Monday, 03 February 2014 12:45

ወደ ደብረማርቆስ ይጓዝ የነበረ መኪና ተገልብጦ ስድስት ሰዎች ሞቱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(19 votes)

ከሞቱት አምስቱ የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች ናቸው

ባለፈው ረቡዕ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ግቢ ተነስቶ ወደ ደብረማርቆስ ይጓዝ የነበረ ሳንሎንግ መኪና ተገልብጦ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ፣ 18 ሰዎች መቁሰላቸው ታወቀ፡፡ ከሞቱት ውስጥ አምስቱ የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች እንደሆኑም ታውቋል፡፡ የአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ፀሐፊ ወ/ሮ ዘይነባ ይመር፣ የጽ/ቤቱ የመልዕክት ሰራተኛ ወ/ሮ መልካሟ አወቀ፣ እንደሁም አቶ ምኒልክ በቀለ፣ አቶ ተስፋዬ ጂኖሬ፣ ወ/ሮ መሠረት ደጀኔ የተባሉ የሚኒስትሩ ሠራተኞች በአደጋው ህይወታቸው አልፏል፡፡

ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የተወከሉት ሴት ግን ምንም አደጋ ሳይደርስባቸው በዚያው ምሽት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የክልሉን የስድስት ወር የትምህርት አፈፃፀም ለመገምገም ከትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ባለሙያዎች፣ የዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች፣ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን የልዩ ፍላጐት ትምህርት ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካሎች የተወከሉ ወደ 30 ያህል ሰዎች በመኪናው ውስጥ ሲጓዙ እንደነበር ከአደጋው ተርፈው ጳውሎስ ሆስፒታል በህክምና ላይ ያገኘናቸው የልዩ ፍላጐት ትምህርት ቡድን አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ወልደቂርቆስ ገልፀዋል፡፡

የአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታውን አቶ ፉአድ ኢብራሂምንና ሌሎች ባለስልጣናትን የያዘው መኪና ቀደም ብሎ የሄደ ሲሆን ደብረማርቆስ ለመድረስ 10 ኪሎ ሜትር ሲቀረው አደጋው መድረሱን ሰምቶ እንደተመለሰም ታውቋል፡፡ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር የተነሳው ሳንሎንግ መኪና፣ አባይ በረሃ ውስጥ አባይ ወንዝ ጋር ሊደርስ በግምት ሁለት ወይም ሶስት ኪሎ ሜትር ሲቀረው ባልታወቀ ምክንያት ድንገት ተወዛውዞ መገልበጡን፣ በቀኝ እጃቸው ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው የተረፉት በትምህርት ሚኒስቴር የሞያ ፍቃድና እድሳት ዳይሬክቶሬት ክፍል ባለሙያ የሆኑት አቶ ጴጥሮስ መላኩ ተናግረዋል፡፡ በአደጋው አራት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ከሟቾቹ ውስጥ የአምስት ልጆች እናት የሆኑትና በአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ጽ/ቤት ፀሐፊ የነበሩት ወ/ሮ ዘይነባ ይመር ይገኙበታል፡፡

አደጋው ከደረሰ በኋላ ከኋላ ይጓዝ የነበረ የትምህርት ሚኒስቴር መኪናና የኩዩ ወረዳ አምቡላንስ ቶሎ ደርሰው አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ጐሀ ፂዮን ጤና ጣቢያ፣ ሌሎቹን ኩዩ ሆስፒታል የወሰዱ ሲሆን ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸውን ደግሞ ወደ አዲስ አበባ እንዳመጧቸው ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ጠቁመዋል፡፡ የአደጋውን መንስኤ በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሚያውቁት ነገር እንዳለ ጠይቀናቸው “ጉዳዩን ትራፊክ ፖሊስ ይዞታል፤ አሁን ምንም ነገር መግለጽ አልችልም” ብለውናል፡፡ አዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ደውለን መንስኤውን ለማጣራት ስንሞክር፤ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ “አደጋው የደረሰው ሌላ ክልል ውስጥ በመሆኑ በአካባቢው ፖሊስ ነው የሚጣራው” የሚል ምላሽ የሰጡን ሲሆን የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን እንደሰሙ አክለው ነግረውናል፡፡ በአደጋው የሞቱት ሰዎች በትላንትናው እለት በየአካባቢያቸው የቀብር ስነስርዓታቸው ተፈጽሟል፡፡

Read 8724 times