Tuesday, 08 July 2014 07:37

ኢቴቪ እና እነ ዲላ ዩኒቨርስቲ ለምን በይፋ ይቅርታ አይጠይቁም!?

Written by  ብዕር ጂ
Rate this item
(12 votes)

        ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን በጣም አነጋጋሪና አስገራሚ ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ የአቶ ሣሙኤል ዘሚካኤል እጅግ መረን የለቀቀ የውሸት መረጃና መግለጫ መጋለጡ፣ አንዱና ዋናው ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ግለሰቡ እጅግ ለማመን የሚያስቸግሩ ታምራቶችን ሁሉ እንደ ጉድ እያንዶሎዶለ በየመድረኩ ሲሰብክ “አረ ቆይ ቆይ…እዚች ላይ እንኳ ማስረጃ ብትጠቅስ! ይኼን እንዴት ልታሳካ ቻልክ…?” ወዘተ ብሎ የሚሞግት “ምሁር” መጥፋቱ ብዙዎች ያሳዘነ ሌላኛው አስገራሚ እውነት ነበር፡፡
በርግጥ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የትምህርት ክፍሎቻቸው መምህራን ሲቀጥሩ፣ በዝውውር እንዲመጣላቸው ሲፈልጉና ሲፈቅዱ፣ በባህል ማዕከል ምረቃቸውና በሌሎች ትምህርታዊ መድረኮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያቀርቡ ምሁራኑን ሲጋብዙ ስለምሁራኑ አንድ ነገር ሳይስቱ ይጠይቃሉ - የትውልድ ቦታና ቋንቋ፡፡ ዩኒቨርስቲው ያለበት አካባቢ ወይም መንደር ተወላጅ ከሆኑ ለተባለው የሙያ መድረክ ይመጥኑም አይመጥኑም፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ማቅረብ ይቻሉም አይቻሉም፣ በሙያው አግባብ ያለው የትምህርት መረጃና የምሥክር ወረቀት ይኑራቸውም አይኑራቸውም በዩኒቨርስቲው መድረክ ላይ መሳተፋቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ዩኒቨርስቲው ከበቀለበት መንደር ተወልደዋላ፤ ወይም  የዩኒቨርስቲውን አካባቢ ቋንቋ ይናገራሉዋ፡፡ እዚህ ላይ የቀረበው አስተያየት፣ በይመስለኛል የተነገረ አለመሆኑን በአጽንኦት መግለጽ እፈልጋለሁ፤ ካስፈለገም የተወሰኑ ዩኒቨርስቲዎችን አፈፃፀም በዋቢነት በመጥቀስ መሞገት ይቻላል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ዩኒቨርስቲዎቻችን ከጐሰኝነትም ወርደው የመንደርተኛ ዜጐች መፈልፈያ እስኪመስሉ ድረስ፣ የብሔር ፖለቲካውን ያለቅጥ እየዘወሩት እንዳሉ ከማንስ ሊሠወር ይችላል?
የአካባቢ ተወላጅነት፣ ትውውቅና ዝምድና፣ የአካባቢ ቋንቋ ተናጋሪነት እንደቀዳሚ መስፈርት የሚያዩ የሚመስሉ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች “ለልጅ” ሣሙኤል ዘሚካኤል በራቸውን ወለል አድርገው ከፍተው፣ በየመድረኮቻቸው እንዳሻው እንዲያወራና እንዲምነሸነሽ እንዴት ፈቀዱ ብሎ መጠየቅ ምንም ክፋት የለውም፡፡
እራሱን የታላቅ ስኬት ባለቤት አድርጐ በመንፈስ እስኪከንፉ ያዘመራቸው ይህ ሰው፣ በየዩኒቨርስቲዎቹ አካባቢ “የመወለድ የተለየ ችሎታና መብት ያለው” ካልሆነ በቀር፣ ጐሰኝነት ብሎም መንደርተኝነትን መለኪያ ያደረጉ የሚመስሉ አንዳንድ “አካዳሚያዊ” መድረኮች ላይ የመሳተፍ ፍቃድ ማግኘቱ በራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡
ግለሰቡ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማትን ሲያንኳኳና ያለምንም ማንገራገር ሰተት ብሎ ሲገባ፣ የተፈቀደለት በአንዳንዶቹ ተቋማት እንደውም በመድረካቸው ላይ እንዳሻው እንዲዘባነን ጥሪ እንዲያደርጉለት የተገደዱት በኢቴቪ ዝግጅት መነሾ ይመስለኛል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን የሥራ ፈጠራ ሊቆችን እንዲዳኝ በ “ሊቀሊቃውንትነት” መንበሩን መውረስ የቻለ ግለሰብ፣ ፊቱን ለሀገሬው ህዝብ በደንብ ማሻሻጡን ከተረዳ በኋላ፣ ሀሰተኛ የትምህርት መረጃን ብቻ ሳይሆን “ቅዠት” እንዴት ወደ ገበያ ይዞ መውጣትና መቸርቸር እንደሚቻል ሙከራ ለማድረግ ቢነሳ ብዙ አይገርምም፤ ሙከራዎቹ ያልተጠበቀ ትርፍ ሲያስገኙ ሲያይ፣ “ፈጠራውን በዕለት ተዕለት እያሻሻለ፣ የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መድረኮች ላይ ጭምር እያላገጠ በቅዠት ዳረንጐት ማግኘት እስኪያስችለው ድረስ እየተካነበት የመጣ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥም ለሱ መንገድ ቀያሾች የሆኑ ሌሎች አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ አለመጠርጠርም ይከብዳል፡፡  
ብስልና ጥሬን “እያንጓለለ” የሚለይ ተቋምና ዜጋ ሲጠፋ፣ እንደ ሳሙኤል ዘሚካኤል ያሉ ብዙ “ታምራት” ፈጣሪ ገድለኞች እንዳሸን መፍላታቸው አይቀርም፡፡
በየዓመቱ ከድህነት ወለል በታች ያለውን መለኪያ እንድታሟላ የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ፣ በድህነት የምትማቅቅ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች፣ ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው ይበጃል ያሉትን የፈጠራ ሥራ አቅርበው፣ የሥራቸውን ዋጋ የዳኛቸው ግለሰብ፣ ከምኑም የሌለበት “ሀሰተኛ መሲህ” መሆኑ ያወቁ ዕለት ልባቸው ምን ያህል በሀዘን ሊሰበር እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ የፈጠራ ውጤታቸውን ተጠቅመው ወደ ሥራ ሲገቡም፣ በፈጠራ ውጤታቸው እራሳቸውና ሀገራቸው ምን ያህል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢያንስ መጠራጠራቸው አይቀርም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግሥት ተቋማት፣ እንደነ ሳሙኤል ያሉ “ደፋር” ሀሰተኛ ዳኞችን መቆጣጠር የተሳናቸው ወይም መቆጣጠር ያልፈለጉ የመምሰላቸው ተምሣሌት፣ ወጣቶቹ የፈጠራ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ተፍጨርጭሮ የሚያድረውን ዜጋ ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ የጥፋት ጐዳና እንዳይሆን፣ አሁንም የመንግስትን ወይም የተቋማቱን ብልህ ውሳኔ የሚሻ ይመስላል፡፡
የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችን እና ትላልቅ ተቋማትን ሥምና ግብር በይፋ እያጣቀሰ፣ የሀሰት ወሬውን በሀገር ተረካቢ ወጣቶች እየነዛ የግለሰቦችንም የመንግስት ተቋማትንም ህልውና ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ግለሰብ፣ በሀገሪቱ የህግ አግባብ ለምን ተብሎ ካልተጠየቀ፣ ነገ ብዙ ሺ ባለ “ራዕይ” ሳሙኤሎች እየተባዙልን እንደሚሄዱ መገመት አያቅትም፤ እስከአሁን የተባዙት ሳሙኤሎችም ካደፈጡበት ሥርቻቸው እየወጡ ሀገሪቱን “የገድለኞች” እና የአጭበርባሪዎች መነኻሪያ ከማድረግ አይመለሱም - ጠያቂ እንደሌለባቸው አውቀዋልና፡፡
እናም የጥፋት ተምሣሌት የሆነው ግለሰብ ሀገራዊ እውቅና እንዲያገኝ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ የሚታወሰው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ለደንበኞቹ “ሀላፊነቴን ተወጥቼ ስለ ግለሰቡ ሣላጣራ ተሳስቼ ስላሳሳትኳችሁ ይቅርታ አድርጉልኝ” በማለት ቢያንስ በይፋ ይቅርታ የመጠየቅ የሥነምግባር ሃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል፡፡ የበለጠ ሃላፊነት የሚሠማው ከሆነ ደግሞ ያሳሳተውን ግለሰብ ወደ ህግ የሚያቀርብበትን አግባብ ቢሞክር መልካም ነው፤ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቶ የፀረ ሽብር አዋጁ እያጣቀሰ “የማስመከር” ብቃቱን መጠቀም ሁሉ ግድ ሳይለው፣ የይቅርታና የውይይት መድረክ ማመቻቸት ይቻላልና፡፡
ዲላ ዩኒቨርስቲም፣ እንደሌሎቹ ዩኒቨርስቲዎች ግለሰቡ ያሻውን የሚያወራበት መድረክ አመቻችቶ፣ አንቱ የተባሉ ምሁሮቹን ሳይቀር ሰብስቦ በሀገር ጊዜና ገንዘብ ላይ ማስቀለዱ ብቻ ቢሆን ጥፋቱ፣ ከሌሎቹ ተለይቶ እዚህ ላይ በስም መጠቀስ ባላስፈለገ ነበር፤ ነገር ግን፣ ባሳተመው አጀንዳ ላይ “የሀሰተኛውን ወሬ አቅራቢ” ምስል አካቶ፣ ተኩራርቶ የመውጣቱ ድፍረት፣ የጥፋቱን ተምሣሌትነት ዘመን ተሻጋሪ ስለሚያደርገው፣ በይፋ ይቅርታ ቢጠይቅ ብልህ ሆነ ማለት ነው፤ ይቅርታ የመጠየቅና ይቅር የማለት ተቋማዊ ባህል ባልፈጠረባት ሀገር፣ ዩኒቨርሲቲው በይፋ ይቅር ማለቱ ብዙ የሚያተርፍለት ይመስለኛል፤ ከአንድ ዩኒቨርስቲ የማይጠበቅ ስህተቱን፣ ከአንድ ዩኒቨርስቲ በሚጠበቅ ይቅርታ የመጠበቅ ብቃቱና እውነት የመፈለግ ምክንያታዊ ተነሳሽነቱ፣ ስህተቱን የሚያነጻበት ንሰሃው ይሆናል፤ ምናልባትም ሀገርን በሙሉ የሚያስተምርበት፣ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርለታል፡፡

Read 7357 times