Saturday, 07 June 2014 14:46

20ኛው ዓለም ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ለምን የምንግዜም ምርጥ ይሆናል?
 የዓለም ዋንጫ ወቅት  ነው፡፡  እያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በመላው ዓለም  ከ350 ሚሊዮን በላይ ስፖርት አፍቃሪዎች ትኩረት ያገኛል፡፡ 20ኛው የዓለም ዋንጫ ሪዮዲጄኔሮ ላይ በታላቁ የማራካኛ ስታድዬም   ብራዚል እና ክሮሽያ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል፡፡ የማራካኛ ስታድዬም 78,838 ተመልካቾችን ያስተናግዳል፡፡  በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛው የስታድዬም ተመልካች የተስተናገደበት  ሆኖ በሪከርድ መዝገብ የሰፈረ ነው፡፡ ብራዚል በ1950 እኤአ ላይ 4ኛውን ዓለም ዋንጫ አዘጋጅታ በኡራጋይ ዋንጫውን ስትነጠቅ ይህ ስታድዬም  199,854 ተመልካች ነበረው፡፡ የመክፈቻ እና የዋንጫ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው ማራካኛ በ500 ሚሊዮን ዶላር መታደሱን ፊፋ ቢገልፅም የብራዚል እግር ኳስ ፌደሬሽን 1.1 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርጊያለሁ ብሏል፡፡
የዓለም ዋንጫው በቡድኖች የተቀራረበ አቋምና በምርጥ ተጨዋቾች ስብስብ የምንግዜም ምርጥ ሊሆን ይችላል፡፡  በታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦች ሪያል ማድሪድ፤ ባርሴሎና፤ ኤሲ ሚላን አና ኢንተርሚላን የተጫወተው እና ብራዚል 5ኛውን የዓለም ዋንጫ እንድታገኝ ከ12 ዓመት በፊት ቁልፉን ሚና የተጫወተው ሮናልዶ   ከወር በፊት የተናገረው ነው፡፡ ከ64 ዓመት በፊት ብራዚል ባስተናገደችው ውድድር ተሳታፊዎች 16  እንደነበር ያስታወሱት የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በበኩላቸው፤ የፈለገ ትችት ቢሰነዘር በ32 ቡድኖች ምርጥ ዓለም ዋንጫ እንመለከታለን ብለዋል፡፡ ካለፉት 19 ዓለም ዋንጫዎች በምንግዜም ምርጥነቱ መላው ዓለም የሚስማማበት በ1986 አኤአ ላይ ሜክሲኮ ያዘጋጀነው ነው፡፡ በዚህ ዓለም ዋንጫ ሜክሲኳን ዌቭ በስታድዬሞች ሲታይ፤ የማራዶና ገድል እና ሌሎች የማይረሱ ታሪኮች በብዛት በመከሰታቸው ነበር፡፡ ውድድሩን ምርጥ ያደረገው በዚያ ዓለም ዋንጫ ማራዶና ብቻ ሳይሆን ዚኮ፤ ፕላቲኒ እና እነ ላውድርፕም ነበሩ፡፡ በእርግጥም የብራዚሉ 20ኛው ዓለም ዋንጫ በክዋክብት ብዛት የሜክሲኮውን ክብር በደንብ ይስተካከላል፡፡ ለዚህም በ16 ቡድኖች ቢያንስ የማንኛውንም ጨዋታ ውጤት የሚቀይር አንድ ምርጥ ተጨዋች መኖሩ ማስረጃ ነው፡፡
ብራዚል ስድስተኛ ዋንጫውን በሜዳዋ ማንሳቷ፤ አውሮፓዊ ቡድን  በደቡብ አሜሪካ የተዘጋጀ ዓለም ዋንጫን ማሸነፉ፤ በታሪክ 9ኛው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አዲስ አገር ማጋጠሙ፤ አፍሪካዊ ቡድን ግማሽ ፍፃሜ መድረሱና ሌሎች አስደናቂ የተጨዋቾች ገድሎች በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ሊፈጠሩ የሚችሉ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው።
የብራዚል ብሄራዊ ክብርና ፈተናው
ውድድሩን በሚያስተናግዱ 12 የብራዚል ከተሞች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከ600 ሺ በላይ ቱሪስቶች ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል እግር ኳስን አንደ ብሄራዊ ክብር የሚቆጥሩ ከ3 ሚሊዮን በላይ ብራዚላውያን በየስታድዬሞቹ በመገኘት ከፍተኛ ድምቀት መፍጠራቸው ተጠብቋል፡፡ 20ኛው የዓለም ዋንጫ በአጠቃላይ ለዝግጅት ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስለፈሰሰበት  በከፍተኛ ወጭው በታሪክ የመጀመርያው ነው፡፡በ2006 እኤአ ላይ ጀርመን በ6 ቢሊዮን ዶላር ፤ በ2002 እኤአ ኮርያ እና ጃፓን በ5 ቢሊዮን ዶላር፤ በ2010 እኤአ ደቡብ አፍሪካ በ4 ቢሊዮን ዶላር ፤በ1998 እኤአ ፈረንሳይ 340 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በ1994 እኤአ አሜሪካ በ30 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ዓለም ዋንጫን አስተናግደዋል፡፡
ከ12 ስታድዬሞች አምስቱ አዲስ በመሰራታቸው ሌሎቹ ከፍተኛ እድሳት አንዳንዶቹ ደግሞ የማሻሻል ስራ ተከናውኖላቸው እስከ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኗል፡፡ እስከ 2.4 ቢሊዮን ዶላር በተለያየ  ከተሞች ያሉ አየር ማረፊያዎች በብቃት ለማዘጋጀት የወጣ ነው የውድድሩን ፀጥታ እና ሰላም ለማስከበር ደግሞ የብራዚል መንግስት በድምሩ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ማድረጉ ይጠቀሳል፡፡ ብራዚል በዚሁ የዓለም ዋንጫ ከመጠቀሟ ይልቅ መጎዳቷ ያመዝናል  ብለው የሚያስቡ ብራዚላዊያን ከአጠቃላይ የአገሪቱ የህዝብ ብዛት 55 በመቶው ናቸው፡፡ ዓለም ዋንጫው ሊጀመር 10 ቀናት ሲቀሩት አስተናጋጇ ብራዚል በአንዳንድ ስታድዬሞቿ የመቀመጫ ወንበሮችን ተክላ አለመጨረሷ አነጋግሯል፡፡ በሌላ በኩል ላለፈው 1 ዓመት የዓለም ዋንጫው መስተንግዶ ለፊፋ ትርፍ ያስገኛል እንጅ ለብራዚል ከኪሳራ በቀር የሚያመጣው ምንም ተዓምር የለም በሚል ብራዚላውያን ሲያደርጉ የነበረው ተቃውሞ  ሰሞኑን በአንዳንድ የአገሪቱ ከተሞች መቆስቆሱ የውድድሩን አጀማመር በስጋት የተሞላ አድርጎታል፡፡
የተቃውሞ ሰልፎቹ በተደጋጋሚ የመደረጋቸው ዋና ምክንያት አገሪቱ በበርካታ ችግሮች በተውተበተበችበት ወቅት በብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጭ ዓለም ዋንጫን ማዘጋጀት አልነበረባትም የሚል ነው፡፡  ብራዚል ዓለም ዋንጫውን በማዘጋጀቷ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ቅር ቢላቸውም መላው ዓለም ግን የእግር ኳስ የትውልድ ምድር በምትባለው ብራዚል የስፖርቱ ዓለም ትልቁ ውድድር መከናወኑን በጉጉት  ሲጠብቀው ቆይቷል፡፡ ዓለም ዋንጫው በብዙ ብራዚላዊያን እንደተሰጋው አክሳሪ አይደለም፡፡  
የዓለም ዋንጫው በሚቀጥሉት አምስት አመታት በብራዚል ኢኮኖሚ እስከ 107 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያንቀሳቅስ የገመቱ የኢኮኖሚስት ጥናቶች በዚህም አገሪቱ እስከ 25 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቷ እንደማይቀር አመልክተዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ500ሺ በላይ ለሚገመቱ ብራዚላውያን አዲስ የስራ እድል እንደሚፈጠርና የቱሪዝም ገቢ እስከ 5.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ጨምረው ይገልፃሉ፡፡ በውድድሩ ሰሞን በተለያዩ የብራዚል ከተሞች  የሚዘዋወሩት ከ600ሺ በላይ የእግር ኳስ ቱሪስቶች ወጭያቸው እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ተተምኗል፡፡ ከዚህ ወጭ የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች ትኩስ ምግቦችና የተለያዩ መጠጦችን የሚያቀርቡ እና ለብራዚል የገቢ ግብር የሚከፍሉ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በተለይ የቢራ እና የትኩስ ምግቦች ገበያ በከፍተኛ ደረጃ ይደራል፡፡  አየር መንገዶች፣ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ከፍተኛ የገቢ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡የ20ኛውን ዓለም ዋንጫ 4 ጨዋታዎች በተለያዩ የብራዚል ከተሞች በመዘዋወር የሚመለከት አንድ የእግር ኳስ ቱሪስት በአማካይ 47.3 ሺ ብር (2488 ዶላር) ያወጣል፡፡  በተለይ ሪዮ ዲጂኔሮ ውዷ የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ከተማ ስትሆን  ለአንድ የእግር ኳስ ቱሪስት የአንድ ቀን አማካይ ውጭ በዚያች ከተማ እስከ 684 ዶላር ነው፡፡
ብራዚል ዓለም ዋንጫን ለ2ኛ ጊዜ ማስተናገድ የቻለች 4ኛው የፊፋ አባል አገር ናት፡፡ የመጀመርያውን ከ64 ዓመት በፊት 4ኛው የዓለም ዋንጫን በ1950 እኤአ ላይ   አዘጋጅታ  ዋንጫውን ያጣችበት ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫ በደቡብ አሜሪካ አገር ለመስተናገድ የበቃው በ1978 አርጀንቲና ካስተናገደችው ዓለም ዋንጫ ከ36 ዓመታት በኋላ ነው። ዓለም ዋንጫ ለሁለት ጊዜ ለማስተናገድ የበቁት ሌሎቹ አገራት ጣሊያን፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመንና፤ ሜክሲኮ ናቸው፡፡
ፊፋና አዳዲስ የገቢ ክብረወሰኖች
4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ፤ 3 ሚሊየን ትኬቶች
20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ብዙ ብር ወጭ ቢሆንበትም በትርፋማነቱ ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱበትና በአትራፊነቱም እየተነሳ ነው፡፡
ዓለም ዋንጫው በውድድሩ የ84 ዓመታት ታሪክ በተለያዩ የመዋዕለንዋይ ሁኔታዎች አዳዲስ ክብረወሰኖች እንደሚመዘገቡበትም ተጠብቋል፡፡ ፊፋ በታሪክ ከፍተኛውን የሽልማት ገንዘብ በውድድሩ ለሚሳተፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች በየደረጃው ለማከፋፈል 570 ሚሊዮን ዶላር ከማቅረቡም በላይ ለሻምፒዮኑ አገር የሚያበረክተው የ35 ሚሊዮን ዶላር ሽልማትም ካለፈው የዓለም ዋንጫ በ5 ሚሊዮን ዶላር የጨመር ነው፡፡   ለውድድሩ 3.3 ሚሊዮን የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ውድድሩ ከመጀመሩ አንድ ወር ቀደም ብሎ መሸጣቸውም አዲስ ክብረወሰን ነው፡፡ 1.1 ሚሊዮን ትኬቶች የገዛችው አዘጋጇ ብራዚል ናት፡፡ አሜሪካ በ187ሺ፣ ጀርመን ለ57ሺ፣ እንግሊዝ በ56ሺ፣ አርጀንቲና በ55ሺ ትኬቶች ግዢ እስከአምስት ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡ በትኬት ግዢያቸው ኦስትሪያ፣ ኮሎምቢያ፣ ቺሊ፣ ፈረንሳይ እና ሜክሲኮ እስከ 10 ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ ለእግር ኳስ ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ብራዚላውያን ስታድዬሞችን በመሙላት ‹ኦሌ ኦሌ ኦሌ ብራዚላዊ ነኝ› በሚል ዝማሬያቸው ለውድድር ድምቀት እንደሚያላብሱ ሁሉ የሜክሲኮ፤ የአርጀንቲና፤ የጀርመንና የእንግሊዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችም እንግድነት ሳይሰማቸው ይታደማሉ፡፡
በዓለም ዋንጫው የፊፋ ወጭ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሲሆን የሚጠብቀው የሪከርድ ገቢ ግን እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለብራዚል የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ እስከ ሰሞኑ 221 ሚሊዮን ዶላር የሰጠ ሲሆን ፤ለ32 ብሄራዊ በድኖች ዝግጅት 48 ሚሊዮን ዶላር ለየእግር ኳስ ፌደሬሽኖቹ ከማካፈሉ፤ በተጨማሪ በየብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾቻቸውን ላሰለፉ ክለቦች ብዙዎቹ የአውሮፓ ናቸው 70 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ 6 አብይ ስፖንሰሮችና 8 አንደኛ ደረጃ ስፖንሰሮች አግኝቷል፡፡ ስድስቱ አብይ ስፖንሰሮች አዲዳስ፣ ኮካ ኮላ፣ ኤምሬትስ፣ ሁንዳይ፣ ሶኒ እና ቪዛ ካርድ ሲሆኑ በድምሩ 177.13 ሚሊዮን ዶላር ከፍለዋል፡፡  ስምንቱ አንደኛ ደረጃ ስፖንሰሮች ደግሞ ቡድዋይዘር፣ ካስትል፣ ኮንትኔንታል፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ ማክዶናልድ፣ ሞዲ ኦይዥ፣ ያንግሉ ሲሆን 524 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ  ሰጥተዋል፡፡ የብራዚል ብሄራዊ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ደግሞ ያሰባሰባቸው ስፖንሰሮች ደግሞ 120 ሚሊዮን ዶላር ሰጥተዋል፡፡
ፊፋ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ በውድድሩ ላይ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የጎል ማረጋገጫ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ከግብ መስመር ያለፉ ኳሶችን ዳኞች በአግባቡ እንዲያፀድቁ እና ከመስመር ያለፈችን ኳስ እንዳያፀድቁ የሚያግዘው ቴክኖሎጂ ጎልኮንትሮል ጂኤምቢኤች በተባለ የጀርመን ኩባንያ የተሰራ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫው 64 ጨዋታዎች በሚካሄድባቸው ሜዳዎች ያሉ ሁሉም የጎል መረቦች በየግጥሚያው 14 ካሜራዎች እየተጠመደባቸው ለዳኞች የጎል ውሳኔ እገዛ ይፈጥራሉ፡፡
የሻምፒዮናነት ግምቶች
ብራዚል ከአርጀንቲና ከተጠበቁ የፍፃሜ ጨዋታዎች የመጀመሪያው ነው፡፡
ዋንጫው የፖርቱጋል ወይም የእንግሊዝ ነው - ሞውሪንሆ
ወደ 20ኛው የዓለም ዋንጫ ያለፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች ከታወቁበት ጊዜ አንስቶ በተለይ ላለፉት ስምንት ወራት ጀምሮ ውድድሩን ማን ያሸንፋል በሚል ጥያቄዎች በርካታ ትንበያዎች እና ግምቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በተለይ አራት ብሄራዊ ቡድኖች ለዋንጫው ድል አድራጊነት ግንባርቀደም ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ አዘጋጇ ብራዚል፤ ሻምፒናነቷን ለማስጠበቅ የምትቀርበው ስፔን፤  ጀርመንና አርጀንቲና ናቸው፡፡ ከቅድመ ግምቶቹ መገንዘብ እንደሚቻለው በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የሻምፒዮናነት ትንቅንቁ በሁለቱ አህጉራት ደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ መካከል መሆኑ ያመዝናል፡፡ የአፍሪካ፤ የሰሜንና የመካከለኛው አሜሪካ፤ የኤስያ እና የኦሽኒያ ዞኖችን የወከሉ ብሄራዊ ቡድኖች ከሩብ ፍፃሜ እንደሚሰናበቱ ጎን ለጎን ይገለፃል፡፡ አፍሪካዊ ቡድን ለግማሽ ፍፃሜ ምዕራፍ ደርሶ የማያውቅ ሲሆን ዘንድሮ አህጉሪቱን የሚወከሉት አምስት ብሄራዊ ቡድኖች ይህን ታሪክ ለመስራት መቸገራቸው አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ፤ ከኤስያና ከኦሽኒያ የተወከሉ ቡድኖች ከምድብ ማጣርያ ማልፍእንደሚሰናቸው በሰፊው የተተነተነ ነው፡፡ ባለፉት 19 የዓለም ዋንጫዎች ሻምፒዮን የሆኑ ስምንቱም ብሄራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ዓለም ዋንጫው በደቡብ አሜሪካ አገር ውስጥ ዘንድሮ የሚካሄደው በታሪክ ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን በዚያው አህጉር አስቀድመው የተካሄዱትን 4 የዓለም ዋንጫዎችን በሙሉ የደቡብ አሜሪካ ቡድኖች አሸንፈውታል፡፡ ይህ ታሪክ የደቡብ አሜሪካ ተወካዮች ሊኖራቸው የሚችለውን የዋንጫ ተስፋ አሳድጎታል፡፡ በተለይ አዘጋጇ ብራዚልና አርጀንቲና ለፍፃሜ መገናኘታቸው ተጠብቋል፡፡ ከዓለም ዋንጫው ቀደም ብሎ ሰሞኑን በወጣው የፊፋ እግር ኳስ ደረጃ በደረጃ መሻሻል ያሳዩት እንግሊዝ ፤ ብራዚል፤ አርጀንቲና እና ስዊዘርላንድ ናቸው፡፡ ስፔን እና ጀርመን አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ሲይዙ ብራዚል ፖርቱጋልን በመብለጥ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ወጥታለች፡፡አርጀንቲና እና ሰዊዘርላንድ ሁለት እርከኖች አሻሽለው 5ኛ እና 6ኛ ናቸው፡፡ ኮሎምቢያ፤ ኡራጋይና ጣሊያን አስከ ዘጠነኛ ሲቀመጡ እንግሊዝ ደግሞ በእንድ እርከን ደረጃዋን አሻሽላ 10ኛ ሆናለች፡፡  ሁለት ደረጃዎችን በመውረድ 12ኛ ላይ የተቀመጠችው ግሪክ ብቸኛዋ ድክመት የታየባት ስትሆን ሌሎቹ አገራት ከወር በፊት በነበሩበት እርከን ላይ ናቸው፡፡ ወርሃዊው የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት ምድብ 4 እና ምድብ 7 ጠንካራ ቡድኖች የሚገኙባቸው እንደሆነ ሲያመለክት በተለይ ምድብ 4 ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ የገቡ ሶስት ቡድኖች ስለተደለደሉበት የሞት ምድብነቱ ተረጋግጧል፡፡  
ጎልድማን ሳክስ በሰራው ስሌት በፍፃሜ ብራዚል አርጀንቲና 3ለ1 አሸንፋ ሻምፒዮን ትሆናለች ብሎ የገመተው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓለም ዋንጫዎች ይሄው ዓለምአቀፍ ባንክ በሰራው ግምት አልተሳካለትም ነበር፡፡ በ2006 እ.ኤ.አ ላይ ብራዚል ብሎ ጣልያን ስታሸንፍ በ2010 እ.ኤ.አ ላይም ብራዚል እንደምታሸንፍ ገምቶ ያሸነፈችው ስፔን ነበረች፡፡
በሌላ በኩል 32ቱን ብሄራዊ ቡድኖች በውጤት ታሪካቸው፤ በወቅታዊ ብቃታቸው፤ በነጥብ ጨዋታዎቸ ያላቸውን ተመክሮ በመከለስ እና ከሚበለጧቸው ቡድኖች ጋር የሚያሳዩትን አቋም በመገምገም የስፖርት ሚዲያ ኩባንያው ኢንፎትራዳ በሰራው ስሌት ለግማሽ ፍፃሜ የሚደርሱት  ብራዚል ፣አርጀንቲና፣ ጀርመንና ስፔን ሲሆን አሁንም ዋንጫውን ብራዚል አርጀንቲናን በማሸነፍ ትወስዳለች ብሎ ገምቷል፡፡ በተመሳሳይ አራቱ ቡድኖች ለግማሽ ፍፃሜ መድረሳቸውን  አንድ የጀርመን ፕሮፌሰር  ከ100ሺ በላይ የውጤት ሁኔታዎች በመቀመር ከወራት በፊት ገምተው ነበር፡፡ በፊፋ ስር ከ1994 የዓለም ዋንጫ ወዲህ የተደረጉ የብሄራዊ ቡድን ከ13ሺ በላይ ጨዋታዎችን በተለያየ ፎርሙላ ያሰላው አንድ የብራዚል ኢንጂነርም ዋንጫው ከብራዚል እንደማያልፍ ከድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡በዓለም ዋንጫ በሌሎች ትልልቅ የእግር ኳስ ውድድሮች በእንስሶች ፍጥረትን ማስተንበይ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ጀርመኖች ፖል በተባለ ኦክቶንስ አስተዋውቀው ነበር፡፡ ይህ የባህር እንስሳ የ8 ጨዋታዎች ውጤት በትክክል ገምቶ ነበር፡፡ ከሁሉ ያስደነቀው ዋናው ግምት ደግሞ ሻምፒዮን የሆነችውን ስፔን መምረጡ ነበር፡፡ ከ20 ዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘም ውጤት የሚተነብዩ እንስሶች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ብቅ እያሉ ናቸው፡፡ በጀርመን ውስጥ በሚገኝ አንድ የእንስሳት ፓርክ፣ ዝሆን ለትንበያው እየተዘጋጀ ነው። በቻይና የዓለም ዋንጫ ውጤቶችን እንዲገምቱ ትንንሽ ፓንዳዎች እየሰለጠኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ፓንዳዎች በምድብ ጨዋታዎች አሸናፊውን የሚጠቁሙት በሁለት ቅርጫት ምግብ ተቀምጦላቸው ከሁለት አንዱን በመምረጥ ነው፡፡ ትንንሾቹ ፓንዳዎች የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ለመተንበይ ግን ይፈተናሉ፡፡ ያለልማዳቸው ዛፍ ላይ ወጥተው ከሁለቱ የምግብ ቅርጫቶች አንዱን በመምረጥ አሸናፊውን ይለያሉ በብዙ የግምት ትንተናዎችና ትንበያዎች በብዙ የግምት ትንተናዎችና ትንበያዎች ብራዚልና አርጀንቲና ለሻምፒዮናነነት ሰፊ ግምት ቢያገኙም በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር በሚዘጋጀው የ20ኛው ዓለም ዋንጫ የጌም ጨዋታ የማሸነፍ ዕድሉ ለጀርመን ተሰጥቷል፡፡ “EA Sports” በተባለ ከባንያ የሚሠራው ይህ የጌም ጨዋታ አዘጋጅ ኩባንያ ጀርመን በደቡብ አፍሪካ ምድር የተዘጋጀን ዓለም ዋንጫ ለማሸነፍ የመጀመሪያዋ አውሮፓዊ ቡድን እንደምትሆን ተስፋ ያደርጋል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ይሄው ኩባንያ ስፔን ለሻምፒዮናነት ጠብቆ ተሳክቶለታል። ለግማሽ ፍጻሜ ብራዚል፣ ጀርመን፣ ፖርቱጋልና ስፔን ይደርሳሉ ብሎ የሚጠብቀው ኢኤ ስፖርትስ በዋንጫ ጨዋታ ጀርመን 3ለ1 ብራዚልን በማሸነፍ ዋንጫውን እንደምትወስድ ገምትዋል፡፡ ጆሴ ሞውሪንሆ ብራዚል በሩብ ፍጻሜ በእንግሊዝ ትሰናበታለች ያሉት ሲሆን ለግማሽ ፍጻሜ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፖርቱጋልና እንግሊዝ እንደሚደርሱ ገምተዋል። ለፍጻሜ የጠበቃቸውፖርቱጋልና እንግሊዝን ነው የዋንጫው አሸናፊ በመለያ ምቶች እንደሚዳኝ ይጠበቃል ያሉት ሞውሪንሆ ሁለቱም ቡድኖች በመለያ ምት መጥፎ ሪከርድ ስላላቸው አሸናፊውን ለመለየት ይቸግረኛል ብለዋል፡፡ በሳንቲም ጥሪ አሸናፊውን ለመለየት ዳኛው ይሞክራሉ ይደውላሉ ብዬ አላስብም ያሉት ሞውሪንሆ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ጣምራ ሻምፒዮኖች ይፈጠራሉ በማለት ስራቸውን ከሚሠሩበት እንግሊዝና ከትውልድ አገራቸው ፖርቱጋል የማይጣላበት መልስ ሰጥተዋል፡፡ በ2002 እ.ኤ.አ እና በ2006 እኤአ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የመሩት ሰቨን ጐራን ኤሪክሰን፣ የሮይ ሆጂሰን ቡድን እንኳን ለዋንጫ ሊደርስ ይቅርና እስከ ሩብ ፍፃሜ መጓዝ የሚችለው በመከራ ነው ብለዋል፡፡  
ከተጨዋቾች እንማን ይገኛሉ፣ እነማን ሳይመረጡ ቀሩ፣ እነማን አመለጣቸው እነማን ጡረታ ይወጣሉ
ተጨዋቾቹ 8.87 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ አላቸው፡፡
20ኛው ዓለም ዋንጫ በየብሔራዊ ቡድኑ  ምርጥ ተጨዋቾች በመብዛታቸው የተለየ ትኩረትም አግኝቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን አገሮቻቸው ማጣርያውን በማለፍ ለተሳትፎ ባለመብቃታቸው፣ በሚሳተፉ ብሄራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች ባለመመረጣቸው እና በጉዳት ሳቢያ በርካታ ተጨዋቾች ከውድድሩ መቅረታቸውም ይነሳል፡፡
በትራንስፈር ማርኬት ድረ ገጽ በቀረበው መረጃ መሠረት በ20ኛው ዓለም ዋንጫ በሚሳተፉ 32 ብሔራዊ ቡድኖች የተያዙት 736 ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው አጠቃላይ የዋጋ ተመናቸው 8.87 ቢሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በዝውውር ገበያ ውዱ ተጨዋች  እስከ 63.8 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የሚተመነው የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ሲሆን፣ የፖርቱጋሉ ሮናልዶ በ136.5፣ የብራዚሉ ኔይማር፣ የኮሎምፒያው ራድማሌል ፋልካኦ፣ የቺሊው ኤዲሰን ካቫኒ  በ81.4 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ተመናቸው ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ በውድድሩ  ላይ በከፍተኛ ብቃት ዓለምን ያስደምማሉ ከተባሉት ተጨዋቾች  መካከል በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ ለመሸለም እና  በኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ ለማግኘት  ግንባር ቀደም እጩ የሚሆኑት የአርጀንቲናው  ሊዮኔል ሜሲ፤ የፖርቱጋሉ  ክርስትያኖ ሮናልዶ፣ የብራዚሉ ፓብሎ ኔይማር ናቸው፡፡ ሌሎቹ የሚጠበቁ ተጨዋቾች ጁዋን ኩዋርዶ ከኮሎምቢያ፣ ሾን ሂውንግ ሚን ከደቡብ ኮርያ፣ ማርዮ ባላቶሊ ከጣልያን፣ ኤዲን ሃዛርድ ከቤልጂየም፣ ያያቱሬ ከአይቬሪኮስት  ናቸው። አብዛኛዎቹ ምርጥ ተጨዋቾች እድሜያቸው ከ30  ዓመት በታች መሆኑ በየግጥሚያው ሊኖር የሚችለውን ፉክክር ማራኪ ያደርገዋል፡፡ ለወጣት ተጨዋቾች መድመቂያ የሚሆነው ውድድሩ ለሌሎች ትልልቅ ተጨዋቾች ደግሞ የመጨረሻ እድል ነው፡፡ የሜክሲኮው ራፋኤል ማርኩዌዝ፤ የአርጀንቲናው ሃቪዬር ማሸራኖ፤ የጣሊያኖቹ ጂያንሉጂ ቡፎን እና አንድሬ ፒርሎ፤ የእንግሊዞቹ ስቴፈን ጄራርድ እና ፍራንክ ላምፓርድ፤ የስፔኖቾ ዣቪ እና ኢንዬስታ፤ ለካሜሮኑ ኤቶ፤ ለአይቬሪኮስቱ ድሮግባ እና ለሌሎች አንጋፋ ተጨዋቾች ዓለም ዋንጫው በጡረታ የሚሰናበቱበት ይሆናል፡፡
በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ሳይካተቱ በመቅረታቸው ዓለም ዋንጫው ያመለጣቸው ምርጥ ተጨዋቾችም ከ10 በላይ ይሆናሉ፡፡ ከእነሱ መካከል አሽሊ ኮል እና ማይክል ካሪክ ከእንግሊዝ፣ ለንደን ዶኖቨን ከአሜሪካ፣ ማርዬ ጐሜዝ ከጀርመን ሴሴና ከስፔን፣ ሪከርዶ ካካ ከብራዚል፣ ሳሚር ናስሪ ከፈረንሳይ፣ ጁሴፔ ሮሲ ከጣሊያን፣ ሪካርዶ ኳሬስማ ከፖርቱጋል፣ ካርሎስ ቴቬዝ ከአርጀንቲና ይጠቀሳሉ፡፡ አንዳንድ ተጨዋቾች ደግሞ ባለቀ ሰዓት በደረሰባቸው ጉዳት እና አስቀድሞ ከነበረባቸው ጉዳት ባለማገገማቸው ተመልካች ለመሆን ይገደዳሉ፡፡ ይህ አይነት ዕጣ ፋንታ ከገጠማቸው ተጨዋቾች መካከል የኡራጋይ ሊውስ ስዋሬዝ ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡  በሌላ በኩል አገሮቻቸው ለዓለም ዋንጫ በተደረጉ የማጣርያ ውድድሮች ማልፍ ተስኗቸው በመቅረታቸው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ጥቂት የማይባሉ ምርጥ ተጨዋቾች እንዳያሳትፍ ሆኗል፡፡ ዋናዎቹ የስዊድኑ ዝላታን ኢብራሞቪች፣ የዌልሶቹ ጋሬዝ ባሌና አሮን ራምሴይ፤ የኦስትሪያው ዴቪድ አላባ የፖላንዱ ሮበርት ሎዌንዳውስኪ ናቸው፡፡
የቲቪ ስርጭት
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ከምድብ ማጣሪያው ጀምሮ እስከ ዋንጫ ጨዋታው የሚደረጉት 64 ጨዋታዎች በሙሉ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት በመላው ዓለም ሽፋን ያገኛሉ፡፡  የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭቱ የሚሰራው በየስታድዬሞቹ ለእያንዳንዱ ግጥሚያ በ34 ካሜራዎች በሚደረግ ቀረፃ ነው፡፡ ይህን ተግባር ለማከናወንም ከ48 አገራት የተውጣጡ ከ3000 በላይ ባለሙያዎች ተመድበዋል፡፡ 20ኛው ዓለም ዋንጫ የሚደረጉ ጨዋታዎች በቲቪ የሚተላለፉት በ “Ultra High Definition” የቀረፃ ቴክኖሎጂ በመሆኑ በውድድሩ ታሪክ የመጀመሪያው ይሆናል፡፡ ፊፋ ከዓለም ዋንጫው የቴሌቭዥን ስርጭት መብትና ከተያያዥ ንግዶች እስከ 1.38 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚጠብቅ ሲሆን ለውድድሩ በሚሰጠው ሽፋን አዳዲስ ክብረወሰኖች እንደሚኖሩትም እየተገለፀ ነው።  በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ስፔን ከሆላንድ የተፋለሙበትን የዋንጫ ጨዋታ ቢያንስ 1 ደቂቃ የተመለከቱ በዓለም ዙሪያ እስከ 1 ቢሊዮን ስፖርት አፍቃሪዎች ናቸው፡፡ በብራዚሉ 20ኛው ዓለም ዋንጫ የፍፃሜው ጨዋታ ቢያንስ ለ1 ደቂቃ እስከ 3.2 ቢሊዮን ተመልካች ያገኛል በሚል ተገምቷል። አዲስ ሪከርድ ነው፡፡ በ19ኛው የዓለም ዋንጫ አገር ጨዋታ በአማካይ ከ188 ሚሊዮን በላይ የቲቪ ተከታታይ እንደበረው የሚጠቁም ጥናት ዘንድሮ ይህ አሃዝ ወደ 350 ሚሊዮን ይደርሳል ብሏል፡፡ 20ኛው ዓለም ዋንጫ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በቲቪ የሚኖረው ድምር የተመልካች ብዛት ከ3.2 ቢሊዮን በላይ ተገምቷል፡፡ በቴሌቭዥን የስርጭት ሽፋን አዳዲስ ክብረወሰኖች የሚመዘገቡት  በቴክኖሊጂ በመታገዝ እና ለስፖርት አፍቃሪዎች በተመቸ የጨዋታ ፕሮግራም በመሰራቱ እንደሆነ የገለፀው ፊፋ ነው፡፡ ብዙዎቹ ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸው ሰዓቶች ምንም እንኳን በሜዳ ላይ ለተጨዋቾች በአማካይ 27 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት እና አስቸጋሪ ወበቅ ሆኖ ቢፈትንም በቲቪ ስርጭት ግን በተለይ ለ3 አህጉራት ለአፍሪካ፤ ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለአውሮፓ አመቺ ሆኗል።  ለኢትዮጵያ ብዙ ጨዋታዎች ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ የሚጀምሩ ናቸው። በኤስያ እና በሰሜን አሜሪካም የዓለም ዋንጫው የቲቪ ተመልካቾች ቁጥር በፍጥነት እድገት ማሳየቱ የሚረጋገጥ ይሆናል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለውድድሩ የተሳካ ስርጭት ለማከናወን ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመደብ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

Read 3649 times