Saturday, 17 May 2014 15:33

የግንቦት 20 ፍሬዎች ይመለሱልን!

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(6 votes)

                     በመቀሌና በባህርዳር ከተሞች ውስጥ ለሰማዕታት መታሰቢያ ተብለው ከቆሙት ሀውልቶች ስር ያሉትን ሙዚየሞች መጐብኘት የቻለ ሰው፣ የህወሓትም ሆነ የብአዴን (ኢህዴን) ታጋዮች፣ ገና በለጋ የወጣትነት እድሜያቸው ነፍጥ አንስተው፣ ፋኖ ተሰማራን እየዘመሩ፣ ለትጥቅ ትግል በረሀ እንዲወርዱ የተገደዱት፣ በወቅቱ በሀገሪቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ በነበረው የዜጐች ነፃነትና እኩልነት መጓደል፣ በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መረገጥና በህግ የበላይነት አለመከበር የተነሳ እንደሆነ ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ለዜጐች እኩልነትና ነፃነት መረጋገጥ፣ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅና ለህግ የበላይነት መስፈን በተደረገው የ17 አመታት እጅግ መራራና ፈታኝ የትጥቅ ትግል፣በሺዎች የሚቆጠሩ የህወሓትና የብአዴን (ኢህዴን) ታጋዮች በፍፁም ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነት የህይወት መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ነፃነትና እኩልነት፣ የዜጐችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥበቃ እንዲሁም ለህግ የበላይነት ልዕልና፣ህገመንግስታዊ ዋስትና የሰጠው አዲሱ የሀገሪቱ ህገመንግስት ሲፀድቅ እጅግ አያሌ ዜጐች በደስታ ተሞልተው፣ በአደባባይ አስዬ ቤለማ የጨፈሩት፣ የእነ አሞራውና እሱን መሰል ልበ ቅን ታጋዮች የከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት መናውን አ ልቀረም በ ሚልም ጭ ምር እ ንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች በከፈሉት ከባድ የህይወት መስዋዕትነት የተነሳ፣ ኢህአዴግ ለ17 አመታት የዘለቀውን ወታደራዊ የደርግ መንግስት ማሸ(ቸ)ነፍ በመቻሉ፤ ከዛሬ 23 አመት በፊት የመንግስት ስልጣን ሲቆጣጠርም፣ በእውነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች፣ በሀገራቸው በኢትዮጵያ አዲስ የነፃነትና የዲሞክራሲ ዘመን ባተ ብለው፣ በልባቸውና በመንፈሳቸው ሃሴት አድርገዋል።

የዚህ ከፍተኛ ህዝባዊ ስሜት መሠረታዊ ምንጩ ደግሞ ሌላ ሳይሆን በወቅቱ የነበረን ሁለት አይነት ቅን ግምትና እምነት ነበር፡፡ አንደኛው እጅግ አያሌ የህዝብ ልጆች መቸም ቢሆን ተመልሶ የማይመጣውን የአፍላ ወጣትነት ዘመናቸውን ብቻ ሳይሆን ውድ ህይወታቸውንና አካላቸውን በፍፁም ፈቃደኝነትና ጽናት የሰዉለት የዜጐች የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥበቃ፣ የነፃነት የእኩልነትና ፍትህ መረጋገጥ ትግል ከእንግዲህ ፍሬ ያፈራል የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዜጐች ነፃነታቸውና እኩልነታቸው ሳይከበር ሲቀር፤ የሰብአዊና የግንቦት 20 ፍሬዎች ይመለሱልን! አልአዛር ኬ. ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሲረገጡና ሲጣሉባቸው እንዲሁም ፍትህ ሲጓደልባቸው፣ ምን አይነት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ከኢህአዴግ የበለጠ የሚያውቅ ስለሌለ፣እነዚህን መሠረታዊ መብቶች ከማስከበር ቸል አይልም የሚል ነው።

እነዚህ ነበሩ ያኔ አብዛኞቻችን ዘንድ የነበሩት ሁለት ቅን ግምትና እምነቶች፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን ብሔራዊ ስልጣንን ከተቆጣጠረ በኋላ “ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና እኩልነት ለዚች ሀገር የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” በሚለው ምህላው፣ አፉን ከፈታ በኋላ እነዚህን ሁለት እምነቶቻችንን በሚገባ እንደተረዳልንና የራሱም እምነቶች እንደሆኑ በተደጋጋሚ አስረድቶናል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የዜጐች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ነፃነታቸውና እኩልነታቸውም እንዲረጋገጥ ህጋዊ ዋስትና የሰጠው አዲሱ ህገመንግስት እንደፀደቀ፣ኢህአዴግ እውነትም በህዝቦች መብት፣ ነፃነትና እኩልነት መረጋገጥ ጉዳይ ላይ ዋዛ ፈዛዛ እንደማያውቅ፣ አብዛኞቻችን ከልባችን አምነን ተቀብለን ነበር፡፡

ጉድና ጅራት ግን ሁሌም ቢሆን በስተኋላ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በልባቸው ያመኑት፤ የተቀረነው እኛም ማተቡን ይዘን አስምለን አደራችንን አብዝተን የሰጠነው ኢህአዴግ፣ ያረጋግጥልናል ያልነውን ነፃነትና እኩልነታችንን ተጋፍቶ፣ ጠብቆ ያስጠብቅልናል ያልነውን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ጥሶና አክብሮ ያስከብርልናል ያልነውን የህግ የበላይነትን ረግጦ መገኘቱ፣ ለእኛ ክፉ እጣ ሲሆን፤ ለኢህአዴግ ደግሞ የእነ አሞራውና መሰሎቹን እልፍ ታጋዮች ክቡር የህይወት መስዋዕትነት ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡ ኢህአዴግን ለመሰለ ለህዝቦች ነፃነትና እኩልነት እንዲሁም ለዜጐች ሁለንተናዊ መብት መከበር በተካሄደው ትግል፣ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ መዝገብ ውስጥ ጉልህ ቦታ ላለው ድርጅት፣ይህ በእርግጥም የሞት ሞት ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ አግባብ ለሚተዳደሩ መንግስታት፣ የሉአላዊ የስልጣን ምንጭ ህዝቡና ህዝቡ ብቻ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከኢህአዴግና ኢህአዴግ ከሚመራው መንግስት በስተቀር ለአብዛኞቻችን የዚህ ገዢና መሪ አስተሳሰብ ትርጉም አጭር፣ ቀላልና፣ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ያልኩት ባጭሩ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት፣ በህገመንግሥቱ ከተቀመጡት ድንጋጌዎችና ከዲሞክራሲያዊ የአሰራር መርሆዎች ውጪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ትንፋሽ በማሳጣትና የመቆሚያ ቦታ በመንሳት፣ የሀገሪቱ “አውራ ፓርቲ” መሆን መቻሉን እንደ ህጋዊ ስልጣን የመቆጣጠሪያ አሰራር አድርጐ መቁጠሩ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ህዝቦች በነፃነትና በገዛ ፈቃዳቸው ብቻ ይሁንታቸውን እንዲሰጡት በማድረግ ሳይሆን የመንግስትነት ስልጣን መቆጣጠሩ በእጁ ስር የጣለለትን የመንግስት አስገዳጅ ሀይሎች (Coercive forces) እና የመንግስትን የቢሮክራሲ ማሽን በመጠቀም፣ ህዝቦች ያልሰጡትንም ይሁንታ መውሰድ መቻሉ ነው፡፡

“አስተዋይ መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። የብልህ ሰውም ጥበብ መንገዱን ያስተውል ዘንድ ነው” ተብሎ በቅዱስ ቶራህ ከተፃፈው በተቃራኒው፣ እንደ ሰነፍ ልጅ ራሱን ታምኖ እንዲኮራና በየጊዜው የተለያዩ አፋኝና ከልካይ ህጐችን በማውጣት፣ በህገመንግስቱ የተጠበቁልንን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ለመቀማት፣ በሀይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥ እጁን እያስረዘመ ጣልቃ እንዲገባብን፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄዎችን መልሻለሁ እያለ በተግባር ግን ለመጭው ትውልድ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ፣ የቂምና የበቀል ቅርስ እንዲያወርስ ድፍረት የሰጠውም ይሄው ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ባለፉት በርካታ አመታት ዲሞክራሲን በተመለከተ ራሳቸውን የጠመዱት በህገመንግስቱ አማካኝነት ህጋዊ ዋስትናና ከለላ የተሰጣቸውን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ማስፋትና መጠበቅ ሳይሆን በሰበብ አስባብ መንጠቅና መርገጥ ነው፡፡ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ላለፉት በርካታ አመታት እጅግ በሚያስነውር ሁኔታ ራሳቸውን ከጊዜአዊ አምባገነን አገዛዝ ጋር በማወዳደር የግለሰብም ሆነ የቡድን የህዝቦች መብት እንዲጠበቅ፣ የሃይማኖትም ሆነ ሌላ እኩልነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ችያለሁ እያለ፣ ነጋ ጠባ ቢወተውተንም እኛ ግን በቡድን ስላልተረጋገጠው እኩልነታችን፣ በግለሰብ ደረጃም ስላልተከበረው የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታችን ዛሬም አቤት ማለታችንን አልተውንም፡፡ እኛ ዛሬም ቢሆን ስለተነፈግነው ስለተዛባብን ፍትህ መጮሀችንን አልተውንም፡፡

ኢህአዴግና መንግስት የፕሬስና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችሁን አስከብሬአለሁ ቢለንም፣ በተግባር እየተፈፀመ ያለው ጉዳይ፣ በአፉ ከተናገረው በእጅጉ የተለየ በመሆኑ የነፃነት ያለህ እያልን መማለዳችንን አልተውንም፡፡ ስለ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ምንም እንኳ ኢህአዴግና መንግስት የተማመኑትን ተማምነው ምናቸውን ውጭ ቢያሳድሩም፣ እኛ ግን የምርጫ ውድድር ሜዳው ለሁላችንም እኩል እንዲሆንልንና በፈቃዳችንና በግልጽ ከሰጠነው ይሁንታ ውጪ ያልሰጠነው ሁሉ በጉልበት እንዳይወሰድብን ዛሬም አበክረን እንጠይቃለን፡፡ ጠቅለል ባለ አገላለጽ፣ እስከዛሬ ድረስ በጉልበት አለአግባብ የተወሰዱብን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን ሁሉ ሳይሸራረፍ እንዲመለሱልን እንጠይቃለን፡፡ የግንቦት 20 ፍሬዎች እንዲመለሱልን አቤት እንላለን!!

Read 3295 times