Saturday, 17 May 2014 15:27

“በጐ አድራጐት” ሕንፃ እንዳይፈርስ ከቅርስ ጥበቃ ድጋፍ አገኘ

Written by  ናፎቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

          የዛሬ 78 ዓመት እንደተገነባ የሚነገርለት ኢትዮጵያ ሆቴል ጐን የሚገኘው “በጐ አድራጐት” ህንፃ እንዳይፈርስ፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ድጋፍ እንዳገኘ ተገለፀ፡፡ ኢትዮጵያ ሆቴል ለግል ባለሀብት መሸጡን ተከትሎ ባለሃብቱ ሊገነቡት ላሰቡት ባለ 63 ፎቅ ሆቴል ቦታው ለማስፋፊያነት በማስፈለጉ ህንፃው ሊፈርስ እንደነበር የ“ሺ ሰለሞን ሃይሉ ሱፐር ማርኬት” ባለቤት አቶ ሞገስ ሀይሉ ተናግረዋል፡፡ “ህንፃው በ1929 ዓ.ም ከመገንባቱም ባሻገር አሰራሩና ውበቱ ዘመናዊነትን የተላበሰ በመሆኑ በቅርስነት ሊመዘገብ ይገባል” ያሉት አቶ ሞገስ፤ ይህንኑ ጉዳይ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና “በጐ አድራጐት” ሕንፃ እንዳይፈርስ ከቅርስ ጥበቃ ድጋፍ አገኘ ለሚመለከታቸው አካላት በማመልከት በህንፃው ላይ የሚሰሩ ነጋዴዎች ከአመት በላይ መድከማቸውን ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩን ግምት ውስጥ ያስገባው የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም፣ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህንፃውን ጉዳይ እንዲያጣራ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ባለስልጣኑም ከተለያዩ ክፍሎች ባለሙያዎችን በማውጣጣት ወደ ስፍራው ልኮ የተለያዩ መረጃዎችን መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የ አዲስ አ በባ ባ ህልና ቱ ሪዝም ቢ ሮ እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው በአዲስ አበባ የቋሚ ቅርሶች ጥናት፤ 236 የሚሆኑ በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች እና ህንፃዎች ዝርዝር ውስጥ የበጐ አድራጐት ህንፃ በቅርስነት ተመዝግቦ አለመገኘቱን ባለሙያዎቹ እንደገለፁ አቶ ሞገስ ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ወቅታዊ መረጃን ለማጠናቀር ከባለስልጣኑ የተውጣጡት ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት፤

ህንፃው በ1929 ዓ.ም ከተገነቡ ጥቂትና ዘመናዊ ህንፃዎች መካከል አንዱ በመሆኑና የተሰራበት የህንፃ ጥበብ ማራኪና የወቅቱን የስነ - ህንፃ ጥበብ አመላካች ከሆኑ ታሪካዊ ህንፃዎች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ምንም እንኳን ህንፃው በቅርስነት ያልተመዘገበ ቢሆንም በከተማው ከሚከናወነው ልማት ጋር በተጣጣመ አግባብ የህንፃውን ታሪካዊ ፋይዳ ያገናዘበ ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚደግፍ መሆኑን በፃፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ በህንፃው ላይ ሺ ሰለሞን ሃይሉ ሱፐር ማርኬትን ጨምሮ የጉዞ ወኪሎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች እና የመጽሐፍት መደብርን የያዘ እንደሆነ የተናገሩት የህንፃው ነጋዴዎች፤ በጐ አድራጐት ህንፃ፣ ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከብሔራዊ ቴአትር ህንፃ ጋር የተሰራ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

በህንፃው ላይ የሚገኙ ነጋዴዎች ተወካይ፣ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ኢንቬንተሪ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ባለስልጣን የሰጠው ድጋፍ ተፈፃሚ እንዲሆን የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጠው እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡ አብዛኞቹ ነጋዴዎች ከ35-40 ዓመት በህንፃው ላይ በንግድ ስራ መቆየታቸውን የገለፁ ሲሆን በአካባቢው ከሚገኙ ሆቴሎች እና ካፌዎች ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ አገልግሎት እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ “ከሁሉም በላይ ህንፃው በቅርስነት እንዲቆይ እንፈልጋለን፤ ለዚህም ነው ከአንድ አመት በላይ እንዳይፈርስ ተከራክረን ከቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ድጋፍ የተገኘው” ብለዋል - ነጋዴዎቹ፡፡

Read 1707 times