Saturday, 06 September 2014 10:52

“ያልተገሩ ብዕሮች”ን ለመግራት…

Written by  መድሃኔ ግደይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ፤ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር
Rate this item
(3 votes)


           ሁለት ማየት የተሳናቸው ጓደኛሞች ናቸው አሉ፡፡ አንድ ዝሆን ያገኙና በእጃቸው በመዳሰስ ስለ እንስሳው የማወቅ ጥረታቸውን ይጀምራሉ፡፡ አንደኛው፤ጭራውን ይዳብሰውና “ዋው! ዝሆን ማለት ቀጭን እንስሳ ነው” በማለት ቀጭንነቱን አምኖ ተቀበለ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፤ ሆዱ አካባቢ ይነካካውና ዝሆን ማለት ጠፍጣፋ እንስሳ ነው ብሎ አመነ፡፡ ልንፈረድባቸው አንችልም፤ ብቻ ሁለቱም ስለ ዝሆን  የተሟላ ምስል አለማግኘታቸውን ተረድተናል፡፡
አሁን ወደ ራሴ ጉዳይ ልግባላችሁ፡፡ የዛሬ አንድ ወር ገደማ ይሆናል ከኢቴቪ(የአሁኑ ኢቢሲ) ተደውሎልኝ “በኢትዮጵያ ሚዲያ ዙሪያ ሙያዊ አስተያየትህን ለመስጠት ፍቃደኛ ከሆንክ--” የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ ሰፋ ያለ ርእሰ ጉዳይ ስለሆነ በጣም ተመቸኝ፡፡ እኔ እንግዲህ  “በነፃነት” የመንግስትና የግል ሚዲያውን በተመለከተ ሙያዊ ብቻ (ፖለቲካዊ አላልኩም) አስተያየቴን ለመስጠት ነበር ያሰብኩት፡፡ ቀኑ ደረሰና ወደ ጣቢያው ሄድኩኝ፤ ልክ ስቱዲዮ ልገባ ስል  ጋዜጠኛው “በማነሳልህ ጥያቄ ዙሪያ ማብራሪያ ልስጥህ” በማለት ፕሮግራሙ በግል ሚዲያ ዙሪያ ብቻ እንደሚያጠነጥን ነገረኝ፡፡ ትልቅ ስህተት ተመልከቱ ፣ለምንድን ነው የግል ሚዲያው ላይ ብቻ ማተኮር ያስፈለገው?
ለነገሩ ኢቴቪ እንደዚህ አይነት ፕሮግራም ሲሰራ፣ የሆነ መልዕክት ለማስተላለፍ አልሞ  እንደሆነ አይደለም ለኔ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ለማንኛውም ወደ ስቱዲዮው ከመግባቴ በፊት ጋዜጠኛውን፤ “ብዙ ነገር የምትቆራርጡ ከሆነ ግን….” ብዬ ስጠይቀው “አይ ያው ከዓውዱ (context) ውጪ ካልሆነ ምንም አይቆረጥም” አለኝ፡፡
እኔም ቃሉን አምኜ ሚዛናዊና ሙያዊ የሆነ አስተያየቴን ለመስጠት ገባሁላችሁ፡፡ ጋዜጠኛው ጥያቄዎችን  ያቀርባል፤ እኔም ያመንኩበትን አስተያየት ሰጠሁ፡፡ በግምት ለአርባ ደቂቃ ያህል፡፡ ፕሮግራሙ ነሐሴ 19 ቀን 2006 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡45 ገደማ ሲተላለፍ ግን በጣም አዘንኩ፡፡
ከዘጋቢው ፊልም ርዕስ ልጀምር፡፡ “ያልተገሩ ብዕሮች” ይላል፤ ማን ይሆን የሚገራው? ኢቴቪ? ስልጣኑን ማን ሰጠው? እኔማ በሚዲያ የሚሰራጨው መረጃ ላይ ውሳኔ የመስጠትና  የመፍረድ… ስልጣኑ የማንም ሳይሆን የህዝብ ነው በማለት በዚህ ዶክመንተሪ ላይ አስተያየት ሰጥቼ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው? ተቆርጦ ወጥቷል፡፡ በነገራችን ላይ ዘጋቢ ፊልሙ መረጃውን ማቅረብ እንጂ በአጠቃላይ የግል ሚዲያውን “ያልተገሩ” ብሎ ለመሰየም  ሙያዊም ሆነ ህጋዊ መሰረት የለውም፡፡
በጋዜጠኝነት ሙያ ፍሬሚንግ (framing) የሚሰኝ ጽንሰ ሀሳብ አለ:: ንድፈ ሃሳቡ ምን መሰላችሁ? አንድ ሚዲያ የሚፈልገውን መልዕክት ለማስተላለፍ ሲል አንድን መረጃ (በቃለ መጠይቅ መልክ የተገኘ ሊሆን ይችላል) ቆራርጦ በደንብ ቅርጽ እንዳይዝ አድርጎ፣ ህዝቡ ዘንድ ለማድረስ የሚፈለገውን አጀንዳ ለማስተላለፍ ብሎም ተጽዕኖ እንዲፈጥር ይጠቀምበታል፡፡ ምንም እንኳን ንድፈ ሃሳቡ በጎ ነገሩ የሚያመዝን ቢሆንም አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የግል ፍላጎታቸውን ለማራመድ ይጠቀሙበታል፡፡ በቀላል አማርኛ ሰዎች ትልቁን ዝሆን ቀጭን ነው ወይም ጠፍጣፋ እንስሳ ነው ብለው እንዲያምኑ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢቴቪ ዝሆን ቀጭን ነው ብሎ ለማስተላለፍ ሲፈልግ ፣ “ዝሆን ወፍራም ሲሆን” በሚል ሰዎች ያብራሩትን ይቆርጥና “ጭራው ግን ቀጭን ነው” የምትለው ተወስዳ፣ “ዝሆን ቀጭን ነው” በሚል ፍሬም ተደርጋ ትቀርባለች፡፡ እና ታዲያ ጎበዝ ያን የሚያክል ግዙፍ እንስሳ ቀጭን ነውን?
እኔ ታዲያ (ሌሎችም እንደሚኖሩ አስባለሁ) የዚህ ዘጋቢ ፊልም ሰለባ መሆኔን የሚያሳዩ ከብዙ ጥቂቶቹን ምሳሌዎች አቀርባለሁ፡፡ በመጀመሪያ ስለ ሚዛናዊነት ተነሳ፡፡ የግል ሚዲያዎች አብዛኞቹ (ሁሉም አይደሉም) ሚዛናዊ አለመሆናቸውን አብራራሁ፡፡ በመቀጠልም ብዙዎቹ ገዢውን ፓርቲ በመደገፍ አልያም በመቃወም ላይ ያተኮረ ዘገባ እንደሚያቀርቡ አከልኩበት፡፡ ልብ በሉ! የመጀመሪያዋ አረፍተ ነገር ቀረበችና ሁለተኛዋ ተቆረጠች፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ (objectivity) ወይም በተቀራራቢ ትርጉሙ ገለልተኝነት ይነሳል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር በዚሁ ዘጋቢ ፊልም ሙሉ በሙሉ አልቀረበም እንጂ ገለልተኝነት ዓላማው ጋዜጠኛው ዘገባውን በሚያቀርብበት ሂደት፣ፅሁፉን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማቅረብ እንዳለበት የሚጠቁም እንጂ የትኛውም ጋዜጠኛ ማንኛውንም አቋም የመያዝ መብቱ የተጠበቀ እንደሆነ በዝርዝር አንስቼ ነበር፡፡
ሌላው ስለ ሚዲያና ዴሞክራሲ ሲነሳ፣ ሚዲያ በመንግስት አካባቢ የሚገኙ ክፍተቶችን ተከታትሎ በግልፅ ማጋለጥ እንዳለበት፣ እንደ አራተኛ መንግስት(fourth state) በመሆን በሶስቱም የመንግስት አካላት ማለትም ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈፃሚውና ህግ ተርጓሚ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ተገቢ የሆነውን ስልጣናቸው እንዲያከናውኑ መከታተልና ማጋለጥ፣ ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት አካላት አካባቢ የሚታየውን ማንኛውንም ብልሹ አሰራር ተከታትሎ ህዝቡን ማሳወቅ እንዳለባቸው በዝርዝር የገለጽኩበት ሃሳብ በሚያሳዝን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ያለምንም ርህራሄ ተቆረጠ፡፡
ሌላው እና ትልቁ ነገር ፕራይቬሲ (ግላዊነት) ሲሆን ይህም ሙሉ ለሙሉ ከተቆረጡትና ኢቴቪ ካልወደዳቸው ሐሳቦቼ እንዱ ነው፡፡ በተለይ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች የማህበረሰቡ የማወቅ መብት ቅድሚያ ስለሚያገኝ፣ ስብዕናቸውን በማይነካ መልኩ ማንኛውም ዓይነት ምርመራ (investigation) ማድረግ እንደሚቻል ነበር ያነሳሁት፡፡ በሌላው ዓለም ያለውን ተመክሮ እንደ ምሳሌ ጠቅሼም ነበር፡፡
ወይ ኢቴቪ! ፕሮግራሙ መጠናቀቅያ አካባቢ፣ እንደ መፍትሔ አንስቼ ከተቆረጠው መካከል ቃል በቃል መንግስት የግል ሚዲያው ላይ በየግዜው የሚያደርገውን ትንኮሳ ማቆም እንዳለበት ገልጬ ነበር፡፡
ምክንያቱም ነጻ ያልሆነ ሚዲያ በአንድ ሀገር የሚኖረው የልማትና ዴሞክራሲ አስተዋጽኦ የተገደበ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ኢቴቪ ከተናገርኩት ውስጥ የቆረጠውን ሃሳብ በመቶኛ አስቀምጥ ብባል፣ 80 በመቶ አካባቢ እንደተቆረጠ እገምታለሁ፡፡ በመጨረሻ ኢቴቪ ቆራረጠው እንጂ ከግል ሚዲያው ይልቅ በመንግስት ሚዲያው ላይ ከፍተኛ የሙያ ክፍተት እንደሚታይም ተናግሬ ነበር፡፡
ስለ አንድ ስማቸውን የማልጠቅሰው ሞጃ ጎረቤቴ አንድ ነገር ላጫውታችሁና ጽሁፌን ልቋጭ፡፡
 እኚህ ጎረቤታችን ሁልጊዜ እኛ ቤት እየመጡ፣ “አትክልት ለጤና ጥሩ ነው” በማለት በልማዳዊ ምክራቸው ያሰለቹን  ነበር፡፡
 በጣም የሚያሳዝነው ነገር ታዲያ ልጃቸውን ብዙ ጊዜ በሽታ ይጎበኘዋል፡፡ ምክንያቱን ሳጣራም፣ አትክልት የሚባል ነገር ቤታቸው ገብቶ እንደማያውቅ ሰማሁ፡፡
 እሳቸው ለካ ተገኘ ብለው ከሰኞ እስከ ሰኞ ስጋ  ነበር የሚበሉት፡፡ አያችሁ፤ ሰውን ለመምከር ከመጣደፍ  በፊት ምክሩን ለራስ መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ እና ኢቴቪም ቢሆን አትክልት ለጤንነቱ ጥሩ መሆኑን የተገነዘበ አይመስለኝም፡፡
 በተረፈ በመንግስት ሚዲያ ላይ ያለውን ክፍተት በተመለከተ፣ ሐሳብ የማይቆራረጥበት አሰራር ሲመጣ መግለጼ አይቀርም፡፡ ሐሳባችሁን  ከሚቆራርጥ ነገር ይጠብቃችሁ፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ ለሁላችንም!!  

Read 3402 times