Saturday, 28 June 2014 10:36

ዓረና ሰላማዊ ሰልፍ “የፖሊስ ኃይል የለንም” በሚል ተሰረዘ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(2 votes)

ሰልፉ የተከለከለው ብዙ ህዝብ ይወጣል በሚል ስጋት ነው - ፓርቲው

ዓረና አንድነትና ለልዑላዊነት ፓርቲ፤ “ፍትህና ውሃ ያስፈልገናል” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በመቀሌ ከተማ ሊያካሂድ የነበረው ሰላማዊ ሠልፍ “የፖሊስ ሀይል የለንም” በሚል እንዲሰረዝ መደረጉን የፓርቲው አመራር አቶ አብርሃ ደስታ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ቀደም ብሎ ለሰላማዊ ሰልፉ የከተማው አስተዳደር ፈቃድ ሰጥቷቸው እንደነበር የጠቆሙት አቶ አብርሃ፤ የቅስቀሳ ስራዎችን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ካደረግን በኋላ በትናንትናው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የክልከላ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ገልፀዋል፡፡
በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ የመጀመሪያውን ጠንካራ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅደን ነበር ያሉት አቶ አብርሃ፤ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የውሃና የፍትህ እጦት ጥያቄዎች እንዲሁም “ፍትህ በጠየቅን አሸባሪዎች አይደለንም” በሚል መንግስት በሚከተለው የሽብር አቋም ላይ ተቃውሞ ለማሰማት ታስቦ ነበር ብለዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር ለፓርቲው በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ፤ ሰላማዊ ሰልፉ የተሰረዘው በመቀሌ ከተማ ከሰኞ ጀምሮ ከሚከበረው “የሲቪል ሰርቪስ ሳምንት ቀን” ጋር በተያያዘ በቂ የፖሊስና ልዩ ሃይል ስለሌለን ነው ብሏል፡፡ ዛሬ ሊካሄድ ታቅዶ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከ5ሺ ሰዎች በላይ እንደሚገኙ ይጠበቅ ነበር ያሉት አቶ አብርሃ፤ ሰልፉ የተከለከለውም ብዙ ህዝብ ይወጣል በሚል ስጋት እንደሆነ የመንግስት ምንጮቻችን ነግረውናል ብለዋል፡፡

Read 2026 times