Saturday, 26 April 2014 12:10

ፊሊንትስቶን ኢንጂነሪንግ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

     ፊሊንትስቶን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ፤ በአንድ ህንፃ ላይ ለበርካታ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አገልግሎት መስጠት ያስችላል ያለውን አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ያደረገ ሲሆን የመጀመሪያው ባለ 8 ፎቅ ህንፃ በቅርቡ ጎተራ ማሳለጫ አካባቢ ግንባታው ይጀመራል፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ በፈጀ ጥናት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ችግርና የእድገት ማነቆዎች መገንዘብ ችለናል ያሉት የኩባንያው ምክትል ኃላፊ አቶ ብሩክ ሽመልስ፤ የኢንተርፕራይዞቹ ዋነኛ ችግሮች በተመጣጣኝ ዋጋ የማምረቻ ቦታ ባለቤት ለመሆን አለመቻልና የገንዘብ እጥረት መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል ብለዋል፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ የማምረቻ ቦታዎችን የግል አድርጎ ለመጠቀም  ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ በኮልፌ፣ መርካቶ እና አውቶብስ ተራ አካባቢ በሚገኙት አምራቾች ላይ በተደረገው ጥናት መረጋገጡንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በአንድ ህንፃ ላይ በርካታ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻ እና የመሸጫ ቦታዎች ባለቤት ማድረግ ያስችላል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፤ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም ጎተራ ማሳለጫ አካባቢ ለሚገነባው ባለ 8 ፎቅ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ በመጣል የሚጀመር ሲሆን በቀጣይም በሌሎች የተጠኑ የከተማዋ አካባቢዎች ተመሳሳይ ህንፃዎች ይገነባሉ ተብሏል፡፡
ጎተራ ማሳለጫ አካባቢ የሚገነባው የመጀመሪያው ህንፃ፤ 134 ለሚሆኑ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የጫማ፣ የጨርቃጨርቅ ስፌት እና የማተሚያ ቤት ኢንተርፕራይዞች የሚውል ሲሆን የማሽነሪና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ ወደ 98 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ተይዞለታል፡፡ ህንፃው ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋል ብለዋል ኃላፊው፡፡
ለህንፃው ከተያዘው አጠቃላይ በጀት 10 በመቶ የሚሆነው ለማሽነሪዎች ግዢ የሚውል ሲሆን ደንበኞች የማምረቻ ክፍሎቹን ከተረከቡ በኋላ በኩባንያው የተተከሉን ማሽነሪዎች የማይፈልጓቸው ከሆነ የራሳቸውን ማሽን ማስተከል ይችላሉ ተብሏል፡
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም ያገናዘበ ነው የተባለው ይህ ፕሮጀክት ከ12 እስከ 40 ካሬ ሜትር የሚደርስ ስፋት ያላቸው ክፍሎች ሲኖሩት እንደየ ኢንዱስትሪዎቹ የሰው ፍላጎት ከ4 እስከ 12 ሰራተኞችን ማካተት ይችላሉ፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡትም በአማካይ ከግማሽ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርስ መነሻ ካፒታል ያላቸው ሲሆኑ ክፍሎቹም ከ650 ሺህ ብር ጀምሮ በተቆጠረ ዋጋ ለሽያጭ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ከ23 ዓመት በፊት የተቋቋመው ፊሊንትስቶን ኢንጅነሪንግ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የመኖሪያ ቤቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ገንብቶ በመሸጥ ይታወቃል፡፡   

Read 2401 times