Saturday, 28 December 2013 10:53

አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በአጋሮ ከተማ ያሰራው ህንፃ ተመረቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

• ባንኩ በአዲስ አበባም በክልል ከተሞች ህንፃ ማስገንባቱን ቀጥሏል

      አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በቡና አብቃይነቷ በታወቀችው አጋሮ ከተማ ያሰራው ህንፃ ታህሳስ 5 ቀን 2006 ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ያሰራው ባለ 4 ፎቅ ዘመናዊ ህንፃ፣ ለግንባታው 22 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን ለአጋሮ ቅርጫፍ የቢሮ አገልግሎት የሚተርፉት ክፍሎች ለአካባቢው የንግድ ማህበረሰብ እንደሚከራዩ ገልጿል፡፡ አዋሽ ባንክ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፤ በተለያዩ ከተሞች ዘመናዊ ህንፃዎች ማስገንባቱን ጠቅሶ በአዳማ ከተማ የተሰራው ባለ 8 ፎቅ ህንፃ ከሁለት ዓመት በፊት ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩን ፣በሻሸመኔ ከተማ የተገነባው ባለ 4 ፎቅና በነቀምቴ ከተማ የተሰራው ባለ ሁለት ፎቅ ህንፃዎችም አገልግሎት መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ቤተክርስቲያን ፊት ከፊት በ250 ሚሊዮን ብር እያስገነባ ያለው ባለ ሁለት ቤዝመንትና ባለ 10 ፎቅ ህንፃ ግንባታ እየተፋጠነ ሲሆን ከካዲስኮ ህንፃ ፊትለፊት ለሚገነባው ባለ 7 ፎቅ የቡልቡላ ቅርንጫፍ ህንፃ፣ የተቋራጭ መረጣ እየተደረገ መሆኑንና በሀዋሳ ከተማ ለሚሰራው ባለ 6 ፎቅ ህንፃ ግንባታ የሰጨረታ ሰነድ ለህንፃ ተቋራጮች እየተሸጠ መሆኑን አመልክቷል፡፡

Read 1483 times