Saturday, 13 September 2014 13:36

የእኔና የአደይ ነገር

Written by  በቅዱስ ሰውነት
Rate this item
(18 votes)

         የካቻምናውን የክረምት ወራት ያሳለፍኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ከገጠር መንደራችን ርቄ በመውጣት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በዘመድ ዘመድ በተገኘልኝ ቤት ውስጥ በሰራተኝነት ተቀጥሬ ለሶስት ወራት ያህል ቆየሁ፡፡ የቀጣሪዎቼ መኖሪያ ወደ ፈረንሳይ ኤምባሲ አካባቢ ነበር፡፡ ሁሉም ያሰሪዎቼ ቤተሰብ አባላት በመልካም ባህርይ የታነጹ ሲሆኑ በእኔ ዕድሜ ያለች አንዲት ወጣት ሴት ልጅ ነበረቻቸው፤ አደይአበባ ትባላለች፡፡
አደይ የኮሌጅ መግቢያ ፈተና በግንቦት ወር በመውሰዷ፣ የክረምቱ ወቅት ሙሉ በሙሉ የእረፍትና የመዝናኛ ጊዜዋ ነበር፡፡ እዚያው ቤት ውስጥ ፊልም በማየት፣ ታላቅ ወንድሟ የሚያመጣላትን የተለያዩ መጽሐፍት በማንበብና የወላጆቿ ምርጫ የሆኑ ምግቦችን በእኔ ረዳትነት በማዘጋጀት ጊዜዋን ታሳልፋለች፡፡ እንደ እረፍት ማሳለፊያ የያዘችው ግብሯ፤ ከመደበኛ ስራ ባላነሰ ወጥሮ ይዟት ስመለከት ይገርመኝ ነበር፡፡ እጅግ ለስላሳ ፀባይ የታደለች፣ ቁመናና መልኳ በጣም የሚያምር፣ ቤተሰቦቿንና በአጠቃላይ ሰው የተባለ ፍጡር የምትወድ፣ በግብረገብ ያደገች ሸግዬ ነበረች፡፡ በእኔና በእሷ መካከል የነበረውን ያስተዳደግ፣ ያኗኗርና፣ የአስተሳሰብ ልዩነት የሚያትት ትልቅ ድርሳን ማዘጋጀት የምችል ይመስለኛል፡፡
ከከተማ ኑሮ ጋር በትረካ እና በተግባር ያስተዋወቀችኝ፣ ያልተገራ አንዳንድ ልማዴን አለዝባ እንዳዲስ የቀረፀችኝ፣ ስለራሴና ስለሰው ልጅ የነበረኝን ያልጠራ እይታ ያረመችልኝ፣ የዕድሜ ዘመን መምህርቴ የእኔዋ እኩያ አደይ ነበረች፡፡ ሴት እንደመሆኔ የግል ንጽህና አጠባበቄን እየተከታተለች፣ ወጣት እንደመሆኔ የስሜት ለውጤን እየታገሰች፣ ባላገር እንደመሆኔ ምስጢረኛነቴን እየሸረሸረች፣ እንደ ዱር እንስሳ አላምዳና ገርታ እሰው መሃል የለቀቀችኝ አደይ ነበረች፡፡ ከምትወዳቸው መጽሐፍ መካከል ቆንጥራ ታነብልኝ ነበር፡፡ የሚያስቋትን የፊልም ትዕይንቶች እንባዋ እስኪፈስ እየተንከተከተች ትተርክልኝ ነበር፡፡ ከእኩዮቿ የትምህርት ቤት እና የሰፈር ወንድ ልጆች የሚደርሷትን የፍቅር ተማጽኖ ያዘሉ ደብዳቤዎች በግልጽ ታነብልኛለች፡፡ የእኔንም ልምድ ትጠይቀኛለች፡፡ ኮሌጅ ስትገባ ለመማር ስላቀደችው ትምህርት እና የወደፊት ዕቅዷ በሰፊው ታወራኛለች፡፡ ከእርሷ ጋር ቁጭ ብዬ ወሬዋን ለመስማት እንኳን ይከብደኝ የነበርኩ እኔ፣ በጥቂት ሳምንታት እጄን አንስቼ ከእርሷ ጋር እስከመላፋት ባደረሰኝ አስማተኛ የለውጥ ዋሻ ውስጥ መራችኝ፡፡ በውስጤ በራስ መተማመንን ገነባችልኝ፡፡
የህይወት ታሪኬን አንድም ሳይቀር አውርቼላታለሁ፡፡ የቤተሰቦቼን አኗኗር፣ የግብርና ህይወትን ገጽታ፣ የአካባቢያችንን ባህልና ልማድ፣ የአገራችንን መልክአምድር፣ የቀዬአችንን የሰርግና የልቅሶ ስነ - ስርዓት ሁሉ ፈልፍላ እየጠየቀችኝ በገባኝ መጠን ተርኬላታለሁ፡፡
በዚህ መልኩ ለሶስት ወራት ያህል አብረን እንደቆየን ነበር ከቤተሰቦቼ ዘንድ “ነይ” የሚል መልዕክት የደረሰኝ፡፡ የምፈልገውን ያህል ገንዘብ አጠራቅሜአለሁ፣ የሚበቃኝን ያህል የአዲስ አበባ ህይወት ቃኝቼአለሁ፡፡ የሚጠቅመኝን ያህል ገንዘብ አጠራቅሜአለሁ፣ የሚበቃኝን ያህል የአዲስ አበባ ህይወት ቃኝቼአለሁ፣ የሚጠቅመኝን ያህል የከተማ ልምድ አግኝቼአለሁ፣ ለሰራሁበት ቤተሰብ በግልጽ አልተናገርኩም እንጂ ቀድሞም የመጣሁት ለእኒሁ ወራት ያህል ነበር፡፡ በቋሚነት ሰራተኛ ለሚፈልጉት ቤተሰቦች፣ ከመነሻው ይህንኑ ሀቅ መናገር የስራውን ዕድል የሚያሳጣኝ ስለመሰለኝ ትንፍሽም አላልኩም ነበር፡፡ ላገለግላቸው ቤታቸው ገብቼ፣ በብዙ መልኩ ህይወቴን ያሻሻሉልኝን እኒህን ቅን የቤተሰብ አባላት ለወራት አታልዬ መኖሬ እንደ ዕዳ የቆረቆረኝ መሄጃዬ የደረሰ ሰሞን ነበር፡፡ ከቶም ውሸት በማይወራበት ቤት ውስጥ፣ መልካምነታቸውን ቀደም ብዬ ተረድቼ እንኳ፣ እውነቱን በውስጤ ደብቄ መቆየቴ በእርግጥ አሻሽያለሁ ያልኩት ጠባዬ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብኝ አደረገኝ፡፡ ጥርጣሬዬን የቀረፈልኝ ግን አሁንም ቢሆን ከጉዞዬ በፊት እቅጩን ለመንገር መወሰኔ ነበር፡፡
“ይቅርታ አድርጉልኝ፤ እኔ ተማሪ ነኝ፤ በክረምቷ ትንሽ ሰራርቼ ቤተሰቦቼን ለማገዝ ነበር ወደከተማ የመጣሁት፡፡ ቀድሞ ያልተናገርኩት ስራውን ላለማጣት ነበር፡፡ ዘግይቼ ደሞ በጐ ጠባያችሁ ውሸቴን አጋኖብኝ ክፉኛ ፈራሁ፡፡ አሁን ግን ጊዜው ደረሰ፡፡ ይቅርታ አድርጋችሁ ሸኙኝ፤ ከናንተ ስለይ የምጐዳው እኔው ነኝ፡፡” ብዬ ሁሉም ለእራት በተሰበሰበበት አንድ ምሽት ተነፈስኩ፡፡
“ዋናው ተማሪ መሆንሽ ነው፤ በርቺ ብቻ አንቺ እኛ ሰው አናጣም፡፡” ብለው አበረታተው፣ ከሰራሁበት በላይ ገንዘብ ሰጥተው፣ በቅንነታቸው ቀጥተው፣ መናኸሪያ ድረስ ሸኝተው አሰናበቱኝ፡፡
ከአደይ ጋር ተቃቅፈን ተላቀስን፡፡
የዘነጥኩት በእሷ ልብስና ጫማ፣ የደመቅሁት በእሷ ጌጣጌጥ፣ የተቀባሁት የእሷን ቅባትና ሎሽን ነበር፡፡ በመንገዴ ላይ ሳለሁ ከሁሉ በላይ የከነከነኝ የአደይ ነገር ነበር፡፡ በእዚያ ሰላም እና ምቾት የተከበበች ፍልቅልቅ ወጣት፣ ከማንም ደብቃ ለእኔ ብቻ ያወራችኝ የህይወት ዘመኗ አሳዛኝ ምስጢር ለዘላለም በውስጤ ተዳፍኖ እንደሚቀር አውቃለሁ፡፡ ከእዚያ ባልተናነሰ ነፍሴን ያብሰከሰካት፣ ተማሪ መሆኔን በደፈናው ከመንገሬ ውጪ ባልገባኝ ምክንያት የደበቅኋት የእኔው እውነት ነበር፡፡
አንዳንድ የእውነት አጋጣሚዎች እውነት አይመስሉም፡፡
እኔና አደይ በፀደዩ ወራት አጋማሽ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ተመድበን፣ የማመልከቻችን ዕለት እዚያው እምዝገባው ቦታ ተገናኘን፡፡ ይሄን እውነቴን ነበር የደበቅኋት፡፡ ራቅ ካለ ቦታ ነበር የተያየ ነው፡፡ መጀመሪያ አፏን ከፍታ አተኮረችብኝ፣ ቀጥሎ እምባዎቿ በጉንጮቿ ሲፈሱ አየኋቸው፡፡ ከዚያ ወደ እኔ ተንደረደረች፡፡ ደንዝዤ፣ ባለሁበት በዝምታ ነበር የምከታተላት፡፡ መጥታ ስትጠመጠምብኝ፣ ዶክመንቶቼ መሬት ላይ ሲበታተኑ፣ አላፊ አግዳሚው ሲያተኩርብን፣ ይታወቀኛል፡፡ ጨርሼ እንደበድን ሆኜ ነበር፡፡
አንድ ዲፓርትመንት ገባን፡፡ አንድ ዶርም ተመደብን፡፡ የመጀመሪያውን መንፈቅ ያሳለፍንበት ፍቅር፣ እምላለሁ፣ እህትማቾች ዘንድ አይኖርም፡፡ በመጀመሪያው መንፈቅ ከቁብ ያልቆጠርናቸው እንቅፋቶቻችን፣ ከመቼው በእረፍቱ እንደፋፋ እንጃ፣ በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ልዩነቶች ይፈትኑን ጀመር፡፡ ተማሪው ሁሉ በመጠነኛ ትውውቁ ወደ መቧደን ያዘነበለው በነዚያ ወራት ነበር፡፡ መቧደኑ ሳይከፋ የጐሪጥ መታያየቱ ባሰ፡፡
በቅድሚያ፣ የከተማና የገጠር ልጅ የሚባል ፈሊጥ መጣ፡፡ በመቀጠል የኃይማኖት ልዩነቶች ተነሱ፡፡ እኔና አደይ ተነቀነቅን፡፡ እንደምንም አመቱ አልቆ ለእረፍት በየፊናችን ተበተንን፡፡ ለከርሞ፣ መንፈሳችን ታድሶ እንገናኝ ዘንድ በሰፊው ስፀልይ ከረምኩ፡፡ ከአደይ ጋርም አልፎ አልፎ ተደዋውለን ነበር፡፡ እኔ’ንጃ…የድሮው ፍቅራችን የሚመለስ አልመስል እያለኝ ስብሰከሰክ ሰነበትኩ፡፡
በሁለተኛው ዓመት እኔና አደይ እንደ አምናው አንድ መኝታ ቤት አልያዝንም፡፡ አመቱን የጀመርን ሰሞን፣ ከዩኒቨርሲቲው ራቅ ብሎ የሚገኝ ሻይ ቤት ተቀጣጥረን ተገናኘን፡፡ የምናውቃቸው ልጆች እንዳይመጡና እንዳየዩን በማጠነቀቅ ስሜት፣ የቻልነውን ያህል የፍቅር መንፈሳችንን ለመጠበቅ እየሞከርን ተጨዋወትን፡፡
በወሬአችን መሃል በክረምቱ የሆነችውን አጫወተችኝ፡፡ ከእናቷ ጋር በግል በማያወጉበት ሰዓት አደይ እናቷን “ብሔራችን ምንድንነው?” ብላ ትጠይቃቸዋለች፡፡ እናቷ መልሱን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ “ይሄንን ተምረሽልኝ መጣሽ?!” እያሉ ብዙ ደቂቃ ወስደው አለቀሱ፡፡ አደይ ግን የዘመድ አዝማድ ወሬ አነፍንፋ በአስራ ዘጠኝ አመቷ ብሔሯን ደረሰችበት፡፡ አደይ እዚያ፤ እኔ እዚህ፡፡
ይሄም ዋና ልዩነት ሆኖ፣ እኔ እና አደይን ሳንፈልገው በተለያየ ጐራ አቆመን፡፡ ግንኙነታችን እየደበዘዘ፣ መራራቃችን እየሰፋ፣ ጓደኝነታችን ጨርሶ እየጠፋ ሄደ፡፡
በጊዜ ሂደት ሰላምታ መቀያየርም ተውን፡፡ እኔና አደይ ገዢ እና ተገዢ፣ እኔና አደይ በዝባዥ እና ተበዝባዥ፣ እኔና አደይ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ ብሔሮች ሆነን ተሰለፍን፡፡ አይገርምም?!እኔም ሌሎች ወዳጆች አፈራሁ፡፡ አደይም ሌሎች ጓደኞች ኖሯት፡፡ በአዲሱ ጓደኝነት ውስጥ ነባር ስነምግባራችንን በወረት አራግፈን፣ መጤ ባህሪዎችን በጥራዝ ነጠቅነት ተላበስን፡፡ ሁለተኛ ዓመት ተጀምሮ ምን ያህል እንደቆየን እንጃ፡፡ አንድ ምሽት፣ እከተማው መሃል ካለ “ባር” እኔና ጓደኞቼ ተሰባስበናል፡፡ ወይን እየጠጣን፣ ሲጋራ እየተቀባበልን እናጤሳለን፡፡ መርዶዬን የሰማሁት ያኔ ነበር፡፡ አደይ የካቻምናውን ክረምቴን ለቅርቦቿ አውርታለች፡፡ ወሬው በምላስ ንፋስ ሃይል ግቢውን አጥልቅልቆታል፡፡ ጓደኞቼ ጆሮ ደርሶ፣ እኔው ብቻ ኖሬአለሁ የገዛ ታሪኬን ሳልሰማ የሰነበትኩ፡፡ በሞቅታ መሃል አንዷ አንስታ ተረተረችልኝ፡፡ አናቴ ነበር የተተረተረው፡፡ በብስጭት እንደቆምኩ፣ ሲጋራዬን በጣቶቼ እንዳንጠለጠልኩ፣ በመጠጥ እና በነገር እንደናወዝኩ፣ በግሌ ምዬ የተገዝትኩለትን፣ የእኔው አድርጌ የኖርኩትን፣ ያንን ዘግናኝ የአደይ ምስጢር እንደዋዛ ዘረገፍኩት፡፡ ጨርሶ ባልነበርንበት፣ ሰምተን ብቻ ባመንነው፣ የወሬ ቅጥልጥል ተጠላልፈን ተጠማመድን፡፡ አንዳንድ የውሸት ታሪኮች ውሸት አይመስሉም፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት መላው የግቢው አየር በዚያ ቀፋፊ ወሬ ታፈነ፡፡ ጓደኞቼ ደህና የመልስ ምት አግኝተዋል፡፡ በሌላኛው ሳምንት አደይ ትምህርቷን እስከወዲያኛው አቋርጣ ግቢውን ለቀቀች፡፡ ያው ወሬው እየነጣጠረ ይመጣል፡፡ ለወላጆቿ አየሩ እንዳልተስማማት አሳምና፣ ትምህርቷን በግል ዩኒቨርሲቲ እንደቀጠለችም ሰማሁ፡፡

 

Read 5267 times