Saturday, 15 February 2014 12:41

ወስላታው ግብር ከፋይ!

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(2 votes)

“ክቡር ፍርድ ቤት፤ መስረቄ እውነት ነው፣ግን ግብር ከፋይ ነኝ”

በየትም አገር ያለ መንግሥት በባህርዩም ሆነ በተቋቋመበት ሕግና ሥርዓት ወይም ርዕዮተ ዓለም ሊለያይ ቢችልም በአስገባሪነቱ ግን አንድ ነው፡፡ መንግሥት ሆኖ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ከሚገዛው ወይም ከሚያስተዳድረው ወይም ከሚመራው ህዝብ ላይ ግብር የመሰብሰብ መብት አለው። ይህ “ተፈጥሮአዊ” መብቱ ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም የማንኛውም አገር መንግሥት ከአገሩ ህዝብ ላይ ግብር መሰብሰብ ካልቻለ ህልውና የለውም፡፡ መንግሥት የሌለው አገርና ህዝብ ደግሞ እንደ ዝንጀሮ መንጋ ጉልበተኞች የሚገዙት፤ ወደፈለጉበት የጥፋት ጐዳና የሚመሩትና ራሱም ለጥፋት የተዘጋጀ ይሆናል፡፡
 መንግሥት ግብር የመሰብሰብ መብቱ ተፈጥሮአዊ  ነው ቢባልም የግብሩን መጠንና ዓይነት ግን በህግ መወሰን ይኖርበታል፡፡ በዚያው ልክ ስልሞውን አንቆ ግብር የሚቀበለውን (በግዱ የሚያስከፍለውን) ህዝብ ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፣ ይህን ካላደረገ ወድዶና ፈቅዶ የመረጠው ህዝብ ወይም እንደ መንግስቱ ባህርይ በግድ የሚገዛና የአምባገነኖች ሰለባ የሆነውም ቢሆን የሰላሙ መደፍረስ፣ የኑሮው ቀውስ እየተባባሰ ሲመጣ፣ወደ አጠቃላይ ትርምስ ያመራና አምባገነኖችም አገሪቱም አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡
ምንም እንኳ ለህዝብ ሰላምና ፀጥታ ሲባል የሚቋቋሙ የፖሊስ፣ የፀጥታ ኃይልና የፍትህ አካላት መሣሪያነታቸው ለገዥ መደቦች እየሆነ አመርቂ ሥራ ማከናወን ቢሳናቸውም፣ በአገራት ሁሉ የመቋቋማቸው ዓላማ ህዝብን ያማከለ ነው፡፡ ግን የሚሾም የሚሽራቸው፣ የሚገነባ የሚያፈርሳቸው መንግሥት ስለሆነ ነገራቸው ሁሉ “እንደንጉሡ አጐንብሱ” ሆኖ ቀርቷል፡፡
በዓለም ላይ ካሉ አገሮች ሁሉ ከፍተኛ ግብር በመጣልና በመሰብሰብ የሚታወቁት የስካንዲቪያን አገሮች ናቸው፤ ሕግና ሥርዓት በማስጠበቅ በኩልም የሚወዳደራቸው የለም፡፡ ቀላል ማሳያ ልጥቀስ፤ አንድ ወቅት ስዊድንን የመጐብኘት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር። በእግር ስንዘዋወር ያስተዋልሁት ጉዳይ መቸም የሚረሳኝ አይደለም፤ ከእኔ ጋር የነበሩ ያገሬ ሰዎችና አስጐብኛችን መንገድ ለማቋረጥ ገና ጫፉ ስንደርስ መኪኖች ሁሉ በርቀት ይቆማሉ፡፡ ጉዳዩ ሲደጋገም አሽከርካሪዎች ለምን እንዲህ እንደሚያደርጉ አስጐብኝያችንን ጠየቅኋት፤ የሰጠችኝ መልስ እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡
“በሀገራችሁ ቅድሚያ የሚሰጠው ለእግረኛ ነው ለአሽከርካሪ?” ብላ መልሳ ጠየቀችኝ
“ዜብራ መንገድ ላይ ገና መች ደረስንና?” አልኋት የምንተፍረቴን፤ አገሬ በሰው አገር ሰው እንዳትታማብኝ በመጠንቀቅ፡፡
“ፖሊስም በአካባቢው አይታይም፤ ቅድሚያ ባይሰጡስ ማን ይቆጣጠራቸዋል?” የሚል ሌላ ጥያቄ አከልሁላት፡፡
“ፖሊስ? ፖሊስ መንገድ ላይ ምን ሊሠራ ይቆማል? እኛ አገርኮ መንገዶች ሁሉ በካሜራ የተደራጀ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ተዘርግቶላቸዋል፤ ፖሊሶች ጣቢያቸው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎቻቸው ቁጭ ብለው በየትኛው መንገድ ላይ ምን እንደተፈጠረ፣ ማን ችግሩን እንዳደረሰ መከታተል ይችላሉ፡፡ በአጥፊው ግለሰብ ላይ ተገቢውን ቅጣት ይጥሉና፣ ከባንክ ሂሳቡ የቅጣቱ ገንዘብ ተቆርጦ ደረሰኙ በአድራሻው ይላክለታል እንጂ ከአጥፊው ጋር ሲጨቃጨቁ የሚውሉበት ምንም ምክንያት የለም፤ ፖሊስ የሚያስፈልገው ምን አልባት ከባድ ወንጀል ከተፈፀመ ብቻ ነው፡፡ እሱም ቢሆን የሚያጋጥምበት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው” አለችኝ፡፡
በእውነት ቀናሁ፤ ካየሁት የመንገድ ጽዳት፣ የቤት አሠራር ውበትና የህዝቡ ዕድገት ይልቅ በዚህኛው ሥርዓታቸው ከልብ ቀናሁ፡፡ ምን አለ የእኛ አገር የትራፊክ ፖሊሶችን ፊት የማያሳይ ሥርዓት ቢዘረጋና አሽከርካሪዎች እንደ ስዊድን ለሰው ፊት ሳይሆን ለህግ ብቻ ተገዥ ሆነው፣ በየቀኑ የንፁሃን ደም አስፋልት ሲያጥብ ከማየት በተገላገልን አልኩ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ምኞት ነው፡፡
እዚያው ስዊድን ውስጥ አንድ ችሎት ላይ የሰማሁት ጉዳይም አስገርሞኛል፤ አንድ ግለሰብ እኩለ ሌሊት ላይ በከተማዋ ሲዘዋወር አንድ የማያውቀው ሰው ያስፈራራዋል፤ ግን የደረሰበት አንዳችም ጉዳት የለም፡፡ ሰውየው ምን አደረገ መሰላችሁ? ጠዋት ላይ “ግብር የምከፍልህኮ መብቴን በተሟላ መልኩ ልታስከብርልኝ ነው፤ አንተ ግን ከስጋት ነፃ የመሆን መብቴን አላስከበርክልኝም” ብሎ በመንግሥት ላይ ክስ መሠረተ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት እሰጥ አገባ ሊል አይችልም፤ ዜጐቹን ከሁሉም በላይ ያምናል፣ የዜጐቹን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣት እንዳለበትም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለዚህ የዜጋውን ከ “ስጋት ነፃ የመሆን መብትን” ለመጠበቅ ሲባል ካሳ ከፈለና ተገላገለ፡፡ እኛ አገርኮ እንኳን ከስጋት ነፃ የመሆን መብት--- ብቻ ሆድ ይፍጀው፡፡
ግብር እንከፍላለን፤ በተቀጣሪነት ከምናገኘው አነስተኛ ገቢ እንገብራለን፤ ከምንጠጣው ሻይና ከምንበላው ምግብ ሳይቀር ግብር ይቆረጥብናል፡፡ ግን ሰላማችን የታለ? ገዢያችንኮ ብዙ ነው፤ የመንደር ዱርዬው፣ የታክሲ ወያላው፣ ወረፋ አስከባሪው፣ ወረዳው፣ ቀበሌው፣ ክፍለ ከተማው፣ ከተማ አስተዳደሩ፣ ምኑ ቅጡ…የገዢያችን ቁጥር መብዛቱ፤ ግን መብታችንን የሚያስከብርልን አካል የቱ እንደ ሆነ በውል አይታወቅም፡፡
ርዕሰ ጉዳያችን ከግብር ጋር የተያያዘ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በሃገራችን የተጨማሪ ዕሴት ታክስ አዋጅ ከወጣ በኋላ በርካታ ሰዎች ለእስራትና ለስደት ተዳርገዋል፤ አንዳንዶች በጥፋታቸው ሌሎች ደግሞ ከግብር ሰብሳቢው ተቋም አንዳንድ ወስላታ ሰራተኞችና ኃላፊዎች ጋር መሞዳሞድ አቅቷቸው፡፡
የተጨማሪ ዕሴት ታክሱ የመንግሥትን ገቢ ከማሳደግ አንፃር ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አያከራክርም፤ የመንግሥት ገቢ ሲያድግ የሃገሪቱ የመሠረተ ልማት አውታሮች ሊስፋፉ እንደሚችሉም እሙን ነው፡፡ ግን በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ይህ እየሆነ አይመስለኝም፤ የመብራት፣ የስልክ፣ የውሃና የፍትህ አገልግሎት እያደር እየዘቀጠ ነው፡፡ በአንፃሩ ወስላታ ባለሥልጣናትና የቆረጣ ነጋዴዎች ከመንግሥት በላይ እያደጉ መሆናቸውን በራሱ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በኩል እየሰማን ነው፡፡
የስድስት ዓመት የመንግሥት ሥራ አገልግሎት ብቻ ያለው ጐረምሳ፣ የሰላሳ አምስት ሚሊዮን ብር ባለቤት ሲሆን “ያንተ ያለህ! እግዚኦ ሰውረን!” ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊባል እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ይህ’ኮ ማሳያ ነው፤ አንድ የቅርንጫፍ ሠራተኛ ያውም ለከፍተኛ ኃላፊነት ያልበቃ ይህን ያህል ገንዘብ መዝረፍ ከቻለ የእሱ የበላዮችስ? አሁንም ሆድ ይፍጀው ነው፡፡
ሙስና አሁን የተፈጠረ አስደንጋጭ ክስተት ነው ባይባልም የተጨማሪ ዕሴት ታክስ አዋጁ ከወጣ በኋላ  ብዙ አስደንጋጭ ጉዳዮችን እየሰማን ነው። በአራጣ አበዳሪነት ወንጀል ተከሰው፣ ያልተፈቀደ ንግድ በማካሄድ ወንጀል ተፈርዶባቸው፣ ሻይ ሲሸጡ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ደረሰኝ ባለመስጠት ተይዘው … በርካታ ሰዎች ከርቸሌ ወርደዋል፡፡
ሰሞኑን በአንድ የወንጀል ችሎት ያየሁት ተከሳሽ ግን እጅግ አስገርሞኛል፡፡ የሰላሳ ዓመት ጐልማሳ ሲሆን ተወልዶ ያደገው ሽሮሜዳ አካባቢ ነው፡፡ ችሎት የቀረበው በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ መሆኑን ከክስ መዝገቡ ላይ ዳኛው ሲያነቡ ሰምቻለሁ፡፡ ዳኛው የክሱን ዝርዝር ጉዳይ ካነበቡለት በኋላ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ ጠየቁት፡፡ ተከሳሹ ምንም ዓይነት የመደናገጥም ሆነ የፍርሃት ምልክት ሳያሳይ “አዎ ሰርቄያለሁ” አለ፡፡ ለምን እንደሰረቀ ማስረዳት ሲጀምር፣ የዳኛውም ሆነ የችሎት ታዳሚዎች ጆሮ እንደ ቀስት ተቀሰረ
 “ክቡር ፍርድ ቤት! መስረቄ እውነት ነው፤ ግን ግብር ከፋይ ነኝ”
“ምን?” ዳኛው አንገታቸውን ወደ ተከሳሹ አስግገው ጠየቁት፡፡
 “አንድ ኪዮስክ ነበረችኝ፤ ለተወሰነ ጊዜ ደህና እሰራባት ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ከሰርሁና ምንም መላወሻ አጣሁ፡፡ መንግሥት ደሞ ግብር አምጣ ብሎ ያዘኝ። የእናቴን ቤት ከማሸጥባት ብዬ ወደ ስርቆት ገባሁ፤ ግን’ኮ የተከበሩ ዳኛ! ምንም ነገር ብሰርቅ ለመንግሥት መገበሬን አላቋርጥም”
“ከሰረቅኸው ላይ?” ዳኛው ጣልቃ ገብተው ጠየቁት፡፡
“አዎ…! ምንም ነገር ብሰርቅ እገብራለሁ፤ ሌላው ቢቀር ሞባይል ነጥቄ እንኳ ከማገኘው ሽያጭ ላይ ለመንግሥት መገበሬን አላቆምም”
“ለምን?” ዳኛው እንደ ገና ጠየቁት፡፡
“ሥራ ነዋ ክቡር ዳኛ! ደሞም ስሰርቅ የምሸማቀቀውን ያህል፤ ለመንግሥት ግብር ሳስገባ ዕዳዬ ሁሉ የቀለለኝ መስሎ ይሰማኛል”
ብዙዎቻችን ሳቃችንን መቆጣጠር ባለመቻላችን ችሎቱን ትተን ወጣን፡፡ ሆኖም ከሌባው የምንማራቸው ሁለት ነገሮች ያሉ ይመስለኛል። በአንድ በኩል ህግን እየጣሰ፣ በሌላ በኩል ለግብር ያለው ከበሬታና ጥንቃቄ የግለሰቡን ልዩ ባህርይ ያመለክታል፡፡
ግብርን በታማኝነት መክፈልን ከወስላታው ግብር ከፋይ ስንማር፤ ሌብነትን የችግሮች ሁሉ መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ከተጠያቂነት እንደማያድን ደግሞ ከህጉና ከፍርድ መማር ይቻላል። ለማንኛውም ግብር ከፋዩን ወስላታ “ልማታዊው ሌባ” ብዬ አምቼዋለሁ፡፡

Read 4131 times