Saturday, 21 June 2014 14:17

ከስደተኞች ጣቢያ በራፍ ላይ ተቀምጠው የጠፉ ልጆቻቸውን ይጠብቃሉ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(1 Vote)

        በጋምቤላ ክልል የምትገኛው ፓጋግ የገጠር ቀበሌ፤ የዛሬን አያድርገውና የኮንትሮባንድ ንግድ የሚጧጧፍባት፤ ዶላር ከፓውንድ የሚመነዘርባት፤ የኤሌክትሮኒክስ እቃ የሚቸበቸብባት የድንበር ከተማ ነበረች፡፡
ዛሬ ግን የመከራና የስደት መናሃሪያ ሆናለች፡፡ የደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞችም ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡባቸው አምስት የድንበር አካባቢዎች አንዷ የፓጋግ መንደር ናት፡፡ በደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ውሎ ሳያድር በጐሳ ወደ ተቧደነ ግጭትና ጦርነት ከተቀየረ ወዲህ ስደት በርክቷል፡፡
በሱዳን ልዩ ወታደሮች፣ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና ልዩ ጥበቃ ‹‹አካባቢው ሰላም ነው›› ሊባል ቢችልም፤ በቅርብ ርቀት ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ ድንበር ጠባቂዎቹ ይገልፃሉ፡፡
እዚያ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን መዝግቦ እርዳታ መስጠት ቀላል ስራ አይደለም፡፡ የጋምቤላ ክልል ነዋሪ የሆኑት የኑዌር ብሔረሰብ አባላት በብዛት እየተቀላቀሉ መሆናቸውን የሚናገሩ የእርዳታ ሰራተኞች፤ የሱዳንና የኢትዮጵያ ዜጎችን ለመለየት እንደተቸገሩ ይገልፃሉ፡፡  
ወደ ኩሌ መጠለያ ጣቢያው ስንደርስ ስንዴ፣ አተር፣ ፋፋ፣ የአትክልት ዘይት፣ ስኳር፣ ማሽላ ለቤተሰብ ሲከፋፈል ነበር፡፡ ከየካቲት 22 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2006ዓ.ም ድረስ ብቻ ከ51ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን የተቀበለው “ኩሌ አንድ” የስደተኛ የመጠለያ ጣቢያ፤ ተጨማሪ ስደተኞች ማስተናገድ ስለማይችል “ኩሌ ሁለት” በሚል ሌላ መጠለያ ተከፍቷል፡፡   
ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. የተከፈተው “ኩሌ ሁለት” የስደተኞች መጠለያ፤ በየቀኑ ሁለት ሺ ስደተኞችን እያስተናገደ እስካሁን ሃያ ሺህ መቀበሉን አስተባባሪ ሃላፊ ላባ ለሚሳ ጠቁመዋል፡፡
ስደተኞች ለምዝገባ ከሚገቡበት የመጠለያ ጣቢያው ደጃፍ ላይ አንዲት ሴት አዛውንት በሃዘንና በትካዜ ተቀምጠዋል - በዚያ ፀሐይ በዚያ ሃሩር፡፡ ወደው አይደለም፡፡ የጠፋ ልጃቸው ይመጣ እንደሆነ ተስፋ በማድረግ እዚያው ገላጣ ቦታ በፀሐይ ሲጠበሱ ይውላሉ። ልጃቸው ከመጣ ያያቸው ይሆናል፡፡ እሳቸው ግን ማየት አይችሉም፡፡ ይሄን ያወቅሁት በኋላ-ነው ከራሳቸው አንደበት፡፡ ሴትየዋን አነጋገርኳቸው፡፡
ስምዎ ማን ይባላል?
ናኛክ ጀውዋጅ
በዚህ ጸሀይ… ለምን ወደ መጠለያው አይገቡም?
ጉዳይ አለኝ…
ከመጡ ስንት ጊዜ ሆነዎት፣ ቤተሰብ አለዎት?
አለኝ፡፡ አሁን ግን ብቻዬን ነኝ፡፡
ትተዋቸው መጡ?
በአካባቢያችን ጦርነቱ የተነሳው ባልታሰበ ሰዓትና ጊዜ ነው፡፡ ከቤቴ በራፍ ላይ ቆሜ ልጆቼን ብጣራ እንኳን የሚሰማኝ አጣሁ፡፡ መሮጥ አልቻልኩም፡፡ እጄን ያዙኝ፣ ምሩኝ እያልኩ ወዲህ አዘገምኩ፡፡ አንዳንድ ጥሩ ሰዎች ስለነበሩ ረዱኝ፡፡
እጄን ያዙኝ የሚሉት ለምንድን ነው? መራመድ አይችሉም?
መንገዱ ጉድጓድ ይሁን ድንጋይ፣ ወንዝ ይሁን ባህር ማየት አልችልም፡፡ አይነ ስውር ነኝ፡፡ (እንባቸው ይወርዳል)፡፡ ከመጣሁ አራት ቀኔ ነው፡፡ እዚህ ያደረሱኝ ሰዎች ናቸው፡፡ ከመጣሁ ሰዓት ጀምሮ ግን ከጠዋት እስከ ማታ ከዚህ ከመጠለያ ጣቢያው በራፍ አልነሳም፡፡ በአጠገቤ ኮቴ ከሰማሁ የጠፋብኝ የአስራ አምስት ዓመቱ ልጄ ሮጦ መጥቶ የሚያቅፈኝ ይመስለኛል፡፡ እናም ኮቴ ስሰማ ጆሮዬን ሰጥቼ በደንብ እሰማለሁ፡፡ እናንተ ሰላምታ ስትሰጡኝ፤ “ልጅሽ መጣ” ብላችሁ የምትነግሩኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ከጦርነቱ ተርፎና አምልጦ ከመጣ… በህይወት ካለ..(ዝም አሉ)
እንደው አየነው የሚል ሰውም አላገኙም?
ብዙ ከብቶች አሉን፡፡ እነሱን እየጠበቀ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበር። እርሻችንንም ልጄ ነበር የሚቆጣጠረው፡፡ እንግዲህ ከአካባቢው ራቅ ብሎ ስለነበር ምናልባት ተኩሱ ደርሶበት ይሆን ብዬ እሰጋለሁ፡፡ ትናንት ከእኔ አካባቢ የመጡ ሰዎች አናግረውኝ ነበር፡፡ በቀያችን አንድም የቀረ ሰው የለም ብለውኛል፡፡  እንግዲህ መንገድ ላይም ከሆነ ወይንም በዚሁ ሰፊ ካምፕ በአንዱ ስፍራ ካለ፣ በዚህ መንገድ ሲያልፍ ሊያየኝ ይችላል በሚል ነው በዚህ ፀሃይ ቁጭ ብዬ የምጠብቀው፡፡ የልጄን ስም ለመንግስት ብትሰጡልኝልና ልጄን ቢያገኙልኝ…፡፡
የእኔ ልጅ ብቻ አይደለም የጠፋው፡፡ ብዙ ሰው ከልጆቹ ጋር ተጠፋፍቷል፡፡ አንድ ጎረቤቴ ዛሬ እዬዬ ሲል ነበር፡፡ “ሶስት ወንድ ልጆቼን በመጠለያው ዞሬ ዞሬ አጣኋቸው፣ ለወታደርነት ወስደውብኛልም” ሲል ነበር። እንግዲህ እኔስ በምን አውቃለሁ..ጦርነት ከሌለበት ሀገር ልጄ በኖረ፡፡ ምን አውቃለሁ… ምን እየበላ እንደሆነ…(መሬቱን ይዳስሳሉ፣ ደረታቸውን በሀዘን ደጋግመው ይመታሉ) ዓይነ ስውር ባልሆን እዚህም እዚያም እሄድ ነበር፡፡
በመጠለያ ጣቢያው ያገኘኋቸው ሌላ አዛውንት፣ ከመጠለያ ጣቢያው ለአንድ ወር የሚሰጣቸውን ራሽን ለመቀበል ወረፋ እየጠበቁ ነበር፡፡
ስምዎትን ማን ልበል?
ታችዋክ እባላለሁ፡፡ ከማታያ ነው የመጣሁ፡፡ መንገድ  ስንጓዝ አራት ቀን ፈጅቶብናል፡፡ በአምስተኛው ቀን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ በረሃ ስለሆነ በእባብ መነደፍ ሁሉ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም የሀገራችን ዘራፊዎች ስላሉ፣ ገንዘባችንን ፈትሸው ይወስዱብናል፡፡
ብቻዎትን ነው ወደዚህ አካባቢ የመጡት?
ልጆቼ ጠፍተውብኛል፡፡ ማን እንደወሰዳቸው አላውቅም፡፡ በመንደራችን ብዙ ሰው በሀዘንና በጭንቀት ተወጥሮ ነው ያለው፡፡ አካባቢያችን በጦርነቱ ተጎድቷል፡፡ ብዙ ሰው ሞቶብናል፡፡  በወባ የሞተውም ብዙ ነው፡፡ እንግዲህ ድርድሩ ጥሩ ከመጣና ሰላም ከሰፈነልን ወደ ሃገሬ መመለስ ነው የሚናፍቀኝ፡፡ የሀገራችን ሰዎች በጦርነቱ እየረገፉ እያለቁ እኮ ነው፡፡  
በምን ነበር የሚተዳደሩት?
በእርሻ ነበር የምተዳደረው፡፡ ሶስት የእርሻ ቦታና 34 ከብቶች ነበሩኝ፡፡ ነድቼ አላመጣቸው ነገር አልቻልኩም፡፡ ተዘርፈው ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለት ሚስቶቼ እና የተወሰኑ ልጆቼ አብረውኝ መጥተዋል፡፡
ሸሽታችሁ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታችሁ በፊት በሀገራችሁ የተነሳው ግጭት ምን ይመስል ነበር?
ጦርነት ምን ቀለም አለው? እኛ የምናሳዝን ህዝቦች ነን፡፡ መሪዎቻችን በአለም እና በአፍሪካ መሪዎች አማካኝነት ካልተዳኙ ህዝባችን ገና ያልቃል፡፡ ህፃናት ሴቶች እየሞቱ ነው፡፡ ወንዶችም ይገደላሉ፡፡ እኛ ሀብታሞች ነን፡፡ ሀገራችን ሰላም ሆኖ ተመልሰን መኖር ነው የምንፈልገው፡፡


Read 2766 times