Wednesday, 30 July 2014 07:56

ሌላው ጦርነት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ሃሎ?! ኮሎኔል ሙሳ ነኝ! ማን ልበል?”
“ሃሎ! ጓድ ኮሎኔል…ይቅርታ! ከሆቴሉ እንግዳ መቀበያ ክፍል ነው!”
“ለምንድነው ከእንቅልፌ የምትቀሰቅሱኝ?! ለራሴ የበላሁት ምሳ አልፈጭ ብሎኝ መከራዬን ያሳየኛል! ከጓድ ሊቀመንበሩ ቢሮ በስተቀር ከየትም ቢደወል እንዳትቀሰቅሱኝ አላልኩም?!”
“ይቅርታ ጓድ ኮሎኔል! አንዲት ባልቴት እዚህ ሆቴሉ በር ላይ ቆመዋል…እናቱ ነኝ ይላሉ!”
“የማን እናት?”
“የእርስዎ መሰለኝ…በጦርነቱ ተፈናቅዬ ከምስራቅ ጦር ግንባር ነው የመጣሁት ይላሉ ጓድ ጌታዬ!”
“ለመሆኑ ማን እባላለሁ አለች?”
“በላይነሽ እባላለሁ ይላሉ ጓድ ኮሎኔል! የእርስዎ ወላጅ እናት ነኝ ይላሉ…”
“ልትሆን ትችላለች…ማነው ያለሁበትን ያሳያት ግን? እኔ እናት አገርና አብዮት እንጂ ሌላ እናት አላውቅም!”
“ምን ልበላቸው ታዲያ ጓድ ኮሎኔል?”
“በቃ አላውቃትም አልኳችሁኮ! እናቴ ብትሆን ባትሆንም ግድ የለኝም! ማነው ግን ያለሁበትን ቦታ ያሳያት? ይሄ የአናርኪስቶች ሴራ መሆን አለበት!”
“ማን እንዳሳያቸው አይታወቅም ጓድ ኮሎኔል!”
“አስር ብር ስጧትና እንደዚህ የሚባል ሰው እዚህ የለም ብላችሁ ሸኟት! ይልቁኑ ያቺን የማታዋን ቆንጅዬ ልጅ የሆቴል ታክሲ ልካችሁ አሁኑኑ አስመጡልኝ! እዚህ ሌላ ጦርነት ውስጥ ነው ያለሁት! ይገባችኋል?”
“ይገባናል ጓድ ኮሎኔል! በደንብ ይገባናል!”
“አልገባ ካላችሁ ደግሞ መጥቼ በሚገባችሁ ቋንቋ አነጋግራችኋለሁ!! አናርኪስት ሁላ! ልክ ነው የማስገባሽ!”
“ይገባናል ጓድ ኮሎኔል! ልጅቷን አሁኑኑ እናስመጣታለን!”
“በጓድ ሊቀመንበርና በአብዮቱ ቀልድ የለም! ይገባችኋል?”
“ይገባናል ጓድ ኮሎኔል! በደንብ ይገባናል!”
(ከደራሲ ሙሉጌታ ጉደታ “ያልተሸነፈው”
የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ፡፡
ሰኔ 2006 ዓ.ም)

Read 3557 times