Saturday, 08 March 2014 12:46

የልማት ከበሮ - የችግር እሮሮ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

በየቦታው የተቆፋፈረው የከተማዋ
መንገድ ትራንስፖርት አሳጥቶ መከራችንን ቢያበላንም “ግድ የለም ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል” ብለን በተስፋ ዘለልነው፡፡ ግን በደህናውም መንገድ ጭምር ታክሲ መጥፋቱን ምን እንበለው? ጉዳዩ መንግሥትን ሊያሳስበው አይገባም? ስንል እንጠይቃለን፡፡

ሀገር ስንል ከተማ ገጠሩን ነውና ያንዱ ጉድለት የሌላውም ጉድለት፣ ያንዱ ሙላት የሌላውም ሙላት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሀገራችን መዲና፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ፣ አልፎም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ለኛ ለነዋሪዎችዋ ግን የመከራና የምሬት ህይወት መግፊያ ከሆነች ውሎ አድሯል፡፡ እንደ አሮጌ ንስር፣ መንቁርዋን ስትሰብር ጥፍሯን ስትነቅል መታደስዋ ነው ብለን በትእግስት ብናያትም፣ ጣጣዋ መብዛቱ ብዙ እያስመረረን ነው፡፡ ይህንን ምሬት መስማት የፈለገ ሰው በቀላሉ ጧት ጧት የታክሲ ወረፋን ቢመለከት ይበቃዋል፡፡
በየቦታው የተቆፋፈረው የከተማዋ መንገድ ትራንስፖርት አሳጥቶ መከራችንን ቢያበላንም “ግድ የለም ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል” ብለን በተስፋ ዘለልነው፡፡ ግን በደህናውም መንገድ ጭምር ታክሲ መጥፋቱን ምን እንበለው? ጉዳዩ መንግሥትን ሊያሳስበው አይገባም? ስንል እንጠይቃለን። ወይስ መንግሥት ህዝቡን የሚፈልገው ግብር እንዲከፍልለት ብቻ ነው? ህግ አክብሮ ግብር የከፈለ ሰው፣ የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶችን ከመንግሥት መጠየቅ አይችልም ወይ?... እንደ ወጉማ ቢሆን መንግሥት የህዝብ ተቆርቋሪ ነኝ ስለሚል፣ የህዝቡ ችግር የራሱ ችግር መሆን ነበረበት፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን እንደዚያ አይመስልም፡፡ የኛ መንግሥት እኮ አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ መሪዎቹ ከላይ እስከታች “ለህዝቡ ኑሮ መሻሻል---” ምናምን ሲሉ እውነት ነው ብለን አፋችንን ከፍተን፣ ጆሮአችንን አቁመን እንሰማቸዋለን፡፡ ግን ህዝብ ማለት እኛ እኮ ነን! ወይስ ሌላ በምናባቸው የፈጠሩት ህዝብ አለ? ከሁሉም የሚገርመኝ አዲስ አበባ እንባዋን በአራት ማዕዘን ስትረጭ መሪዎቿ “ልማት … ልማት” እያሉ ከበሮ መደለቃቸው ነው፡፡ ልማቱ እንደሚሉት ለእኛ ከሆነ ለምንድነው አንዳንዴ እንኳን ቀልባቸውን ሰብስበው ምሬታችንን የማይሰሙን?
 “ኢህአዴግ-መልዐክ ነው!” እያለ ይዘምርልኝ የነበረ ወዳጄ፤ ሰሞኑን እንባ ቀረሽ ምሬቱን በረዥም ስልክ አወጋኝ - ግራ የሚያጋባ ጊዜ ነው እያለ፡፡ በአንድ ክፍለ ከተማ ትላልቅ ስራዎችን ለመስራት አቅዶ ቢነሳም በአግባቡ የሚያስተናግደው እንዳጣ ተማሮ ነገረኝ፡፡ ነገሩ እውነት ይሁን ለመንግሥታችን እራርቶ ባላውቅም “ሁሉም ክፍለ ከተማ ግን እንደዚያ አይደለም” ሲል በጥቅሉ ከመውቀስ ተቆጠበ-ይሄው ወዳጄ፡፡ ይገርማል! ታዲያ ኢህአዴግ ለዚህ አይነቱ የምር ወዳጅ (ዘማሪ) እንኳን ካልሆነ ለማን ይሆናል? አልኩ - በልቤ፡፡
መቼም ኢህአዴግ በሙሉ ሙሰኛ ነው ማለት በጅምላ ማጠቃለል ይሆናል .. ጨዋዎችም እኮ አሉ፡፡ አንዳንዶች እንደ ጅል ቢቆጥሯቸውም ታማኝ ለመሆን የሚሞክሩ፣ አቅማቸው የቻለውን ያህል የሚሰሩ ሞልተዋል፡፡ እስቲ እነዚህንና ሌሎች ሀሳቦችን ጎላ ፈካ አድርጎ ያሳየን ዘንድ በአዲስ አበባና በክልሎች  የታዘብኩ ያስተዋልኳቸውን ላስቃኛችሁ።
ሰሞኑን ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቅ ብዬ ነበር፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ እዚያው ሆስፒታል ገብቼ አልትራሳውንድ ክፍል ስለገጠሙኝ ቅን ነርሶች አድንቄላችሁ ነበር፡፡ ሰሞኑን ስሄድ ግን “ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል” የሚለው ስያሜው ተቀይሮ “ጥቁር አበሳ ሆስፒታል” መባሉን ሰማሁ፡፡ እዚህ ሆስፒታል በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ ሆስፒታሎች የላኳቸው በርካታ ታካሚዎች ይመጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ህክምናዎች እንደሌሉ ታዝቤአለሁ። ለምሳሌ እኔ ራሴ ከሰማኋቸው ውስጥ ሲቲ ስካን (MRI) ፣የደም ምርመራ (HCT) ፣ የእርግዝና ሽንት ምርመራ (HCG) ፣ የማህፀን ምርመራ (HSG)፣ የወንድ ዘር ምርመራ (Seminal analysis) የሉም። አልትራሳውንድ ደግሞ አንዱ ተረኛ አለ ሲል፣ ሌላኛው የለም ይላል፡፡ ለዚህ በቂ መረጃ አለኝ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ህመምተኞችን በወጉ ማስተናገድ መቅረቱንም ታዝቤአለሁ፡፡ ማመናጨቅ እየበዛ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ባለቤቱ በገጠማት የፅንስ ማቋረጥ ደም እየፈሰሳት ብትቸገር፣ እንዲረዱለት ብሎ ወደዚሁ ሆስፒታል ቢያመጣትም ተቀብሎ የሚረዳው ሰው አላገኘም፡፡ ማህፀኗ ውስጥ የቀረ ነገር ካለ እንዲጠረግላት ቢማፀን ማን ይስማው? እናም “ለምን ሆስፒታሉን አትዘጉትም?” እያለ በንዴት በመጮህ ሃኪሞቹን ዘልፏቸው ሄደ፡፡ ምን ያድርግ? ቃለ-አባይ ሆነውበውት እኮ ነው፡፡ ሆኖም እነሱ ግን ነገሬም አላሉት፡፡ “አንዲትም እናት በወሊድ አትሙት” የሚለው መፈክር ነጋ ጠባ ቢያደነቁረንም ሀኪሞቻችን ግን መፈክሩን ለመተግበር ዝግጁ አይመስሉም፡፡ ሀኪሞችን ስል ግን ለወገኖቻቸው እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉና የሚከፍሉ እንዳሉ ዘንግቼው አይደለም፡፡ የይርጋለሙ ሀኪም ዶክተር ይገረሙ የሞተው፣ በማከም ላይ ሳለ በደም በተጋባበት በሽታ ነው፡፡ በቡታጅራ ሆስፒታል “የእናቶች እናት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ዶክተር ጌትነት፣ ለህመምተኞች ሲል በህክምና ሥራ  ላይ ሳለ እስከ መውደቅ የደረሰ ባለሙያ ነው፡፡ ሌሎችም ወገናቸውን ለመርዳት በየገጠሩ እስከህይወት መስዋዕትነት ድረስ የሚከፍሉ ሀኪሞች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ለነርሱ ያለኝ ክብርም ታላቅ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ህሊናቸው የሚሰጣቸው ክብርም የላቀ ነው፡፡ ጥቁር አንበሳ ግን “ጥቁር አበሳ” ሲሆን ለህዝብ ቆሜያለሁ የሚለው መንግሥት ምን እየሰራ ይሆን? ካድሬዎቹስ የማንን ጎፈሬ ያበጥራሉ?
እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ታካሚዎችን በፍቅርና በርህራሄ የሚያገለግሉ ባለሙያዎች በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ አይቻለሁ፡፡ ያውም የአእምሮ ህመምተኞችን! መንግሥታችን ክፉ አመሉ ሲሞገስና ሲደነቅ እንጂ ጉድለቱን ሲያሳዩት አለመውደዱ ነው፡፡ ለርሱ ወዳጆቹ ሀገር ሲቃጠል “ሰላም ነው!” የሚሉት አስመሳዮች ናቸው፡፡ በ1997 ምርጫ የዚህ ዓይነቶቹ ሀሰተኛ ካድሬዎች ገደል የከተቱት ኢህአዴግ ፤ዛሬም ከጭብጨባ ሌላ አታሰሙኝ እንዳለ ነው፡፡ ግን ሰምቶ ከስህተቱ ቢታረምና ቢቃና ለእኛም ሆነ ለራሱ ምንኛ ጥሩ ነበር! በተለይ ከልባቸው የሚሰሩ ሰዎች ተገቢውን ቦታ ቢያገኙ አገር እንደምትቀና ቢገነዘብ እንዴት ሸገና ነበር?
ወደ ክልል ወጥቼ ያየኋቸውን ጥቂት በጎ ነገሮች ደግሞ ልመስክር፡፡ ባለፈው ሳምንት ጉራጌ ዞን ምስቃን ወረዳ ገጠሩን ሳይቀር ለስራ ጉዳይ ዘልቄበት ነበር፡፡ ማረቆ ወረዳንም በከፊል አይቻለሁ፡፡ ታዲያ ደስ ያሉኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ አንዱ ቀበሌ (ኩም ቀርጠፋ እሚባል ቦታ) ሳለሁ፤ ኩላሊቴን እንዳያመኝ በሚል መፀዳጃ ቤት አስፈልጎኝ አንዱን ስጠይቀው፤ አጥር ስር መሽናት እንደሚቻል ነገረኝ። አልተመቸኝም፡፡ እና ድንገት አይኔን ወደ አንድ አቅጣጫ ስሰድ በአራት ማዕዘን የተሰራች ጎጆ ቢጤ አየሁና ልጁን ጠየቅሁት፤ ለካስ መፀዳጃ ቤት ተቆፍሯል፡፡ ራሴ መጠቀሜ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ለዚያ አይነት አመለካከት መብቃቱ አስደሰተኝ፡፡ ውዬ ሳድር መስቃን ወረዳም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ አየሁ፡፡ እንደዚሁ ሶዶ ወረዳ ገጠር ውስጥ ወጣቶች ተደራጅተው የሰሩትን መዝናኛ፣ ሻወር ቤት ወዘተ ስመለከት ተደመምኩ፡፡ የቡታጅራ ከተማ የመንገድና የቱቦዎች ፅዳትም እንደዚሁ የሚመሰገን ነው። የህክምና ተቋማት ባለሙያዎችም ህዝቡን እንደማያጉላሉ ታዝቤአለሁ። ቢያጉላሉትም አሰራሩ ተጠያቂነት ስላለው የተሻለ አገልግሎት ይሰጣልና ሹመኞች ወደ ኋላ እንዳይመለሱ እመኛለሁ፡፡ ወገንን በቅንነት ለማገልገል መብቃት ህሊና ላለው ሁሉ ትልቅ እድልና ክብር ነው፡፡
ሌላው ለአዲስ አበባ መኪና አሽከርካሪዎች ትምህርት የሚሆነው የሻሸመኔ ከተማ አሽከርካሪዎች ስርአትና ዲሲፕሊን ነው፡፡ በሻሸመኔ ከተማ ዜብራ ባለበት መንገድ ላይ የሚያቋርጡ ከሆኑ፣ የትኛውም ተሽከርካሪ ይቆምልዎታል፡፡ እዚያው ከተማ ሁለተኛውና የባሌ ጎባ መስመር ላይ ያለውን መናኸሪያ ስርአትም ተደንቄበታለሁ። ስነ-ስርአት አስከባሪዎች አይሳደቡም አያመናጭቁም፣ ይልቁኑ በአክብሮት ያስተናግዳሉ፡፡ ምናልባት ከቡታጅራ ከተማ፣ ሆሳዕና ወላይታ በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ መስተካከል ያለበት የመስተንግዶ ችግር አይቻለሁ።  ስለዚህ እባክህ መንግሥት ሆይ፤ ካድሬና ሰልፍ ከማብዛት ህዝብን በአግባቡ ማገልገልና ማክበር ይሻላል  እላለሁ፡፡ ካድሬዎች የሚደልቁትን ከበሮ ተወውና በዙሪያህ ያሉ እውነቶችን ለማየት ዓይንህን ግለጥ፡፡


Read 3512 times