Saturday, 10 May 2014 12:09

አሁን በወጣትነት እድሜ ላይ የደረሱ ከእናት ወደ ልጅ ኤች.አይ. ቪ የተላለፈባቸው ልጆች /ክፍል 2/

Written by  አበበ ተሻገር abepsy@yahoo.com
Rate this item
(0 votes)

እድሜህ ስንት ነው?
“አስራ አራት”
ስምንተኛ ክፍል ነህ?
“ስድስት”
ዘግይተህ ነው ትምህርት የጀመርከው?
“አሁን ስምንት ነበር የምሆነው ሁለቴ ወድቄአለሁ”
ቫይረሱ እንዳለብህ መቼ ተነገረህ?
“ባለፈው አመት መሰለኝ እድሜዬ 13 እያለ”
እንዴት ተነገረህ ማን ነገረህ?
“እናቴ ነች ኤች. አይ. ቪ/ኤድስ’ኮ አለብህ አለችኝ “እንዴት አልኳት” እና ይህ የምትወስደው መድሃኒት ምንድን ነው?

ከፈለክ ሂድና ሃኪም ጠይቅ አለችኝ እኔ ግን አላመንኩም ነበር”
ለምን?
“ት/ቤት የተማርነው……….”(በዝምታ ተዋጠ)  
ት ጨ ነ ቃ ለ ህ?
“አዎ”
ምንድነው የሚያስጨንቅህ?
“ትምህርት አይገባኝም ሁለቴ ወድቄአለሁ……”
ከ20 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፤ ኤች. አይ. ቪ ወደ ሃገራች ገባ ከተባለና የመጀመሪያው ክስተት (case) ከታዬ፡፡

የቫይረሱ ተፈጥሮ፣ የመተላለፊያ መንገዶቹ፣ የሚያስከትለው የጤና፣ የስነ ልቦናና የማህበራዊ ችግሮቹ ከአመት አመት

እየተባባሰ ብዙዎች ከጎናችን እየተነጠቁ፣ ተፈራርተን፣ ተደባብቀን፣ ችግሩን እሳትና ጭራቅ ነው ብለን ፈርጀን ፣

ወገኖቻችንን አግልለን፣ በግልፅ እንዳናወራ ተገደድን፡፡ በወቅቱ የሳይንስ ተስፋ የመነመነ ይመስል ነበር፡፡ ያም ሆኖ

ምርምርና ጥናቱ መቀጠሉ አልቀረም - ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ሊፈውስ የሚችል ባይሆንም ፀረ ኤች. አይ. ቪ

መድሃኒት ደረሰ፡፡ ምንም እንኳን መድሃኒቱ ወደ ሃገራችን በተፈለገው መጠንና ጊዜ ባይደርስም እስከደረሰበት ጊዜ የቆዩ

ወገኖች እንደገና ነፍስም ተስፋም ዘሩ፡፡ እነሱ ብቻም ሳይሆኑ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ ዘመድ አዝማድ ሀገር በሞላ ተነፈሰ፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ ታዲያ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ ወገኖች የሚወለዱ (በወራት ግፋ ቢል እስከ አምስት አመት ሳይደርሱ

ያልፉ የነበሩት) ልጆች ፀረ ኤች. አይ. ቪ መድሃኒቱን በማግኘታቸው እንደማናቸውም ልጆች የአይን ተስፋ ሆኑ፡፡

ለወላጅም “ራሱን በራሱ የማየት፣ ራስን የመተካት” ምኞት እውን ሆነ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የኤች. አይ. ቪ ቫይረስ

ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ፀረ ኤች. አይ. ቪ መድሃኒቱ አገዘ፡፡ ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ ልጆች መወለድ ቀጠሉ፡፡

ይኸኛው ደግሞ ለወላጆች ትልቅ ብርታት፣ ትልቅ ተስፋ፣ ህይወትም ሆነ፡፡
የእኔ ወግ መነሻ ግን ፀረ ኤች. አይ. ቪ መድሃኒት ሳይደርስ የተወለዱና በህይወት መድሃኒቱ የደረሰላቸውና

መድሃኒታቸውን በአግባብ እየተከታተሉ ዛሬ በአፍላ ወጣትነት እድሜ ላይ የደረሱ ልጆች ናቸው፡፡ ሰፊ ቆይታ

ያደረኩትም ከእነዚህ ታዳጊዎች ጋር ነው፡፡ ከመሃከላቸው ግራ በመጋባት ስሜት ውስጥ ያሉም ጥቂት አይደሉም፡፡

በልጅነት ፊታቸው ላይ ሳቅ፣ ተስፋ፣ ደስታ…..መታየት ሲገባው የእንባ ዘለላዎችን የሚያወርዱ ልጆችን አይቻለሁ
ለምን ታለቅሻለሽ?
“እናቴ ለምን ከቫይረሱ ጋር እንደምኖር ቀድማ እንዳልነገረችኝ አላቅም….... ስለደበቀችኝ…… መሰለኝ”
መቼ ነው የተነገረሽ?
“ባፈው አመት በ2005 ነው”
እድሜሽ አሁን ስንት ነው?
“17….እኔ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የደረሰብኝ ተፅእኖም የለም ጤነኛ ነኝ ግን (እንባዋ ይቀጥላል)”
እናትሽ ለምን የደበቁሽ ይመስልሻል?
“አላቅም ….የራሷ ምክንያት ይኖራታል…አላቅም”
ፈርተው ይሆን?
“ሊሆን ይችላል”
ቀድመው ቢነግሩሽ ምን ታደርጊ ነበር?
“መድሃኒቴን በአግባብ መውሰድ እችላለሁ…ራሴ መምጣትና ክትትሉን ማድረግ እችል ነበር….ግን የእናቴ ድብቅነት ነው

የሚያስለቅሰኝ….ብዙ ነገር እንደምትደብቀኝ ተሰማኝ”
ህፃናቶች በአንድ በኩል መድሃኒት እዲወስዱ በሌላ በኩል ለምን እንደሚወስዱ አለማወቃቸው በውስጣቸው የሚፈጥረው

ጥያቄ ብዙ ነው፡፡ የሚወስዱት መድሃኒት ደግሞ ለሁለት ሳምንት የሚሰጥ ወይም ለስላሳ ቀናት የተመደበ መጠን (ዶዝ)

አይደለም፡፡ ለአንድ አመት ወይም ለአስር አመታት ብቻም አይደለም፤ በየቀኑ ለእድሜ ልክ የሚሰጥና የሚወሰድ ነው

(የሳይንስ እድገት ነገ የተለየ መፍትሄ ካላመጣ በስተቀር)፡፡
ህፃናት እድሜአቸው ነውና ይጠይቃሉ፣ ማወቅ ይፈልጋሉ፣ ለማወቅ ይጓጓሉ፡፡ በተለይ እስከ 14 ዓመት ባለው ጊዜ ልጆች

የማወቅ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ የመሞከር ስሜት ይቀጥላል፡፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ህፃናትን ደግሞ

መድሃኒት ለማስጀመር ያለው ፈተና እንዳለ ሆኖ፣ ሌሎች ልጆች አለመውሰዳቸው፣ የሚስዱበት ሰዓት ቁጥጥር መደረግ፣

በየጊዜው ወደ ሃኪም መቅረብ ወዘተ በውስጣቸው ጥያቄዎች እንዲበዙ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ወላጆች

የሚጋፈጡት ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ እንዴት እንደሚነግሯቸው ይጨነቃሉ፣ መቼ መናገር እንደሚያስፈልግ ግራ

ያጋባሉ፣ ከነገሯቸው በኋላ ስለሚፈጥረው ያስባሉ፡፡ ሆኖም መንገር ግዴታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ታዳጊ ወጣቶች ሲያወጉኝ

ጉዳዩን ራሳቸው በመጠርጠር፣ በማንበብ፣ ከሌሎች ሰዎች መረጃ በመውሰድና ከራሳቸው ሁኔታ ጋር በማገናዘብ

ይደርሱበታል፡፡ እንዲህ ባለ አጋጣሚ ደግሞ ጉዳዩን ከደበቋቸው ወላጆችና አሳዳጊዎች ጋር ቅራኔና ጥላቻ ይፈጥራል፡፡
ሌላው እውቀት፣ የስነ ልቦና ብርታት፣ ጓደኞች፣ መዋያና መዝናኛ ቦታ የሚያገኙባቸው ሁኔታዎች አሁን መቋረጡ  

ለታዳጊ ወጣቶቹ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአንድ በጎ አድራጊ ድርጅት አማካኝነት ታዳጊዎቹ በዘውዲቱ

ሆስፒታል በሚገኘው የፈቃደኝነት ምርመራና ምክር አገልግሎት መስጫ በሳምንትና ሁለት ሳምንት ጊዜ ይገናኛሉ፡፡

በስነ-ልቦና አማካሪዎች እየታገዙ ይወያያሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፣ አንዱ ከሌላው የኑሮ ዘዬ ይወርሳል፣ ጓደኝነትም

ይፈጠራል፣ ብቸኛ እንዳልሆኑ ይረዳሉ፣ ወዘተ፡፡ በዚህ መንገድ አንዱ ሌላውን (ቤቱ የተዘጋበትን ልጅ) ይጋብዛል፣

ለህክምናና ክትትል ልጆቻቸውን ይዘው የሚዘልቁ ወላጆችም የዚህን ልምድ ሁኔታ ይረዳሉ፡፡ ልጆቻቸውንም በቀጣይ

ይልካሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለወላጆችም ከእናት ወደ ልጅ ቫይረሱ ለተላለፈባቸው ልጆችም ትርጉም ያለው ስራ ነው፡፡ ሆኖም

እገዛውን ያደርግ የነበረው ድርጅት ፕሮጀክቶቹን ሲዘጋ ይህም ስራ ተቋርጧል፡፡ አሁን አይገናኙም፡፡
ወጣትነት ብዙ የሚሞክርበት እድሜ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ እነዚህ ታዳጊ ወጣቶችም ይማራሉ፣ ማህበራዊ ተራክቦ

አላቸው፣ ጤናማ ናቸው፣ ተስፋ አላቸው፣ ህልም አላቸው፣ ነገ በእግር የሚተኩ መሪዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እንዴት

ከቫይረሱ ጋር መኖር እንዳለባቸው፣ ከፆታዊ ግንኙነት በፊት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ሌላው ማህበረሰብ እንሱን

እንዴት መቀበል እንዳለበት፣ በመሳሰሉት ላይ ስራ መስራት ካልተቻለ ለልጆቹም ለወላጆቻቸውም እንዲሁም በአጠቃላይ

ለማህበረሰቡም ራሱን የቻለ ችግር ይሆናል፡፡ እኛ ችግሩን ችላ ብንለውም ችግሩ ግን እኛን ችላ ላይለን ይችላል፡፡

በምንም መነሻ እንዚህ ልጆች ጥፋተኞች ናቸው ብለን ልንፈርጃቸው አንችልም (አጠፋ የምንለው ማንኛውም ሰውም

ቢሆን ከጥፋቱ ሊመለስ የሚችለው በማስተማር ነው) አሁንም ያለ እውቀትና ግንዛቤ ከአፍላ እድሜ ጋር በተያያዘ

በሚዝናኑበት ጊዜ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ካልተገነዘቡ ለጥፋቱ ተጠያቂው አካባቢያቸው ይመስለኛል፡፡ በአፍላ እድሜ

ላይ መዝናናት የአብዛኞች ወጣቶች ፍላጎት ነው። እድሜው ለሚጠይቀው ጥያቄ ደግሞ መልስ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ሊጠጡ፣

ሊያጨሱ፣ ልቅ የሆነ ወሲባዊ ተራክቦ ሊፈፅሙ፣ ወደ አደገኛ ሱሶች ሊገቡ ወዘተ ይችላሉ፡፡ ለምን ይህን ይፈፅማሉ ብለን

ከጠየቅን ሊመጣ የሚችለውን ችግር በውል ስላልተረዱና ኃላፊነቱ ያለበት አካል ቤተሰብ፣ ት/ቤት፣ በተለይ በኤች.

አይ.ቪ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች፣ መንግስት ….. ኃላፊነታቸውን ስላልተወጡ የሚል መደምደሚያ ነው መውሰድ

የሚቻለው፡፡
በአጠቃላይ እኔ ፊት ለፊት አግኝቼ ያወጋኋቸው ታዳጊ ወጣቶችና ሌሎችም ምናልባት መድሃኒቱን እየወሰዱ ግን ለምን

እንደሚወስዱ የማያውቁ፣ አውቀውም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ የተጋቡ፣ ከግንዛቤ ጉድለት መድሃኒት መውሰድ

የማይፈልጉ (መውሰድ እያለባቸው)፣ ከቤተሰብ ከአካባቢና ከት/ቤት መገለል የደረሰባቸው (ይህን ያልኩበት ምክንያት

ካናገርኳቸው ውስጥ አንዷ ታዳጊ ከአካባቢዋ ጎረቤቶች ውስጥ አንዳንዶቹ አብሮ ለመብላት እንኳን ፈርተው እዳገለሏት

ስለገለፀችልኝ ነው) ሁሉም በተለይ የጤና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ሁሉ በስነ ልቦናም ብርቱ መንፈስ

እንዲኖራቸው ሊሰባሰቡና እርስ በእርሳቸው እንዲወያዩ የሚያስችል ሁኔታ ቢፈጠርላቸው ብሩህ ነገር ሊመለከቱ

ይችላሉ፡፡ ህልማቸውንም እውን ለማድረግ ያግዛቸዋል፡፡ አስተያየታችሁን ለሰጣችሁኝ ከጣሊያን  ሳሙኤል ተስፋዬ

ከአዲስ አበባ ፀጋዬ ያቆብ ሃሳባችሁን በከፊል እንዳካተትኩ ተስፋ አደርጋለሁ አመሰግናችኋለሁ። ለምትደውሉልን

ስልካችን 0115 159126 ወይም 0115506068/69  

Read 4098 times