአጥቂው አዳነ ግርማ “ወፍጮ” የሚለውን ስም ሸልመውታል፡፡ አዳነ ስለዚህ ቅፅል ስሙ የሚሰማውን ሲገልጽ መጀመሪያ አካባቢ በጣም እናደድ ነበር አሁን ግን በጣም የምወደው ስም ነው ይላል፡፡

ሌላውን ዋልያ በሀይሉ አሰፋንም የሚገርም ስም አውጥተውለታል፡፡ በሀይሉ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጠውን ማብራሪያ በማየት አፈ-ጉባኤ ብለውታል፡፡ እያዝናኑ መስራቱን ያውቁበታል ፡፡
ጀማል ጣሰው ቡሽራ በፕሪሚዬር ሊግ እና በክለብ ውድድሮች በተደጋጋሚ በሚያጋጥሙት ጉዳቶች ይታወቃል፡፡ በ2002 ዓ.ም የፕሪሚዬር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው…ከሩቅ ለሚመለከተው አይን አፋርና ዝምተኛ ሆኖ ይስተዋላል…ከተግባባ እና ከቀረበ በኋላ ደግሞ የሚጥላቸው አማርኛዎች ለየት የሉ ናቸው፡፡ የሰፈረ - ሰላሙ ሰው በቀልድ አዋዝቶ የሚፈልገውን መልእክት ጣል ማድረጉን ተክኖበታል፡፡
ደጉ ደበበ ገብረየስ የዋልያዎቹ አምበል ነው፡፡ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የጀመረው አሁን ካለው ስብስብ ውስጥ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከ10 ዓመታት በላይ አሳልፏል፡፡ የሰውን ሃሳብ መረዳት የሚችል ስብእና አለው፤ ለስራው የሚሰጠው ትኩረት እና ታዛዥነቱ ብዙዎቹ ያመሰግኑታል። ተግባቢና ሰው አክባሪ ነው፡፡ ስለ ተጋጣሚያቸው ናይጄርያ ሲናገር ‹‹ናይጀሪያን ለማሸነፍ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ከ2012ቱ አፍሪካ ዋንጫ እኛ እንዳስቀረናቸው የሚረሱት አይመስለኝም›› ብሏል፡፡
አይናለም ሃይለ ረዳ አዲግራት እያለ ኳስን የጀመረው በሚሰራበት ፕሮጀክት በግብ ጠባቂነት በመሰለፍ ነበር። በልጅነቱ ቁጡና ሃይለኛ ነበር አሁንም በስራው ላይ ይህ ኮስታራነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡…ትልቁ ነገሩ ግን ተነጋግሮ ይግባባል፤ ከዛ ውጪ ባለው ህይወቱ የቀረበውን ለማስጠጋት ችግር የለበትም፡፡ በትንሸ ነገር ቢናደድም ቂመኛ ግን አይደለም፡፡ ከኳሱ ጐን ለጐን ንግዱንም እያስኬደ ነው፤ የአንድ ልጅ አባትም ነው፡፡
ስዩም ተስፋዬ ሞገስ በብሄራዊ ቡድን የቀኝ የተከላካይ መስመር ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ሰውን እስኪግባባ ተቸጋሪ ነው ፡፡ ቀድመው ከቀረቡት ግን የሚከብድ ሰው አይደለም፡፡ ሁሌም የተረጋጋ ስፍራን ይመርጣል፡፡ ወከባን ነፍሱ ትጠላለች…ለቀለደው ይቀልዳል ቁም ነገር ላወራው ያወራል…አስተያየት ከመስጠቱ በፊት ቁጥብነትን ያበዛል…ጥንቃቄውም ለጉድ ነው…ከቡድኑ ልጆች ጋር ግን ጥሩ ግንኙነት አለው፡፡ ወደፊት በበጐ አድራጐት ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ፍላጐት እንዳለው ይናገራል፡፡ ድክመቱን በአግባቡ ለሚነገረው ማንም ሰው ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ስለ ወሳኙ ጨዋታ በሰጠው አስተያየት ‹‹…ለናይጀሪያ ብለን ልዩ ስራ አንሰራም ጥሩ ነገር እንጠብቃለን ፡፡›› ብሏል፡፡
አበባው ቡጣቆ ቡኔ ኳስን መጫወት የጀመረው አሁን በሚሰለፍበት የተከላካይ መስመር ነው፡፡

ቶሎ ተናዳጅ ነው፤ ብዙም የመጨነቅ ነገር አይሆንለትም፡፡ ህይወትን ቀለል አድርጐ መግፋት ይፈልጋል፡፡ ከእሱ ጋር ግን ለመግባባት መጀመሪያ መጨረሻ የሚባል ነገር የለም ቀለል አርጐ ይቀርባል…ሙዚቃ ይወዳል ለአሰልጣኝ ትእዛዝ ግን ጆሮ ይሰጣል…ከስራው ውጪ መዝናናት ይወዳል …ግልጽነትም መለያው ነው፡፡
አስራት መገርሳ ጐበና አስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረዶችን ያስተናገደ ጠንካራ ሰው ነው ፡፡ በግሉ ያያቸው ነገሮች አስተማሪዎቹ ሆነዋል ቀልደኛና ተግባቢ ነው። በዕምነቱ ጠንከር ያለ አቋም አለው፡፡ ቁመቱ ረጅሙ ተጫዋች…ሚስጥር ማፈኑን ያውቅበታል ይሉታል፡፡ በቡድኑ አባላትም ተወዳጅ ነው፡፡ እርስ በእርስ በመቀላለድም ዋናው ተዋናይ ነው፡፡ የዋልያዎቹ ስብስብ በጨዋታ እና እየሰሩ በመዝናናት ተወዳዳሪ እንዳልተገኘለት ብዙዎቹ ይናገራሉ፡፡
አዲስ ህንፃ ተክሌ በክረምቱ ዝውውር የሱዳኑን አል ሂላል ሸንዲ ተቀላቅሏል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መልከመልካም ከተባሉ አማላይ ተጨዋቾች መካከል ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በዚሁ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከዛምቢያ ጋር በተደረገው የምድቡ መክፈቻ ጨዋታ ላይ ኮከብ ተብሎም ነበር፡፡ ግድየለሽ እና ብዙም የንግግር ችሎታ ከማይሆንላቸው የዋልያዎቹ አባላት ውስጥ ይመደባል፡፡ የዋህ ነው ፡፡ላመነበት ነገር ስለ ማንም የማይጨነቅ ቀጥተኛ ተናጋሪ ነው፡፡ በጣም ለቀረበው እና ለወደደው ደግሞ ጆሮ ይሰጣል፡፡ እሱም ጭንቃ ጭንቅ ነገር አይመቸውም፡፡ …ብሶት የሚያበዛን የቡድን አጋር በማብሸቅ ደግሞ የሚያክለው የለም፡፡
ሽመልስ በቀለ ጐዶ ከዋልያዎቹ መካከል ለጐል ምቹ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ፤ የመሃል ሜዳ ሞተር ሆኖ ቡድኑን በማንቀሳቀስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ከፊቱ ላይ ፈገግታ አይታጣም፤ ሳቂታና ደስተኛም ነው፡፡ በየጨዋታው ከመሳተፍ ይልቅ በጓደኞቹ መቀላለድ ይደሰታል፡፡ ያልገባውንም ይጠይቃል፡፡ ብዙ ከማውራት ለማዳመጥ ትኩረት ይሰጣል፡፡
ከናይጄርያ ጋር ስለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ የሚያስበውን ሲገልፅ ‹‹ባለፈው አመት የኛ ነበር፡፡ ዘንድሮም ይደገማል፡፡›› ብሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሊቢያው ክለብ አልኢትሃድ የሚጫወተው ሽመልስ በዚሁ ክለብ የሚጫወት ናይጄርያዊ ስለ ዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ እየጠየቀ አላስቀምጥ ብሎት መሰንበቱን ሲናገር ምላሹ አሁን ምንም መናገር አልፈልግም የሚል ነበር። ሙያ በልብ ነው፡፡
ምንያህል ተሾመ በየነ በዋልያዎቹ አስደናቂ ታሪክ ውስጥ ከብዙዎች አዕምሮ በማይጠፉ ክስተቶች ትኩረት የሳበ ነው፡፡ ሁለት የቢጫ ካርድ ቅጣት እያለበት ከቦትስዋና ጋር በተደረገው ጨዋታ ተሰልፎ ብሄራዊ ቡድኑ 3 ነጥብ ለተቀነሰበት ጥፋት ምክንያት መሆኑ የመጀመርያው ነው። ሌላው ደግሞ በምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ጨዋታ ላይ በኮንጐ ብራዛቪል ወሳኟን የማሸነፊያ ጐል ከመረብ በማዋሃድ ታሪክ ሰሪ ሆኖ ጥፋቱን ያረመበት ነው። ምንያህል ተረበኛና ቀልደኛ ነው፡፡

ትንሽ የመነጫነጭ ባህርይ ቢኖረውም እያዝናና ስሜቱን በመናገር ይታወቃል። በብሄራዊ ቡድን ሲጫወት ለውጤታማነት በሚከፍለው መስዋትነትና ያልተቆጠበ ጥረት በአሰልጣኙ እንዲወደድ አድርጐታል፡፡ ምንያህል ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድኑ የተሰለፈው ከአራት ዓመት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከናይጄሪያ ጋር በተደረገው የመልስ ግጥሚያ ነበር፡፡ ያንግዜ ዋልያዎቹ በናይጄርያ ሜዳ 4ለ0 በሆነ ውጤት በንስሮቹ መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ግን ናይጄርያን ጥለን በማለፍ በዓለም ዋንጫ ከስፔንና አርጀንቲና ጋር መጫወት እንፈልጋለን እያለ ነው፡፡
አዳነ ግርማ ገ/የስ አትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደራቀችበት አህጉራዊ ውድድር በመመለስ በ29ኛው አፍሪካው ዋንጫ ላይ በተሳተፈችበት ወቅት ብቸኛዋን ጎል ለብሄራዊ ቡድኑ በማስቆጠር ታሪክ ሰርቷል፡፡ በዚሁ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በደረሰበት ጉዳት ግን ያለፉትን ወራት ሁኔታዎች ለሱ መልካም አልነበሩም፡፡ ከጉዳቱ ለማገገም ረጅም ጊዜ ቢፈጅበትም አሁን ግን ወደ ቀድሞ አቋሙ በመመለስ በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ የቡድኑ አዝናኝ እንደሆነ የተመሰከረለት አዳነ ጨዋታ አዋቂ ነው። በአጨዋወቱም በማንኛውም ቦታ በመሰለፍ ለቡድኑ አስተዋፅኦ ለማበርከት ቅሬታ የለውም፡፡ ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ መስመር መጫወትን ለምዶታልና… በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ዋልያዎቹ ደቡብ አፍሪካ ላይ መንገድ ሰይመውለት ነበር ፡፡ በዚያች አገር ብዙ ሰው ስለማውቅና ወንድሜም ስለሚገኝ አገር ምድሩን ሳሳያቸው ስለነበር ነው መንገድ የሰየሙልኝ ይላል፡፡ ወፍጮ በሚል በአሰልጣኝ ሰውነት የወጣለትን ቅጽል ስሙንም ይወደዋል። ስለ አሰልጣኝ ሰውነትን ሲናገር ደግሞ እንድትታዘዘው የሚያረግ አሰልጣኝ ነው ብሏል፡፡ ‹‹ተጋጣሚያችን በቁጥር ከኛ የተሻለ ነው ግን አሁን ጭንቀቱ ከኛ ይልቅ የእነሱ ነው›› በማለት በናይጄርያው የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ዙርያ የተሰማውን ተናግሯል፡፡
ሰለሃዲን ሰኢድ አህመድ ለዋልያዎቹ ወሳኝ ጎሎችን በተለይም በመጀመሪያዎቹ የምድብ ማጣሪያዎች ላይ በተከታታይ በማስቆጠር ወሳኝነቱን አስመስክሯል። ሰለሀዲን ሰኢድ ለቡድን አጋሮቹ የህይወት ልምዱን በቅንነት ያካፍላል፤ ምክሩንም ይለግሳል፡፡ ብዙ ማውራት ባይሆንለትም ከሁለት ቋንቋዎች በላይ ተናጋሪ ነው፡፡ ላገኘው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ይሰጣል፡፡ ቀደም ሲል ስለ ልምምድ የነበረው ግንዛቤ ወጥቶ መጫወት ከጀመረ በኋላ ተቀይሮአል፡፡ በግብፁ ዋዲ ዳግላ ክለብ ስር የሚገኘው ሳላ ዝምታን ያበዛል፡፡ ስለ ናይጄርያው ትንቅንቅ ሃሳቡን ለሱፐር ስፖርት ሲሰጥ “እናከብራቸዋለን እንጂ አንፈራቸውም…እነሱም ለእኛ ንቀት ማሳየት የለባቸውም ጠንቅቀው ያውቁናል ስለዚህ በግባቡ ስራችንን ጠንክረን እየተዘጋጀን ነው›› ብሏል፡፡
ጌታነህ ከበደ ጊቤቶ የዲላው ተወላጅ …የእግር ኳስ ሂወቱ ፈጣን ነው በ2001 ዓ.ም እውቅና የሰጠው ሂደቱ አሁንም ወደ ማንዴላዋ ሀገር ደቡብ አፍሪካ አሻግሮት ቢድቪስት ዊትስ ለተባለ ክለብ እየተጫወተ ነው፡፡ጐሎችንም እያስቆጠረ ነው፡፡ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር በነበረው ጨዋታ ባጋጠመው ድንገተኛ ጉዳት ባለመሳተፉ ክፉኛ ማዘኑን ቢገልጽም ለውጤቱ መገኘት የቡድን አጋሮች ባደረጉት ርብርብ ኮርቷል፡፡ ከእሱ ጋር ረዘም ያለ ወሬ ለማውራት ጥሩ የርእስ ፈጠራ ክህሎት ያስፈልጋል፡፡ አይን አፋርነቱ ቀደም ሲል ያጠቃው ነበር አሁን ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ መጥቷል፡፡ ልክ እንደ አይናለም ሁሉ እሱም ኳስ መጫወት ሲጀምር በግብ ጠባቂነት ነበር፡፡ በስብስቡ ውስጥ ግን የጨዋታ ፈጠራ ባይሆንለትም ቀልዱም ላይ ብቅ ይላል፡፡

ለቅርብ ወዳጆቹ ግልጽነቱ አንዱ መገለጫ ባህሪው ነው ፡፡
በሀይሉ አሰፋ ጐበዜ ዋልያዎቹ ገደኛው ይሉታል። ተቀይሮ በገባባቸው ግጥሚያዎች ጐል ባያስቆጥርም እንዲቆጠር ምክንያት ሲሆን በተደጋጋሚ በማጋጠሙ ነው። የበርካታ ቅጽል ስሞች ባለቤት ነው ቱሳና ዶክተር ከነዛ መካከል ይገኝበታል፡ ወደ ቀለም ትምህርቱ ያመዝናል። ነገርን አብራርቶ መግለጽ ይችልበታል፡፡ ማንም ለሚጠየቀው ጉዳይ ምላሹን ከነማብራሪያው ይሰጣል፤ ቁም ነገሩ ያመዝናል…ሰው አክባሪም ነው …በቡድኑ የዲፕሎማትነት ባህርይም አለው …ለተረቡም ጆሮው ክፍት ነው የማህበራዊ ህይወት ግንኙነቱ ጥሩ ነው፡፡ ስብሰባ ላይ ሃሳቡን በሚፈልገው መንገድ የመግለጽ ፍርሃት የለበትም፡፡ ለጠቅላላ እውቀት ግንዛቤም ቅርብ ነው፡፡
ሲሳይ ባንጫ ባሳ ለብሄራዊ ቡድኑ የሳቅ ምንጭ የሆነ ወሳኝ ሰው ነው፡፡ ደስታውንም መከፋቱንም ለመግለጽ ቦታ እና ጊዜ አይመርጥም፡፡ ሰው ምን ይለኛልም እሱ ጋር ቦታ የለውም፤ በቃ…ማድረግ ያለበትን ከማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡ አንዳንዶች ስሜታዊ ይሉታል፡፡ ቶሎ መናደድ እንደገና መቀዝቀዝ ባህርይው ነው፡፡ በቡድኑ ጭፈራና ልዩ ድምጽ ሲያስፈልግ የሚጋበዘው እሱ ነው፡፡ መለያ ምት በማዳን ብቃቱም ይደነቃል፡፡
ብርሃኑ ቦጋለ ቦይዛ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የጀመረው በ1998 ዓ.ም ነበር፡፡ ዝምታን ያበዛል ረጋ ያለ ነው፤ በጣም ካልቀረቡት ላይረዱት ይችላሉ፡፡ የኳስ ሜዳው ልጅ የንግግር ችግር ባይኖርበትም ብዙ ከመናገር የተቆጠበ ነው፡፡ ቀለል ያለ ቀረቤታ ይስማማዋል፡፡ ተገቢውን አክብሮ መስጠቱ ላይ እሱም የተካነ ነው፡፡ የሚዲያ ሰው አይደለም ግን ከተጠየቀ ለትብብሩ ቀና ምላሹን ይሰጣል፡፡

Read 7084 times